Saturday, April 12, 2014

ኢህአዴግ፣ ምርጫ እና አማራጭ ፓርቲዎች




ግርማ ሠይፉ ማሩ
ባለፈው ፅሁፌ በሀገራችን ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ እጅ ጣት ቁጥር ከማይሞሉት ውጭ ያሉት እንዲሁም ምርጫ ቦርድ ተገፍተው እንኳን ለመነሳት ባትሪያቸውን የጨረሱ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡ ይህን ሀሳብ የሚያጠናክር ዜና በጋዜጣ ላይ አነበብኩኝ እና ድጋሚ ስለ ኢህአዴግ፣ ምርጫ እና አማራጭ ፓርቲዎች ግንኙነት ለመፃፍ ወሰንኩ፡፡ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነው የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ የፈረሙ አና በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ ፓርቲዎች ኢህአዴግ (ልብ በሉ መንግሰት አላሉም) ከዚህ በፊት ሲሰጣቸው የነበረውን ብር አንድ ሚሊዮን ድጋፍ ወደ ብር ሁለት ሚሊዮን ሊያሳድገው እንደሆነ ነገር ግን እነርሱ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እንዲረዳቸው ወደ ብር አራት ሚሊዮን እንዲያሳድግላቸው ፍላጎታቸው መሆኑን፤ ይህን ጥያቄም በቀጣይ የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደሚያነሱት ገለፁ የሚል ዘገባ ማንበቤ ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲች ገዢውን ፓርቲ ገንዘብ ጠየቁ የሚለው ፌዝ መሳይ እውነት ለብዙ ሰው እንዲገባ በእግር ኳስ ምሳሌ ማስረዳት ጥሩ ነው፡፡ አቶ ሀይማሪያም ደሳለኝ የክልል ርዕስ መስተዳደር በነበሩ ጊዜ ለክልል ምክር ቤት አባላት ምርጫን በእግር ኳስ ምሳሌ ሲያስረዱ፤ ከከንባታ ዞን፣ ከአንጋጫ ወረዳ የተወከለ ተቃዋሚ አይደለም በሩጫ ይሁን ብሎ ተሰብሳቢውን አሰቆ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ እኔ በእግር ኳስ ላስረዳ የእንግሊዝ ጫወታ ለሚወድ ማንችስተር ሲቲ ወይም ማንችስተር ዩናይትድ ተቀናቃኛቸው አርሴናል ዋናጫ መብላት ስለተቸገረ ቡድኑን ለማጠናከርና ለዋንጫ እንዲበቃ ማሊያ እና ጠንከር ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾች መግዣ ብለው ገንዘብ እንደመስጠት የሚቆጠር ነው፡፡ ወይም በሀገራችን ጊዮርጊስ ቡናን ለማጠናከር የገንዘብ ድጋፍ እንደማድረግ ነው፡፡ የልምድ ልውውጥ እንዳይመስላችሁ ጊዮርጊስ ብዙ ዋንጫ ስለበላ በአዘኔታ ቡና ዋንጫ እንዲያገኝ ለማገዝ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስላቅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ነብስ ዘርቶ ነው ያለው፡፡
ለነገሩ እነዚህ ፓርቲዎች በኢህአዴግ ተቆራጭ እየተደረገላቸው የሚቆሙ በመሆናቸው ለወጉ ነው እንጂ አማራጭ ናቸው ብለን የምናስባቸው አይደሉም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎቸ ከኢህደዴግ ሀጋር ድርጅቶች የሚለያቸው የአብዮታዊና ልማታዊ መንግሰት ፍልስፍና ተቀብለናል ብለው በኢህአዴግ ፕሮግራም ነው የምንመራው ያለማለታቸው ነው፡፡ ከዚህ በሰተቀር በሚባል ደረጃ የፓርቲያቸው ፕሮግራም ስለመኖሩ አይታወቅም እና አማራጭ አላቸው ብለን እኛም አናምንም ህዝቡም በዚህ ጉዳይ አይጠረጥራቸውም፡፡ ሁሌም እንደምለው የእነዚህ ፓርቲዎች መኖር በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ለማገዝ ሳይሆን ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ብዙ ፓርቲዎች አሉ ለማስባል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ለረዥም ጊዜ ያለተቀናቃኝ በስልጣን ለመቆየት ያስቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት ጭምር የሚጠቀምበት ነው፡፡ አማራጭ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው ፓርቲዎች በተቃራኒው ቆመው ሀገር አማራጭ ያሳጣሉ፡፡
ይህ ተግባር የሞራልና የመርዕ ጥሰት ብቻ ሳይሆን ህገወጥ ድርጊት ነው፡፡ ኢህአዴግ ለእነዚህ ፓርቲዎች የሚያድለውን ገንዘብ የሚያገኘው ከመንግሰት ካዝና ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ለምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት መሰረት ለፓርቲዎች የሚሰጠው ድጋፍ በክልልና በፌዴራል ምክር ቤቶች ባገኙት መቀመጫ መሰረት በመሆኑ እነዚህ በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ ፓርቲዎች ደግሞ መቀመጫ ስለሌላቸው ገንዘቡን በሙሉ ጠቅልለው የወሰዱት ኢህአዴግና አጋሮቹ መሆናቸው አስታውቆዋል፡፡ ኢህአዴግ ግን በዚህ መሰረት ያገኘውን ገንዘብ በቸርነቱ ለነዚህ ፓርቲዎች እንዲታደል አድርጎዋል፡፡ ለዚህም ምርጫ ቦርድ ትብብር ማድረጉን በአደባባይ አምኖዋል፡፡
የመጀመሪያው ህገወጥ ተግባር ኢህአዴግ እንዲጠቀምበተ ከመንግሰት ካዝና በምርጫ ቦርድ በኩል የተሰጠውን ገንዘብ ለሌሎች ፓርቲዎች አሳልፉ የሚስጥበት አንድም የህግ አግባብ የለም፡፡ ለምሳሌ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ከመንግሰት የተመደበለትን በጀት ለክልል ጤና ቢሮ ወይም ለትምህርት ሚኒስትር አሳልፎ መስጠት አይችልም፡፡ ካልተጠቀመበት ወደ መንግሰት ካዝና መመለስ ብቻ ነው ያለው አማራጭ፡፡ ይህን ድርጊት ለምርጫ ቦርድ ሃላፊው ፕሮፌሰር መርጊያ በቃና የተነገራቸው ቢሆንም አሁንም ለማረም ዝግጁ የሆኑ አይመስልም፡፡ በሹመት ላይ ሆኖ ህግ የሚተላለፍ ባለስልጣን የሚቀጣበት ሀገር ስለአልሆነ በማንአለብኝነት በህገወጥ ድርጊቱ ቀጥለዋል፡፡ ቀን የጨለመ ዕለት ግን ማጣፊያው እንደሚያጥር ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህን ፅሁፍ እያዘጋጀው እያለ ፕሮፌሰር መርጊያ መግለጫ ሲሰጡ ሰማው እንዲህ ብለው “ገለልተኛ አይደላችሁም ይሉናል፤ ለገዢው ፓርቲ ያደላሉ ይሉናል፤ በእውነት ገዢው ፓርቲ የእኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል?” እስኪ አንድ ዳኛ ጫወታ ከመጀመሩ በፊት እንዲ ማለት ምን ማለት ነው? ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን እንደሚበልጥ እርግጠኛ ቢሆኑ እንኳን እንዲህ ዓይነት አስተያየት አይሰጥም፡፡ ቢያንስ በአደባባይ፡፡ ለነገሩ ከኢህአዴግ ጋር ተባብሮ የመንግስት ገንዘብ በማከፋፈል ተግባር መሰማራት ድጋፍ ካልሆነ ምን ይሆናል?
ስለዚህ ሌላኛው ህገወጥ ተግባር ምርጫ ቦርድ ከመንግሰት ካዝና ወስዶ ለኢህአዴግ የሰጠውን ገንዘብ በህጉ መሰረት ለታለመለት ዓላማ ብቻ ማዋሉን ማረጋገጥ ሲገባው ይልቁንም በዚህ ጉዳይ ኢህአዴግ ለሚፈልጋቸው ፓርቲዎች የማሰራጨት ተግባርን መስራቱ ቦርዱ ከተሰጠው ኃላፊነት እና ተግባር ውጭ ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙን የሚያሳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለፈፀመው ህገወጥ ተግባራም ቦርዱ ተባባሪ ነው፡፡ ይህ ቦርዱ አድሎዋዊ መሆኑን ያሳያል፡፡ ቦርዱ በግፊም አይነሳም ወይም በግፊ የሚነሳው ኢህአዴግ ሲገፋው ነው ያልኩት ለዚህ ነው፡፡
ሌላ አስቂኙ ነገር ደግሞ ኢህአዴግ ለሰጣቸው ገንዘብ የኦዲት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ከተጠየቁት ውስጥ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ የቻሉት ሶሰቱ ብቻ ናቸው የሚለው መረጃ ነው፡፡ የሚያስቀው የኦዲት ሪፖርት ያለማቅረባቸው ወይም የኦዲት ሪፖርት ያቀረቡት ትንሽ መሆናቸው አይደለም፡፡ የኢህአዴግ ሪፖርት ጠያቂነት እና እነርሱም ሪፖርት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸው ነው፡፡ ለነገሩ እነዚህ ፓርቲዎች መሞታቸው የተረጋገጠው ገንዘብ ከኢህአዴግ ለመቀበል የወሰኑ ዕለት ነው፡፡ የዛን ዕለት አለቃቸው ማን እንደሆነ ተጠሪነታቸውም ለማን እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች እንዴት ብለው አማራጭ ያቀርባሉ? ሌላው አስገራሚ ነገር የተጠበቀባቸውን አማራጭ ያለማቅረባቸው ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግንም ፖሊሲ በቅጡ ሊደግፉ የሚችሉ ያለመሆናቸው ነው፡፡ ከሁለቱም የሌሉ ጉዶች ናቸው፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎች ስብስብ አባል ነው እንግዲህ ሰሜን አጣፋችሁ እያለ ክስ መስርቶ ዜጎችን በየጣቢያው እያስጠራ የሚያንገላታው፡፡ ሰም ሲኖር መስሎኝ የሚጠፋው!!
ፓርቲዎች በዋነኝነት የገቢ ምንጫቸው መሆን ያለበት ከአባላት የሚያገኙት መዋጮ ነው፡፡ አባላት ከሌሏቸው ደግሞ ፓርቲ ናቸው ብሎ ከምር መውሰድ አይቻልም፡፡ በዚህ ፅሁፍ ያነሳሁትን ሃሳብ የሰጠሁት ኢህአዴግ ለነዚህ ፓርቲዎች የሚያድለው ገንዘብ ከምርጫ ቦርድ የወሰደውን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የኢህአዴግ የገንዘብ ምንጭ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በህገወጥ መንገድ ከያዛቸው የንግድ ድርጅቶች በሚስጥር ከሚያገኘው በተጨማሪ የፓርቲውን አቅም ለማሳደግ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የመንግሰትን ሀብትና ንብረት ያለአግባብ ይጠቀማል፡፡ የተወሰኑ ማሳያዎችን ለመግለፅ፤
·         በቅርቡ ኢህአዴግ ያሰለጠናቸውን ካድሬዎች ለምሳሌ የመንግሰት ተቋም በሆነው የሲቪል ሰርቪስ ዮኒቨርሲቲ ሲያስመርቅ፣ በተከታታይ በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ ውለው አድርው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሲሰለጥኑ ማየትና መስማት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ፓርቲው በተዘዋዋሪ ከመንግሰት የሚወስደው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ኢህአዴግ ከመንግሰት በተዘዋዋሪ የሚወስዳቸው እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ የፓርቲ አባላት በተደራጁበት መዋቅር አይደለም ወርሃዊ መወጮ የሚከፍሉት፤ በመንግሰት መዋቅር በኩል ነው መዋጮ የሚሰበሰበው፡፡
·         በቅርብ በማውቀው የተወካዮች ምክር ቤት ከላይ እስከ እታች ያለው መዋቅር በመንግሰት የስራ ሰዓት ሁሉ የፓርቲ ስብሰባ ይደረጋል እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ተግባራትንም ያከናውናሉ ለነዚህ ተግራራት ሁሉንም አስተዳደራዊ መዋቅር ይጠቀማል፡፡
·         የኢህአዴግ ቢሮዎች በሙሉ የመንግሰት ናቸው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ከመንግሰት ቢሮዎች ጋር ብዙ ሀብት በሚጋሩበት ሁኔታ ነው ቢሮዎቹን የሚከፈቱት፡፡
