Wednesday, February 21, 2018

አገራችን ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በሰላም እንድትሸጋገር ለማድረግ የቀረበ የመነሻ ኃሣብ



ግርማ ሠይፉ ማሩ
ሕዳር 2010
ኢትዮጵያ ሀገራችን አሁን የምትገኘው ዜጎች የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በህገመንግሰት በተቀመጠው መሰረት የማይከበርበት፤ይህን ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር የሚጠበቅባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በፍፁም መንቀሳቀስ ያልቻሉበት እና የአንድ ፓርቲ ፍፁም አንባገነን ኢ-ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ የሰፈነበት ሁኔታ ነው፡፡ አሁን በሀገራችን የሚታዩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች በምንም መመዛኛ ኢህአዴግ እንደሚለው በኢህአዴግ መስመር ብቻ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ሰለ እውነት ለመናገርም በኢህአዴግ አገዛዝ ብቻ የተፈጠሩም አይደሉም፡፡ ሰለዚህ ሁሉንም ባለድርሻ ተሳታፊና ባለቤት ሊያደርግ የሚችል ሁሉን አቀፍ መፍትሔ መፈለግ ወቅቱ የሚጠየቀው ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ ከፊታችን ቀርቧል፡፡
ችግር መኖሩን ተገንዝበው እጅግ ብዙ ባለሞያዎች እና ያገባናል የሚሉ ዜጎች በተደጋጋሚ አሰተያት ሲሰጡ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለንበትን ሁኔታዎች በግልፅ የተገነዘቡ የተለያዩ አካላት ቀደም ሲል የህወሃት ታጋዮች የነበሩና ስርዓቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ ችግሩ መኖሩን እና ለውጥ እንደሚያስፈልግ ምክር እየለገሱ  ሲሆን፣ ችግር መኖሩን መንግሰትም ቢሆን የካደው ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሰት ችግሩን አምኖም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ መገደዱ ይታወሳል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳም በኋላም ሁኔታዎች መሻሻል አለመታየቱ ብቻ ሳይሆን፤ መንግሰት ችግሮቹን በኢህአዴግ መስመር እፈታቸዋለሁ ከሚለው አቋሙ ፈቀቅ ማለቱን የሚያሳይ ፍንጭ ያለመታየቱ፣ ጉዳዩን በማባባስ ሌሎች ሀይሎችም ማንኛውንም አማራጭ ተጠቅመው ለውጥ ለማምጣት መወሰናቸው እና ህዝቡ በይፋ “በቃ” ብሎ አደባባይ መውጣቱን መቀጠሉ ነው፣ የምንወዳት አገራችን በጥፋት ጎደና ላይ እንደሆነች እንዲሰማን እያደረገ ያለ ያፈጠጠ ሀቅ ነው፡፡
የዚህ ምክር ሃሣብ ዓላማም መንግሰት ለዚህ ውስብስብ ችግር በተናጠል መፍትሔ ለማምጣት የማይችል መሆኑን በመገንዘብ አቋሙን እንዲያለሳልስ በመጠየቅ በመፍትሔ ፍለጋው ላይ ሌሎች ኃይሎችም እንዲሳተፉበት ለማድረግ ፖለቲካዊ እርምጃ እንዲወስድ ሲሆን፤ ሌሎች ተሳታፊ ኃይሎችም በተመሳሳይ አቋማቸውን እንዲያለዝቡ እና ወደ አማካይ መስመር እንዲመጡ ለማድረግ መንገዱ ተቀራርቦ መወያየት መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ህዝቡም አሁን የጀመረውን የመብት ጥያቄ መስመር ወደ ከፋ ብጥብጥና ቀውስ ሳያድግ የሚፈልገውን ለውጥ በዲሞክራሲያዊ መስመር ማሳካት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት ሁኔታ መኖሩን በማመን ወደ መደበኛ ተግባሩ እንዲያተኩር ለማስቻል ነው፡፡  
