Friday, November 27, 2015

ድርቅ በአንባገነን ስርዓት ችጋር ነው!!!




ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; www.girmaseifu.blogspot.com
“From Derge I to Derge II’ - ከደርግ አንድ ወደ ደርግ ሁለት የሚል ፅሁፍ ኢህአዴግ ሀገሪቱን በተቆጣጠረ ጥቂት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያን ሪቪው በሚባል መፅሄት ላይ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ ፀሃፊ ፐ/ሮ ጌታቸው ሀይሌ ይመስሉኛል፡፡ ታዲያ  ደርግና ኢህአዴግ በዘወትር ውሎዋችን ጭምር ሲመሳሰሉብኝ ይህ ፅሁፍ ትዝ ይለኛል፡፡ የፅሁፉ ዝርዝር ይዘት በምን በምን እንደሆነ ባላስታውሰውም ብዙ ግን መመሳሰል እንዳለ ይገባኛል፡፡ አሁንም ይህን ትዝታዬን የቀሰቀሰው ዋነኛው ነገር የዘንድሮ እኛ ችጋር/ርሃብ የምንለው እነርሱ/ገዢዎቹ ደግሞ ድርቅ አለ፣ እናንተ የምትሉት ችጋር ግን የለም የሚሉት መሬት ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በእኔ እምነት በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ድርቅ ርሃብ/ችጋር ሆኖ የዜጎች ህይወት እንደሚቀጥፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡
በ1977 የነበረው ክፉ ቀን ዜጎችን እንደሚጨረስ መረጃ ያላቸው ሁሉ የዜጎች ህይወት እንዳይቀሰፍ ሲጮሁ የዚያነው “ደርግ” ባሕላችንን በድምቀት እንዳናከብር የኢምፔራሊስት ወሬ ነው እያለ፣ ሲፈልግም ሰምቶ እንዳልሰማ ጭጭ ብሎ አሁን የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ሀውልት፣ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ቢሮና አዳራሻ ያለበትን ህንፃ እና ሌሎችም በጊዜው ድንቅ የሚባሉ የልማት ስራዎችን/ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፣ ቢራ ፋብሪካዎች፣ ወዘተ/ እየሰራ በጎን ደግሞ ለባሕሉ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠር ህዝብ ለሰልፍ ማድመቂያ ስልጣና እያደረገ ነበር፡፡ ሰልፈኞችም ባህሉን በሚያደምቅ ሁኔታ የተለያየ አልባሳት እየተገዛላቸው ይለብሱ ነበር፡፡
በቅርብ ርቀት ግን ዜጎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ተርበውና ታርዘው ምትክ የሌለው ህይወታቸውን ይነጠቁ ነበር፡፡ በወቅቱ የነፃ አውጪ ቡድንኖች ይህን ለማጋለጥ ደፋ ቀና ሲሉ ወደ ሀገር ውስጥ ለባህሉ የገባውን ውስኪ ቁጥር እንዲሁም  የገንዘቡን መጠን እያጋነኑ ለፕሮፓጋንዳ ጭምር ሲነግሩን ነበር፡፡ ደርግ ባህሉን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ አክብሮ ሲጨርስ የፖሊት ቢሮው አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ድርቁን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያሰችል ዕቅድ አለኝ በማለት - እግረ መንገዱንም “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን” የሚል መፈክር ይዞ ብቅ አለ፡፡ አስከትሎም ድርቁን ለማድረስ አማፂያን/ገንጣይ አስገንጣዮች/ ለህዝቡ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት እየሆኑ ነው ብሎ ለችግሩ የተገላቢጦሽ ምላሽ ይሰጥ ጀመር፡፡ /በነገራችሁ ላይ እነዚህ  ገንጣይ አስገንጣይ የተባሉት ኃይሎች እርዳታ እንዳይደርስ ሲያደናቅፉ አልነበረም የሚል አቋም የለኝም፡፡ ይህን ስለማድረጋቸውና የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሰሩትን ስራ የሚገልጥ የራሳቸው ኤግዚቢሸን ምስክር ነው፡፡/
