ሬዲዮ ፋና በ1987 ተመሰረትኩ ይበል እንጂ ከጫካ ጀምሮ የኢህአዴግ
ልሳን ሆኖ የመጣ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህግ ፓርቲዎች ሬዲዮ ጣቢያ ማቋቋም ክልክል ቢሆንም ገዢው ፓርቲ በግል ተቋም
ስም ይህን ተቋም በማቋቋም በፈለገው ጊዜ ካርድ እየመዘዘ አጀንዳ ማሰቀመጫ እና ህዝብን ማወናበጃ ያደርገዋል፡፡ ሲፈልግ ደግሞ ኮንፈረንስ
አዘጋጅቶ ውይይት አድርጉ ብሎ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድራማ ይስራል፡፡ ገዢው ፓርቲ ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ የቅድሚያ ፋና ወጊ
ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ይህ ሬዲዮ ጣቢያ በምንም መመዘኛ ስልጣን ከኢህአዴግ እጅ እንዲወጣ አይፈልግም፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ
ሌት ተቀን ይሰራል፡፡ አሁንም በተግባር በአንድነት ፓርቲ ላይ እያደረገ ያለው ይህንን ነው፡፡ ምርጫ ሲቃረብ አማራጭ አለን የሚሉ
ፓርቲዎችን ከስር ከስር እየተከተለ መሰረተ ቢስ ዜና፣ ዜና ትንተና፣ ሲያስፈልገው ሙሉ ፕሮግራም ሰርቶ ህዝብን ውዥንብር ውሰጥ ይከታል፡፡
ለዚህ ተግባር ደግሞ የሚውሉ በፓርቲዎች ውስጥም ዙምቢዎች አይጠፉም፡፡ ትግሰሰቱ አወሎም እና መሰሎችን የመሰለ ዙምቢዎች ለማግኘት
ደግሞ ብዙ ርቀት መሄድ አያሰፈልግም፡፡
ሰሞኑን እንደተከታተላችሁት በአንድነት ውስጥ የአመራር ክፍፍል አለ
የሚል ዋነኛ ርዕስ ሆኖ ቀርቦዋል፡፡ በአንድነት ውስጥ ይህ የሚሉት መዓት የሌለ ቢሆንም የአመራር ክፍፍል ቢኖር እንኳን ሬዲዮ ፋና
ለአንድነት ጥንካሬ ይስራል ብሎ ማመን አይቻልም፡፡ ይህ ማለት ኢህአዴግ አንድነትን ለማጠናከር በጀት በጅቶ አንድነትን አጠናክሮ
ስልጣኑን ለመልቀቅ ተዘጋጅቶዋል እንደ ማለት ነው፡፡ እኛ ከኢህአዴግ የምንጠብቀው እራሱን ከተቸነከረበት ችንካራ ለማውጣት ተግቶ
መስራት፤ እኛ ደግሞ በሰላም ለመደራጀት እንድንችል መንግሰታዊ መዋቅሩን በህግና በህግ ብቻ እንዲሰሩ ማድረግ ነው፡፡ ሬዲዮ ፋና
ለህገወጥነቱ ዋጋ የሚከፍልበት ጊዜ ይራቅ እንጂ እንደሚኖር ጥርጥር የለኝም፡፡ አንድነትን እና አመራሩን ህገወጥ ብሎ ለመፈረጅ የገዙትን
መኪና እና ፎቅ ያለመረጃ በሚዲያ ከሚያቀርብ ግን በዚሁ በያሰዘው እጁ የአለቆቹን ህንፃ ቆጥሮ ከየት አመጣችሁት? ቢልልን ባይገባውም
ክብር እንሰጠው ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሬዲዮ ፋና ይህንን ፎቅ ከየት አመጣው?
