Monday, September 19, 2016

አቶ ጌታቸው ረዳ የሸገር ካፌ ቆይታ …..



የኮሚኒኬሸን ሚኒሰትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ በሸገር ካፌ ላይ ቀርበው ከእሸቴ አሰፋ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጥያቄዎቹ የህዝብ መልሶቹ ግን የተለመዱ የኢህአዴግ ናቸው፡፡ ያሰገረሙኝን ብቻ ላካፍላችሁ፡፡
አቶ ጌታቸው ያለምንም ይሉኝታ ዳግም ተሃድሶ የታችኛውን ክፍል እንደሚጠራርግ ነግረውናል፡፡ ምክንያቱም መመረያ በሚል ሰበብ ህዝብ አያጉላሉ ያሉት እነርሱ በመሆናቸው የሚል አስቂኝ ሰበብ ሰጥተዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውም ሚኒስትሮች እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህግ በላይ እንዲሆኑም ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ሚኒስትሩ/ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሲያዙ መመሪያ አይፈቅድም ይላሉ፡፡ እኔ እስከ ዛሬ ባለኝ ልምድ የመመሪያው ባለቤቶች እነዚያው ሚኒስትሮች መስለውኝ፡፡ መቼም እዚህ ሀገር ጉድ ሳይሰማ መሰከረም ስለማይጠባ በየመስሪያ ቤቱ ያሉ ኤክስፐርቶች መመሪያ የማውጣት ስልጣን ተሰጥቶ ከሆነ ልክ አይደሉም ሰልጣናቸውን ያለ አግባብ ሚኒሰትሮች እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማሳቀቅ ሊጠቀሙበት ባልተገባ ነበር፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እርሰ በእርሱ የሚጋጭ መመሪያ ያወጣ ሚኒስትር ያወጣውን መመሪያ ኤክስፐርት ቢያስታውሰው ክፋቱ አልታየኝም እና አቶ ጌታቸው በድጋሚ ቢያብራሩልን፡፡ በነገራቸን ላይ መመሪያ ደንብ የሚያከብሩና የሚያስከብሩ ሚኒስትሮች እና ጠቅላይ ሚኒስትር ነው የሚያስፈልገን፡፡ መቼም አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝን ያዘዙት እንቢ ያለ ኤክስፐርት ማን እንደሆነ ማወቅ ጥሩ ነበር፡፡ ይህ ኤክስፐርት አቶ መለስንም እንዲህ ይል ነበር? የሚል ጥያቄም ያጭራል፡፡ አቶ መለስ እንዲህ ብለዋል እየተባለ ባልወጣ መመሪያ እንተዳደር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ እኮ የቅርብ ጊዜ ነው፡፡
ሌላው አቶ ጌታቸው ረዳ ካለፈው ስህተታቸው መማር ያልቻሉት በሚዲያ በሚተላለፍ ውይይት ቃላት መረጣ አለመቻላቸው ወይም ፍላጎት ያለማሳየታቸው ነው፡፡ ጭራቅ እና አጋንንት መውደዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡ ለምሳሌ “ህዝብ አሁን ካሉት 28 ካቢኔ ሚኒስትሮች ስንቱ ቢታሰር፣ ስንቱ ቢሰቀል እንደሚረካ አይገባኝም” ብለዋል፡፡ እኛ ይስቀሉ አላልንም፡፡ ነገር ግን እሰከሚገባኝ ድረስ ያለ አግባብ ከተሰቀሉበት ስልጣን ይውረዱ፡፡ ወርደው ባለጉዳይ ሆነው ይህችን ሀገር ይመልከቷት ነው የተባለው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ኢህአዴግ እስከ አሁን በፍፁም እንዲገባው የማይፈልገው ተጠያቂነት በውክልና አይተላለፍም ውክልና ለበታች ሰራተኛ ሲሰጥ ስራውን/ሃላፊነቱን ብቻ ነው፡፡ የተወከለው ሰራተኛ ካጠፋ የሚጠየቀው የወከለው ሃላፊ ነው፡፡ ይህ ሀሁ እንዲት ለሃያ አምስት ዓመት መረዳት ያቅታል፡፡ መቼም የጫካውን ዘመን እንርሳው ብዬ ነው፡፡
እሸቴ አሰፋ በግልፅ ያቀረበላቸው አንዱ ጥያቄ የአንድ ብሔር የበላይነት/የህወሃት የበላይነት አለ የሚል ቅሬታ አለ የሚል ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በግምገማቸው ላይ ተነስቶ በስፋት ውይይት መደረጉ አቶ ጌታቸው ነግረውናል፡፡ የተነሳው የአንድ ብሔር /የትግራይ/ የበላይነት አለ የሚለው አንድ በጎ ነገር ሲሆን የተደረሰበት ነገርም ጥሩ ነው፡፡ አንዱን ኪራይ ስብሳቢ በሌላ ብሔር ኪራይ ስብሳቢ መተካት አይደለም፡፡ ህዝቡ እያለ ያለው ህውሃት ወርዶ በብአዴን ወይም በኦህዴድ ይተካ አይደለም፡፡ ሁላችሁም ውረዱ ነው፡፡ አሁን ያለው የህወሃት የበላይነት እንዲነግስ ያደረጉ አሁን ጥያቄያቸው በተራችን እኛ እንሁን ከመሆን ሊዘል አይችልም፡፡ የእኛ ጥያቄ ግን የዚህ ዓይነት ስርዓት አያስፈልገንም የሚል ነው፡፡