·         በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ፅ/ቤቶች በዋና ዋናዎቹ የክልል ፖሊሶች ጥበቃ ሲያደርጉ ብታዩ በፍፁም መገረም አይኖርባችሁም፤ አሁን እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ ሬዲዮ ፋና በፌዴራል ፖሊስ ነበር የሚጠበቀው፡፡ ሸገር ኤፍ ኤምን ፌዴራል ፖሊስ የሚጠብቀው አይመስለኝም፡፡
·         የመንግሰት መኪና ያለምንም እፍረት ለፓርቲ ስራ ሲያውሉ ማየት በፍፁም የሚያሸማቅቅ ሳይሆን፣ በኩራት ልብ የሚያስነፋ ነው፡፡ ለፓርቲ ስብሰባ ከመንግሰት ነዳጅ ሞልተው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡
ይህን ሁሉ ስታሰቡት ኢህአዴግ ለአነዚህ ፓርቲዎች ያሰበውን ብር ሁለት ሚሊዮን ወይም እነርሱ የፈለጉትን ብር አራት ሚሊዮን ቢሰጣቸው በእጅ አዙር ከመንግሰት የሚቀበለው ነው፡፡ አሉኝ ከሚላቸው ስባት ሚሊዮን አባሎችም ሃምሳ ሳንቲም ቢሰበስብ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ የገንዘቡ ምንጭ ሳይሆን መርዕ ያለመከበሩን ስናስብ ነው ጉዳዮን ጉዳይ ብለን እንድናነሳው የሚያስገድደን፡፡
በነገራችን ላይ እነዚህ ከኢህአዴግ ድርጎ/ደሞዝ የሚቆረጥላቸው ድርጅቶች ከመንግሰት ለፅ/ቤት የሚሆን ቢሮ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ አከራይተው እንደሚጠቀሙበት እና ለግል ጥቅም እንደሚያውሉት እርስ በራስ ሲካሰሱም ሰምተናል፡፡ ለማነኛውም ገንዘብ ሰጪው ኢህአዴግ፣ ገንዘብ ተቀባይ ፓርቲ ተብዬዎችም ሆኑ ምርጫ ቦርድ ይህን በማድረጋቸው ምንም ቅር የሚላቸው አይመስልም፤ ዶክትር በድሉ ዋቅጅራ ባለፈው ሳምንት ባቀረበው መጣጥፍ ላይ በተጠቀመው አባበል ብዘጋው ወደድኩ፡፡ እነዚህ ተዋንያን ተግባራቸው ለአስደሳች ህልም ካልሆነ በቀር ለአሰፈሪ ቅዠት አይዳርጋቸውም፡፡ ይህ ሲሆን ስታዩ አንድ የጎደላቸው ነገር ያለ አይመስላችሁም፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

Wednesday, April 2, 2014

የኑሮ ውድነት ሽክም የጫነብን ማን ይሆን? ግርማ ሠይፉ ማሩ



በሀገራችን የኑሮ ውድነት ከእለት እለት እየከፋ የድሃውን ህዝብ ጉስቁልና እያበዛ እንደሆነ ነጋሪ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በቤተ መንግሰትና አካባቢ የሚኖሩት ይህ ጉዳይ አይመለከታቸውም፡፡ ለዚህ የኑሮ ውድነት አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት የዋጋ ንረት መሆኑን ብዙዎች ይረዳሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዛሬ ለፅሁፌ ዋና ማጠንጠኛም የማደርገው የዋጋ ንረት ምንስዔው ምን እንደሆነ በተለይ የመንግሰት ሚና ከዚህ አንፃር ምን እንደሆነ ማስረዳት ነው፡፡
በእኔ አረዳድ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት የሚከሰት የዋጋ ንረት አቅርቦቱ ሲሻሻል እንደሚቀንስ በሀገራችን እንደ ሲሚንቶ ያለ ጉልዕ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ከወጣበት ጣራ ወርዶ ትክክለኛም ባይሆን ጥሩ የሚባል ደረጃ ደርሶዋል፡፡ ጊዜው መቼ እንደሆነ ባላስታውሰውም በደርግ መንግሰት ማስታወቂያ ሚኒስትር የሚታተም አንድ መፅሄት “ወደ ላይ ተወርውራ የቀረች ኳስ” ብሎ በሀገራችን ዋጋ ከናረ የማይመለስ ነገር እንደሆነ መጣጥፍ ማቅረቡ ትዝ ይለኛል፡፡ እንደምሳሌ የተጠቀመው ግን አንድ ብር የነበረ ውስኪ ሦሰት ብር ገባ የጠርሙስ ውስኪ ዋጋ ቢቀንስም የመለኪያው አልቀንስ አለ የሚል ነበር፡፡ ይህ ግን የኛ ችግር አይመስለኝም፡፡ የእኛ ችግር ስኳር ቢቀንስ፤ ዱቄት ቢቀንስ፤ ወዘተ የሻይና የኬክ ብሎም የዳቦና ማኪያቶ ዋጋ ይቀንሳል የሚል ተሰፋ የለንም፡፡ ተስፋችን ለምን ጠፋ? ማን አጠፋው? የዚህ ፅሁፍ ማጠንጠኛ ይሆናል፡፡
ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ወደ መቃብር ካልወረደ ወይም አሁን ያሉተ ሰዎች መቃብር ከመውረዳቸው በፊት የዚህችን ሀገር የመሬት ስሪት የሚለውጥ ነገር ለህዝብ ይዘው በመቅረብ ይህን ጉዳይ ከህገ መንግሰት ድንጋጌነት ማውጣት የሚችሉበትን ዕድል ካልተጠቀሙና ተሰፋ ካልሰጡን ተሰፋችንን ያጠፋው ኢህአዴግ መሆኑ ግልፅ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ገዢው ፓርቲም እንደሚያምነው አብዛኛው ሌባ የተሰባሰበው በመሬት ዙሪያ ነው፡፡ መሬት የመንግሰት ነው፡፡ በፍፁም የህዝብ አይደለም፡፡ በፓርቲ ተመርጠው በመንግሰት የተሾሙት ሌቦች እንደፈለጉ የሚያዙበት የሀብታቸው ምንጭ ነው፡፡ ይህ እንዴት ዋጋ ያንራል ማለት ተገቢ ነው፡፡ ዋጋ ማናር ብቻ አይደለም ህይወትም ያስከፍላል፡፡ አለማየሁ አቶምሳን ልብ ይሏል!!
