Monday, September 19, 2016

አቶ ጌታቸው ረዳ የሸገር ካፌ ቆይታ …..



የኮሚኒኬሸን ሚኒሰትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ በሸገር ካፌ ላይ ቀርበው ከእሸቴ አሰፋ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጥያቄዎቹ የህዝብ መልሶቹ ግን የተለመዱ የኢህአዴግ ናቸው፡፡ ያሰገረሙኝን ብቻ ላካፍላችሁ፡፡
አቶ ጌታቸው ያለምንም ይሉኝታ ዳግም ተሃድሶ የታችኛውን ክፍል እንደሚጠራርግ ነግረውናል፡፡ ምክንያቱም መመረያ በሚል ሰበብ ህዝብ አያጉላሉ ያሉት እነርሱ በመሆናቸው የሚል አስቂኝ ሰበብ ሰጥተዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውም ሚኒስትሮች እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህግ በላይ እንዲሆኑም ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ሚኒስትሩ/ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሲያዙ መመሪያ አይፈቅድም ይላሉ፡፡ እኔ እስከ ዛሬ ባለኝ ልምድ የመመሪያው ባለቤቶች እነዚያው ሚኒስትሮች መስለውኝ፡፡ መቼም እዚህ ሀገር ጉድ ሳይሰማ መሰከረም ስለማይጠባ በየመስሪያ ቤቱ ያሉ ኤክስፐርቶች መመሪያ የማውጣት ስልጣን ተሰጥቶ ከሆነ ልክ አይደሉም ሰልጣናቸውን ያለ አግባብ ሚኒሰትሮች እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማሳቀቅ ሊጠቀሙበት ባልተገባ ነበር፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እርሰ በእርሱ የሚጋጭ መመሪያ ያወጣ ሚኒስትር ያወጣውን መመሪያ ኤክስፐርት ቢያስታውሰው ክፋቱ አልታየኝም እና አቶ ጌታቸው በድጋሚ ቢያብራሩልን፡፡ በነገራቸን ላይ መመሪያ ደንብ የሚያከብሩና የሚያስከብሩ ሚኒስትሮች እና ጠቅላይ ሚኒስትር ነው የሚያስፈልገን፡፡ መቼም አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝን ያዘዙት እንቢ ያለ ኤክስፐርት ማን እንደሆነ ማወቅ ጥሩ ነበር፡፡ ይህ ኤክስፐርት አቶ መለስንም እንዲህ ይል ነበር? የሚል ጥያቄም ያጭራል፡፡ አቶ መለስ እንዲህ ብለዋል እየተባለ ባልወጣ መመሪያ እንተዳደር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ እኮ የቅርብ ጊዜ ነው፡፡
ሌላው አቶ ጌታቸው ረዳ ካለፈው ስህተታቸው መማር ያልቻሉት በሚዲያ በሚተላለፍ ውይይት ቃላት መረጣ አለመቻላቸው ወይም ፍላጎት ያለማሳየታቸው ነው፡፡ ጭራቅ እና አጋንንት መውደዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡ ለምሳሌ “ህዝብ አሁን ካሉት 28 ካቢኔ ሚኒስትሮች ስንቱ ቢታሰር፣ ስንቱ ቢሰቀል እንደሚረካ አይገባኝም” ብለዋል፡፡ እኛ ይስቀሉ አላልንም፡፡ ነገር ግን እሰከሚገባኝ ድረስ ያለ አግባብ ከተሰቀሉበት ስልጣን ይውረዱ፡፡ ወርደው ባለጉዳይ ሆነው ይህችን ሀገር ይመልከቷት ነው የተባለው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ኢህአዴግ እስከ አሁን በፍፁም እንዲገባው የማይፈልገው ተጠያቂነት በውክልና አይተላለፍም ውክልና ለበታች ሰራተኛ ሲሰጥ ስራውን/ሃላፊነቱን ብቻ ነው፡፡ የተወከለው ሰራተኛ ካጠፋ የሚጠየቀው የወከለው ሃላፊ ነው፡፡ ይህ ሀሁ እንዲት ለሃያ አምስት ዓመት መረዳት ያቅታል፡፡ መቼም የጫካውን ዘመን እንርሳው ብዬ ነው፡፡
እሸቴ አሰፋ በግልፅ ያቀረበላቸው አንዱ ጥያቄ የአንድ ብሔር የበላይነት/የህወሃት የበላይነት አለ የሚል ቅሬታ አለ የሚል ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በግምገማቸው ላይ ተነስቶ በስፋት ውይይት መደረጉ አቶ ጌታቸው ነግረውናል፡፡ የተነሳው የአንድ ብሔር /የትግራይ/ የበላይነት አለ የሚለው አንድ በጎ ነገር ሲሆን የተደረሰበት ነገርም ጥሩ ነው፡፡ አንዱን ኪራይ ስብሳቢ በሌላ ብሔር ኪራይ ስብሳቢ መተካት አይደለም፡፡ ህዝቡ እያለ ያለው ህውሃት ወርዶ በብአዴን ወይም በኦህዴድ ይተካ አይደለም፡፡ ሁላችሁም ውረዱ ነው፡፡ አሁን ያለው የህወሃት የበላይነት እንዲነግስ ያደረጉ አሁን ጥያቄያቸው በተራችን እኛ እንሁን ከመሆን ሊዘል አይችልም፡፡ የእኛ ጥያቄ ግን የዚህ ዓይነት ስርዓት አያስፈልገንም የሚል ነው፡፡