በሀገራችን ኢትዮጵያ በዋነኝነት በፖለቲካ መድረክ ተሳትፎ አለን የምንል በግራም ሆነ በቀኝ መታዘብ የሚቻለው ሀቅ ቀደም ሲል በተከናወኑ ለታሪክ መተው ባለባቸው ኩነቶች ላይ ስንነታረክ እና በአንድ ወይም በሌላ አጋጣሚ አባል የሆንበትን ቡድን በመከላክል እና ሌላውን ጥፋተኛ በማድረግ/Self Defensing and Blaming Others/ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ከአርባ ዓመታት በላይ አብሮን በመኖሩ ተፍጥሮዋዊ እስኪመስለን ድረስ ተዋህዶን ለልጆቻችን እያስተላለፍን እንገኛለን፡፡ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት የሚያስችል የመፍትሔ ሃሳቦች በተለያዩ አካላትና ግለሰቦች ቀርበዋል፤ ነገር ግን ሰሚ አግኝቶ ወደ ተግባር መግባት አልተቻለም፡፡ አሁንም ይህን የመፍትሔ ሃሣብ ትኩረት ሰጥቶ ወደ ተግባር መሸጋገር ከፊታችን የተደቀነ ወሳኝ የወቅቱ ፈተና ነው፡፡ ኳሱ በገዢው ፓርቲ ሜዳ ቢሆንም ሌሎችም ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡
አሁን በሀገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ባጠቃላይ ሲታይ ገዢው ፓርቲ እና መንግስት ዜጎች የሚፈልጉትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በአግባቡ እና በተገቢው መንገድ ለመመለስ ያለመቻላቸውን በግልፅ የሚያመላክት ነው፡፡ የዜጎች ሁለገብ ጥያቄዎች በተበራከቱበት እና መንግሰት ጥያቄዎቹን መመለስ ባልቻለበት ሁኔታ በተደረገ “ምርጫ” ገዢው ፓርቲ መቶ-በመቶ ምርጫ አሸንፊያለሁ ብሎ ስልጣን ላይ ለመቆየት በወሰነበት የመጀመረያ ዓመት ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ ከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ተፈጥረው ለብዙ ዜጎች በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ሲሆን፤ እጅግ በርካት ንብረቶችም ወድመዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በዚሁ እንዲቀጥል ከተተው ሀገሪቱ ልትወጣው ወደማትችለው የቀውስ አዙሪት ውስጥ ልትገበ እንደምትችል የብዙዎች እምነት ነው፡፡
አሁን በሀገራችን ያለውን ቸግር ለመፍታት ዋነኛውና ወሳኝ ጉዳይ ሁሉም ያገባኛል ባይ “የእኔ መንገድ ብቻ ነው ልክ” ከሚል ግትር አስተሳሰብ ወጥቶ ለውይይት እራሱን በማዘጋጀት “በሰጥቶ-መቀበል” ስልጡን ፖለተካ አካሄድ መፍትሔ እንደሚገኝ በማመን፣ በሂደቱ ውስጥ ለመሳተፍ ሲወስን ነው፡፡ ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት/win-win/ መንገድ ለመፈለግ ተነሳሸነት መውሰድ የግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ መንግሰት ከፓርቲዎች ጋር እየተወያየሁ ነው፣ በሚል የተለመደውን በድርድር ሰም በሕዝብና በአገር ላይ የሚደረግ ቀልድ መቆም እንዳለበት  በዚሁ አጋጣሚ አብክሮ መጠቆም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ በአገራችን ያለው ችግር የምርጫ ስርዓት ሳይሆን የፖለቲካ ምዕዳሩ ሆን ተብሎ ለአንድ ገዢ ቡድን መተዉ ነው፡፡
