Monday, April 6, 2015

ክርክር 4፡ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት- በእኔ ዕይታ

ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; girmaseifu.blogspot.com
ተከራካሪዎች
·         እያሱ መኮንን እና አዳነ ታደስ                  ኤዴፓ
·         ተሸመ ወልደ ሓዋሪያት                       መኢብን                 
·         ትዕግሰቱ  ደበላ እና ግዑሽ ገ/ሰላሴ              ኢድአን
·         ካሳሁን አበባው እና ተሰፋሁን አለምነህ          መኢሕአድ
·         መኩሪያ ኃይሌ እና አህመድ አብተው            ኢህአዴግ
በግንቦት 2007 የሚካሄደው “ምርጫ” አማራጭ በሌለበት መሆኑ በዋነኝነት የጎዳው ለምርጫ ከምር የተዘጋጁትን ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን መራጩን ህዝብ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ይህ አሁን በገዢው ፓርቲ ላይ ለምንመለከተው የፀጥታ ስጋት ምንጭ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ዘንድሮ የፕሮፓጋንዳ ማሽን የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ምርጫ ቦርድ የሰጠው ውሳኔ ፍትሐዊ ነው፣ የምርጫ ቦርድ ታጋሽነት ያስደስታል፣ ወዘተ ከሚሉ አንድ-አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘገባ፤ ምርጫ ክርክሩ በመረጃ ላይ ተመስርተን እንድንመርጥ የሚያስችል ነው “አሉ” አንድ-አንድ ነዋሪዎች ወደሚል አድጓል፡፡ ይህ መልዕክት አማራጭ አለ የሚል የተሳሳተ መልዕክት ለማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ከአማራጮቹ “ምርጡ ኢህአዴግ” ነው ወደሚለው ቀጣይ ዘመቻ መግቢያ ነው፡፡ በዚህ አሰቀያሚ የማስመሰል ድራማ ውስጥ አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት የሚሳተፉ እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ድራማ ውሰጥ አውቀው በድፍረት ከሚሳቱፉት አንዱ ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ክፍል ነው፡፡ ምርጫው አማራጭ እንደሌለው እየታወቀ “የሚዲያ ሚና በመርጫ” ምናምን እያለ ድራማውን ያዳምቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሌላ ቀን መመለስ ይቻላል እና ወደ መጋቢት 25 እና 26 የምርጫ ክርክር ትኩረት እናድርግ፡፡
ኢህአዴግ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱም ቢሆን ከግብርና ወደ ኢነዱስትሪ የሚደረግ ሽግግር የማድረግ ሃሳብ አልነበረውም፡፡ በዋነኝነት እድገቱ መሰረት ያደርጋል ተብሎ ታሳቢ የተደረገው በአነስተኛ ማሳ ላይ በሚደረግ ምርታማነት ማሳደግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዋነኝነት የሰራ እድል በመፍጠርም ሆነ የተለየ ምርታማነት ማሰደጊያ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የሚያስችል አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ከግማሽ ሄክተር በታች ማሳ ያላቸው ገበሬዎች ከበሬ የዘለለ የእርሻ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያስቸግራቸዋል፡፡ ሰለዚህ ዋነኛው የምርት ማሳደጊያው ግብዓት ማደበሪያ አጠቃቀምም ነው የሚሆነው፡፡ ይህም ቢሆን የመሬቱን የማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሳይሆን “ለሁሉም አንድ ጃኬት” በሚመስል መልኩ ለሁሉም ዩሪያና ዳፕ የሚባሉ ማዳበሪያዎች የሚቀርቡበት አሰራር ነው ያለው፡፡ የማዳበሪያ ንግድ በሀገራችን የማንን ኪሲ እንደሚያደልብ እያወቅን ተጨፈኑ እናሞኛችሁ ይሉናል፡፡ የግብርና ምርት ማሰደጊያ ግብዓቶች ማቅረብ በዋነኝነት ግቡ የተወሰኑ ኩባንያዎች ኪስ ማደለቢያ እንጂ በወሬ እንደሚባለው ምርታማነት ለመጨመር አይደለም፡፡ አማልጋሜትድ የሚባል በኢትዮጵያዊ የሚመራ የግል ኩባንያ ለምን ከዚህ ሀገር ተገፋ?