መንግሰት ዜጎችን እያፈናቀለ በሊዝ የሚቸበችበው መሬት አሁን ባለው ሁኔታ እስከ ሰላሳ ሺ ብር በካሬ ሜትር እየተከፈለበት ነው፡፡ በአዲስ አበባችን፡፡ ይህን በሰላሣ ሺ ብር በካሬ ሜትር የሚገዙ ሰዎች የገንዘብ ምንጫቸው ምንድነው? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በህጋዊ መንገድ ያገኘውን ገንዘብ በካሬ ለባዶ መሬት (ወርቅ ውስጡ የሌለ ማለት ነው) ይህን ያህል ገንዘብ ከከፈለ፤ ይህን ገንዘብ ለማስመለስ ግልፅ የሆነው ህጋዊ መስመር መሬቱ ላይ ለሚገነባው ቤት ከፍተኛ ዋጋ መጠየቅ ነው፡፡ ይህ ቤት በሽያጭም ይሁን በኪራይ ውድ ይሆናል ስለዚህ እዚህ ቤት ውስጥ የሚሰጥ አገልግሎት ወይም የሚሸጥ ዕቃም ቢያንስ የቤት ኪራዩን መሸፈን ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ዋጋውን መጨመር የግድ ይላል፡፡ ይህ ትንተና የሚሰራው አዲስ በሚሰሩ በሊዝ ለተገዙ ቤቶች ነው የሚል የዋህ አይጠፋም፡፡ ነገር ግን ቤት አከራዮች አዲሶቹ ዋጋ ሲጨምሩ የድሮዎችም ይህንኑ ተከትለው ነው የኪራይ ዋጋ የሚጨምሩት፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ ሰርቪስ ቤት በሁለት መቶ ብር ተከራይቶ መኖር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት በምንም ዓይነት አንድ ሰርቪስ ቤት ከሺ አምሰት መቶ በታች ማግኘት አይቻልም፡፡ ከገቢያችን አንፃር ማሰተካከያ ቢሰራለት ይህ ዋጋ አሜሪካን አገር እንኳን እንዲህ ዓይነት ዋጋ የለም፡፡
በቅርቡ ከአንደ ጓደኛዬ ጋር የመኖሪያ ቤት ገንብተው የሚሸጡ ሪል ኤስቴቶች አካባቢ ጎራ ብለን ነበር፡፡ እነዘህ ቤት ገንቢዎች ዋጋቸው በፍፁም በሀገር ውስጥ የምንኖር ዜጎችን ያማከለ አይደለም፤ ቤታችንን መንግሰት አይሰራልንም የምንል ዜጎችም ብንኖርም እጃችን ተጠምዝዞ መንግሰትን ደጅ እንድንጠና የሚያደርግ ነው፡፡ ለእነዚህ ቤቶች መወደድ አንዱ ምክንያት የመንግሰት የሊዝ ፖሊስ እንደሆነ መረዳት ብዙ እውቀት የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ቤት ገንቢዎች ከቤት ገዢዎች የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሰበው ለመንግሰት ገቢ ያደርጋሉ፡፡ ከቤቱ ዋጋ አስራ አምሰት ከመቶውን የያዘው ለመንግሰት የሚከፈለው ታክስ ነው፡፡ ሌላው የታዘብኩት ነገር ደግሞ ለዋጋ ንረቱ ከሊዝና ታክስ በተጨማሪ ሌላ አቁስል ምክንያት መኖሩ ነው፡፡ ከጋደኛዬ ጋር ቤቱን መግዛት እንዳለብን ከምታግባባን የሽያጭ ሰራተኛ ማዶ ሌላ ሽያጭ ሰራተኛ ሁለት ሴቶችን ከፊት ለፊቷ አሰቀምጣ ቤቱን እንዲገዙ በተመሳሳይ ዝርዝር መረጃ ሰጥታ የማግባባት ሰራዋን ሰታጠናቅቅ፤ በዋጋው ውድነት ብስጭት በማለት የተለያየ ሃሳብ መሰንዘር ይጅምራሉ አንዷ ግን እንደ መፍትሔ ሃሣብ አቅረበች “አንገዛም ማለት አለብን!!” አለች፡፡ ልክ ነበረች ገዢ ሲጠፋ ዋጋ መቀነስ የታወቀ የንግድ ሰርዓት ውስጥ የሚወሰድ እርምጃ ነው፡፡ ትክክለኛ የገበያ ህግ በሚሰራበት ሀገር ማለቴ ነው፡፡ ጓደኛዋ ግን በዚህ መፍትሔ አልተስማማችም እንዲህ አለች “ምን መሰለሽ እዚህ ሀገር ብዙ በህገወጥ መንገድ ገንዘብ የሚያገኙ ሰዎች አሉ፤ እነርሱ ደግሞ በህገወጥ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ህጋዊ ማድረጊያ መንገዳቸው አንዱ ቤት መግዛ ነው” ብላ ተጨማሪውን የዋጋ ንረት ምንጭ ነካችው፡፡
ቤት ገንቢዎች ለምን ቤቱን አስወደዱት ብዬ እንደማልከሳቸው ማወቅ አለባቸው ግን በፍፁም ልክ ያልሆነ ነገር በእግረ መንገድ ላስቀምጥ “ይህን ያህል ካሬ ሜትር ቤት በዚይን ያህል ዋጋ” ብለው ማስታወቂያ ሰርተው ለመግዛት የሚሄደው ሰው ግን የሚያገኘው ሰባ ከመቶ አይሆንም፡፡ ምን ነው ? ሲባል ለመኪና ማቆሚያ፤ ለመተላለፊያ፤ ለሊፍት፤ ለጋራ አገልግሎት፤ ወዘተ የሚሉ ቦታዎች ተደምረውበታል ይባላል፡፡ ይህ ምን ያህል ቤት ፈላጊዎችን እንደሚያሳስት ግን ከሻጮቹም የተሰወረ አይደለም፡፡ ማስታወቂያው ሀቅን መሰረት ያድርግ!! ለቤት ገንቢዎች በእግረ መንገድ ያለኝ ምክር ነው፡፡
