Thursday, March 10, 2016

መንግሰታችን ለመጪው ግንቦት ሃያ አብዮት ይጠራ ይሆን?



የካቲት 21 2008 በኢትዮጵያ ታሪክ ተመዝግቦ አልፏል፡፡ ቀጣዩ ታሪካዊ ቀን ደግሞ የሚመጣው ግንቦት 20 2008 ነው፡፡ የግንቦት 20 ማግሰት ምን አዲስ ነገር እንደሚመጣ ግን ማንም የሚያውቅ የለም፡፡ መገመት ግን ይቻላል፡፡ የመጪው ግንቦት ሃያ ቀደም ብለን እንድንነጋገርበት ያሳሰበኝ በቅርቡ የአዲስ አበባ የትራንሰፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ያደረጉት የሰለማዊ ተቃውሞ/የስራ ማቆም አድማ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአዲስ አበባ አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች መደዳ ቁጥር ሰላሣ ሺ የደረሰ ሲሆን በእርግጠኝነት በስራ ላይ የሚገኙት ግን ከግማሽ የሚበልጡ አይደለም፡፡ በተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡትን ታክሲ ያልሆኑ ሚኒባሶች ሲጨመሩ ሃያ ሺ የሚሆኑ መኪኖች በአግልግሎት ውስጥ ናቸው የሚል ታሳቢ መውሰድ ይቻላል፡፡ እነዚህ የትራንሰፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በሰራቸው የሚተዳደረውን በመቶ ሺ የሚቆጠረ ቤተሰብ አባል ችግር ላይ ሊጥል የሚችል እርምጃ በመውሰድ መንግሰትን የተጋፈጡ ሲሆን፣ በማህበራቸው በኩል ተደረገ በተባለ ድርድር ለተቃውሞ መነሻ የሆነው መመሪያ ለሶሰት ወር ተግባራዊ እንዳይሆን ከስምምነት በመደረሱ ተቃውሞ ተቋርጦዋል፡፡ ሶሰት ወር የሚሞላው ደግሞ ግንቦት 20 2008 ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መነሳት ያለበት ጥያቄ ከሶሰት ወር በኋላስ? የሚለው ነው፡፡ በተለይ ጥያቄውን ከአሸከርካሪዎች አንፃር የተወሰኑ መሰረታዊ ነጥቦችን በማንሳት እንመልከተው፤
 የመጫኛ እና ማውረጃ ቦታ በቂ ያለመሆን
እንደሚታወቀው ለታክሲ ማቆሚያና ማውረጃ በቂ ቦታዎች በከተማው ውስጥ የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ታክሲዎች ባመቻቸው ቦታ ይጭናሉ ያወርዳሉ፡፡ ተሳፈሪውም በየአስር ሜትሩ ወራጅ አለ ብሎ መውረድ ይፈልጋል፡፡ ተሳፋሪን በየቦታው ለማውረድ ብቻ ሳይሆን ለመጫንም ይቆማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በመንገድ ዳር የቆሙ መኪኖችን ደርበው መጫንና ማውረድ መደበኛ የታክሲ ስራ አካል ነው፡፡ ይህ ድርጊት አሁን በወጣው መመሪያ መሰረት ከፍተኛ ቅጣት የሚያስጥል ነው፡፡ ሰለዚህ በሚቀጥለው ሶሰት ወር ውስጥ  መንግሰት ይህን ችግር ለመፍታት እና መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅምም ፍላጎትም የለውም፡፡ አማራጩ ደርቦ መጫንና ማውረድ ትክክለኛ ተግባር ተደርጎ እንዲወሰድ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ሌላው አማራጭ ደግሞ ለታክሲ ማቆሚያ ሲባል በመንገድ ላይ መኪና ማቆም መከልከል ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንገድ ተከትለው የተሰሩት ህንፃዎች እና የተከፈቱ የንግድ ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የፊት ለፊቱ ችግር ሲሆን መንገድ ላይ ፓርክ ማድረግ መከልከል ከዚህ የከፋ ሌላም ችግር እንደሚኖረወ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ለማነኛውም መንግሰት ይህን ችግር እንደማይፈታው ታውቆ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡
የትራፊኮች የሰነ ምግባር ጉዳይ
