Wednesday, January 14, 2015

ግልፅ ደብዳቤ
ለክቡር ፕሮፌሰር መርጊያ በቃና
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስብሳቢ
ከግርማ ሠይፉ ማሩ (በግል)
ጉዳዩ፤ በሚዲያ ቀርበው አንድነት ፓርቲትን በተመለከተ የሰጡትን የቦርድ ውሳኔ ይመለከታል
ቦርዱ ሰጠ የተባለውን ውሳኔው ከመግለጫው እንደተረዳሁት የውስጥ ችግራቸውን ፈተው በጋራ ጉባዔ እንዲጠሩና የሚመራቸውን ፕሬዝዳንት ይምረጡ የሚል ነው፡፡ ቦርዱ በግልፅ ፕሬዝዳንት ይምረጡ ባይልም ታህሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም በቁጥር አ/573/ፓአ/405 በተፃፈልን ደብዳቤ ይዘት ስንረዳ የቦርዱ ጥያቄ በዋነኝነት የሚያጠነጥነው በፕሬዝዳንት ምርጫ ላይ በመሆኑ ነው ይህን ግምት ለመውሰድ የተገደድኩት፡፡ ከዚህ በመነሳት በአንድነትፓርቲ በአባላት መካከል የሚፈጠርን አለመግባባት የሚፈታበት ህገ ደንብ አለው፡፡ ከዚህ ውጭ ቦርዱ በፓርቲ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ በየትኛው ህግና ደንብ ወይም መመሪያ እንደተሰጠው መረዳት ተቸግሪያለሁ፡፡ የቦርዱ ስብሳቢ ዘወትር እንደሚሉት በቅንነትና በሆደ ሰፊነት ከሆነ ግን በምንም መመዘኛ እርሶ የሚመሩት ቦርድም ሆነ እርሶ በግል ለፓርቲያችን እድገት ቅን እንደማታሰቡ እሰከ አሁን ባደረግናቸው ውይይቶችና ቦርዱ በሚፈፅማቸው ድርጊቶ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ አሁንም በህግ አመልካ ከፓርቲያችን የውስጥ ጉዳይ እጃችሁን እንድታነሱልን እጠይቃለሁ፡፡
ሌላው የቦርዱ ውሳኔ ከሚዲያ እንደሰማሁት በጋራ ጉባዔ ጥሩ የሚለው ነው፡፡ ክብር ሰብሳቢ ዘወትር በውይይታችን የሚያነሱልን የህግ አማካሪዎች በበቂ እንዳላችሁ፣ የፅ/ቤቱ ኃላፊም የህግ ባለሞያ እንደሆኖ የምትሰሩትም በህግና በህግ ብቻ እንደሆነ ነው፡ ፓርቲያችንንም የውስጥ ደንቡን ጨምሮ ሌሎች ህጎችን እንዲያከብር ዘወትር ይመክሩናል፡፡ ሀቁ አንድም ቀን ከህግ ውጭ ሰርተን አለማወቃችን ሲሆን ይልቁንም ቦርድ የሚላቸውን ጉዳዮች ከመስመር ወጥተን ለማስተናገድ መሞከራችን ነው፡፡

ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ በጋራ ጉባዔ ጥሩ ሲባል የአንድነት ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ የጉባዔ አጠራር እንዴት እንደሆነ ካለማወቅ ነው የሚል እምነት የለንኝም፡፡ ይልቁን አንድነትን ወደ ሌላ ህገወጥ ተግባር በመክተት ችግሮችን ለማወሳሰብ በፅ/ቤታችሁ በኩል እየተሰራ ያለውን ህገ ወጥ ግለሰቦችን የማደራጀት ደባ እኛ በምንፈፅመው ስህተት ለማጠናከር ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ ክቡር ሰብሳቢ የአንድነት ፓርቲ ደንብ የጠቅላላ ጉባዔ የመጥራት ስልጣን የሰጣቸው ህጋዊ አካላት እና አጠራሩ፤
1.  የብሔራዊ ምክር ቤት፤
2.  የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት ጉባዔ በማንኛውም ምክንያት ጉባዔ እንዲጠራ ከፈለጉ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን አንድ ሶስተኛ አሰፈርመው ሲያቀርቡለት በዚሁ መሰረት ብሔራዊ ምክር ቤቱን ሲያዝ፤ ወይም፤
3.  ብሔራዊ ምክር ቤቱ ትዕዛዙን ካልፈፀመ ኦዲትና ኢንስፔክሽን በቀጥታ ጉባዔ እንዲጠራ
 በማድረግ ነው፡፡
ከዚህ ውጭ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እንደ ፓርቲ ከፍተኛ መሪ ወይም የፓርቲው ስራ አሰረፃሚ ኮሚቴ እንደ አካል የብሔራዊ ምክር ቤት የመጥራት ስልጣን የላቸውም፡፡ ከዚህ አንፃር ሲመዘን ሁለት ጠቅላላ ጉባዔ ተካሄደ ብለው በሚዲያ የሰጡት መግለጫ አግባብነት የሌለው ነው፡፡ ይልቁን በርሶ ደረጃ በኃላፊነት ያለ ግለሰብ በሚዲያ ቀርቦ “መሪዎች ክሊክ እየሰበሰቡ የሚያካሂዱት ጉባዔ” በማለት በመረጃ ያልተደገፈ ያልተገባ ቃላት ተጠቅሞ መግለጫ መስጠት ከባድ ስህተት መሆኑን እና በህግ የሚያስጠይቅ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ 
ከዚህ ውጭ በጋራ ጠቅላላ ጉባዔ ሊጠራ የሚችልበት ሁኔታ ካለ ቦርዱ ህግ ጠቅሶ ቢያስረዳን ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ ይህ በማይሆንበት ሁኔታ የፓርቲው መልካም ስምና ዝና የማይመጥን መግለጫ በሚዲያ እየቀረቡ መስጠት ምርጫ ቦርዱ የአንድነት ፓርቲ በቆራጥነት ምርጫ ለመሳተፍ መወሰኑን ተከትሎ በገለልተኝነት ለማገልገል አለመዘጋጀቱን ነው፡፡ አሁን እየተደረገ ባለው ህገ ወጥ ተግባር ምክንያት ፓርቲያችን መራጩ ለምርጫ በንቃት እንዲሳተፍ ለመቀስቀስ ፓርቲያችን ያለውን እቅድ በከፍተኛ ደረጃ እያስተጓጓለ ሲሆን፣ በፓርቲው ዕጩ አመላመል ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረብን መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ጭምር እንዲያውቅ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ደግሞ በገለልተኝነት እንዲያገለግል የሚጠበቅበት የምርጫ ቦርድ ለገዢው ፓርቲ ግልፅ ወገንተኝነት በማሳየት የህግ ጥሰት እየፈፀመ መሆኑን ያጋልጣል፡፡
በመጨረሻም ቅሬታ አለን የሚሉት አባላት በፅ/ቤቱ ቀጥተኛ ድጋፍ የሚደረግላቸው እና ዝርዝራች በቦርድ ፅ/ቤት የሚታወቅ ሲሆን አንድነት በጠራው ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ የደረሳቸው ስለመሆኑ፤ ነገር ግን በጉባዔው ተገኝተው እንደማይሳተፉ፤ የማይሳተፉበትም ምክንያት በድምፅ ብልጫ አንደሚሸነፉ ስለሚያውቁ መሆኑን ፤ ወኪል ነን ያሉት በሚዲያ ቀርበው የሰጡት መግለጫ በእጄ ይገኛል፡፡ ቦርዱ ይህን የግለሰቦች ጉዳይ ይዞ ባሰለፈው ህገወጥ ውሳኔ ፓርቲያችን ከምርጫ እንዲወጣና ገዢው ፓርቲ ያለምንም ተቀናቃኝ እንዲሮጥ እየፈቀደ ነው፡፡ ቦርዱ ይህንን ስህተት አርሞ ፓርቲያችን ካቀረባቸው አማራጭ ምልክቶች አንዱን ወሰኖ በአስቸኳይ እንዲያሳውቀን፤ ፓርቲያቸንን የሚመራልንን ሰው መምረጥ ደግሞ የአንድነት አባላት ብቻ መሆኑን ተረድቶ በአዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀፅ 16 መሰረት የፓርቲያችንን ነፃነት እንዲያከብር በማክበር እጥይቆታለሁ፡፡


                            

No comments:

Post a Comment