መጋቢት 25 እና 26 በተደረገው የፓርቲዎች ክርርክር ርዕሱ “ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት” የሚል ነበር፡፡ ኢህአዴግን ባለፉት 24 ዓመት ብቻ ሳይሆን ባለፉት አምሰት ዓመታት አሳካዋለሁ ብሎ የቀረበውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንኳን ለማሳካት የማይችል ብቻ ሳይሆን እነዚህን በቁጥር ያስቀመጣቸውን ግቦች ያለ ማሳካቱን ግልፅ ሆኖ እያለ በኩራት አሳክቻለሁ ይላል፣ ጥሩ ጅምር ነው እያለ ሲፎክር በመረጃ አስደግፎ ሊሞግተው የሚችል ፓርቲ አላገኘም፡፡ በግሌ ይህ ክርክር በኤዴፓው ተከራካሪ እያሱ መኮንን እና በኢህአዴግ ተወካዮች ብቻ ቢሆን ምርጫዬ ነበር፡፡ ለኢዴፓ ካለኝ ፍቅር ሳይሆን አቶ እያሱ በተረጋጋ ሁኔታ በነጥብ ሲሞግት ስላየሁት ነው፡፡ አብሮት ለክርክር የገባው አቶ አዳነ ታደሰ ሊረዳው በሚገባው ልክ ከመርዳት ይልቅ ኢዴፓዎች አንፈልገውም የሚሉትን ሰሜታውነት መቆጣጠር ሳይቻለው ቀርቶ ታዝበነዋል፡፡
ወደ ዝርዝሩ ስንገባ የመጀመሪያ ቅድሚያ እድል ያገኘው ኢዴፓ በአቶ እያሱ መኮንን ተከራካሪነት ነው፡፡ እያሱ በመግቢያው ላይ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የከተማ ታሪክ ያላት መሆኗን በጨረፍታ አንሰቷል፣ ከአፍሪካ አንፃርም ቢሆን ከተሜነት በዝቅተኛ ደረጃ እንደምንገኝ፤ በዚህ ዝቅተኛ ደረጃ ባለ ከተሜነት አስፈላጊ የሆኑ አግልግሎቶች ማቅረብ ያለመቻሉን፣ ኢህአዴግ ወዳጄ ያለው ግብርናም ቢሆን ይህን አነስተኛ ቁጥር ያለውን ከተሜ መመገብ አቅቶት ስንዴ፣ ሰኳር የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍጆታ ከውጭ በግዥ እንደሚገባ አሰረድተዋል፡፡ የኢህአዴጉ ተወካይ ግብርና ባፈራው ጥሪት ነው ሰንዴና ሰኳር የተገዛው የሚል አስቂኝ መልስ የሰጡ ቢሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ልካ በምታመጣው ገቢ ከነዳጅ ውጭ ሌላ ነገር ለመግዛት የሚያስችል አቅም እንዳልፈጠረች፣ አብዛኛው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከእርዳታ፣ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የሚገኝ ገቢ፣ ወዘተ እንደሆነ ለኢህአዴጉ ተወካይ ማስታወስ ያስፈልግ ነበር፡፡