በዚህች ሀገር የገበያ ህግ እንዳይሰራ እነዚህ ህገወጦች በቀጥታ በጉቦ፣ አገልግሎት በመንፈግ የሚያደርሱብን ጉዳት አልበቃ ብሎዋቸው ሰርቀው ያገኙትን ገንዘብ ህጋዊ ለማድረግ ምስኪን ዜጎች ማረፊያ እንዳይኖረን የሚያደርጉት አስተዋፅኦ እንዲሁም ለዚህም ዋነኛው ተባባሪ በውድ መሬት የሚቸበችበው መንግሰት መሆኑ ታሰቦኝ፤ እንደ አዲሰ እውቅት መብገን ጀመርኩና እናንተም ትበግኑ ዘንድ ነው ይህን ላካፍላችሁ የወደድኩት፡፡ እንግዲ ይህ ገፊ ምክንያት ሆኖን የመሬት ሰሪቱ በዕለት ከዕለት ኑሮዋችን መጥቶ እያሰቃየን ነው ብልን ለለውጥ ካልተነሳን፣ ሌላ ምን በቂ ምክንያት ነው የምንጠብቅው? የሚለው ጥያቄ በእንጥልጥል የሚቆይ ነው፡፡
በህጋዊ መንገድ መሬት የሚፈልጉ ሰዎችም ከህገወጦቹ ጋር ነው ግብ ግብ የሚያያዙት፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የቁጥ ቁጥ መሬት አቅርቦት ፖሊስ ነው፡፡ መንግስት የመሬት አቅርቦቱን ሆን ብሎ እያሳጠረ፤ ሌቦቹ እንዲመቻቸው ዕድል እንዲፈጠር እያደረገ ነው፡፡ መሬት በመግቢያዬ እንዳልኳችሁ የመንግሰት ነው እንጂ በፍፁም የህዝብ አይደለም፤ ህዝብማ በመንግሰት እጅ በተያዘ መሬት ሰበብ የሻይና ማኪያቶ ዋጋ ላይ ጭምር ጫና የሚፈጥር ሆኖበታል፡፡ የዚህ መሬትን በመንግስት እጅ የማቆየት ፖሊስ ዋናው ገፊ ምክንያት ፖለቲካም መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ መሬቱን ይዞ የሊዝ ሂሣብ ሳይከፍል፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይኖርበት፣ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ አሰገብቶ ኮንዶሚኒየም በርካሽ እሰራላሁ እያለ ለዚህም በስልጣን መቆየት አለብን እያለ ይገኛል፡፡ ገዢው ፓርቲ፡፡ ዋናው ፖለቲካዊ ግቡ በስልጣ ገዢውን ፓርቲ ማቆየት ነው፡፡ ይህ ገዢ ፓርቲ በስልጣን ላይ ከቆየ ገዢ መደቦች እየሰረቁ ገንዘብ ያገኛሉ፤ በስርቆት ያገኙትን ገንዘብ ደግሞ በውድም ቢሆን መሬት በመግዛት ዘላቂ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸው በኢኮኖሚ ደንዳና የሆነ ሰርዓት ይገነባል ብለው ያምናሉ፡፡ ይህች ፍልሰፍና ግን የብዙሃኑን ተጠቃሚነት በጎዳ መልኩ ስለሆነ እየተሰራ ያላው በምንም መልኩ ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡ በአሸዋ ላይ የተሰራ ቤት ዓይነት  ነው፡፡ አውሎ ንፋስ አይጠብቅም ትንሽ ንፋስ ጠራርጎ ያፈርሰዋል፡፡ ልብ መግዛት ያለብን ይመስለኛል፡፡
ፅሁፌን ከዘጋው በኋላ ዋጋው በአቅርቦት መሻሻል ይቀንሳል ብለን ተሰፋ ያደረግነው ሰኳርም ቢሆን የዋጋ ጭማሪ ያደረገ መሆኑን በሬዲዮ ሰማው፡፡ ይህ ምንም አያስገርምም፡፡ የሚያስገርመው መግለጫ የሰጡት ኃላፊ ማብራሪያ ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪ የሚባል ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ለትራንስፖርት ተብሎ ዘጠና አምሰት ሳንቲም በኪሎ ተጨመረ እንጂ፤ የዚህ ምክንያት ደግሞ ቀደም ብሎ ሰኳሩ ከውጭ ስለሚመጣ ከጅቡቲ በቀጥታ ይገባ ስለነበር ነው፡፡ በማለት ቀደም ሲል ስኳር የትራንሰፖርት ወጪ የለበትም የሚል መንፈስ ያለው መግለጫ ሰጡ፡፡ ይህ መግለጫ ህዝቡን እንዴት እንደናቁት ከማሳየት ውጪ አንድም የእውቀትና እውነት መሰረት የለውም፡፡ የዋጋ ጭማሪ አይደለም የትራንሰፖርት ነው!! ምን የሚሉት ፌዝ ነው፡፡ ዋጋ እንዴት ነው የሚተመነው? ፋብሪካው ይህ የመጀመሪያ ምርቱ ነው? እሰከዛሬ ትራንስፖርት ማን ነበር የሚሸፍነው? መግለጫውንም ሁሉንም ትተን አሁንም ቢሆን በተጨመረው ዋጋ ስኳሩ የታለ ነው? ያለው ጭማሪውን ዋጋም ጨምሮ ይገዛል፡፡ የሌለው ድሮ ከሚገዛው መጠን ቀንሶ ይገዛል፡፡ በተለይ የመንግሰት ሰራተኛው በቅርቡ የትራንሰፖርት ዋጋ ተጨመረበት፣ አሁን ደግሞ የስኳር ማጓጓዣ ተጨመረበት፣ ቀጥሎ ስኳርን ተከትሎ ዳቦ ይጨምራል ወዘተ.. ደሞዝ ግን እንዳለች ነው፡፡ መፍትሔው ልጆችን ስኳር ለጤና ጥሩ አይደለም ብሎ ማስተው ነው፡፡ ዳቦ እንዴት ተብሎ ይከለከል ይሆን?
