Saturday, March 31, 2018

ዶክተር አብይ አህመድ እንደ ጠቅላይ ሚኒሰትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ



ተሰፈኞች ተሰፋ የምናደርገው ሞኞች ስለሆንን አይደለም፡፡ ይልቁንም ጮሌዎች፣ በልጣ ብልጦች ሳንሆን አንቀርም፡፡ ይህም በሠላም የመኖራቸን የጤንነታችን መሠረት እንደሆነን እምነቴ ነው፡፡ ተስፋ ቢስነት ምን ያደርጋል? ተስፋ ቢስነት (Negative Energy) ኃይል ጨራሻ ነው፡፡ በሆነው ባልሆነው ተስፋ እየቆረጥን ኃይላችንን መጨረስ ያለብን አይመስለኝም፡፡ ተስፋ የምትቆርጡ ሁሉ የተሰፈኞችን ቡድን ብትቀላቀሉ ምክሬ ነው፡፡ መፅሃፉ እንደሚለው ለራስህ እንዲሆን የምትወደውን፤ ለባልንጀራህም አድርግ እንደሚለው ማለት ነው፡፡ ባለፈው አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በወንበር ገፍ ሥልጣን ሲይዙ “ማወከብ ሳይሆን ማገዝ አለብን” ብዬ ስሟገት ነበር፡፡ ይህን በማለቴ ከፓርቲዬ (ነብሱን ይማርና አንድነት ድንክ ሳይሆን) ጭምር ከፍተኛ ውግዘት ደርሶብኛል፡፡ አይቼ አይቼ ሲበቃኝ ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት መሆኑ ነው፤ እባኮትን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን ይልቀቁ ብዬ ፃፍኩ፡፡ ሁለቱም ጊዜ ልክ ነበርኩ፡፡ በእርግጥ ከእኔ በተቃራኒ የቆሙትም ቢሆኑ በራሳች መለኪያ ልክ ናቸው፡፡ ብለን ነበር፤ ይኽው ለውጥ የሚባል ነገር አላመጡም፣ ብለው ሊሟገቱ ይችላሉ፡፡ ልዩነቱ የእኔ ብጤዎች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በተስፋ ዳቦ ኖረናል፡፡ በእኔ እምነት አቶ ሀይለማሪያም ደሣለኝ ላይ ተሰፋ እንድጥል ያደረጉኝ ነገሮች ሁሉ ተሰፋ ለማድረግ ከበቂ በላይ ነበሩ፡፡ እሳቸው ይህን ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ ይህ በወርቅ ሳሕን ታሪክ የሰጣቸውን እድል ባለመጠቀማቸው ጥፋቱ የእርሳቸው እንጂ የእኔ እና የእኔ ቢጤ ተስፈኞች ሊሆን አይችልም፡፡ ዶክተር አብይ አህመድ በአቶ ሀይለማረያም ደሣለኝ ላይ ተስፋ እንዳደርግ ያደረጉኝ ምክንያቶች በሙሉ ያሏቸው ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ችሎታዎችም አይቼባቸዋለሁ፡፡ ሰለዚህ ተሰፋ ማድረጌን እቀጥላለሁ፡፡ ተሰፋዬ እውን ባይሆን አሁንም ጥፈቱ የእኔ ሳይሆን የዶክተር አብይ አህመድ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ዶክተር አብይ አህመድ ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ሲመረጡ በፌስ ቡክ ገፄ ላይ እንዲህ ብዬ ከትቤ ነበር፡፡ “ለታሪክ የተፃፈን ሰው ከታሪክ መዝገብ መፋቅ አይቻልም፡፡ ከአሁን በኋላ አብይ አህመድ በታሪክ መዝገብ ተፅፏል በደግ ይሁን በክፉ ወሳኙ እርሱና እርሱ ብቻ ናቸው፡፡”
በዚህ መነሻ ዶክተር አብይ በመጪው ለምክር ቤቱ ወይም ደግሞ ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ በሚያደርጉት ንግግር በምንም መመዛኛ ዝም ብሎ ለሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ ተብሎ የሚደረግ የፖለቲካ ቃላት ድረቶ መሆን የለበት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢህአዴግን እንደ ፓርቲ ከዘመኑ ጋር ሊያቀራርቡት መስራት እንደሚፈልጉ ሊነግሩን ሙከራ ባያደርጉ እመክራለሁ፡፡ ይህ የድርጅት የቤት ሥራቸው ስለሚሆን የሚያደርጉት ንግግር በሙሉ መቃኘት የሚኖርበት በጠቅላይ ሚኒስትርነት እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በመሆናቸው የሚያደርጉት ንግግር መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህን ካልተረዱት የውድቀታቸው መጀመሪያ ይሆናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማሪያም መውደቅ የጀመሩት “የመለስን ራዕይ አስቀጥላለሁ”፣ “ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለታላቁ መሪ”፣ ወዘተ ማለት ሲጀምሩ ነው፡፡ ተሰፋ ሳንቆርጥ አሻራዎን ያኑሩ ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር ብንልም አልሰሙን፡፡ መጨረሻቸው ይህ ሊሆን፡፡