እናላችሁ ዛሬ የዚያን ጊዜ ነፃ አውጪዎች የደርግን ቦታ ይዘው ከሰላሳ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈፅሙ ማየት አንዴ ብቻ ሳይሆን ሲደጋግሙት መስማትና ማየት ህሊና ማቁሰሉ አይቀርም፡፡ ብአዴን የሚባል የኢህአዴግ እህት/ወንድም ድርጅት 35 ዓመት ሞላኝ ብሎ ደርግን በሚያስንቅ ሁኔታ ሲጨፍር ሲደንስ ከርሞ፣ ጭፈራውን ቢያንስ በአደባባይ ያለውን እንደጨረሰ ስብሰባ ቢጤ ተቅምጠው ችግሩ አሳስቦናል ብለው በዜና ሰማን፡፡ እነዚህ ሰዎች የፕሮፓጋንዳ ሰዎቻቸው ከኢሠፓ ካልመጡ በሰተቀር እንዲ ዓይነት መመሳሰል ከየት ይመጣል ብዬ ልገምት፡፡ ለዚህ ነው ከደርግ አንድ ወደ ደርግ ሁለት የሚለው ፅሁፍ ከሃያ ዓመት በኋላ ትዝ ያለኝ፡፡ ይህ ፅሁፍ ያለው ሰው ጀባ ቢለን ከድሮ ጀምሮ ያለውን መመሳሰል ልናይበት እንችላለን፡፡ አንባገነን ሰርዓት ሄዶ አንባገነን ሰርዓት ቢመጣም ድርቅ ርሃብ እንዳይሆን ማድረግ አይችልም፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን ማንም በስልጣን ላይ ቢመጣ በአሁኑ ጊዜ መወዳደሪያ ነጥብ አድርጎ መቅረብ ያለበት ስልጣን በያዘ በአምስት ዓመት ውስጥ ዜጎች በፍፁም ችጋር ውስጥ እንደማይገቡ የሚያረጋግጥ መሆን አለበት የሚል አቋም አለኝ፡፡ ሌሎች የልማት ስራዎች ሁሉ ይህን ለማረጋገጥ እገዛ የሚያደርጉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ሃያ አራት ዓመት በግብርና መር ፖሊስ ሲመራ የኖረ መንግሰት ለተከታታይ አሰር ዓመት በሁለት አሃዝ እድገት አስመዝግቢያለሁ እድገቱ በአብዛኛው የተገኘው ከግብርና ነው ሲል የከረመ የፖለቲካ መሪ ዛሬ “ኤሊኖ” የሚባል ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የተፈጥሮ ችግር ገጥሞን ነው ቢሉን የምንሰማቸው አይሆንም፡፡ ፕሮፓጋንዲሰቶቹ “ተፈጥሮ በቁጥጥር ስር እናውላለን” የምትለዋን መፈክር ረስተውት ይመስለኛል እንጂ የሰሞኑ መግለጫ ሁሉ የደርግ ጊዜ መግለጫ ነው የሚመስለው፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ጉደኛው “ኢቢሲ - የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን” ድርቁ የእኛ ብቻ አይደለም ሀብታሞቹም ሰፈር ጎራ ብሎዋል ለማለት ይመስላል፣ የደቡብ አፍሪካ “አርብቶ አደሮች” ችግር ላይ መሆናቸውን ለማሳየት ሙከራ አድርጎዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካዎቹ አርብቶ አደሮቹም ሆኖ ከብቶቹ እንዴት ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሆኑ ግን በደጋፊነት የቀረበውን ፊልም ተመልክተን  ግምት የምንወስድ አይመስላቸም፡፡ ንቀውናል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ገበሬዎች በድርቁ ምክንያት የመኖ እጥረት ስለሚፈጠር መኖ ቢኖርም በድርቁ መነሻ ዋጋው ውድ ስለሚሆን ብዙ ከብት ያላችሁ ብትሸጡ ይሻላል የሚል የባለሞያ ምክር ነው የተሰጣቸው፡፡ ይህም በገበያ ላይ ከሚፈለገው በላይ አቅርቦት ስለሚጨምር የከብት ዋጋ መቀነሱ ሀቅ ነው፡፡ ይህ ከእኛ አርብቶ አደሮች ጋር እንዴት እንደሚገናኝ አልገባኝም፡፡ የገባው ካለ ቢያስረዳኝ ደስታውን አልችለውም፡፡