ከከተሜነት አንፃር አሁን የተፈጠረውም ሽግግር በኢዴፓው ተወካይ በኢንዱስትሪ ነው የሚል አቀራረብ የነበራቸው ቢሆንም እውነታው ግን አብዛኛው ወደ አገልግሎት የመጣ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፍ በሰራ ፈጠራ አሁን ወደ ከተማ የገባውን ሁለት ከመቶ ህዝብ አልተቀበለም ምክንያቱም ኢንዱስትሪ የሚባለው እዚህ ግባ በሚባል ደረጃ የለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ 70 ከመቶ በሀገር ውስጥ ባለሀብት ተይዞዋል የሚባለው ኢንዱስትሪ በቤተሰብ ደረጃ የሚሰሩ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የከተሜንት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የምታጋራው ልምድ የነበራት/ያላት ሀገር ነች፡፡ እንደ ብራዚሊያ ያሉ ከተሞች የሚኒሊክ ሞዴል ተከትለው ዋና ከተማቸውን በሀገሪቱ አማካይ ቦታ ለማድረግ ችለዋል፡፡ አዲሰ አበባ በሀገራችን አማካይ ቦታ መገኘቷን ልብ ይሏል፡፡ ሌሎችም የረጅም የከተማናት ታሪካችንን መጥቀስ አለመቻላቸው ቅር አስኝቶኛል፡፡ የአፍሪካ ከተሜነት ከ40 በመቶ በላይ ሲሆን በዓመት በአማካይ ላለፉት 20 ዓመታት 3 በመቶ እያደገ ሲሆን ኢህአደግ የሚመራት ኢትዮጵያ ግን በ24 ዓመት 3 ከመቶ ዕድገት ማምጣት አልቻለም፡፡ ኢህአዴግ ቢዘህ ሊያፍር አልቻለም የሚያሳፍረውም ተከራካሪም አላገኘም፡፡
የኢዴፓው እያሱ መኮንን በኢትዮጵያ ከተሞች “ለምን ዕድገት አላሳዩም? ተብሎ ሲጠየቅ ኢህአዴግ ሳይፈልግ ቀርቶ ሳይሆን በፖሊስ ችግር ነው፡፡ ግብርናን መሰረት አድርጌ ለውጥ አመጣለሁ ይላል፤ ግን አይችለም” የሚል አስተያየት አስቀምጦዋል፡፡ ይህ አተያየ በኤዴፓ የፖለቲካ ቅኝት ልክ ቢመስልም፣ “ከተሞች አድገው ስልጣን ከማጣ፤ ከተሞች ባያድጉ ይሻላል” የሚል ፖሊስ የነደፈ ገዢ ፓርቲ አንፃር ለምን የከተሞች ዕድገት አልታየም? ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ እንዴት ሊተረጎም እንደሚችል አይገባኝም፡፡ ይህን ውሳኔ ለአንባቢ መተው ይሻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢህአዴግ ከተሜነት እንዲያድግ ይፈልጋል?
የኢዴፓ ተወካዮች ጥቃቅን እና አነስተኛ በመባል የተደራጁትን እንደሚደግፉ ነገር ግን እነዚህ አደረጃጀቶች ከፖለቲካ ሴል ወደ ኢኮኖሚ ሴል መለወጥ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ያሰቀመጡ ሲሆን ከጥቃቅን እና አነስተኛ አባላት ጋር ግብ ግብ መፍጠር እንዳልፈለጉ ያሰታውቅባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ትክክል የፖለቲካ አያያዝ ይመስለኛል፡፡ ይህን ነጥብ ብዙዎቹ ተከራካሪዎች የተጋሩት በመሆኑ ኢህአዴግ ከዚህ አንፃር ነጥብ እንዳያሰቆጥር አድርገውታል፡፡ በሀገራችን አለ የሚባለው እድገት ከተሜው በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት ሰቃይ ውስጥ ሆኖ የተገኘ ሲሆን ይህ ደግሞ ዘላቂነት እንደማይኖረው አስረድተዋል፡፡ ይህ ለአብዛኛው አድማጭ በምን