ዶክተር አብይ ኢህአዴግን ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚሆን ፓርቲ ማድረግ ለእኔ እና ለእኔ መሰል ዜጎች አንድም የሚፈይደው ነገር እንደሌለው መረዳት አለባቸው፡፡ ይህ ለፓርቲ አባሎቻቸው ማድረግ የሚገባቸው ንግግር ነው፡፡ በፓርቲያቸው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይህን ንግግር ማቅረብ ተገቢ ቦታ ነው፡፡ እኛ ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር በንግግራቸው ውስጥ እንዲያካትቱት የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ ዋና ዋናዎቹን በመጠቆም ሃላፊነቴን ለመወጣት እሞክራሉ፡፡
ፖለቲካዊ ጉዳዮች፤ የኢትዮጵያ አገራችን ፖለቲካ በመንግሰት ሚዲያ ሠላም፣ሠላም፣ ሠላም በሚሉ ዘፈኖች፤ እንዲሁም በቴሌቪዥን በሚበሩ ነጫጭ ወፎች የሚገኝ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፈውስ የሚያገኘው፣ ሁሉም ዜጋ በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ በመረጠው መስመር መደራጀት እና ሃሣቡን በነፃነት ለህዝብ ማቅረብ ሲችል፡፡ ሃሣቡን የሚያቀርብበት መድረክ ደግሞ ክፍት እንዲሆን ማድረግ፤ የመንግስት ሃላፊነት ነው፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ይህ ሊሆን ባለመቻሉ በነፍጥ ያሸነፉት ቤተ መንግሥት በገቡ ማግስት ሌሎች ደግሞ ጥራኝ ጫካው፣ ጥራኝ ዱሩ ብለው ነፍጥ አንስተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቀለበስ በማንኛውም ሁኔታ ነፍጥ አንስተው ሥርዓቱን ለመጣል የተሰለፉትን ቡድንኖች ወደ ሠላማዊ መድረኩ እንዲመጡ ከልብ የመነጨ ከፖለቲካ ብልጣብልጥነት የፀዳ ጥሪ መደረግ ይኖርበታል፡፡ የሂደቱን ታማኝነት ለማረጋገጠ ደግሞ ገለልተኛ የሆኑ አካላት እንዲሳተፉበት ማደረግ ክብር ያሰጣል እንጂ ውርደት ሊሆን የሚችልበት አንድም ምክንያት አይኖርም፡፡ ይህን ጉዳይ መምራት የክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ኃላፊነት ነው፡፡ በሴራ የተካኑ የቀድሞ ፖለቲከኞች በፍፁም ከዚህ ተግባር ለአገር ፖለቲካ ድህነት ሲባል መራቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ቢቻል በፈቃዳቸው ገለል በማለት ሥራቸውን እንዲያቀሉላቸው ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በአገር ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኖ ሌሎች ለመንቀሳቀስ ፍላጎት ያላቸው ሁሉ በአገር ውስጥ መንቀሳቀስ እንዲችሉ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር የግድ መሆኑን ያህል፤ በግል ጥቅም (ሥልጣን፣ ገንዘብ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል) ተነሳሰተው ሕዝብን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል እንቅስቃሴ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸውን ሀይሎች ለመቆጣጠር እና ለማጋለጥ የሚያስችል ጠንካራ የሲቪል ማህበራትና የሚዲያ ተቋማት ሚናቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ሲቨል ማህበራት ሕዝቡ አማራጮችን ገምግሞ እንዲወስን ውሣኔውን ደግሞ መቼና እንዴት እንደሚያደርግ ማሰተማር እንዲችሉ ድጋፍ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ሚዲያዎች አሁን ካለቸው የአየር ሰዓት ሕዝቡ አማራጨን ለማድመጥ እና ለመመልከት እንዲችል ማድረግ እንዲችል መፈቀድ ይኖርበታል፡፡ ማለትም አሁን የተጫነባቸው የፍርሃት ቆፈን በጠቅላይ ሚኒሰትሩ ንግግር ተስፋ እንዲጫርባቸው ያስፈልጋል፡፡