ልብ በሉ የእኛ አርብቶ አደሮች ካሉት ከብቶች ግማሹን ሸጠው ቀሪውን የማትረፍ አማራጭ ላይ አይደሉም፡፡ ከብቶቹ በቁም ደርቀው የሚቀምሱት አጥተው በቆሙበት መውደቅ ነው፡፡ የእኛ አርብቶ አደሮቹ በሚያሳዝን ሁኔታ ለከብቶች አይደለም ለልጆቻቸው የሚሰጡት አጥተው ልጆችም እራሳቸውም ቀዬ ለቀው የመንግሰት እጅ የሚጠብቁት፡፡ ይህ ጉደኛ ቴሌቪዥን ታዲያ ምን ማለቱ ነው ማለታችን አይቀርም፡፡ ለማነኛውም በደርግ ጊዜም ተመሳሳይ ዜናዎች በቴሌቪዝን እንመለከት ነበር፣ በሀገራችን የዚህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር የመጀመሪያ አይደለም በሚል በሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ የነበረን ክፉ ቀን ያስተዋወቁን እነዚሁ ጉደኛ የደርግ ፕሮፓጋንዲስቶች ነበሩ፡፡ በአሜሪካም ተመሳሳይ ችግር አለ ምን ያስገርማል ይሉን ነበር፡፡ በዓለም ላይ ድርቅ እንደሚኖር ማንም ያውቃል ልዩነቱ አምባገነኖች ባሉበት ብቻ ሀገር ድርቅ ችጋር እንደሚሆን የምንረዳ አይመስላቸውም፡፡
ዲሞክራሲያዊ መንግሰት ባለበት ሀገር  ድርቅ በሚኖርበት ወቅት ዋነኛው ችግር የዜጎች ህይወት አደጋ ላይ መውደቅ አይደለም፡፡ የምግብ ዋጋ መናር ትልቅ ጉዳይ ይሆንና መንግሰታት ይህን መቆጣጠር ካልቻሉና ዜጎችን የዋጋ ንረት ከሚፈጥረው ችግር ለመታደግ የሚያስችል የፖሊሲ እርምጃ ካልወሰዱ ስልጣናቸው አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ የእኛ አምባገነኖች በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ነብሱ ከስጋው ልትለያይ እያጣጣረ ችግሩ በቁጥጥር ላይ ነው ይሉናል፡፡ ስልጣናቸውም ከሌላው ጊዜ በተለየ ይመቻቸው ሁሉ ይመስለኛል፡፡
ለማጠቃለል የትግራይ ርዕስ መሰተዳደር ቁንጮ አቶ አባይ ወልዱ የሰጡት መግለጫ ላሰታውሳችሁ እና ልሰናበት፡፡ አቶ አባይ ወልዱ እንዲህ ይላሉ “ችግሩ በጥቂት ቀበሌዎች ውስጥ ብቻ ነው፣ ይህ ችግር ደግሞ ከክልሉ አቅም የሚያልፍ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከፌዴራል መንግሰት ጋር በመሆን እርዳታ ማቅረብ ጀምረናል” የሚል ነው፡፡ ሀገራችንን የሚመሩት ሰዎች ሁለት መስመር አንዱ ከአንዱ ጋር የማይገጭ ማቅረብ  እንደማይችሉ ማሳያ ነው፡፡ ከክልሉ አቅም ውጭ አይደለም ብለው ደቂቃ ሳይቆዩ ከፌዴራል መንግሰት ጋር በመተባበር ይላሉ፡፡ በዚህች ሀገር ጋዜጠኛ ቢኖር አፋጦ ከስልጣኛቸው ሳያወርድ እይመለሰም ነበር፡፡ ምን ያረጋል ይህ አልሆነም፡፡ በመጡበት መንገድ መርጠው ይሆናል፡፡ እነርሱም መውረድ አልፈለጉም፡፡ እሰከዚያው ድረስ በዚህ ችግር መሃል እነዚህን ሰዎች መሪዎች ብሎ የተቀበለ ህዝብ ምርጫው ነው ብለን ምርጫውን ማክበር አለብን፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!

Thursday, November 12, 2015

ፕሮፓጋንዳው ስብዓዊነት ይኑረው!!! ሰው እየሞተ ነው!! ቁጥሩን ቤቱ ይቁጠረው!!!