ያህል ደረጃ እንደሚረዳው አላውቅም፡፡ ከተሞቻችን ጥቂት የሚባሉ ባለ ሀብቶች እጅ የወደቀች ሲሆን ዋናው መንግሰት የሚቆጣጠረው ሀብት ነው፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ለድሃ ምቹ ያልሆነች ከተማ ነች፡፡ አዲስ አበባ ፓርክ የሌላት፣ መዝናኛ የራቃት ከተማ ብቻ ሳትሆን ለወጣቶች ያዘጋጀችው መዝናኛ ትውልድ ገዳይ የሆነ ሱስ ማዘውተሪያ ቦታዎችን ነው፡፡ የስራ እድልን በተመለከተ ከኢህአዴግ የተነገረን የስራ እድል ቁጥር የተጋነነ ነው፡፡ በጡረታ የሚደጎም ወጣት የሚኖርበት ሀገር ይህ ሁሉ የሰራ እድል ተፈጠረ ማለት ምፀት ነው፡፡ ኢዴፓ በበኩሉ በዓመት 1.7ሚሊዮን በላይ የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ ነገሮናል፡፡ ኢዴፓዎች ይህን ቃል ሲገቡ እንደሌሎች ፓርቲዎች ሁሉ መንግሰት የመሆን እድል እንደሌላቸው እየታወቀ አጉል ተሰፋ ሊመግቡን እየፈለጉ እንደሆነ ማወቃችንን ማወቅ አለባቸው፡፡
የኢዴፓው አቶ አዳነ ታደሰ ካነሱት ሃሳብ የከተሞች እድገት ላይ ዋነኛው እንቅፋት የሆነው ከተሞች በካድሬ መመራታቸው ብቻ ሳይሆን የከተማ ህይወት የማያውቁ ሰዎች በመሆናቸው የተፈጠረ ነው ብለውታል፡፡ ይህ በአዲስ አበባ ከላይ እስከታች ባለው መዋቅር የሚታይ አዲስ አበቤዎችን የገፋ፤ ይልቁን የአዲስ አበባ ልጆችን በጠላትነት የሚያይ ሰርዓት መሆኑን ማሳያ ነጥብ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፍም ቢሆንም በሀገራችን አሁን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየወጣ ወደ ሀገር የሚገቡት ጁስዎች በሀገራችን የጥሬ እቃዎች ምርት በሚበላሸበት ሁኔታ እንደሆነ እያወቅን ይህን መለወጥ የማይችል የኢህአዴግ ፖሊስ አይሰራም ብለው ነጥብ አስቀምጠዋል፡፡ ሰልጡን ፖለቲካ ከፈለጋችሁ ኢዴፓን ምረጡ ብለውን ተሰናብተዋል፡፡
መኢብን የሚባው የአቶ መሳፍንት ፓርቲ ዛሬም አቶ ተሾመ ወልደ ሓዋሪያትን በድጋሚ ይዞ የመጣ ሲሆን በኢህአዴግ ፖሊሲ ምክንያት የከተሜነት ችግር ለመፍታት አለመቻሉን የከተሜውን ችግር በሚያሳይ ሁኔታ ዘርዝረውታል፡፡ በምርጫ ውድድርም ውስጥ የገቡት መንግሰት ለመሆን ሳይሆን እና የዘረዘሩትን ችግሮች ለመፍታት ሳይሆን ይህን ብሶቱን ለማሰማት እንደሆነ በግልፅ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ልናከብራቸው ይገባል (ፓርቲያቸውን ሳይሆን አቶ ተሸሞን በግል)፡፡ አቶ ተሾመ ትውልዳቸው ዱራሜ አካባቢ እንደሆነ በሚያሳይ መልኩ ፓርቲያቸውን በሚመጥን መልኩ የተሰጣቸውን ጊዜ በቀበሌኛ ጉዳዮች አባክነው “በከተማና ኢንዱስትሪ” ጉዳዮች ነጥብ ሳይሰጡን አልፈዋል፡፡ ነጥብ አገኛለሁ ብዬም ስለአልጠበኩ አልገረመኝም፡፡ ምርጫ ቢኖረን መኢብን የሚባል ፓርቲ ከአሁን በኋላ በቤታችን ቴሌቪዥን ባይመጣ በመረጥን ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድ ከሚንከባከባቸው ፓርቲዎች አንዱ ብቻ ሳይሆን በማነኛውም ሀገራዊ ጉዳዮች ተቃዋሚ ፓርቲን ወክሉ በግንባር ቀደም ከሚገኙት አንዱ ነው፡፡ ለውርደታችን ምሳሌ ይሆን እንደሆነ እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲን የሚወክል ቁመና ያለው ፓርቲ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
ኢድአን ባለፈው ክርክር ወቅት እንቅልፍ ሲያሰቸግራቸው በነበሩት በአቶ ትዕግሰቱ ደበላ የተወከለ ቢሆንም “አዲሰ አበባ የመቶ ዓመት እድሜ ያላት ሀገር ናት” ብሎ በስህተት ጀምሮ በቅጡ እንዳንከታተለው አድርጎናል፡፡ በመጀመሪያ አዲስ አበባ ሀገር አይደለችም፣ ሲከተል መቶ ዓመት ብቻም አይደለችም፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው ያላት ብሎ ጫካ ገባ ጫካ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ 40 ዓመት ሙሉ የመቶ ዓመት ታሪክ ያወራል፡፡ ኢህአዴግ ስዓትና ጊዜው ቆሞበት ከሆነ አቶ ትዕግሰቱ ደበላም ይህንኑ መቀበላቸው ትክክል አይደለም፡፡ በሌላ በኩል አቶ ትዕግሰቱ ደበላ ባለፈው ፓርቲያቸው በገጠር መንደር ምስረታ ሲያነሳ የነበረውን ሃሳብ ወደፊት ለከተማ ምስረታ እንደሚውል የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ “ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” እንደሚባለው በየክልሉ ያሉት ከተሞች ከተማ ቢሆኑ ብዙ ለውጥ እንደሚኖር ኢድአን የገባው አይመስልም፡፡ የኢድአን ከመንደር መስረት የሚመጣ ከተሜነት፤ ከኢህአዴግ ከገጠር በኋላ ከተሜነት ከሚለው አተያይ ልዩነቱ አልታየኝም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ትዕግሰቱ ደበላ ያለችውንም አጭር ጊዜ ሳይጨርሱ ትንፋሽ ይሁን ሃሳብ አጥሯቸው ለአቶ መኩሪያ ኃይሌ የሚወዱትን የኮብል ሰቶን ጉዳይ አቀብለው ክርክሩን አቁመዋል፡፡
በአቶ ትዕግሰቱ ደበላ አቀራረብ ያልተደሰቱ የሚመስሉት አቶ ግዑሽ ገ/ስላሴ ቀጣዮችን ክፍሎች በሙሉ ይዘውታል፡፡ ዛሬም እኛ ከተመረጥን እንዲህ እናደርጋለን የሚል ከልብ ያልሆነ ቃል በተደጋጋሚ እየገቡ መግቢያ በሚመስል ነገር ጊዜ ሲያባክኑ ነበር፡፡ ከአቶ ግዑሽ ነጥብ አርጌ ልይዝላቸው የቻልኩት የኢህአዴግ “የፓርቲ አክራሪነት” በሚል የገለፁት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ጥቃቅን እና አነስተኛ በሚል የተደራጀው በአብዛኛው የፓርቲ አባል ነው በሚል እቅጩን ተናግረዋል፡፡ ለማነኛውም አቶ ግዑሽም ቢሆን ሰዓት በአግባቡ ለመጠቀም ሳይችሉ ጊዜው አልቆዋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ጊዜም ቢሰጣቸው ምን ማድረግ እንደሚችሉ አላውቅም፣ አቅማቸውም ከዚህ የሚዘል አይደለም፡፡
