ለዚህ
ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ በሪፖርተር ጋዜጣ የካቲት 13/2008 እትም እስጢፋኖስ ሲሜ የተባሉ ፀሃፊ “የመወዳደሪያ ምህዳር የጠበበባቸው የግል ባንኮች ተግዳሮት” በሚል
የፃፉት ፅሁፍ በማንበቤ ነው፡፡ ፀኃፊው በመግቢያቸው ላይ የገለፁትን “የፖለቲካ
ምዕዳር ጠቧል አልጠበበም የአንድ ሰሞን የኢህአዴግና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሩ መከራከሪያ አጀንዳ ነበር፡፡ ኢህአዴግ አለመጥበቡን፣
ተቃዋዋሚ ፓርቲዎችም መጥበቡን ሳያሳዩን እንዲሁ ጠቧል፣ አልጠበበም
በሚል ደረቅ ክርክር ብዙ “እድሜ ገዙ”” በሚል የተነሱበትን ፍሬ ነገር ፍሬ የሚያሳጣ ሀሳብ ደንቅረው ሲያበቁ ይህን ለፖለቲካ
ተንተኞች እተዋለሁ በማለታቸው እንደ ፖለቲከኛ ለመልሱ አቤት ለማለት ነው፡፡ የመወዳደሪያ ሜዳው ለግል ባንኮች ቢጠብም አሁንም በህይወት
አሉ፤ የምዕዳሩ ጥበት አማራጭ ሜዳ መፈለግ እስኪያስመኝ የጠበበው ግን በፖለቲካው በኩል መሆኑን እግረ መንገድም ለማሰታወስ ነው፡፡
አቶ እስጢፋኖስ
ለባንኮች ምዕዳር መጥበቡን የገለፀላቸው አዕምሮ ግን የፖለቲካ ጉዳይ ሲሆን መስመር ይዞ አቋም ለመውሰድ ሲያቅተው ማየት የፖለቲካ
ምዕዳሩ በዜጎች ሃሳብ በነፃነት በመግለፅ ላይ ያሳረፈውን ጫና የሚያሳይ ነው፡፡ አቶ እስጢፋኖስ የግል ባንኮች ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶች
ብለው ያነሱዋቸው ነጥቦች በሙሉ የፖለቲካ መልእክት እንዳለው ለመረዳት የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ የባንክ
ባለሞያ ከሆኑ መንግሰት ለምን በግል ባንኮች ላይ አላሰፈላጊ ጫና እንደሚያደርግ በፊት ለፊት ከሚሰጠው የብሄራዊ ባንክ ከሚያወጣቸው
መመሪያዎች የፊት ገፅ መግላጫ ጀርባ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካል- ኢኮኖሚ ትንተና መስመር እንደሚቃኝ ማወቅ አለባቸው፡፡
ለዛሬው
አቶ እስጢፋኖስ አውቀው ካልተኙ በኢትዮጵያ ውስጥ እሳቸው የአንድ ሰሞን መከራከሪያ ከነበረበት ጊዜ በላይ የፖለቲካ ምዕዳሩ መጥበቡን
ለማሳየት የተወሰኑ ነጥቦችን አንስቼ ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የምዕዳሩ መጥበብ ሌሎች አንባቢዎችም እንዲያስታውሱት
ያግዛል ብዬ ሰለማምን በአጭር በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡
ኢህአዴግ
የፖለቲካ ምዕዳሩን መለካት የሚፈልገው በሀገሪቱ ውስጥ የተፃፈ ህገ መንግሰት በመኖሩ፣ ይህን መሰረት አድርገው የወጡ የምርጫ ህጎች
ከመኖራቸው ጋር ነው፡፡ በተጨማሪ ኢህአዴግ ዓይናችሁን ጨፍኑ ብሎን ፍርድ ቤት ብትሄዱ ሁሉ መፍትሄ አለ ሊለን ይሞክራል፡፡ በኢትዮጵያ
ውስጥ ግን የህግ የበላይነት ብሎ ነገር የለም፡፡ ሰለዚህ ጉዳይ ሁሉ የሚያልቀው በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ነው፡፡ ህገ መንግሰቱ እንኳን
በፈለጉት ጊዜ በሚያወጡት አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ እንደሚሻር የእለት ከዕለት ምስክርነት የምንሰጥበት ነው፡፡
በእኔ
እምነት በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ለማካሄድ የሚያስችል የፖለቲካ ምዕዳር ፈፅሞ የለም፡፡ ገዢው ፓርቲ
በአውራ ፓርቲነት ለመቀጠል ወስኖ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ደፍጥጧቸዋል፡፡ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ለማካሄድ ከገዢው ፓርቲ በተጨማሪ ሌሎች
ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖር የግድ ይላል፡፡ በእኛ ሀገር አሉ እንደሚባሉት 73 ፓርቲዎች ዓይነት ሰርተፍኬት በቦርሳ ይዘው ምርጫ ቦርድ