ከአንድ ብሔር የበላይነት ጋር ተያይዞ የተነሳው አንድ ቁልፍ ነገር የቁልፍ ቦታዎች ነገር ነው፡፡ ቁልፍ የሚባሉት ቦታዎች ለምን ቁልፍ ሆኑ? ሲባል ኪራይ ማደያ ሰለሆኑ ነው:: ምርጥ መልስ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡ አንድ የመንግሰት ተቋም ሃላፊ መሆን የራስን ግሳንግስ መሰብሰቢያ ስርዓት ከመገንባት የከፋ ውርደት ከየት ይመጣል፡፡ በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ታሪክ ሚኒስትር መሆን የራስን ቡድን መጥቀሚያ እንዲህ ዓይን ባወጣ መልኩ የሆነበት ጊዜ አሁን ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ ስራተኞች ምደባ ከብቃት ይልቅ በድርጅት ሰለሚሆን ኢህአዴግ አራት ድርጅቶች እንዲሁም በጨረፍታ ለአጋር ድርጅቶች ይታደላል፡፡ ከውጭ ጉዳያ ጋር ተያይዞ በቅርቡ የሰማሁት አንድ ነገር አለ፡፡ ህወሃት የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩን ቦታ ቢይዝም ዋና ዋና የሚባሉትን ቦታዎች ለብአዴን/ብራሰልስ፣ እንግሊዝ፣ እስራኤል፣ወዘተ/ ለቋል የሚል ቅሬታ አለ፡፡ በአሜሪካ ግርማ ብሩም ቢሆን ከኦህዴድ  ይልቅ የሸዋ ሴረኝነቱ ይበልጣል ይሉታል- ህወሃቶች፡፡ ይህ እንግዲህ ህወሃቶች አሁን በያዙት የውጭ ጉዳይ ኪራይ ስብሳቢነት አልረኩም ማለት ነው፡፡ ይህን ለማስተካከልም ሙከራዎች አሉ ይባላል፡፡ መቼም ለምን ከፊት አልሆንም ካልሆነ በሰተቀር በሁሉም ቦታ እንዳሉ በግሌ አውቃለሁ፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ አንድ አሰቂኝ ምላሽ ሰጥተዋል “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የከበቧቸው አማካሪዎች ወሳኝ አይደሉም” የሚል፡፡ እንደ ምሳሌም ያቀረቡት እራሳቸውን አማካሪ በነበሩበት ወቅት ወሳኝ አልነበርኩም በማለት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ቦታዎች በሶሰት ሊከፈሉ እንደሚችሉ ነው፡፡ አንደኛው የእውነት የማማከር ስራ የሚሰሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የተቀጠሩ ባለሞያዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሸተኞች እና ጡረታ እስኪወጡ ሊጠቀሙ የሚፈልጉ ሰዎች የሚገኙበት ነው፡፡ ይህ ምድብ እንደ ማግለያም ማገገሚያም ያገለግላል፡፡ የኤምባሲ ክፍት ቦታም እስኪገኝ መጠባበቂያም ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሶሰተኛው ደግሞ ወሳኝ የሚባሉት የሚገኙበት ነው፡፡ በቁጥርም ውስን ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በፓርቲ ማዕቀፍ መስመር በማስያዝ ውሳኔ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ይህ ሶሰተኛው ቡድን አማካሪ በአቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ አልነበሩም- ሊኖሩም አይችሉም፡፡ ሰውዬ በራሳቸው ወሳኝ ነበሩ፡፡ የተቀሩት ሁሉቱ ዓይነት አማካሪዎች ግን ድሮም የነበሩ ናቸው፡፡ ይህን ህዝቡ በደንብ ያውቀዋል ማን በየትኛው ምድብ እንዳለም ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ የአቶ ጌታቸውን መልስ አልተቀበልነውም፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

Saturday, September 3, 2016

የማሪያም መንገድ ሲዘጋ የገብሬሉ ይከፈታል ብለን ነበር!!!