ከአንድ ብሔር የበላይነት ጋር ተያይዞ የተነሳው አንድ ቁልፍ ነገር የቁልፍ ቦታዎች ነገር ነው፡፡ ቁልፍ የሚባሉት ቦታዎች ለምን ቁልፍ ሆኑ? ሲባል ኪራይ ማደያ ሰለሆኑ ነው:: ምርጥ መልስ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡ አንድ የመንግሰት ተቋም ሃላፊ መሆን የራስን ግሳንግስ መሰብሰቢያ ስርዓት ከመገንባት የከፋ ውርደት ከየት ይመጣል፡፡ በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ታሪክ ሚኒስትር መሆን የራስን ቡድን መጥቀሚያ እንዲህ ዓይን ባወጣ መልኩ የሆነበት ጊዜ አሁን ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ ስራተኞች ምደባ ከብቃት ይልቅ በድርጅት ሰለሚሆን ኢህአዴግ አራት ድርጅቶች እንዲሁም በጨረፍታ ለአጋር ድርጅቶች ይታደላል፡፡ ከውጭ ጉዳያ ጋር ተያይዞ በቅርቡ የሰማሁት አንድ ነገር አለ፡፡ ህወሃት የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩን ቦታ ቢይዝም ዋና ዋና የሚባሉትን ቦታዎች ለብአዴን/ብራሰልስ፣ እንግሊዝ፣ እስራኤል፣ወዘተ/ ለቋል የሚል ቅሬታ አለ፡፡ በአሜሪካ ግርማ ብሩም ቢሆን ከኦህዴድ  ይልቅ የሸዋ ሴረኝነቱ ይበልጣል ይሉታል- ህወሃቶች፡፡ ይህ እንግዲህ ህወሃቶች አሁን በያዙት የውጭ ጉዳይ ኪራይ ስብሳቢነት አልረኩም ማለት ነው፡፡ ይህን ለማስተካከልም ሙከራዎች አሉ ይባላል፡፡ መቼም ለምን ከፊት አልሆንም ካልሆነ በሰተቀር በሁሉም ቦታ እንዳሉ በግሌ አውቃለሁ፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ አንድ አሰቂኝ ምላሽ ሰጥተዋል “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የከበቧቸው አማካሪዎች ወሳኝ አይደሉም” የሚል፡፡ እንደ ምሳሌም ያቀረቡት እራሳቸውን አማካሪ በነበሩበት ወቅት ወሳኝ አልነበርኩም በማለት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ቦታዎች በሶሰት ሊከፈሉ እንደሚችሉ ነው፡፡ አንደኛው የእውነት የማማከር ስራ የሚሰሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የተቀጠሩ ባለሞያዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሸተኞች እና ጡረታ እስኪወጡ ሊጠቀሙ የሚፈልጉ ሰዎች የሚገኙበት ነው፡፡ ይህ ምድብ እንደ ማግለያም ማገገሚያም ያገለግላል፡፡ የኤምባሲ ክፍት ቦታም እስኪገኝ መጠባበቂያም ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሶሰተኛው ደግሞ ወሳኝ የሚባሉት የሚገኙበት ነው፡፡ በቁጥርም ውስን ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በፓርቲ ማዕቀፍ መስመር በማስያዝ ውሳኔ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ይህ ሶሰተኛው ቡድን አማካሪ በአቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ አልነበሩም- ሊኖሩም አይችሉም፡፡ ሰውዬ በራሳቸው ወሳኝ ነበሩ፡፡ የተቀሩት ሁሉቱ ዓይነት አማካሪዎች ግን ድሮም የነበሩ ናቸው፡፡ ይህን ህዝቡ በደንብ ያውቀዋል ማን በየትኛው ምድብ እንዳለም ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ የአቶ ጌታቸውን መልስ አልተቀበልነውም፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

No comments:

Post a Comment