ዜጎች የተሳሳተ አማራጭም ቢሆን የመምረጥ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብታቸው ሊከበር ይገባል፡፡ በተጨማሪ፤ የክልል መንግሰታት ነፃነት ሊከበር እና ፌዴራል መንግሰቱ ደግሞ በጥብቅ የሰብዓዊ መብት አያያዛቸውን ሊከታተል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ የክልል መንግስታት የፖለቲካ ነፃነት ለአካባቢያቸው እድገት ብቻ ሳይሆን ለሠላማችን ጭምር ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሰቱ ከማገዝ የዘለለ ሚና ሊኖረው አይችልም፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚወለደው በክልሎች እንደሆነ በግሌ ይሰማኛል፡፡
ከላይ ከተገለፁት አጭር ፖለቲካዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እንዲያነሷቸው የሚጠበቀው፤ ምን አልባት በተሻለ ያስቀምጡታል ብዬ የማስበው ኢትዮጵያዊያን ያለን ማህበራዊ ግንኙነት በዘርና ብሔር መከፋፈል እንደሌለበት ይህም ከከፍታችን ያወርደን እንደሆነ እንጂ የሚጨምርልን ነገር አለመኖሩን፣ ሁሉም ዜጋ አገሩ የጋራ መሆኑን አፅዕኖት ይሰጡታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን የሚደምቀው በማህበራዊ ግንኙነታቸን ውስጥ እንጂ ባለን የፖለቲካ ልዮነት ወይም አስተሳሰብ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህን ስፅፍ በፆም ወቅት ምርጥ ዶሮ ወጥ በህሊናዬ እየታየኝ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ በአገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል እየተባለ፤ አንዱ በፎቅ ለይ ፎቅ ሲደርብ ሌላው ለምፅዋት እጁን የሚዘረጋበት የኤኮኖሚ ስርዓት መፍረሱን ማብሰር አለባቸው፡፡ ፍትሓዊ ተጠቃሚነት ሲባል፣ ዜጎች በኤኮኖሚ ደረጃ መለያየት መኖሩን ማስወገድ የማይቻል ቢሆንም ልዩነቱ ግን በጥረት የሚመጣ እንጂ ከባልሥልጣን ጋር በመሻረክ እና የእገሌ ዘር በመሆን እንደሌለበት መሰመር ያለበት እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሥራ ታጥቆ እንዲነሳ ሊያበረታቱት ይገባል፡፡ ፍትሓዊ ያልሆነ ተጠቃሚነት ምንጩ የፖለቲካ ሥርዓት በመሆኑ ይህ ደግሞ ቀድሞ ማህበራዊ ግንኙነታችንን ቀጥሎም ደግሞ ሥርዓቱን እንደሚገረስሰው ፍንትው ብሎ ታይቷል፡፡ መቼም ይህ ያልተገለፀለት የኢህአዴግ አባል ካለ ችግር ላይ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ባለፈው ሶሰት ዓመታት በአገራችን በፖለቲካው ውጥንቅጥ መንስዔ ማህበራዊ እሴቶቻችን እንዲሁም የኤኮኖሚ መሰረቶቻችን አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ ሰለዚህ ፖለቲካውን በማከም አገራችንን ከውድቀት ልንጠብቃት የግድ ይለናል፡፡ ማንኛውም ዜጋ ደህንነቱ የሚረጋገጠው ኢትዮጵያዊ መንግሰት ሲኖር መሆኑን በማመን የእኔ ብሔር መከላከያ፣ የእኔ ብሔር ደህንነት ካልሆነ አደጋ ላይ እወድቃለሁ ከሚል ስጋት ነፃ እንዲሆን ማድረግ የመጪው ጠቅላይ ሚኒሰትር ትልቁ ሥራ ነው፡፡ የመከላከያ እና የደህንነት እንዲሁም የፖሊስ ተቋማት በሙሉ ለዜጎችና ለአገር ደህንነት እንጂ ለአንድ ቡድን ታዛዥ የሚሆኑበት ሥርዓት ማክተም ይኖርበታል፡፡ የዜጎችን ሃሣብ የሚሰልል ተቋም አያስፈልገንም፡፡ ዜጎችን ከውጭ ጠላት የሚጠብቀን ሠራዊት ያስፈልገናል፡፡ በአገልግሎታችሁ እንኮራለን የምንላቸው የሠራዊት አባላት ይናፍቁናል፡፡ በትምህርት ቤት የሠራዊት ቀን ተብሎ ዩኒፎርም ለብሰው ልጆቻችን ፎቶ ሲነሱ ለማየት ይናፍቀናል፡፡ የኢትዮዮጵ መለዮ ለባሾች ልብስ ዜጎችን ማስፈራሪያ መሆኑ ማብቃት ይኖርበታል፡፡
መልካም የሥራ ዘመን ክበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
ከግርማ ሠይፉ ማሩ


No comments:

Post a Comment