በሚያዘጋጀው ግብዣ ላይ የሚገኙትን ማለት አይደለም፡፡
ተቃዋሚ
ፓርቲ ማለት አማራጭ ያለው በህዝብ ውስጥ ገብቶ ለመስራት አባላትን ለመመልመልና ለማደረጃት ከዚህ ውስጥም ብቃት ያላቸውን የፖለቲካ
መሪዎች ለማውጣት የሚችል ፓርቲ ማለት ነው፡፡ ይህን መንገድ ይዞ የነበረውን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መንግሰት ምን
እንዳደረገው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የፖለቲካ ምዕዳሩ ጠቧል ከሚሉት ፓርቲ አንዱ ስለነበር ሰለ መጥበቡ ለማሳየት
ለፖለተካ ፓርቲ ዋና ምሶሶ ናቸው በሚባሉት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የአንድነት ፓርቲን ምሳሌ በማድረግ ብቻ ላስረዳ፡፡
ሕዝባዊ ስብሰባዎችና ሰለማዊ ስልፉችን ማድረግ
አንድ
ፓርቲ ከደጋፊዎችና ከሌሎች የህብረተሰብ ከፍሎች ጋር የቅርብ ግንኙነት የሚያደርገው ህዝቡን ለለውጥ እንዲነሳሳ የሚያደርገው በተመረጡ
እና ለህዝብ ልብ ቅርብ ናቸው ያላቸውን አጀንዳዎች በማንሳት ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሰለማዊ ሰልፉችን በማድረግ ነው፡፡ ይህ በመንግሰት
ቀጥተኛ ተሳትፎ ማንነታቸው ባልታወቀ የደህንነት ሰዎች ጭምር በመታገዝ ተግባራዊ እንዳይሆን ይደረጋል፡፡ አንዱ በመንግሰት በቀጥታ
የሚደረገው ማደናቀፊያ የሚያደረጉት ማነኛውም ህዝባዊ ስብሳባዎች እና ሰላማዊ ስልፎች እውቅና በመከልከል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ
የመንግሰት ሰራተኞች ሳምንት ሙሉ ስራ የማይገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ከፍ ሲል ደግሞ ከፍተኛ ሹም ተብዬዎችም ከቢሮ ውጭ በመሆን
ውሳኔ እንዳይሰጥ ያደርጋሉ፡፡ በከፍተኛ ወጭ በግል ሆቴሎች ለሚደረግ ስብሰባም ፈቃድ አይገኝም ፈቃድ ሲገኝ ባለቤቶቹ “እንኑርበት”
የሚል የፍርሃት መልስ ይሰጣሉ፡፡ ኢህአዴግ በፈለገው አዳራሽ በፈለገው አደባባይ ስብሰባ ይጠራል፡፡ አቶ እስጢፋኖስ ይህ ሜዳው እኩል
መሆኑ ያሳያል?
ፓርቲዎች የሚሰሩበት ቢሮ አለማግኘት
አንድ
ፓርቲ የዕለት ከዕለት ስራውን ለማከናወን ቢሮ እንሚያስፈልገው ግልፅ ነው፡፡ ባንክ መቼም ቢሮ ለመከራየት ችግር አልተፈጠረበትም
ይልቁንም ህንፃው ሁሉ ባንኮችን ነው የሚጠብቀው፡፡ ፓርቲዎች ቢሮ ለመከራየት በሚያደርጉት ጥረት አከራዮችን ቢሮ እንዳያከራዩ ከፍተኛ
ጫና በመንግሰት መዋቅርና በደህንነት ተብዬ ሰዎች ይደረግባቸዋል፡፡
በሚስጥር ውስጥ ለውስጥ ቢሮ ኪራይ ከተፈፀመ በኋላ ውል እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ አንድነት በአብዛኛው በቢሮነት የሚጠቀምባቸው ቦታዎች
በአባላት በጎ ፈቃድ ለሌላ ጉዳይ ቢያከራዩት ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኙበትን በመልቀቅ እና በአባላት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነው፡፡
አንድነት በአዲስ አበባ በዋና ቢሮነት ሲጠቀምበት የነበረው ቢሮ በወር ብር35000/ሰላሳ አምሰት ሺ/ ለመከፍል ግዴታ ገብቶ እንደነበር
አውቃለሁ፡፡ ኢህአዴግ ግን በየወረዳ መስተዳደሩ እና በየቀበሌው የያዛቸው ቢሮዎች ኪራይ እንኳን መክፈሉን እርግጠኞች አይደለንም፡፡
በአንድ ወቅት በሰበታ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ያየሁት የኦህዴድ ፅ/ቤት፤ ዛሬም በአዲስ አበባ ካዛንችስ የኢህዴግ ፅ/ቤቶች በመስተዳድር
ጊቢ ውስጥ ናቸው፡፡ መቼም አቶ እስጢፋኖስ እነዚህን ነጥቦች ሲያነቡ ንግድ ባንክ እና ሌሎች የግል ባንኮች ትዝ እንደሚሎት አልጠራጠርም፡፡
የፖለቲካ ምዕዳር ለማጥበብ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መስሪያ ቦታ ከማሳጠት የበለጠ አሳማኝ ነገር ማቅረብ ይቻላል?
