Tuesday, March 27, 2018

ኢትዮጵያችን በመንታ መንገድ በገደል አፋፍ ትገኛለች ዜገች ምን እንወሰን?



የአገራችን ፖለቲካ መበላሸቱ ብቻ ሳይሆን፣ የአገር እልውናን አደጋ ላይ የሚጥል ሊሆን እንደሚችል ስጋት ያላቸው ብዙ ናቸው፡፡ እኔም የፈለገ ተሰፈኛ ብሆን ከዚህ ስጋት ነፃ ነኝ ልል አልችልም፡፡ አፍቃሪ ህወሓት/ኢህአዴግ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያም ይሆን ሌሎች መገናኛ ብዙዓን ይህን ስጋት አጉልተው ለማሳየት የማያደርጉት ጥረት የለም፡፡ ከጥረታቸው ሚዛን የሚደፋው በቅርቡ በመታመስ ላይ ያሉተን ሊቢያ፣ ሶሪያና የመንን እንደምሣሌ በማቅረብ ነው፡፡ ይህ በምሥልና ድምፅ እየተደገፈ የሚቀርበው ዘግናኝ ትዕይንት ለመማር ለሚፈልግ ጥሩ ማሣያ ነው፡፡ ነገሩ ግን ሌላ ነው፡፡ እንደ እነዚህ አገሮች እንዳንሆን አርፋችሁ ተቀመጡ የሚል መልዕክት ያዘለ፣ ሠላም፤ ሠላም፤ ሠላም በሚል መዝሙር አጅበው ማቅረባቸው ነው፡፡ ሊቢያ፣ ሶሪያ እና የመን ለዚህ ደረጃ ያበቋቸው አንባገነን መሪዎች ናቸው፡፡ ከዚህ መማር ያለባቸው አንባገንን መሪዎች እንጂ ህዝቡ ሊሆን አይችልም፡፡ መቼም በእነዚህ አገሮች ውድመት ህዝቡ ነው ተጠያቂ የሚል ሰምቼም አንብቤም አላውቅም፡፡ የእኛም አገር መሪዎች እባካችሁ አገራችን እንደነዚህ አገሮች እንዳተትሆን ከግል ሥልጣን መሻት እና ሌላ ማንኛውም ግላዊ ፍላጎት እራሳችሁ አፅድታችሁ ታሪክ ስሩ እያልነናችሁ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከላይ ከተጠቀሱት አገሮች እንደ አንዳቸው እንዳትሆን ኃላፊነቱ ያለው በፖለቲካ መሪዎች ይልቁንም በህወሓት/ኢህአዴግ እጅ ውስጥ ነው፡፡
አገራችን በመሰቀለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝ፡፡ ከመገዶቹ ዳር እና ዳር ደግሞ ጥልቅ ገደል መኖሩን እንገነዘባለን፡፡ ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ እና ከገደሉ መራቅ የግድ ይላል፡፡ ይህ የአሰተዋይ ምርጫ ነው፡፡ የሰሞኑ ነገሮችን አያያዝ ለሚያስተውል ግን የብልዕ አያያዝ አይመስልም፡፡ እስረኞችን መፍታት መጀመሩ በጎ ጎኑ ሲሆን ሌሎችን ያለመፍታት ሲከፋም በተመሳሳይ ሁኔታ እስርን መጀመሩ አሳኙ ክስተት ነው፡፡ እስረኞች የተፈቱበት ምከንያት ለጋራ አገር በጋራ መፍትሔ ለመፈለግ የመሰለን ሰዎች ተሳስተናል ማለት ነው፡፡
የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት በቁርጠኝነት የተሻሉ እርምጃዎች ይወሰዳሉ የሚለው ቀርቶ ለቀጣይ ስድስት ወር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንድንሆን ያለፍላጎታችን ሲፈረድብን ደግሞ የበለጠ ግምታችን የተሳሳተ፣ ተሰፋችንም የዕልም እንጀራ እየሆነብን ይገኛል፡፡ ሌላው ተሰፋ የጣልንበት ወፌ ቆመች እያልነው የነበረው ፓርላማ መዋረዱ ተስፋችንን ያጨልምብናል፡፡ ፓርላማውን የሚያዋርዱት ደግሞ “የተከበሩ” ተብለው በምክር ቤት ውስጥ ያሉት ጭምር መሆናቸው ነው፡፡
እንዲህ እንድንል የሚያድርገን ደግሞ ግንባሩ ከዚህ በፊት በሚስጥር ሲያደረግ የነበረው ሁሉ አሁን በይፋ እያደረገው መሆኑ ነው፡፡ ግንባሩ ሸፍጥ እና የሸፍጥ ድርጅት እንደሆነ በግልፅ አውቀናል፡፡ በቅርቡ ኢህአዴግ እንደ ግንባር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈልገኛል ብሎ ቆርጦ ተነስቷል፡፡ በግልፅ ቋንቋ ወታደራዊ አገዛዝ ያስፈልገኛል እያለ ነው፡፡ ይህን ደግሞ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በተለመደው አካሄድ ከፀደቀ በኋላ ወደ ካቢኔ በመሄድ ለወጉ እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡ ፓርቲው ያፀደቀውን የመንግሰት አካል ተብዬው “ካቢኔ” የሚባለው የሚቃወምበት አቅም የለውም፡፡ ለዚህ ነበር ቴክኖክራት ካቢኔ ዋጋ የለውም ስንል የነበረው፡፡ ይህ ጉዳይ ወደ ፓርላማ መቅረብ ሰለነበረበት ደግሞ በተመሳሳይ በፓርላማ አባላትም ቀድመው ውይይት እንዲያደርጉ በየድርጅቶች የስራ አሰፈፃማዊ ውሳኔው ተነገራቸው፡፡ ውይይቱ ውሣኔ ለመቀየር ሳይሆን እንደተtለመደወ የስራ አሰፈፃሚውን ውሳኔ እንዲቀበሉ ነበር፡፡ ድርጅታዊ ማዕከላዊነት በሚባል አስራር፡፡ ይህ በተመሳሳይ አጋር ለሚባሉት ድርጅቶችም ተደርጓል፡፡ ሁለት ሶሰተኛ ድምፅ የሚያስፈልግ በመሆኑ 46 ድምፅ ያላቸውን አጋሮችንም ችላ ማለት ሳያስፈልግ፣ አፈ ጉባዔው ፈልገውት እንደነበረው በተባበረ ድምፅ ለማጽደቅ ታስቦ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ቲያትር ለመስራት፡፡
ድርጅቶቹ ውስጥ ለውስጥ ውሳኔ ካሳለፉ በኋላ ምክር ቤት ሰብሰባ ብለው ይቀመጡና ለቀለድ ጥያቄና መልስ ሲያደርጉ ቆይተው በሙሉ ድምፅ ፀደቀ ለማለት አፋቸው ደንቀፍ ሳይል ለማጠናቀቅ ወስነው ነበር፡፡ ይህን የድርጅታዊ አስራር በመተማመን ነበር አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በተባበረ ድምፅ እንዲፀድቅ የሚል ደፋር ጥያቄ ለምክር ቤት ተብዬው ያቀረቡት፡፡ ለማንኛውም ይህ እንዲሆን ለጊዜውም ቢሆን ያልፈቀዱት እጅግ ብዙ አባላት በታሪክ ፊት በኩራት የሚያቀርባቸውን ውሳኔ ወስነዋል፡፡ በየድርጅቱ ሲደረገ ከነበረው ውትወታና ማገባባት ይልቅ ወደ ሕዝብ ድምፅ፤ የህሊና ፍርድ እና ሕገ መንግሰቱን ወደ ማክበር አድገዋል፡፡ ይህ የፈጣሪ ስራ ነው፡፡