አንድትን ፓርቲን ድንክ ለማድረግ ከመወሰናቸው በፊት አንድነት የሚከተለውን ሰላማዊ የትግል ስልታ፤ ሰላማዊ የሰለጠነ የስልጣን ሽግግር እንዲቀበሉ በተደጋጋሚ አሳሰብን ነበር፡፡ ከመሃከላችን እየመረጡ ማስር ትግሉን እንደማያዳክመው ይልቁንም እንደሚያጠነክረው ነግረናቸዋል፡፡ ከከፋም ትግሉ ወደ ሌላ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው በቅርብ ላገኘናቸው ሁሉ ነግረናል፡፡ መግለጫዎች አውጠተን አቋማችን ህዝብ እንዲረዳው አድርገናል፡፡ የመንግሰት ተቋማት ህዝብን እንዲያገለግሉ፣ ከተሰጣቸው ህዝብን የማገልገል ሃላፊነት ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ የበኩላችን ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ማነኛውም ያደረግናቸው እንቅስቃሴዎች ከፍርሃት ተቆጥሮብናል፡፡ ከሁሉም በላይ በምን ያመጣሉ ትዕቢት የፈለጉትን አድርገዋል፡፡ ይህ እንዲሆን በውስጣችን ታቅፈናቸው የነበሩትን ጭንጋፎች ተሳትፎ የሚያሳንሰው አይደለም፡፡ ይህም ቢሆን ግን ገዢው ፓርቲ በማይመለከተው የፓርቲ የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ህገወጥ እርምጃ የፖሊስ ሰራዊት በማሰማራት ወስዶዋል፡፡ ዛሬ በሰላማዊ ትግል ጥላ ስር ለውጥ እናመጣለን ሲሉ የነበሩ ወጣቶች በማነኛውም መንግድ ለውጥ ለማምጣት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ተገፍተው የገቡበት መሆኑን ስለምናውቅ ምርጫቸውን ማክበር ብቻ ሳይሆን በባርነት ከመኖር ሞትን መምረጥ የሰው ልጅ ትክክለኛ ምርጫ ነው ብለን እናከብራቸዋለን፡፡
የታፈነ ህዝብ ለመተንፈስ የሚያደርገው የዚህ ዓመት ህዝባዊ እንቅስቃሴ በምንም መመዘኛ ሰህተት ሊሆን አይችልም፡፡ ጥያቄዎቹን በየቦታው ያስነሱት ጉዳዮች የተለያዩ ቢመስሉም መንግሰት እንደሚለው የመልካም አስተዳደር ጉድለት አይደለም፡፡ የህዝብ ጥያቄ ያልገባው መንግሰት ደግሞ መልሱን ሊያገኘው እንደማይችል ደግመን ደጋግመን ተናግረናል፡፡ በየቦታው የተነሳውን ህዝባዊ ንቅናቄ ተከትሎ መንግሰት ህገወጥ እርምጃዎችን መውሰዱን ቀጥሎበታል፡፡
መንግሰት በቅርቡ እያደረገ ያለው ዜጎችን መቅጠፍ በምንም መመዘኛ ቀለም አልተሰጠውም እንጂ ከቀይ ሽብር- ነጭ ሸብር የሚለይ አይደለም፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ ልዮነቶች በውይይት እና ህዝብ በሚመርጠው መስመር መፈታት አለበት ተብሎ በሚታመንበት ጊዜ መንግሰት ገዳይ ጥይቶቸን በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየረጨ ይገኛል፡፡ ይህ መቼም ቢሆን ከተጠያቂነት የሚያድን አይደለም፡፡ የህዝብ መተንፈሻ የሚባሉትን መሰመሮች ሁሉ የዘጋ መንግሰት ህዝብ ለምን