የፓርቲ ጋዜጣ ለማተምና ለማስራጨት መቸገር
አንድነት
ፓርቲ የሚያትማቸውን ጋዜጦች በየትኛውም ማተሚያ ቤት ማትም እንዳይቻል ተደርጎዋል፡፡ ይህን መልስ ለመስጠት ብለን የገዛነው የማተሚያ
ማሸን እና ጄኔሬተር ፓርቲያችን እንዲፈርስ የደህንነት መስሪያ ቤት ውሳኔ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ፓርቲያችን
በምንም ምክንያት የጠበበውን ምዕዳር በራሳችን መንገድ ለማስፋት የወሰድነው ቆራጥ እርምጃ ምዕዳሩን ባጠበቡት አካላት በኩል ተቀባይነት
ባለማግኘቱ ነው፡፡ ጋዜጣ አዙዋሪዎች በግልፅ እንዳያሰራጩ ይከለከላሉ፡፡ ሰብሰባ ማድረጊያ ቦታ፣ የመስሪያ ቦታ ብሎም ጋዜጣ ፅፎ
ዜጎች በገንዘባቸው ገዝተው ምን እንደምናስብ ለማወቅ ከመከልከል በላይ የፖለቲካ ምዕዳር መጥበብ በምን ሊለካ ይችላል?
የፓርቲ አባላት ምልመላና ማደራጀት ማደናቀፍ
አቶ እስጢፋኖስ
አንድ ባንክ ተቀማጩን ማሰፋት እንዳለበት ያምናሉ፡፡ አንድ ፓርቲም አባላትና ደጋፊዎቹን ማስፋት ግዴታው ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲ
አባላት ለመሆኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የፓርቲውን ጊቢ ረግጠው ሲወጡ በደህንነት ሰዎች በሚደረግባቸው ክትትልና ማስፈራሪያ በድጋሚ
ላለመምጣት ይወስናሉ፡፡ ማስፈራሪያ የሚደረገው በቀጥታ አባል ለመሆኑ ፍላጎት ላሳየው ግለሰብ፣ ለቤተሰቦቹ በሚሰራበት መስሪያ ቤት
በኩል ጭምር ነው፡፡ ብዙዎች ይህን ተቋቁመው አባል ሲሆን ከሚሰሩበት መስሪያ ቤት ይባረራሉ፡፡ የኢህአዴግ አባል ከሆኑ ግን ሹመት
ያገኛሉ፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ለፖለቲካ ስልጣን የሚወዳደሩ ሁለት አካላት በተለያየ ሁኔታ ሲዳኙ ምዕዳር ጠቧል ካልተባለ ምን ሊባል
እንደሚችል አላውቅም፡፡ ወደ ሌላ ከመሄዴ በፊት አቶ እስጢፋኖስን አንድ ጥያቄ ልጠይቃቸው፣ እርሶ ወይም ጓደኞቾ ለምን የፖለቲካ
ፓርቲ አባል ለመሆን “ፈራችሁ”? መልሶ ምንም ይሁን ምን የረፋችሁት የሚያስፈራራ ስለአለ እና እርሶም ስለሚፈሩ ነው፡፡ ምዕዳር
ማጥበብ ማለት ማስፈራራት ማለት ነው፡፡
የፓርቲ ፋይናንስ
ኢህአዴግ
አቶ እስጢፋኖስ በግልፅ እንደሚረዱት ብዙ የገንዘብ ምንጭ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ከፍ ሲልም በቀጥታ ነጋዴዎች ተሰብሰበው በመቶ ሚሊዮኖች
እንደሚሰጡት ይታወቃል፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲ ድጋፍ የሚያደርግ ነጋዴ ቢኖር ግን ይህች ሀገር የእርሱ ልትሆን አትችልም፡፡ ድጋፍ ማድረግ
የሚፈልጉ ነጋዴዎች በፓርቲ አባላት ስም ብቻ ነው ድጋፍ ሊያደርጉልን የሚችሉት፡፡ ይህንንም ቢሆን በከፍተኛ ሚስጥርና ስጋት፡፡ ተመጣጣኝ
የፋይናንስ ምንጭ የሌላቸው አካላት እኩል ይወዳደሩ ማለት ፌዝ ከመሆኑ የሚዘል አይደለም፡፡ ያለ ውዴታ መቶ ሚሊዮኖች መስጠትም ሆነ
ተደብቆ መስጠት የፖለቲካ ምዕዳሩ ውጤት ነው፡፡ የሚያስቀው ነገር ግን ከየት አምጥታችሁ ነው ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ የምታደርጉት?
የሚለው የፍርሀት ወለድ ጥያቄ ነው፡፡ በመቶ ሚሊዮኖች ገንዘብ መድቦ የሚፏልል ገዢ ፓርቲ በሳምንት ሁለት ጋዜጣ ለዚያውም አንባቢ
ገዥቶ የሚያነበውን ከየት አመጣችሁ ገንዘብ? ብሎ እንቅልፍ ያጣል፣ ነውረና አፈና ይፈፅማል፡፡
ሚዲያ አጠቃቀም
ሁለት
ተወዳዳሪዎች እኩል ለመውዳደር ለሚመርጣቸው አካል እኩል ቅርብ መሆን አለባቸው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አንዱ ሚዲያ ነው፡፡ የመንግሰት
ሚዲያዎች ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ሰሞን ከሚከፍቷት ውስን ቀዳዳ በስተቀር ዘወትር የሚተጉት የገዢውን ፓርቲ በማወደስ ላይ ሲሆን፣
በተቃራኒው ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ የሚፈጠርን ኮሽታ እንደመሃት በማውራት ህዝቡ ከተቃዋሚዎች እንዲርቅ አበክረው በመስራት
ነው፡፡ በየትኛውም የመንግሰት ሚዲያ ተቃዋሚዎች የሚያደርጉት በጎ እንቅስቃሴ አይዘገብም፡፡ ይባስ ብሎ በተቃዋሚዎች ላይ የተቀነባበረ
ዘጋቢ ፊልም እየተሰራ ይሰራጫል፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ በኢህአደግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለው የፖለቲካ ምዕዳር እኩልነት፡፡
ለማጠቃለል
ከዚህ በላይ የተነሱት ነጥቦች በኢትዮጵያ ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ለማካሄድ በሩ የተዘጋ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በተቃራኒው
ደግሞ የመድበለ ፓርቲን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ ባለመቻሉ ሌሎች የሀይል አማራጮች በጠጴዛው ላይ ቀርቧል፡፡ ቀላል የማይበለው
ዜጋም ይህን አማራጭ እንደምርጫው እየወሰደ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በኦሮሚያ የምንመለከተው እንቅስቃሴ ሰልፍ ለማድረግ ከዞን ወረዳ
ፈቃድ ጠይቀው አይደለም፡፡ እነዚህ ዓይነት ብሶት ማቅረቢያ መንገዶች ፈቃድ መጠየቅ እያበቃ መመጣቱን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ሚዲያው
ሲታፈን አማራጭ ሚዲያ መፈለግ የግድ ይላል፡፡
ገዢው
ፓርቲ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን የምር የሚፈልጉት ላይ በር መዝጋቱ እንደሚፈልገው በአውራ ፓርቲ ስም እድሜወን የሚያረዝምለት ሳይሆን
እድሜውን የሚያሳጥረው መሆኑን መካሪ ካለው ቢመክረው ካልሆነም የእኛንም ግፉዋን ምክር ቢሰማ ጥሩ ነው፡፡ የፖሊቲካ ምዕዳሩ ሲሰፋ
እና መድበለ ፓርቲ እውን ሲሆን በባንኮች ላይ ከጀርባው የሚሸረበው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካል- ኢኮኖሚ ቦታውን ያገኛል፡፡ ከዚህ
ውጭ የባንኮችም የመወዳደሪያ ምዕዳር ወደፊትም ከዚህ በላይ ይጠባል፡፡ የባንኮች መወዳደሪያ ፍታሃዊ እንዲሆነ የፖለቲካ ምዕዳሩ መስፋት
የግድ ነው፡፡
ቸር ይገጠመን!!!!!
No comments:
Post a Comment