ኢቲቪ የሚባል የሚዲያ ተቋም የስም ለውጥ አድርጌያለሁ ቢልም ግብሩን
መቀየር ግን የተሳነው ተቋም ሆኗል፡፡ አንድነት ፓርቲ የተለያዩ መግለጫዎች ሲሰጥም ሆነ በአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝቶ ፊልም
ከመቅረፅ የዘለለ አንድም የረባ የሚዲያ ስራ አይሰራም፡፡ በገዢው ፓርቲ ሹሞች እጅ የወደቀ በመሆኑ ዘወትር አማራጭ አለን የምንል
ፓርቲዎችን ችግር ብቻ ሲዘግብ ይኖራል፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት አጥር ላይ ሆኖ አንድነቶች ተደባደቡ ሲል የነበረው ኢቲቪ፤ ምንም
ፎርማት ሳይቀይር አንድነቶች ተሰነጠቁ ለማለት ዛሬም አይቸገርም፡፡ ኢቲቪ አንድነት ተሰነጠቀ ብሎ ከመዘገብ ባለፈ ስለ ገዢው ፓርቲ
ልማታዊነት ዘወትር ኢህአዴግ ስለ አመጣው ልማት የደም ስራቸው እስኪገተር የሚያላዝኑ ጋዜጠኞች ማምረትም የተቸገረ አይመስለም፡፡
ህዝቡ አንድነት ፓርቲን እንደ አማራጭ እንዳይመለከት የገዢውን ፓርቲ ሴራ በህዝብ ዓይንና ጆሮ እንዲደርስ እያደረገ ነው፡፡ ኢቲቪ
የሬዲዮ ፋና ጋር ባለው ልዩ ግንኙነት ሬዲዮ ፋና የሰራውን ፕሮግራም ተቀብሎ ያስተጋባል፡፡ ይህን ፕሮግራም ምን አልባትም ኢቲቪ
ከሬዲዮ ፋና በግዢ ይሆናል ያገኘው፡፡ ይህን የምልበት ምክንያትም በመንግሰት በጀት የሚተዳደረው ኢቲቪ ለግል ተብዬው ሬዲዮ ፋና
ገንዘብ ማቀበያ ዘዴም ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ስለ አለኝ ነው፡፡ ይህ ካልሆነም ሬዲዮ ፋና በነፃም ቢሆን ለኢቲቪ ሰጥቶ አንድነት
ለማፍረስ የተያዘውን እቅድ መተግበር ትልቅ ግብና ሰኬት ነው፡፡ እንደ ገዢው ፓርቲ ልሳን አድርገን ስንወስደው ይህ በጣም ቀላሉ
የደባ ሰራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የኢህአዴግ አመራሮች አገር ጥለው ሲጠፉ፣ የምክር ቤት አባላት የነበሩ በወጡበት ተሰውረው ግንባሩን
ሲያጋልጡ ለምን ኢህአዴግ ተሰነጠቀ ብሎ አይዘግብም፡፡ ትዕግሰቱ አወሉ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የጅማዋ የምክር ቤት አባል ያላትን
ያህል ቦታ እንደሌለው ኢቲቪ ሳያውቅ ቀርቶ ነው ያልዘገበው ብለን ልንወስድ አንችልም፡፡ ዋናው ነገር ኢቲቪ ሚናው አንድነትን የማዳከም
ብሎም የማፍረስ ዘመቻ ሰለሆነ ብቻ ነው፡፡
ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን በግለጫ እንዲዋረድ አደረግነው እንጂ የዘወትር
ምግባሩም አንቱ የሚያስብለው እንዳልሆነ ሁሉም ያውቃል፡፡ አንድም ቀን ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደው የማያውቁ፤ የፓርቲዎቹ አመራሮች እነ ማን እንደሆኑ የማይታወቁ፣ የፓርቲ ማህተምና ሰርተፊኬት ይዘው
ከተማውን ያጣበቡ ፓርቲዎች በብዛት ባሉበት ሀገር በሰርዓት ለመመራት ወሰኖ የሚንቀሳቀስ ፓርቲን እየተከታተሉ ችግር መፍጠር የተቋሙን
ነውረኝነት የሚያሳይ ነው፡፡ ፓርቲዎች ችግራቸውን መፍታት ያለባች በውስጥ ደንባቸው መሆኑ እየታወቀ በሚዲያ እየወጡ ፓርቲዎችን ማጠልሸት