አደባባይ ወጣችሁ ብሎ ለመግደል የሚያስችል ስልጣን ማንም አልሰጠውም፡፡ ነገር ግን ጊዚያዊ ማዘዣውን ተጠቅሞ በተግባር ዜጎችን እየገደለ ይገኛል፡፡ ይባስ ብሎ ከነብስ ወከፍ መሳሪያ አልፎ የቡድን መሳሪያዎች፣ በእኔ ግምት ለውጭ ወራሪ ሀይል የተዘጋጀን መከላከያ አንቀሳቅሶ የህዝብን ድምፅ ለማፈን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ለሚታዘብ ወቅቱ የመንግሰት የእብደት ደረጃ ልክ ያለፈበት እንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እሰከ ምስራቅ የጠየቀው ለሰው ልጅ የሚገባውን ነፃነት እና ክብር ነው፡፡ መንግሰት ደግሞ ሆዳችሁን ከሞላቸሁ ፎቅ፣ ባቡር እና መኪና መንገድ ካያችሁ መች አነሳችሁ የሚል ይመስላል፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰብሰበው ለወጣቶች የሚነግሩት በሙሉ ሆድ ሰለሚሞላበት መንገድ ነው፡፡ ወጣቱ በአደረጃጀት ካልገባ ማግኘት እንደማይቻል ያስረዱት ደግሞ የስፖርትና ወጣቶች ሚኒሰትር መስሪያ ቤት የወጣት አደረጃጀት ሃላፊ ናቸው የተባሉ ሰው ናቸው፡፡ በሀገራችን ያለው የተፈቀደ አደረጃጀት መንግሰትን ለማወደስ የተቋቋሙት የወጣቶችና የሴቶች ሊጎች ናቸው፡፡ እነዚህ አደረጃጀቶች ገዢው ፓርቲ ሲየስነጥስ እንባቸው የሚመጣ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ የወጣቱን ችግር ሊናገሩ አይችሉም፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በወጣት ሰም ስብሰባ ተቀመጡ የተባሉ ሰዎች አብዛኞቹ በእውነት ይናገራሉ ተብለው የሚጠበቁ እንዳልሆነ ብዞዎች የተሰማሙበት ነው፡፡ እነዚህ ተሰብሳቢዎች ቢያንስ እድሜያቸው የወጣት አይደለም፡፡ ወጣት ያልሆነ የወጣት ችግር አያውቅም ማለት ሳይሆን በዚህ ስብሰባ ለመካፈል ለሚከፈል አበል ለማግኘት ሲሉ ወጣቶችን ትተው እራሳቸውን መርጠው የመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ በዚህ በትንሹ ያልታመኑ በትልቁ ሊታመኑ አይችሉም፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የምር ውይይት ማድረግ ከፈለጉ የወጣቶችና ሰፖርቲ ሚኒስትሩ ሬዲዋን ሁሴን ስብሰባ ላይ የነገራቸውን የሚናግሩ ወጣቶችን መሰብሰብ ሳይሆን በአዲስ አበባ እና በየክልሉ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ሊወጡ ፈልገው የተከለከሉትን ወጣቶች ወይም ደግሞ የደህንነት ሰራተኞች በየጊዜው እያፈሱ በእስር ቤት የሚያጉሩዋቸውን ወጣቶች ማናገር አለባቸው፡፡ ለምሳሌ እነ አንጋው ተገኝ እና ጓደኖቹን ከጎንደር፣ እነ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወይንሸት ሰለሺ  ከአዲስ አበባ፣ እነ ምርቱ ጉታ ከአዳማ፣ እነ ዘሪሁን ገሰሰ ከወሎ፣ ወዘተ ጠርተው ምን ጎደለባችሁ? ማለት ነበረባቸው፡፡ ለነገሩ እንጂ ጉዳዩ ከወጣቶቹ ጋር የሚያልቅ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስተሩ እና ጓዶቻቸው የምር ለዚህች ሀገር መፍትሔ የመፈለግ ፍላጎት ካላቸው ከማን ጋር መነጋገር እንዳለባቸው ይጠፋቸዋል ብዬ አላምንም፡፡