በሀገራችን ያለው ድርቅ ክብደት ከ1977ጋር የሚመሳሰል እንደሆነ የመንግሰት ሹም ከሸገር ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ምልልስ አረጋግጠዋል፡፡ ልዩነቱ ግን አሁን መንግሰት ይህን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም አለን የሚልው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አቅም ግን መሬት ላይ ወርዶ ስናየ ወኔ ብቻ ይመስላል፡፡ ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ የፈረንጆቹን ደጅ እንዳይጠኑ የሚያደርጋቸው አይደለም፡፡
“ደርግ” በ1977 የነበረፈውን ድርቅ ለዓለም ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን የዚያን ጊዜ በነበረው ቀዝቃዛ ጦርነት መነሻ በሁለቱ ጎራ በሚደረገው ፍልሚያ ግዳይ የሚጣልብት ወቅት ነበር፡፡ ደርግ ለዓለም ህብረተሰብ ጥሪ ባቀረበበት ወቅት የሶሻሊስቱ ተከታይ በመሆኑ ይህ ጎራ ይህን ድጋፍ የሚያደርግበት አቅም የሌለው ሲሆን ይህን ለማድረግ አቅም ያላቸው ምዕራባዊያን ግን ውጤቱን በደንብ ሳናየው ድጋፍ ላለመስጠት መቁረጣቸው ለችግሩ ክብደት አንዱ እንደ ነበር ለመረዳት ሊቅ መሆን አያስፈልግም፡፡ በተጨማሪ ለ1997 ድርቅ ተገቢው ምላሽ በምዕራባዊያን እንዳይሰጥ በወቅቱ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት በተለይ ህወሃት እና ሻቢያ የተጫወቱት ሚና ቀላል የማይባል ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ሆነን ስናየው ሰብዓዊነትን ለፖለቲካ ጥቅም እንዳዋሉት ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የኢህአዴግ መንግሰት ከምዕራባዊያኑ ጋር ያለው ቅርበት ከደርግ እንደሚሻል ስለሚታመን በተጨማሪ ህውሃትና ሻቢያ በዛን ጊዜ የሰሩትን ዓይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለመስራት የሚችል ታጣቂ ሀይል ባለመኖሩ ችግሩን ለመቋቋም በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ መንግሰት አቅሙ የከብቶቹን ህይወት ለመታደግ ለምን አልተጠቀመበትም? ካልቻለ ደግሞ ምዕራባዊያኑ ድጋፍ ለማድረግ ከፈለጉ አሁንስ ቢሆን ከብቶቹ ሳይሞቱ እንዲደርሱልን ለምን አልተደረገም? የሚለው ጥያቄ ለማንሳት አርብቶ አድር መሆን አይጠበቅብንም፡፡
ሁሉም የሚረዳው አንድ ሀገር በድርቅ መቼም ቢሆን ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ይህ በዓለም ላይ ተደጋጋሚ ክስተት እንደሆነ ማንም ያውቃል፡፡ ድርቅ ሲኖር ግን ይህን ድርቅ የሌላ ሶሰተኛ ሀገር ድጋፍ ሳይጠየቅ ለመፍታት አቅም መፍጠር መቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባላት ስነ ምህዳር ከዚህ የተሻለ ማድረግ እና ለሌሎች መትረፍ ይገባት ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አሰማት ሳይሆን ሊተገበር የሚችል የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ ነው ብሎ የሚያምን መንግሰት ያስፈልጋል፡፡ ኤክስፖርት የሚደረግ ታንክ ሰራን በፍፁም በዚህ ወቅት ሊያኮራን የሚችል ስ አይደለም፡፡ አሁን የምንረዳው መንግሰት ችግሩን ሪፖርት አድርጊያለሁ ማለትን እንደመውጫ ቀዳዳ እየተጠቀመበት መሆኑን ነው፡፡
አሁን በመሬት ላይ ያለው ሀቅ በምግብ እና ውሃ እጥረት ከብቶች በብዛት እየሞቱ ሲሆን፤ መቼም እንደ እንሰሳቱ በብዛት ሰው እየሞተ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የነበረባቸው የጤና ችግር አግርሽቶም ይሁን አዲስ ጤና መቃወስ ተፈጥሮ ህፃናት ብቻ ሳይሆን አረጋዊያንም ሆኑ ባለጡንቻው ጎልማሳ የሚሞቱበት ሁኔታ እንዳለ ግን መካድ አይቻልም፡፡ ከዚህ ስንነሳ በምግብ እጥረት ምክንያት ሞት የለም ብሎ ፈሊጥ፤ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሁለት ህፃናት በቀን ይሞታሉ ያለው ለሌላ ዓላማ እና የሀገር ገፅታ ለማበላሸት ነው የተባለውን የመንግሰት ሹም መግለጫ ስንሰማ ከማፈር ውጭ ምን ልንል እንችላለን፡፡ የመንግሰት ሹሞቸ ፕሮፓጋንዳውን ጋብ አድርገው ሰብዓዊነት በመላበስ እየሞተ ያለውን ሰው መታደግ የግድ ነው፡፡ ስንት ሰው ሞተ ቤቱ ይቁጠረው፡፡