ዋሊያው መኢአድ አቶ ካሳሁን አበባው በተባሉ አዛውንት የመጀመሪያውን ክፍል የጀመረ ሲሆን፣ የከተማ መልሶ ማልማትን አስመልክትው በተለይ ከማህበራዊ ኑሮ አንፃር በሰፈር ያሉ አሉባልታዎች ጭምር የያዙ ቅሬታዎችን አቅርበዋል፡፡ እንደ ፓርቲ ለአዲስ አበባ ህዝብ፣ በሌሎች ከተሞች ለሚኖር ከተሜ እና ርዕሱ የሚጠይቀውን “ኢንዱስተሪና ከተማ ልማትን” የሚመለከት አልነበረም፡፡ የመኢህአዱ አቶ ካሳሁን ከመኢብን አቶ ተሾመ ግልፅነት መማር ሰልአልፈለጉ አልተማሩም፤ መንግሰት መሆን የሚያስችል ዕጩ እንዳላቀረቡ እያወቁ መንግሰት ብንሆን ብሎ ማላገጥ ተገቢ አልመሰለኝም፡፡ በደርግ የተወረሱ ቤቶቸ አብዛኞቹ ፈረስው ማለቃቸውን ዘንግተው፤ የተወረሰ ቤት እንመልሳለን፡፡ የመንግስት የገቢ ምንጭ ውስን መሆኑን ዘንግተው፤ ይሁን ሳያውቁት ቤት በነፃ እየሰራን እንሰጣለን፡፡ እንደ ፓርቲ አማራጭ ማቅረብ እየተጠበቀባቸው ህዝብ እናማክራለን፡፡ እና ሌሎች ተመሳሳይ ፋውል ሰርተው ጊዜያቸውን አጠናቀዋል፡፡
ሌላኛው ተከራካሪ ተሰፋሁን አለምነህ መኢአድን  ወክሎ ለክርክር መመጣቱ በራሱ አስገራሚ ነው፡፡ ከምርጫ በግሌ እራሴን አግልያለሁ ማለቱን ካልቀየረ በስተቀር ማለቴ ነው፡፡ ተሰፋሁን ያለውን የሀገር ፍቅር ሰሜት አደንቀዋለሁ፡፡ በፌስ ቡክ በሚሰጣቸው አስተያየቶቹም ቢሆኑ ሰሜታዊነት እንደሚታየበት ያስታውቃል፡፡ በክርክሩም ይዞት የቀረበው ይህን ሰሜታዊነቱን ነው፡፡ የደም ሰሩ እስኪገተር ድረስ እየተጨነቀ በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ጥቅም የማያስገኙ ለምሳሌ “ጥሬ እቃው ዲላ፤ ፋብሪካው አድዋ” የመሳሰሉ አስተያየቶች ለተንኮለኞቹ የህውሃት ካድሬዎች የሚመች ነው፡፡ በ1997 የበድሩ አደምን ንግግር እንዴት አድርገው እነደተጠቀሙበት ማሰተዋል ያስፈልጋል፡፡
ተሰፋሁን አብረውት ክርክር ከመጡት ሰው ጋር ተመካክረው እንዳልገቡ ግለፅ ነው፡፡ ተሰፋሁን በፌስ ቡክ ካሰራጨው አቋሙ ጋር የሚሄደው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመኢህአድ ጋር እንዲሰለፍ እንጂ መኢህአድን እንዲመርጥ እና መንግሰት እንሆናለን የሚል መልዕክት የለውም፡፡ መጨረሻ ላይ በችኮላ የመኢህአድ አቋም ብሎ የገለፀው “ለባለ ሀብቶች ብድር ከወለድ ነፃ ይሰጣል” ያለው ግን በስህተት እንደሆነ አድርገን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ በማጠቃለየውም ቢሆን ተሰፋሁን ያስተላለፈው መልዕክት “ነፃነት በነፃ ስለማይገኝ ለመሰዋዕትነት እንዘጋጅ” የሚል ነው፡፡ ለማነኛውም መኢህአድ ድሮ የምናውቀው ባለ ግርማ ሞገሱ አይደለም፡፡ ረጅም እድሜ አለው የሚለው ብቻ ነው አብሮት ያለው፡፡ ኢ/ር ሀይሉ ሻወል በህይወት እያሉ መኢህአድ እንዲህ ሲሆን ማየታቸው ምን ሰሜት እንደሚሰጣቸው እና የእርሳቸው ሚናም ምን እንደሆነ የሚነግሩን አይመስለኝም፡፡ ለማነኛውም የመኢህአድ አወራረድ “ጎፈርያም ውሻ” የሚያስንቅ ነው፡፡

የኢህአደግ ተወካይ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ክርክር የጀመሩት የቀድሞ ስርዓት በመክሰስ ነው፡፡ ከተሞችን የከሰሱበት ድህነት እና የፀጥታ ችግር ምንጩ አሁን በመንግሰት ሹም እንዲሆኑ ያደረጋቸው የአሁነ መንግሰት የዛን ጊዜ “ወንበዴ” የሚባለው ነበር፡፡ ኢህአዴግ ከተማ የሚባል ነገር ለዕድገት ወሳኝ መሆኑን ለማወቅ ከአሰር ዓመት በላይ አንደወሰደበትም የማናውቅ አስመስለውታል፡፡ የከተማውን ችግር መፍታት ሲያቅተው የጀመረው “የአደገኛ ቦዘኔ” አዋጅ የበለጠ አደገኛ ሲሆንበት የተወው መሆኑን ከአቶ መኩሪያ ይልቅ እንደምናውቅ የሚነግራቸው አላገኙም፡፡ የመኢህአዱ ተወካይ አቶ ተሰፉሁን አለምነህ በስሜት ተውጦ ሰለ ቁጥር የነገራቸውን የውሸት ቁጥሮች እንደወረደ የምንቀበል እስኪመስለን ድረስ 8 ሚሊዮን ሰራ ፈጥረናል ሲሉ፣ ሰምንት ሚሊዮን ችግኝ መትከል እስኪመስለን ድረስ ነው፡፡ ኢህአዴጎች ምንም ዓይነት የፖሊሲ ለውጥ እንደሌላቸው በጀመሩት የተሳሳተ መሰመር ልክ ነው ብለው በድርቅና እንደሚቀጥሉ ለማረጋገጥ ነው መድረኩን የተጠቀሙበት፡፡ ያመኑት የመልካም አሰተዳደር ችግር፣ የአገልግሎት አቅርቦት ችግር በቁልምጫ ኪራይ ስብሳቢ በማለት የሚጠሩትን ጉበኝነትና ዘራፊነት ስልጣናቸውን ስጋት ላይ የሚጥል ሳይሆን ተራ ሊሻሻል የሚችል ነገር አድርገው አቃለው አይተውት፤ እኛም በዚሁ ልክ እንድናይ ይፈልጋሉ፡፡
የኢህአዴጉ አቶ አህመድ አብተው ብዙ ሰው የማያውቃቸው የኢንዱስትሪ ልማት ለማሰረዳት የቀረቡ የኢህአዴግ ሹም ናቸው፡፡ ተናዳፊ ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ እንደማነኛውም የኢህአዴግ ሹም የድሮ ሰርዓት በመክሰስ ነው ክርክሩን የጀመሩት፡፡  እንዲህ እያሉ “የኢህአዴግ ኢንድስቱሪ ልማት ፖሊሲ ሲቀረፅ - ድህነት በተንሰረፋበት፣ የግል ባለሀብት በሌለበት፣ ሁሉም ነገር በመንግስት ቁጥጥር ስር በሆነበት፣ ማህበራዊ ልማት በሌለበት፣ ካፒታል በሌለበት ወዘተ ነው” ብለው ጀምረው፤ በማስከተልም “ፖሊሲው ሲቀረፅ መሬትና ጉልበት ብቻ ነበር ያለን፡፡ ለዚህ ነው ግብርና መር መሆን አለበት ያልነው፡፡” ብለዋል፡፡ ይህን ሲሉ የፖለቲካ መሰረቴ አርሶ አደሩ ነው በሚል ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ፖሊሲው እንደተቀረፀ የሚያውቅ ዜጋ አለ ብለው አይገምቱም፡፡ የኢህአዴጎች ዋነኛው ችግር መረጃም ሆነ ማስረጃ ከተፈቀደላቸው አንድ ምንጭ ብቻ የማግኘት አባዜ እና ሌላውም እንዲሁ እንዲሆን ማሰብ ነው፡፡