ዛሬ በጫካ የሚገኙት የሰላማዊ ትግል መስመር ሲዘጋ ወደ ትጥቅ ትግል የገቡት ልጆች በምንም መመዛኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለወጣቶቹ እንደገለፁት በውይይት የሚገኘውን ውጤት ዘንግተው እና በድንጋይ ውርወራ መንግሰት ለመገልበጥ ፈልገው አይደለም፡፡ ይልቁንም መንግሰታቸው ውይይት ሰለሚፈራ እና በተወያየበት ሁሉ በጉልበት አንበርክኮ ለመውጣት ሰለሚፈልግ ነው፡፡ አሁንም በከተማ በድንጋይ ውርወራ መንግሰት ፋታ ለመከልከል የተዘጋጁ ወጣቶች መንግሰት ባዘጋጀው አደረጃጀቶች/ፎረሞች ብቻ እንዲሳተፉ በመምከር መፍትሔ አይገኝም፡፡ የተለያየ አስተሳሰብ ያላች ወጣቶች ሊደራጁበት የሚችሉበት መንገድ መከፈት አለበት፡፡ ትላንት ለእስር የተዳረገቸው የአንድነት አባል የነበረችው ወይንሸት ሰለሺ  በኢህአዴግ ወጣት አደረጃጀት የነበረች ቀጥሎም የባለ ራዕይ ወጣቶች አባል የነበረች ነች፡፡ በሲቪል ሶሳይቲነት ይንቀሳቀስ የነበረው ባለራዕይ ወጣቶች መንቀሳቀስ ሲከለከል አንድነት ተቀላቅላ ስርዓቱን ለመለወጥ ቆርጣ ተነሳች፡፡ ለዚህም ብላ አንድነትን ተቀላቀለች፡፡ አንድነት በህገወጥ መንገድ ሲፈርስ ደግሞ በፌስ ቡክ ትግል የምታደርግ ንቁ ወጣት ነች፡፡ በእኔ እምነት ወይነሸት ላይ የሚያቀርቡት አንድም ወንጀል የለም፡፡ ወንጀለኞች ቢወነጅሏት ለልጇ ዲሞክራሲያዊት ሀገር ለመመስረት ባደረገቸው ጥረት ነው፡፡ ለሆዴ አላድርም ነፃነት ይበልጥብኛል ሰለአለች ብቻ ነው፡፡
አሁንም ጥሪያችን መንግሰት የማሪያሙን መንገድ ክፍት ያድርግ በነፃነት መደራጃት የምንችልበትን መንገድ ክፍት ማድረጉን ማረጋገጫ ይስጠን፣ ከዚያ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን እንደሚያደርግ ያውቃል፡፡ በአዲስ አበባ የተኮለኮሉ ኮብል እስቶኖችን መናፈቅ ትቶ በውይይት ወደ መፍትሔ ይገባል፡፡ ለመጀመር በአዲስ አበባ የወጣትና ሴቶች ፎረም አባል ያልሆኑ የአዲስ አበባ ልጆችን ለማነጋገር ከወሰኑ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር ስራ ላለማብዛት እኛ የዞን ዘጠኝ ወጣቶችን ወክለናል ያነጋግሩዋቸው፡፡
መልካም አዲስ ዓመት በተለመደው ሁኔታ ሳይሆን ለለውጥ የእውነትም አዲስ ዓመት ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ክብር ህይወታቸውን ለሰጡ ጀግኖቻችን ….
ቸር ይግጠመን!!!!!