አንድም ሰው በድርቅ አልሞተም የሚል መግለጫ የሰጡትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ከላይ እንደገለፅኩት ቀደም ሲል በአካባቢዎቹ የኖረው ችግር ላይ ሲታከል ሰዎች እንደሚሞቱ መገንዘብ አቅቷቸው ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የተደረገ መሆኑን ማውቅ ግድ ይለናል፡፡ በዚህ ፕሮፓጋንዳ ማፈራችን እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ የምናፍረው ደግሞ ከ30 ዓመት በኋላ ድርቅን ለመቋቋም የሚችል ህብረተሰብ ሊገነባ የሚችል ስርዓት መመስረት ያለመቻላችን ነው፡፡ ይህን መንግሰት ዛሬም ስህተቱን “በኤሊኖ” ክስተት አሳቦ በስልጣን እንዲቆይ የፈቀድነው እኛው ነን፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን በምንም መመዘኛ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በፈለገ የተራዘመ የተፈጥሮ ችግር ጊዜ ቢሆን እንኳን ምግብ ለመለመን የማትችል ሀገር ለማድረግ የሚያስችል ፖሊሲና ሰትራቴጂ የሌለው መንግሰት እንዳይኖር ማድረግ ካልቻልን ምርጫው የራሳቸን ነው፡፡ ምን ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ እኛ ከላፈቀድን መሬትን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ፤ ሴፍቲኔት በሚባል የመንግሰት ድጎማ ስር ህዝቡን በተራዘመ ሰንፍና እንዲኖር በማድረግ በአምስት ዓመት በሚመጣ የይስሙላ ምርጫ ካርድ አግኝቶ አገዛዙን ለማራዘም የሚፈልግ መንግሰት ይህን ዓይነት ሰርዓት ሊዘረጋ አይችልም፡፡ እንዲህ ሲያደርገን እንቢ ብለን መከላከል ምርጫው የእራሳችን ይሆናል ማለት ነው፡፡
በተለጠጠ ዕቅድ ተሰፋ ውስጥ (የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ልብ ይሏል) የከተማ ነዋሪውን ሸምቶ ለማብላት የውጭ ሀገር የሰንዴ ገበያን አማራጭ ያደረገ መንግሰት፤ በሀገር ውስጥ በእርሻ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዘመናዊ ገበሬዎች እርሻ መሰሪያና ሌሎች ግብዓቶች ድጎማ አድርግ ሲባል ነፃ ኢኮኖሚ ነው ይለናል፡፡ አንድ በዘመናዊ እርሻ ለመሰማራት የሚፈልጉ ዘመናዊ ገበሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰበሰቡት ስብሰባ ላይ ከጎኔ ቁጭ ብለው የነገሩኝ አስደማሚ ነገር “መንግሰት ሰንዴ ለመግዛት በጨረታ የሚያባክነው ጊዜ እና ገንዘብ ለእኛ ድጋፍ ቢያደርግ ለጨረታ ከሚባክነው ጊዜ ባነሰ በሀገር ውስጥ ሰንዴ ለማምረት እንችላለን” የሚል ነው፡፡ ይህን ሀቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ለግብርና ሚኒሰትሩ የኪራይ ስብሰቢዎች ወሬ ነው የሚሆነው፡፡ ግብርና መር ስትራቴጂና ፖሊሲ ብለው ምግብ በሀገር ውስጥ ማሟላት ሳይችሉ ለዘላለም ሊገዙን ሲፈልጉ እሺ ብለን አለን፡፡
ለማነኛው ኢትዮጵያ ሀገራችንን ምድሯ “በኤሊኖ” ክስተት ይሁን በሌላ “ድርቅ” ጎብኝቷታል፡፡ ይህ ድርቅ አድጎ ደግሞ ዜጎችን ህይወት ቀሰ በቀስ እየወሰደ ነው፡፡ ይህን “ችጋር” ለመቋቋም ዜጎች በጋራ መነሳት ይኖርብናል፡፡ ፈረንጆቹ ይህ ውጤት እንዲቀለበስ ከልብ ከፈለጉ አንድም ሰው ሳይሞት ሊደርሱ የሚያስችል ሰርዓት አላቸው ነገር ግን የሰጡት ድጋፍ ህይወት አድን መሆኑ እንዲታወቅ ችግሩ እስኪሰማን ብዙ ሀይወት መጥፋቱ በሚዲያ ታይቶ ቅሰቀሳ እስኪደረግ ሊዘገዩ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሃል ምትክ የሌለው የሰው ልጅ ህይወት ያልፋል፡፡ ይህ እንዳይሆን መንግሰት አሁን ከጀመረው ተራ ፕሮፓጋንዳ ወጥቶ ወደ ቀጥተኛ ህዝቡን ያሳተፈ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ይኖርበታል፡፡