ግብ አደርጎ አስቀምጦ፤ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት እሰራለሁ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን ተግባር እየፈፀሙ ያሉ የምርጫ ቦርድ
ሀላፊዎች የታሪክ ተጠያቂነት እንዳለባቸው የተገነዘቡ አይመስለኝም፡፡ በአንድነት ውስጥ አንድም የአመራር ክፍፍል ሳይኖር የአመራር
ክፍፍል አለ ብሎ በሚዲያ ቀርቦ ማውራት፤ ሚዲያውም እሰኪ ማን ነው አመራር? በምን ደረጃ? ብሎ እንዳይጠይቅ የተደረገበት ምክንያት
ዘመቻው በቅንጅት የሚተገበር ከገዢው ፓርቲ የተሰጠ ተልዕኮ መሆኑ ጉልዕ ምስክር ነው፡፡ ሬዲዮ ፋና እየሰራ ያለው የኢህአዴግ (የአባቱን)
ገዢነት እድሜ ለማራዘም ነው፡፡ እነርሱ በወንጀል እንጂ በታሪክ ፊት አይቆሙም፡፡ ምርጫ ቦርድ ግን ሁለቱም የሚቀርለት አይደለም፡፡
ይህ ሁሉ የሚደረገው ዜጎች በፖለቲካ
ጉዳይ አማራጭ እንዳይኖራች ማድረግ እና ገዢውን ፓርቲ አውራ ፓርቲ አድርጎ ለማቆየት የተወሰደደው አማራጭ ገዢውን ፓርቲ ከማጠናከር
ይልቅ አማራጮችን ማደከም እንደ ስልት በመያዙ ነው፡፡ ይህ ሰልት ደግሞ በሌላ ግንባር አማራጭ በሚፈልገው ወጣት ላይ በግልፅ ተከፍቶ
ታገኙታላችሁ፡፡ በዚህኛው ግንባር አማራጭ ሞልቷል፡፡ እግር ኳስን በሬዲዮ ይሁን በቴሌቪዥን መመልክት፣ ሙዚቃ፣ መጠጥ፣ ጫት፣ ሲጋራና
አሽሽ የመሳሰሉት ለወጣቶች የቀረቡ
አማራጭ መፋዘዣ እና ማደንዘዣ ናቸው፡፡ ለሀገሬ ያገባኛል ብሎ ግን በፖለቲካ ፓርቲ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ መጠቀም፣ ለሰላምና ለለውጥ
የሚጠቅም ስራ መስራት ግን ያስወነጅላል፡፡ ያለ ስም ስም ያሰጣል፡፡
ይህን በተመለከተ አንድ ወጣት ጓደኛዬ
ስልክ ደውዬለት የትነህ? ምን እያደረክ ነው? የሚል ተከታታይ ጥያቄ
ሳቀርብለት የሰጠኝ መልስ መንግሰታችን በዚህ በኩል ልቅ እንደሆነ ማሳያ ይሆናል፡፡ መንግሰታችን የሚወደውን ቢራ እየጠጣሁ ነው አለኝ፡፡
አስከትሎም ቢራ ጠጥተህ ሰክረህ ብትጮሆ፣ ወይም ኳስ አፍቃሪ ነኝ ብለህ ማንቼና አርሴ እያልክ ብትሰበሰብ ማንም ምንም አይልህም፡፡
ነገር ግን የዚህ ሀገር ጉዳይ ያገባኛል ብለህ ላይብረሪ ሄደህ አንብበህ የተሰማህን ለህዝብ ለማድረስ ከፃፍክ ግን ቤትህ ወህኒ ይሆናል
አለኝ፡፡ እኔም እንደምታውቀው ያገባኛል ብዬ የአንድነት ፓርቲ አባል ሆኜ ፖለቲካ ውስጥ ስሳተፍ ድርጅቴን ለማፍረስ ምርጫ ቦርድ
በሚባል ተቋም ውስጥ የመሸጉ ጉግ ማንጉጎች የሚሰሩትን እያየህ ነው አለኝ፡፡ በእኔ እምነትም ይህ የምርጫ ቦርድ አጎራ ዘለል ተግባር ሚዛን የጠፋለት ነውረኛ ተግባር እንደሆነ አሁን ግልፅ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል፡፡
ሁላችሁም እንደምታውቁት ይህ ወጣት የትግል
አጋር በግልፅ እንዳሰቀመጠው ወጣቱ በሀሽሽ ቢናውዝ፣ ሰክሮ ቢጨፍር፣ እህቶቻችን እርቃናቸውን ውጪ ሲሄዱ ቢያድሩ፣ ጫት፣ ሺሻ ሲጀነጀኑ
ውለው ቢያድሩ መንግሰት ተብዬው ከቁም ነገር የሚቆጥረው ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ወጣቶች በምርጫ በመራጭነትና በታዛቢነት ከፍ
ሲል ደግሞ በዕጩነት ለመሳተፍ ፍላጎት ካሳዩ ግን የማይሸርበው ሴራ የለም፡፡
በቅርቡ የምርጫ ቦርድ እና ሚዲያ በአንድነት ፓርቲ ላይ የከፈቱት ዘመቻ