አቶ አህመድ አብተው የኢንዱስትሪ 20 ከመቶ እድገት ያስታወሰኝ አንድ ፋብሪካ ባለበት ሀገር አንድ ሲጨመር እድገቱ መቶ እንደሚሆን ያለማወቃቸው ነው፡፡ እዚህ ግባ የሚባል ኢንዱስትሪ በሌለበት ሀገር 20 ከመቶ አይደለም መቶ ከመቶ እድገትም ብዙ ለውጥ አያመጣም፡፡ በ24 ዓመት የኢህአዴግ ጉዞ ሰንት ሰው ከገጠር ግብርና ወጥቶ ኢንዱስትሪውን ተቀላቀለ የሚለው ትርጉም ያለው መከራከሪያ ሊያቀርቡልን አልቻሉም፡፡ በ24 ዓመት አሁንም “ጅማሮ ታይቶዋል” የሚል ገዢ ፓርቲ ነው ያለን፡፡ በሃያ አራት ዓመት የውጭ ባለሀብት ተነሳሽነት እና ፍላጎት በማሳይት ላይ ይገኛል፤ መቼ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ አይታወቅም፡፡ 80 ከመቶ ኢንዱስትሪ በግል ባለሀብት የተያዘ ነው በአሁኑ ስዓት 70 ከመቶ በሀገር ውስጥ ባለሀብት የተያዘ ነው ይሉናል፡፡ መንግሰት በሜጋ ፕሮጀክት በመሳተፍ መሰረት በመጣል ላይ ይገኛል፡፡ ግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማታችን ፍሬ እያፈራ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ኢህአዴግ ከሃያ አራት ዓምት በኋላ የሚመግበን ተሰፋ ነው፡፡
አቶ አህመድ ከሌሎች የኢህአዴግ ተወካዮች የሚለዩት በማንበብ ማጠቃለላቸው ብቻ ሳይሆን ሰዓትም ሳያልቅ አቁመዋል፡፡ ለማነኛውም አቶ መኩሪያም ሆኑ አቶ አህመድ ተናዳፊነት አልታየባቸውም፡፡ ይህ ኢህአዴጎች ያመጡት በጎ አቀራረብ ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ለነገሩ ቀድመው ያፈዘዙትን ተቃዋሚ አሁን ቢነድፉት ሌላ ስህተት ከመሆን አልፎ ጥቅም አያመጣም፡፡ ኢህአዴጎች በሌሎች የሚዲያ ቅስቀሳዎች ተቃዋሚዎችን ተላላኪ እያሉ መሳደባቸውን ባያቆሙም በፊት ለፊት ይህን ማቆማቸው አንድ በጎ እርምጃ አርገን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ አማራጭ ለሌለው ምርጫ ከዚህ በላይ መዘጋጀትም አያሰፈልጋቸውም፡፡ ይህም እነርሱ ሆነው ፍርሃታቸው ልክ አጥቶ ነው እንጂ በምድር ላይ ያለው ሀቅ ይህን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ፍርሃታቸው ልክ ማጣቱን ለመረዳት ግን በፖሊሲ ጣቢያዎች የቁሙትን አዳዲስ ፒክ ሀፕ የፖሊስ መኪኖች መመልከት ይበቃል፡፡ አሁን ይህ ምርጫ ምርጫ ሆኖ ይህ ሁሉ ዝግጅት ያስፈልገዋል ወይስ ያልገባኝ ነገር አለ?
ቸር ይግጠምን


No comments:

Post a Comment