ታስታውሱ እንደሆነ የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደረ ዋጋ ይጨምር የነበረው ሙገር ሲምንቶ ፋብሪካ አሁን ዋጋ መቀነሱን ማስታወቂያ ከፍሎ እየነገረን ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሰት ያልሆኑ ተወዳዳሪዎች ስለመጡበት እና እየመጡበት ስለሆነ ነው፡፡ ስኳር ይህን እድል እንዳያገኝ ማዕቀብ ያደረገብን መንግሰት ነው፡፡ ሁሉም ፋብሪካ እኔ እስራለሁ ብሎ፡፡ ቢሰራውም ዋጋ አይቀንስም፡፡ ለምን? የሚታለብ ላም ነው ይለናል፡፡ ስለዚህ ይህን የኑሮ ውድነት የጫነብን እየጫነብንም ያለው፣ በመንግሰት ስም የተቀመጠው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዘራፊ ቡድን ነው፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

Sunday, March 23, 2014

በግፊያ የሚነሱ አሉ…… በግፊያ የማይነሱትስ?



ግርማ ሠይፉ ማሩ
ለዚህ ፅሁፍ የሚሆን ርዕስ ያቀበለኝ ዶክተር ምህረት ደበበ ነው፡፡ በቅርቡ ብዙዎች “የተቆለፈበት ቁልፍ” በሚለው መፅሃፉ ነው የምናውቀው፡፡ ከዚያ በኋላም በሸገር ሬዲዮ ከመዓዛ ብሩ ጋር በሚያደርጋቸው ውይይቶች ሬዲዮ እንዳንዘጋ ከሚያደርጉን ጥቂት ሰዎች አንዱ ሆኖዋል፡፡ የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የደፋሮች መፈንጫ ሆነው ባሉበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለልብ የሚሆን መልዕክት ከሚያስተላልፉልን አንዱ እንግዳ እንደ ነበር መመስከር ግድ ይለኛል፡፡ በቅርቡ ታዲያ ብዙዎቻችን በግፊ ካልተነሳን በስተቀር ተልዕኮ ኖሮን የምናሳካው ነገር እጅግ አነስተኛ ወይም የሌለ መሆኑን ሲነግረን ነበር፡፡ ይህንን መልዕክት ተንተርሼ ነው ለዛሬ በተለያየ መልኩ በግፊ ሰለመነሳት ለማንሳት እና ሲከፋም ተገፍተው የማይነሱም መብዛታቸው ይህችን ሀገር ምን ያህል ከባድ ፈተና እንደተጋረጠባት ለማሳየት የምሞክረው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ ቦርድ
ምርጫ ቦርድ አሉኝ ብሎ ከሚላቸው 75 ፓርቲዎች ግማሾቹን ደግሞ ደግሞ የሚቆጥራቸው ቢሆኑም ራዕይ ኖሯቸው ሊደርሱበት ወደሚፈልጉት ግብ እንዴት እንደሚደርሱ ሃስበው ይህን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚሰሩ ፓርቲዎች ቢቆጠሩ የአንድ እጅ ጣት አይሞሉም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የሚንቀሳቀሱት ወይ ገዢው ፓርቲ አበል አለ ብሎ ሲጠራቸው፣ አሊያም አንድ የፖለቲካ ትርፍ የሚያስገኝ ኩነት ተገኘ ሲባሉ ነው፡፡ አብዛኞቹ ግን መኖራቸው የሚታወቀው ምርጫ የሚባል ነገር ሲመጣ ነው፡፡ በዚያን ሰሞን አለን ለማለትም ገፊ የሚሆነው ምክንያት ምርጫ ቦርድ የሚያድላት ገንዘብ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ከዘህ ውጭ ሌላ ብዙ ገፊ ምክንያት ብናስብም ለእኔ በተግባር የገጠመኝ ግን ከፓርቲ መዝገብ ላለመሰረዝ ምርጫ መወዳደር የግድ ስለሚል ነው፡፡ መሰረዝ የማይፈልጉበትን ምክንያት ግን እዚህ ማንሳት ተገቢ አይደለም በሚል ባልፈው መረጥኩ፡፡ ላነሳው ያልፈለኩት ጉዳይ በእውነቱ ዋነኛው ገፊ ምክንያት እንደሆነ ግን ይታወቃል፡፡ ለአንባቢያን አይመጥንም በሚል ነው የማልፈው፡፡
በግፊ የሚነሱ ፓርቲዎች ለዚህች ሀገር የመድበለ ፓርቲ ሰርዓት ግንባታ የሚመጥኑ እንዳልሆኑ እነርሱም ያውቃሉ ህዝቡም ያውቃል፡፡ ገዢው ፓርቲም በደንብ አውቆ ከግፊ ውጪ እንዳይነሱ ቆመው እንዲከርሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ዋናው ግን ቆመው ለመክረም የወሰኑት እራሳቸው መሆናቸውን ሳንዘነጋ ነው፡፡ በኢህአዴግ ማሳበብ ማቆም ይኖርባቸዋል፤ ይኖርብናል፡፡ ለውጥ ለማምጣት ከሆነ ግን ከግፊ ወጥተን በራስ ተነሳሽነት በልምድ ከተሰመረው መስመር ውጭ መንቀሳቀስ ግድ ይላል፡፡
የምርጫ ቦርድ መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ ለልዩ ልዩ ጉዳይ ጎራ ብዬ አውቃለሁ፡፡ የሚፈልጉትን ሠራተኛ በመንግሰት የስራ ሰዓት ማግኘት ዘበት ነው፡፡ የቦርዱ አባላት በቋሚ ሰራተኛነት መገኘት ባይኖርባቸው በቀጠሮ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ምን ያደርጋል ቢገኙስ መፍትሔ የሚባል ነገር ሊሰጡ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ዝም ብሎ ምርጫ ቦርድን ለመክሰስ እንዳይሆን ማሳያ ላቅርብ፡፡ ነጋዴ ችግር ሲገጥመው ንግድ ሚኒስትር እንደሚሄደው እኛም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ችግር ገጥሞናል መፍትሔ ስጡን ብለን የምንሄደው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ፖሊስ በየመንገዱ የፖለቲካ ስራ ልንስራ እየከለከለን ነው፤ አዳራሽ የሚያከራዩ ሰዎች ፈቃድ ይሉናል ፈቃድ ሰጪ አካል ደግሞ የለም ምን እናድርግ፤ ማተሚያ ቤት የንግድ ፈቃድ አምጡ ይላል እኛ ነጋዴ አይደለንም ይህን