የትራፊኮች የስነ ምግባር ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ሁሉም ይረዳዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት መንግሰት መፍትሔ ብሎ ያሰቀመጠው አቅጣጫ ግን ከህግም ከሞራልም አንፃር ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ትራፊክ ላይ ከጠቆመ ትራፊኩ ከስራ ይባረራል፡፡ ምን ማለት ነው? የትራፊኮች የሰነ ምግባር ችግር በሌሎች ዜጎች የሌለ ይመስል ሌሎችን አምኖ እርምጃ መውሰድ የህግ መሰረት የለውም፡፡ ትራፊክ ያለጥፋት ሊቀጣን ይችላል የሚል ስጋት ሲቀርብ ትራፊኩን ያለጥፋቱ የሚያስቀጣ አስራር ይፈጠር ማለት አይደለም፡፡ አንድ ትራፊክም ቢሆን ያለጥፋቱ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ለምንል ሰዎች ግን ይህ ህገወጥ ነገር ግን በአደባባይ እየተነገረ ያለ የእርምጃ ዓይነት ዜጎችን አሸማቃቂ ነው፡፡ ለማነኛውም ዋነኛው ችግር ግን ትራፊኮች በዚህ ዓይነት ህግ ውስጥ ምን ያህል ሊቆዩ ይችላሉ? የሚለው ሲሆን የትራፊኮች የስራ ማቆም አድማ መንገድ ከመዝጋት አልፎ የተለየ ነገር ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ እርምጃ ሰዎች በትራፊኮች ላይ ጥቆማ ከማድረግ ይልቅ ትራፊክና አሸከርካሪ ተጣምረው ለበለጠ ውስብስብ ችግር የሚዳርግ ነው የሚሆነው፡፡ ልብ ማለት ያለብን ትራፊኮቹም ቢሆኑ የማህበረሰቡ አካል መሆናቸው እና ለትራፊክነት ፍላጎት ያላቸው ከሰራ ፍቅር ወይም ከደሞዙ አማላይነት የተነሳ አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት ሪፖርት ጋዜጣ ያወጣው ዜና ትዝ የሚለኝ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች በጉምሩክ ለፈታሽነት ስራ በሺዎች መመዝገባቸው የስራ ፍቅር እንዳልሆነ ግልጥ ከመሆን አልፈን ወጣቶቻችን የደረሱበትን የገንዘብ ማግኛ ፍላጎት መስመር የሚያጋልጥ ነው፡፡ ሃሳቤ ግልፅ ይመስለኛል፡፡ ዲግሪ ይዞ ኬላ ላይ ፈታሽ መሆን መመኘት የጤና አይመስለኝም፡፡
የቅጣቶች ተደራራቢነት
ቅጣቶች ተደራራቢ ከመሆናቸው አንፃር አንድ የቤት መኪና አሸከርካሪ ሰድስት ወር ወይም ሁለት ዓመት ቢቀጣ በትራንስፖርት መሄድ አማራጭ ሲሆን አቅም ካለው ደግሞ በሾፌር መሄድ ይችላል፡፡ በአሸከርካሪነት የሚኖር ለመደበኛ አሸከርካሪ በስራው ፀባይ የተነሳ ደንብ ለመተላለፍ የተጋለጠ አሸከርካሪ ግን ዲግሪውን ነው የሚቀማው፡፡ ለምሳሌ እኔ ዲግሪ ብቀማ የምሰራውን ስራ የሚከለክለኝ ነገር ስለሌለ ተቀጥሬ መስራት ብቻ ነው የሚቀርብኝ፡፡ አንድ አሸከርካሪ ግን መንጃ ፍቃዱ ከተቀማ ከሰራ መስኩ ነው የሚባረረው፡፡ ለስድስት ወር ለሁለት ዓመት ምን እየበላ እንዲኖር እና ቤተሰቡን እንዴት እንዲያስተዳደር እንደታሰበ መመሪያው አይገልፅም፡፡ በትራፊክ አደጋ ሰው እንዳይሞት በረሃብ ግን ይሙት የሚል ይመስላል፡፡ አንድ ቀደም ሲል በህገወጥ ተግባር ሲሰማራ የነበረ፣ ነገር ግን ፀባዩን አርቆ ስርዓት ይዞ የታክሲ ረዳት ከዚያም ሁለተኛ፣ ሶሰተኛ ብሎ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ በስራ ላይ ያለ አሸከርካሪ ቃል በቃል አለ የተባለው “ችግር የሌም ተመልሼ ወደ ቀድሞ ስራዬ እገባለሁ” ነው፡፡ ማጅራት እየመታ ሰው ገድሎ እንዲኖር ማለት ነው፡፡ ሌሎች ሀገሮች የዚህ ዓይነት ህግ ሲተገብሩ በሀገራቸው ስራ የሌለው ሰው የማህበራዊ ዋስትና የሚባል ክፍያ የሚያገኝ በመሆኑ ስራ አጥቼ ምን ልሁን አይልም፡፡ ይህን ስናስብ ህጎችን ስንቀዳ በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ማድረግ ይኖርብናል፡፡ አሁንም መነሳት ያለበት ጥያቄ የዛሬ ሶሰት ወር መንጃ ፍቃዱን  የተቀማ አሽከርካሪ ምን ይሁን? ፈቃድ የማይጠይቁ ስራዎች ገቢ የሚያስገኙ አማራጭ ካሉም ይነገረን፡፡ አንዱ የገዢው ፓርቲ አባልነት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ከአባልነት በመለስ ማለቴ ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ካለው የድርድር ባህሪ አንፃር ለማሳያ ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ሊፈታቸው አይችልም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሊያደርግ የሚችለው ብዙ ቢሆንም ከልምድ ግን የተወሰኑትን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንደኛ ይህን ተቃውሞ ሲመሩ የነበሩትን በተለያየ መንገድ በመደለል የተደረገውን የስራ ማቆም አድማ በድጋሚ ሊጠራ የማይችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ለዚህም  እነዚሁኑ ሰዎች የአገልግሎት ሰጪ ሾፌሮችና ረዳቶችን በመከፋፈል ባቀደው መሰረት ከሶሰት ወር በኋላ መመሪያውን በማን አለብኝነት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህም ሲሆን ከዚህ ቀደም የተደረገውን ድርጊት እንዲያወግዙ ጭምር በማድረግ ሞራላቸውን ማኮላሸት ዋናው ግብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በንግድ ባንክ ሰራተኞች ላይ የተወሰደውን እርምጃ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
በቀጣይ ደግሞ ተጨማሪ ታክሲዎች በመንግስት ድጋፍ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ወይም ይገባሉ እያሉ በማስወራት አሁን ያሉትን አገልግሎት ሰጪዎች ከጫወታ ሊያሰወጣን ነው ወደሚል የሰነ ልቦና ጦርነት መፍጠርና ማሰጨነቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደምም ተሞክሮ የሰራ ሲሆን በቀጣይ በተመሳሳይ መልኩ ስራ ላይ አይውልም አይባልም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ከዚህ ቀደም በባለ ታክሲዎች የተደረጉ የስራ ማቆም አድማዎች ናቸው፡፡
እኔ ከዚህ የስራ ማቆም አድማ በግሌ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ ዋነኛው ነገር ህዝቡ ከተባበረ ማንኛውም መብቱ የተነካ ስብስብ መብቱን ማስከበር እንደሚቻል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የታክሲ ሾፌሮች ዘወትር በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚደርስባቸው ዘለፋ አዘል አስተያየቶች በተቃራኒው የእነርሱ መኖር በሁሉም እንቅስቃሴ ውስጥ ሞተር መሆኑን ለዘነጋው ዜጋ ትምህርት አስተላልፈዋል ብዬም አምናለሁ፡፡ በቀጣይ ሁሉም በጋራ የማይቆሙ ቢሆን እንኳን ጉዳዩ የበለጠ የከነከናቸው አሸከርካሪዎች በተናጥል መኪናውን ለባለቤቱ አስረክበው ዋነኛ የሰራ ሰርተፊኬት ከማሰረከብ ይህ ህግ እስኪሻሻል በሾፌርነት ላለመስራት ቢወስኑ ባለንብረቶች መኪናው በፈረስ ስለማያሰጎትቱት መንግሰትም ባለቤቶቹን ለማስገደድ አቅም አይኖረውም፡፡ ሰለዚህ ጫናውን ማስቀጠል ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሌላው መንገድ ደግሞ ሾፌሮች ሰራቸውን ለመስራት አሁን ከሚከፈላቸው በላይ የሚመጣውን የወደፊት አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል ደሞዝ እና የቀን አባል ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ታሪፍ ሲሻሻል እና ገቢው ሲጨምር ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አዲሱ ተግባራዊ የሚሆነው መመሪያ ወደ ህዝቡ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ይጠራል ማለት ነው፡፡ ህዝቡ ደግሞ አሁንም ያለው ዋጋ መሸከም አልቻለም እና በሌሎች ዕቃዎችም ላይ የዋጋ ንረት ሊጠራ ይችላል፡፡ እነዚህ ሲደመሩ ደግሞ ሌላ ጦስ ላለመጥራታቸው ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡
የዛሬ ሶስተ ወር አጭር ጊዜ ነው፡፡ አሸከርካሪ፣ የመኪና ባለቤቶች፣ ተጠቃሚው ህዝብ፣ በተለይም መንግስት ከፍተኛ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ግንቦት 20 2008 በሚያበቃው ሶሰት ወር መንግሰት ምን ይዞ እንደሚመጣ በጉጉት እንጠብቃለን፡፡ መንግሰታችን ለመጪው ግንቦት ሃያ አብዮት ይጠራ ይሆን?
ቸር ይግጠመን
ግርማ ሠይፉ ማሩ

No comments:

Post a Comment