ይህ ፅሁፍ ሁሉም አሸናፊ ይሁን ከሚል መንፈስ እና ማንም ተንበርካኪ ሆኖ በተሸናፊነት ሰሜት የሚቀርብበት መሆን የለበትም፤ የአገሬ ገዳይ ያገባኛል በሚል መነሻ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ኃሣብ መድረሻው ቢዘገይ በቀጣይ 2012 በሚደረግ ምርጫ ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ በሚያደርጉት ውድድር ተጠያቂነት ያለበት መንግሰት እንዲመሰረት የሚያስችል ጥርጊያ መንገድ መክፈት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ መንግሰት የሚጠበቅበት አሁን ከያዘው ብቻዬን መልስ እሰጣለሁ ማለቱን ማቆም ሲሆን፣ ሌሎች ተፉካካሪዎችም እኛ ከምንለው ውጭ ከሚል ግትር አቋም እራሳቸውን መግራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን የመፍትሔ ኃሣብ ተግባራዊ ለማድረግ መነሻ የሰምምነት ነጥቦች/Point of Reference or Pillars/ የሚከተሉት ቢሆኑ ከተለመደው የቀድሞውን አጥፍቶ ከዜሮ ከመጀመር የዜሮ ድምር አስተሳሰብ የሚታደግ ይሆናል፡፡ ሰጥቶ የመቀበል አስተሳሰብም በተግባር እነዚህን ነጥቦች ከመቀበል ይጀምራል፡፡
1.  አሁን ተግባራው እንዲሆን የሚታሰበው የፖለቲካ ምዕዳር ማስፋት እንቅስቃሴ/Political Reform/ ህገ-መንግሰቱን መስረት አድርጎ ሲሆን፣ ህገ መንግሰቱ እንደ አስፈላጊነቱ በህዝብ ይሁንታ ሊሻሻሉ የሚችሉ ጉዳዮች እንዳሉት ከግንዛቤ በማስገባት ነው፡፡ ህገ መንግሰቱ እንዲሻሻል ፍላጎት ያላቸው ሀይሎች አማራጫቸውን በሚፈጠረው ነፃ የፖለቲካ ምዕዳር ማቅረብ ይችላሉ፡፡
2.  ነፃ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ (በሁሉም ተወዳዳሪዎች በቂ ዝግጅት ለማድረግ የሚሰጠው ጊዜ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀኑ በሂደት የሚወሰን ይሆናል ነገር ግን ከግንቦት 2012 ሊያልፍ አይችልም) ተደርጎ መንግሰት እስኪመሰረት ድረስ ኢህአዴግ እና አጋር ፓርቲዎች የመንግሰትን የዕለት ከእለት ተግባራትን በከፍተኛ የሃላፊነት ሰሜትና ተጠያቂነት እንዲወጡ መፍቀድ፡፡ ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመስጠት እንዲታቀቡ ማድረግ፡፡
3.  የፓርቲና የመንግሰት ስራ በግልፅ ተለይተው ይከናወናሉ፡፡ ኢህአዴግ እንደማንኛውም ፓርቲ በሂደቱ ውስጥ ተሳትፎ ያደርጋል የመንግሰት ሃላፊዎች ያለባቸውን የመንግሰትና የፓርቲ ኃላፊነት በሚመጥን ደረጃ እንዲንቀሳቀሱ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ በመንግሰት መዋቅር ውስጥ የተደራጁ የፓርቲ መዋቅሮች በሙሉ ይፈርሳሉ፣ ወደ ፓርቲያቸው መዋቅር ፓርቲው በሚያዘጋጀው መስመር ይጠቃለላሉ፡፡
4.  የመከላከያ፣ የፖሊስ ሠራዊት እና የደህንነት መስሪያ ቤቶች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ተረጋግጦ ማንኛውም አሸናፊ ፓርቲ ለሚመሰርተው መንግሰት በሚሰጠው መመሪያ መሰረት ህዝብን ማገልገል በሚችል መልኩ ተከታታይ ስልጠና እና የማውቅር ማሻሻያ ይደረጋል፡፡ በሁሉም ጊዜ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚያስችለው ቁማና ላይ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ የፖለቲካ ተሳትፎ ፍላጎት ያላቸው የሠራዊት አባላት በፈቃዳቸው ከስራቸው መልቀቅና በፖለቲካ ቀጥታ መሳተፍ ይችላሉ፡፡
5.  ልዩ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር በሀገር ውስጥ የሚከናወኑ የፀጥታ ስራዎች በሙሉ በፌዴራልና ክልል ፖሊሶች ብቻ ይከናወናል፡፡ በአገሪቱ ልዩ ሀይል የሚባል አደረጃጀት በሙሉ ወደ ፖሊስና መከላከያ ይጠቃለላል፡፡
6.  የፍትህ ስርዓቱ ከማነኛውም የስራ አስፈፃሚ ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ እንዲሰራ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታና ድጋፍ በተከታታይ ይስጣል፡፡
ከዚህ በላይ የተቀመጡት ሃሳቦች በዋነኝነት የመንግሰት ሥልጣን የሚያዘው በህዝብ ይሁንታ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ እየቀረበ ያለው ጥያቄ የሥልጣን በአቋራጭ የማግኘት ያለመሆኑን፣ መንግሥትን ከፖለቲካ ፓርቲ በመለየት የስርዓት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ፣ ገዢው ፓርቲ በተሸናፊነት ሰሜት ሳይሆን በሃላፊነት ሰሜት እንዲንቀሳቀስ የሚጠበቅበት መሆኑን ለማሳየት፣ ሌሎች ኃይሎችም በጭፍን ምክር ቤት ይፍረስ፣ የሸግግር መንግስት ይቋቋም የሚሉትን የሁለት ወገን አሸናፊነት የማያሳይ መሆኑን ለማስጨበጥ፣ ወዘተ የሚረዱ ሰለሆነ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ሀይሎች በቅንንት ተመልክተው ሊቀበሉት ይገባል፡፡
ከላይ በቀረቡት የመነሻ የሰምምነት ሃሳቦች መግባባት ከተደረሰ ይህን መሰረት ያደረገ ለውጥ እንዲደረግ የሚከተሉት ወሳኝ ተግባራት መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡
1.  አገር አቀፍ ጉባዔ ሊጠራ የሚችል በመንግሰት፣ በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ሀይሎች ይሁንታ ያገኙ የጉባዔ ጠሪ ኮሚቴ ማወቀር፤
2.  በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያላቸው ዜጎች የሚወከሉበት ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በአጭር ጊዜ እንዲጠራ ተደርጎ የሸግግር ስራዎችን የሚሰራ ኮሚሸን እንዲቋቋም ማድረግ፤
3.  የኮሚሸኑ አባላት በመንግሰትና በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ በሚገኙ አካላት ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ፡፡
ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ተግባራት በአጭር ጊዜ በማከናወን ገዢው ፓርቲ አሁን ከገባበት ምን አልባትም አገርን ሊበትን ከሚችል አዙሪት ለመውጣት መወሰኑን ያረጋግጣል፡፡
ይህ ኮሚሸን በዋነኝነት በአገሪቱ ወሳኝ የሆነውን ምቹ የፖለቲካ ምዕዳር ለመፍጠር ነው፡፡ ይህ ኮሚሽን የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራት ማከናወን እንዲችል በህግ ስልጣን ይሰጠዋል፤ (የሚቀነስ የሚጨመር መኖሩ የሚታይ ነው፡፡)
·         በቀጣይ በአዲሰ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ሊደረግ የታሰበውን ምርጫ እንዲራዘምና ከቀጣይ አገር አቀፍ ምርጫዎች ጋር በጋራ እንዲከናወን ያደርጋል፡፡
·         ለሀገራዊ መግባባት አስፈላጊ ናቸው ተብለው የሚታመንባቸው እስረኞች እንዲፈቱ፣ በውጭ የሚገኙ ማንኛቸውም የፖለቲካ ዓይሎች በነፃነት በሀገር ውስጥ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ መንግሰት አጠቃላይ የምዕረት አዋጅ እንዲያውጅ ሃሣብ ያቀርባል፤
·         የመንግሰት ሚዲያዎች ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በህገ መንግሰት ድንጋጌ መሰረት ክፍት ይሆናሉ፡፡ የመንግሰት ሚዲያ ቦርድ አባላት ይህን በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንደገና ይደራጃል፡፡