ጉዳይ በአዋጅ መሰረት መፍትሔ ስጡን፤ ወዘተ. ለምርጫ ቦርድ በግንባር ቀርበን ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ናቸው፤ አንድም መፍትሔ የለም፡፡ መልሳቸው አነጋግረን መልስ እንሰጣችኋለን ይሉናል፡፡ መልስ ግን የለም፡፡ ይልቁንም በአውራ ፓርቲ መኖር ተገቢነት ላይ በሚቀርብ የገዢው ፓርቲ መድረክ ላይ በተሳታፊነት ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ በግፊም አይነሳም ወይም ገፊውን ይመርጣል ማለት ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በአሰተዳደራዊ መስመር አልፈታ ሲለን ነው እንግዲህ ሌላ ተቋም ለመፈተሽ ወደ ፍርድ ቤት የተሄደው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን በግፊ ይነሱ አይንሱ እዚህ ማንሳት አያስፈልግም፡፡ ይደር ብለን እንለፍ፡፡

መንግስት /አሰፈፃሚ አካል
መንግሰት የሚባለው አካል ሰራውን የሚያሰራው የሲቪል ሰርቪስ ወይም የመንግሰት ሰራተኞች በመባል በሚታወቁት በአብዛኛው የባለሞያዎች ስብስብ ነው፡፡ በአብዛኛው እነዚህ ሰራተኞች ጠዋት 2፡30 ወደ ሰራ ገብተው ማታ 11፡30 ከስራ የሚወጡ መሆናቸውን ከግንዛቤ አስገብተን (በቀን ሰምንት ሰዓት ማለት ነው) ይህን ሁሉ ሰዓት በስራ ገበታቸው ተገኝተው የተጣለባቸውን ሃላፊነት ሲከውኑ ነው የሚውሉት ብለን ስናስብ ግን መልሱ አዎንታዊ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ለዚህም ነው መንግስት የሚባል አካል የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ መርዓ ግብር ብሎ የሚዳክረው፡፡ ግን ለምንድነው እነዚህ ሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞች በግፊ ካልሆነ በስተቀር የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለመስጠት ዳተኛ የሆኑት ማለት ይኖርብናል፡፡ ለማነኛውም ያለግፊ የሚሰሩ ከተሰመረላቸው መስመር ወጥተው የሚያገለግሉ የሉም ማለት አይደለም፡፡ የአብዛኛው መገለጫ ግን በግፊ መነሳት መሆኑ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው መንግሰት የሚባለውን አካል የሚያዋቅረው እና የሚመራው ደግሞ ገዢው ፓርቲ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ደግሞ እንቅስቃሴው ጎልቶ የሚታየው ልክ እንደተቃዋሚዎቹ ሁሉ በምርጫ ሰሞን መሆኑ ነው፡፡ ለገዢው ፓርቲ ገፊው ምርጫ የሚሆነው ግን እንደ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ከምርጫ ቦርድ የሚያገኘው ገንዘብ አይደለም፡፡ ከምርጫ ቦርድ የሚያገኘውን ገንዘብ ከህግ አግባብ ውጭ በምርጫ ቦርድ በኩል ለሌሎች ፓርቲዎች እንደሚያድለው እናውቃለን፡፡ ለገዢው ፓርቲ ምርጫ ገፊ የሚሆነው ለመግዛት የሚያስችለውን ውጤት አግኝቻለሁ ብሎ አለማቀፍ ማህበረሰቡን ለማሳመን እንዲቻለው በማሰብ ነው፡፡ ለዚህም ህዝቡን በልማት ስም የልማት አርበኛ ነኝ ብሎ ድምፅ ለማግኘት ያስችለኛል ያለውን ከመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ እስከ የልማት ሰራዎች ሳይጠናቀቁም ቢሆን ምርቃ ለማድረግ ደፋ ቀና የሚለው፡፡ እንግዲህ ሰሞኑን በምርጫ ግፊ እነዚህን ክስተቶች እስኪያነገሸግሸን እንሰማለን፡፡ በነገራችን ላይ የ1997 ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ምርጫ እንደዋዛ የማይመለከተው ገዢ ፓርቲ በግፊ የሚሰራቸውንም ቢሆን ህዝቡ አሁን ድረስ እድሜ ለቅንጅት እንደሚል መረጃ አለን፡፡ በተለይ በጉራጌ ዞን ከቅንጅትም አልፎ የአንዳንድ ቅንጅት ግንባር ቀደም ሰዎችን ስም በማንሳት ነው በአካባቢያቸው ሰለሚጀመሩ ልማቶች ምስጋና የሚያቀርቡት፡፡ አዲስ አበባም ቢሆንም ወጣቱን ከአደገኛ ቦዘኔ ከሚል ፍረጃ በማንኛውም ሁኔታ ወጣቱን መያዝ ወደሚል ገዢውን ፓርቲ ያሸጋገረ ገፊ ጉዳይ ምርጫ ነው፡፡ ይህ ወጣቱን የማቀፍ አቅጣጫ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ግን በግፊ የሚነሳና ቁም ነገር የሚሰራ ነው ተብሎ በብዙዎች ዘንድ አይወሰድም፡፡ በነገራችን ላይ በግፊ የሚነሱ ሰዎችም ቢሆኑ የተለየ ነገር ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ገዢው ፓርቲም የሰዎች ስብስብ ነው፡፡ ዶክተር ምህረት ደበበ እንደነገረን ከሆነ “በግፊ የሚነሱ ሰዎች ሰራ ሲቀጠሩ እንዲያከናውኑ ከተሰመረላቸው መስመር ዘለግ አድርገው ሰራ ለመስራት ብዙም ተነሳሸነት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ልዩ ፈጠራ በማድረግ ሰራን ለማሻሻል አቅም የላቻውም፡፡ ሰራቸውንም ለመስራት ሁልጊዜ ጎትጓች ይፈልጋሉ በጉትጎታ ደግሞ ፈጠራ የለም፡፡” ነው የሚለው፡፡ ገዢው ፓርቲ ደግሞ የሰዎች ስብስብ ነው ብለናል፡፡ እነዚህ አባላቱ ደግሞ አብዛኞቹ ሰለግል ነፃነት ግድ የሌላቸው ብሎም የሚያደርጉት ነገር ሁሉ በግምገማ እና ግምገማን ተከትሎ በሚከተላቸው ቁንጥጫ ፍርሃት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ከነዚህ በግፊ ከሚንቀሳቀሱ አባላት ደግሞ አዲስ ነገር መጠበቅ የዋህነት ነው፤ ፈጠራ ከነፃነት የሚመነጭ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በግፊ የሚነሱ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች እሰከተሰመረላቸው መስመር ድረስ ሊሰሩ እንደሚችሉ እሙን ነው፤ ይህም የሚሆነው ገፊው አካል ወይም ሁኔታ በሚያደርሰው የግፊት መጠን እና ገፊው በተገፊው ላይ ባለው ኃይል የሚወሰን መሆኑን መረዳት ይኖርበናል፡፡ የሚገርመው ግን ሀገራችን የሚያስፈልጋት ያለ ግፊ የሚሰሩ ሰዎችና ተቋማት ቢሆንም አሁን ግን በግፊም በደንብ የማይሰሩ ሲከፋ ደግሞ በግፊም የማይነሱ መብዛታቸው ነው፡፡
ስንቶቻችን የሰዓት ፊርማ ባይኖር በሰራ ሰዓት በስራ ቦታችን እንገኛለን? ብሔራዊ የሆኑ የበዓል ቀናት ቅዳሜና እሁድ ሲውሉ የማይበሳጭ ስንቱ ነው? የስራና የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜ ባይኖር ሪፖርት የሚባል ነገር ይኖራል ወይ? ተማሪዎች ፈተና ባይኖር ለዕውቀት ብሎ ጥናት ይኖር ነበር ወይ? ወዘተ ብለን ስንጠይቅ በሁሉም መስክ ግፊት የግድ የሚለን ጉዳይ ሆኖዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ሆኖ ግን የማይንቀሳቀስ ብዙ ሰው እንዳለ ሳይዘነጋ፡፡
በሀገራችን ጭቆናው በዝቶብኛል የሚለው ዜጋ እጅግ ብዙ ነው፤ ይህ የጭቆና መብዛት ገፊ ሆኖ እምቢ ለነፃነቴ ብሎ ግን የሚነሰው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ነፃነትን ለማግኘት ከጭቆና መብዛት የተሻለ ገፊ ሁኔታ ከየት ሊመጣ ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ጭቆና እምቢ የሚባልበት መንገድ አንዱ የምርጫ ካርድ መውሰድ ሲሆን፤ የምርጫ ካርድ ወስዶ የሚመርጠው አማራጭ ካጣ ደግሞ ካርዱን ቤቱ ይዞ በመቀመጥ ጨቋኞችን እምቢ ማለት የግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ አብዛኛው ግን አማራጭ ከሌለ ካርድ መውሰድ ምን መልዕክት እንዳለው አይረዳም፡፡ ሌሎችም ጭቆና እምቢ የሚባልባቸው መንገዶች እንዳሉ ባለመዘንጋት ነው፡፡ እምቢኝ ብሎ ቤት ከመቀመጥ ጅምሮ ጎዳና ወጥቶ እምቢ ብሎ እስከመጮህ፡፡ እምቢኝ ለማለት ግፊው አልበቃንም ወይም ቢገፉንም አንነሳም ብለናል ማለት ነው፡፡
በግፊ አልነሳ ያሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ አካለት ወዘተ ለመዘርዘር በሃሳቤ ቢመጣም ወደ ዝርዝሩ ገብቼ መሄድ አልፈቀድኩም እሰኪ ይህን ፅሁፍ ለማንበብ እድል የገጠማቸሁ ሁሉ እራሳችሁን ገምግሙት፡፡ በራሳችሁ ተነሳሽነት የምትንቀሳቀሱ ፣ በግፊ የምትነሱ መሆኑን ወይም በግፊም ቢሆን ለመነሳት ባትሪያችሁን የጨረሳችሁ መሆኑን ፈትሹ መልሱን ስታገኙ ቢያንስ በዚህ ዓመት ካላችሁበት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት ውሳኔ አድርጉ ግፊን እምቢ በሉ፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

Sunday, March 16, 2014

ዜና ውህደት



ዛሬ በመኢህአድ ፅ/ቤት የመኢህአድ እና የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት የጋራ ስብሰባ አድርገው አንድ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህውም ለቀጣይ ሐሙስ መጋቢት 11/2004 ዓ/ም የቅድመ ውህደት ሰምምነት እንዲደረግ እስከ አሁን ውህደቱን ለማዘግየት የተወሰደው ጊዜ ከበቂ በላይ በመሆኑ አጅግ አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ ይህን ጉዳይ አጠናቆ የጋራ ጉባዔውን የሚያመቻች ኮሚቴም በእለቱ ይፋ እንዲደረግ ከስምምነት ተደርሶዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ውህድ በሚሆኑበት ወቅት ፈታኝ ይሆናሉ የተባሉ የፕሮገራም እና የደንብ ልዮነቶች የሚባሉት ውሕዱን ፓርቲ የተሻለ ደንብና ፕሮግራም እንዲኖረው ከማድረግ የዘለለ ውህደቱን ለማዘግየት ምክንያት እንዳይደሉ መግባባት ላይ ተደርሶዋል፡፡  የውህዱን ፓርቲ ስያሜ በተመለከተም ተሳታፊዎቹ በአዲስ መሆን እንዳለበት እና ይህም ተጠንቶ ለጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ የሚወሰን እንደሆነ ግንዛቤ ተይዞዋል፡፡ ትልቁ ነጥብ የነበረው በሁለቱም ፓርቲዎች በኩል አመራሮች በምንም ሁኔታ ውህደቱን ለማዘግየት ቢሞክሩ አባላት ተዋሕደው አመራሮች ተንጠልጥለው እንደሚቀሩ በተደጋጋሚ የገለፁ ሲሆን ይህም በከፍተኛ ጭብጨባ ድጋፍ አግኝቶዋል፡፡ እውነት እውነት እላችኋለው ይህ ጉዳይ ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ እውን ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የፈረሰው ቅንጅት ሶስት አራተኛው እንደተመለሰ ይሰማኛል፡፡ ቸር ወሬ ያሰማን፡፡ የመጋቢት 11 ሰው ይበለን፡፡