ከህዝብ ጀርባ፤ ከህዝብ ፍላጎት ውጭ ይህ ሁሉ ሲደረግ በእኔ አሰተያየት አቶ ሀይለማሪያም ደሣላኝ ከስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረብኩ ከሚሉን፤ በእውነትም የለውጡ አካልና መሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን እድል በሚያሳዝን ሁኔታ አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ይህንን ምክር ቤት በህገ መንግሰቱ አንቀፅ 60 መሠረት በትነው በስድስት ወር ውስጥ ምርጫ በማድረግ ለአሸናፊ ስልጣን ማስረከብ ነበር፡፡ ይህ ታሪክ በወርቅ ሳህን ያቀረበላቸውን እደል ሳይጠቀሙበት አልፈዋል፡፡ እናዝናል፡፡ አሁን ደግሞ ማንም ይሁን የሚመጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ታሪክ እንዳይስራ እንቅፋት የሚሆን አፈና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም ለምን እንዳሰፈለገ አልገባንም፡፡ ለለውጥ የተነሳን ህዝብ ማንኛውም የአፈና አካሄድ አያቆመው፡፡ በውሰጥ ለውስጥ ስምምነት ተደርጎ በመጣ ውሳኔ በምክር ቤት ስም ለማላገጥ የመጣን ቡድን አምላክ በኪነ ጥበቡ አጋለጠለን፡፡ አሁን የተፈጠረው የቁጥር ስህተት ለአንደኛ ደረጃ ተማሪም ቢሆን ከባድ አልነበረም፡፡ እንኳን ስማርት ፎን/ስልክ ይዞ ሂሣብ ለሚስራ የምክር ቤት አፈ ጉባዔ፡፡ ፈጣሪ ግን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ የተሰራን ሴራ በአደባባይ አጋልጦልናል፡፡ ይህን ሸፍጥ ለማጋለጥ ብርታት ላገኙት የምክር ቤት አባላት ምስጋና እና ክብር ይገባቸዋል፡፡ ይህን ስህተት ማረሚያ መንገድም ወደ ምክር ቤቱ መድረክ ተመልሶ በግልፅ በሚሰራ ማስተካከያ ብቻ ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ አቶ ሀይለማሪያም ደሣለኝ እድላቸውን ባይጠቀሙበትም ሌሎች ታሪክ እንዲሰሩ እድል ፈጥረዋል ለማለተም ይቻላል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒሰትር ማን ይሆናል? የሚል ጥያቄ እንዲነሳ በማድረግ፡፡ ነገር ግን ይህ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሰየም ጣጣ አሁንም በድርጅት ሴራና አሻጥር ውስጥ መውደቁ አሳዛኙ የህወሓት/ኢህአዴግ ቲያትር ሌላኛው ክፍል ነው፡፡ ሰሞኑን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒሰትር ማን ይሁን? የሚለው ጥያቄ እያስነሳ ያለው ጭቅጭቅ የኢትዮጵያ ህዝብ በግልፅ መሪውን የመምረጥ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አቅም አንዳለውም የሚያመላክት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ህወሓት በተለይ አቶ መለስ ዜናው በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ዝቅተኛ ተቀባይነት ከግምት በማስገባት “ፓርላሜንታዊ ሥርዓት” በሚል ሸፋን ዜጎች መሪያቸውን በቀጥታ እንዳይመርጡ ይልቁንም ድርጅቶች ከህዝብ ጀርባ መሪ ተብዬ የሚመርጡበት ሴራ ሰርተውብን አልፈዋል፡፡ ይህ አካሄድ ግን ማብቂያው ጊዜ ደርሷል፡፡ ራዕይ አለኝ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመምራት እችላለሁ የሚል ዜጋ በይፋ ወጥቶ ለህዝብ ቀርቦ ዳኝነቱን ከህዝብ መጠበቅ አለበት፡፡
ኢትዮጵያዊያን በመንታ መንገድ በገደል አፋፋ ላይ ብንገኝም መውጫውን መንገድ እናውቀዋለን፡፡ ደንቃራ የሆነብን አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው መንፈስ እና የመንፈሱ ተሸካሚ የሆኑት የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮች ናቸው፡፡ ለዚህች አገር ትንሣዔ ሲባል አገራችን የጋራ መሆኗን ከግንዛቤ በማስገባት በጋራ መፍትሄ እንፈልግ፡፡ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒሰትር ከዚህ የሚበልጥ ታሪካዊ አጋጣሚ አያገኝም፡፡ ይህን እድል ይህችን ትልቅና ታሪካዊ አገር ወደ ከፍታው ማማ ለማውጣት በጋራ አብረን እንቁም!!!!!
ግረማ ሠይፉ ማሩ
መጋቢት 2010

No comments:

Post a Comment