·         የግል ሚዲያ ተቋማት በህግ መስረት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል (በዘርና ሀይማኖት መሰረት ወይም ደግሞ ለኢትዮጵያዊነት ባህል ውጭ የሆኑት ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ)፤ በተቻለ መጠን ጋዜጠኞች መረጃ ከመስጠት በተጨማሪ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የመረጃ ማግኘት ነፃነታቸው ይከበራል፤
·         ለነፃ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንቅፋት የሆኑ ህጎች ተለይተው እንዲሻሻሉ ወይም ተግባራዊ እንዳይሆኑ ያደርጋል፤
·         በፖለቲካ አስተምህሮ ላይ መስራት የሚፈልጉ ነፃ ሲቪል ማህበራት በተጠያቂነት ሰሜት እንዲንቀሳቀሱ እና ህዝቡ ስብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም እንዲችል ድጋፍ እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡
·         በህገ መንግሰት የተፈቀደውን የዜጎች የመደራጀት መብት ሳይጋፋ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ይህን ለማድረግ የሚየስችል አቅም ያላቸው መሆኑ ለማረጋገጥ ህግ ይወጣል በዚሁ መሰረት ተረጋግጦ ምዝገባ ይደረጋል፡፡ (ዝርዝሩ በህግ የሚወሰን ይሆናል) ይህን መስረት አድርጎ የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ እንዲሻሻል ይደረጋል፡፡ አሁን ተመዝግበው ያሉ ፓርቲዎች የሚቀመጠውን ዝቅተኛ መስፈርት ማሟላታቸው ሲረጋገጥ ድጋሚ ምዝገባ ያደርጋሉ፡፡
·         የምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች ተጠሪነታቸው ለምክር ቤት የሆኑ አካላት (አሁን ምክር ቤቱ በአንድ ፓርቲ የተያዘ መሆኑ ከግንዛቤ በማስገባት) አወቃቀራቸው ተቀባይነት እንዲኖረው ከማድረግ በተጨማሪ ሪፖርታቸውን ለህዝብና ለሚዲያ በይፋ ያቀርባሉ፤ ያቀረቡት ሪፖርት በማነኛውም አካል ይፋ ሆኖ ተዓማኒነቱ ይረጋገጣል፡፡
ከላይ የቀረበው ሃሳብ በዋነኝነት መንግሰት የዚህችን አገር ለብቻዬ ልፍታ ከሚል የተለመደ መንገድ እንዲወጣ፤ ተቃዋሚ ወገኖችም በሚፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምዕዳር ለአገራቸው የሚያስቡትን በጎ ነገር ሁሉ ለህዝብ በይፋ እንዲያቀርቡ፤ ወሳኙ ሕዝብ መሆኑን ሁሉም አካል ተቀብሎት አገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሸግግር በሰላም እንድታደርግ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ መነሻ ኃሣብ መሰረት መንግሥት ሌሎች ሁኔታውን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ተጨማሪ ጉዳዮችን በመጨመር ለተግባራዊነቱ በይፋ መነሳት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን አሁን በስልጣን ላይ ያሉትም ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች አገር የግላቸው እንደሆነ አድርገው ብቻቸውን ከመጨነቅ የሚወጡበት መንገድ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ይህች አገር በአፋጣኝ ወደ ወሳኝ የፖለቲካ ምዕዳር ለውጥ ማሸጋገር ሳይቻል ቀርቶ አሁን በተያዘው ሁኔታ በሚደረጉ ጥገናዊ ለውጦችና ሠራዊት በመጠቀም በሚደረግ አፈና ከቀጠለ ወደማንወጣው ቀውስ ከመውሰድ የዘለለ ምንም ለውጥ ሊሆን የሚችል ነገር መጠበቅ አይቻልም፡
ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu@gmail.com


No comments:

Post a Comment