ዋና መልዕክት ወጣቱ አማራጭ ስለሌለ ለምርጫ አትመዝገብ የሚል ነው፡፡ ይህን አማራጭ የሚባል የሌለውን ምርጫ ከምትከታተል አርሴና
ማንቼ እያልክ ተዝናና፣ ኤፍ.ኤም ሬዲዮኖች የሚለቁልህን ሙዚቃና የስልክ ጥያቄና መልስ፣ ከአውድ ዓመት ጋር ተያይዞ ያለን ሽልማት
ላይ ተራኮት፣ ሲመች ደግሞ ማምሻውን ድራፍታ ቢራ እየኮሞከምክ ዓለምህን ቅጭ እየተባለ ነው፡፡ አማራጭ ያለበት ምርጫ ስልጣኑን እንደሚያሳጣው
የተረዳው ገዢው ፓርቲ ምርጫ ቦርድን ከለላ አድርጎ ፍልሚያ ከፍቶዋል፡፡ ከህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ደሞዛቸውን የሚበሉ የቦርድ ሰራተኞችና
ሹሞኞች በማን አለብኝነት የእብድ ገላጋይ መስለው ድንጋይ እያቀበሉ የአንድነትን መንፈስ ለመሰበር ላይ ታች እያሉ ነው፡፡ ይህን
ለማሳካት ከምንጊዜውም በላይ ተግተው በስራ ላይ ናቸው፡፡ የሰንበት ቀን አይበግራቸውም፡፡ ኃላፊ ተብዬዎች ነውር የሚባል ነገር አጥተው
ደብዳቤዎች ባልተፃፉበት ቀን ወጪ እንዲደረጉ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በመንግስት ቢሮና ሀብት ከፓርቲ አኮረፍን ያሉ ግለሰቦቸን በፓርቲ
ላይ ከህግ ውጭ ያደራጃሉ፡፡ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ማበብ የመስረት ድንጋይ ያስቀምጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ሰዎች መሰረቱን ንደው
ለአውራ ፓርቲ ግንባታ እራሳቸውን አዋርደው ይስራሉ፡፡ እራሳቸውን ያዋረዱ ሰዎችን ደግሞ በምን መመዘኛ ለክብር እንደምናጫቸው እየተቸገርን
ነው፡፡ በእነዚህ ሰዎች የሚመራ ተቋም ደግሞ ክብር እንዴት ሊያገኝ ይችላል፡፡ እጅግ ጥቂት የሚባሉ ከህሊናቸው ያሉ ካሉ ግን ሳይረፍድ
የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ መሰረት እንዲጥል በተቋቋመ ተቋም ውስጥ እየተሰራ ያለውን ደባና ህገወጥ ተግባር ሊያጋልጡ ይገባል፡፡
ጥሪው ሀገራው ጥሪ ነው፡፡ በምንም ዓይነት ይህ ተቋም በመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ ሽፍጥ የሚሰራበት መሆን የለበትም፡፡
ሽፍጠኞችም በህዝብ ዳኝነት የሚያገኙበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡
ለማነኛውም ኢትዮጵያ ሀገራችን ነች በምንም ሁኔታ ቢሆን ለጊዜው ህገወጦች
ሊያይሉ ይቸላሉ ህጋዊ መስመር ላይ ያሉ የተሸነፉ ይመስላሉ እውነቱ ግን የተለየ ነው፡፡ ለእውነት የቆሙ ከመርዓቸው ጋር የሆኑ ሁሉ
ያሸንፋሉ፡፡ ለማሸነፍ ሁሌም ከመርዕ ጋር መሆን ጠቃሚ ነው፡፡ መርዕ ሲባል ግን ለሆድና ለግል ዝና መቆም አይደለም፡፡ መርዕ ሲባል
ከግል ጥቅም እና የግል ፍላጎት አለመገዛት ነው፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ለግል ፍላጎት ግዴለሽ መሆን ማለት ነው፡፡ አንድነት አባላት
አሁን የሚፈልጉት ከግል ፍላጎታቸው የነጹ እና ለውጤት የሚተጉ አመራሮች ነው፡፡ ለውጥ ግን የግድ ነው፡፡ አንድነት ይምራው ወይስ
ሌላ ይህ የታሪክ ጥሪ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር