ግርማ ሠይፉ ማሩ
ለዚህ ፅሁፍ የሚሆን ርዕስ ያቀበለኝ
ዶክተር ምህረት ደበበ ነው፡፡ በቅርቡ ብዙዎች “የተቆለፈበት ቁልፍ” በሚለው መፅሃፉ ነው የምናውቀው፡፡ ከዚያ በኋላም በሸገር ሬዲዮ
ከመዓዛ ብሩ ጋር በሚያደርጋቸው ውይይቶች ሬዲዮ እንዳንዘጋ ከሚያደርጉን ጥቂት ሰዎች አንዱ ሆኖዋል፡፡ የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች
የደፋሮች መፈንጫ ሆነው ባሉበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለልብ የሚሆን መልዕክት ከሚያስተላልፉልን አንዱ እንግዳ እንደ ነበር መመስከር
ግድ ይለኛል፡፡ በቅርቡ ታዲያ ብዙዎቻችን በግፊ ካልተነሳን በስተቀር ተልዕኮ ኖሮን የምናሳካው ነገር እጅግ አነስተኛ ወይም የሌለ
መሆኑን ሲነግረን ነበር፡፡ ይህንን መልዕክት ተንተርሼ ነው ለዛሬ በተለያየ መልኩ በግፊ ሰለመነሳት ለማንሳት እና ሲከፋም ተገፍተው
የማይነሱም መብዛታቸው ይህችን ሀገር ምን ያህል ከባድ ፈተና እንደተጋረጠባት ለማሳየት የምሞክረው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ ቦርድ
ምርጫ ቦርድ አሉኝ ብሎ ከሚላቸው
75 ፓርቲዎች ግማሾቹን ደግሞ ደግሞ የሚቆጥራቸው ቢሆኑም ራዕይ ኖሯቸው ሊደርሱበት ወደሚፈልጉት ግብ እንዴት እንደሚደርሱ ሃስበው
ይህን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚሰሩ ፓርቲዎች ቢቆጠሩ የአንድ እጅ ጣት አይሞሉም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የሚንቀሳቀሱት ወይ ገዢው
ፓርቲ አበል አለ ብሎ ሲጠራቸው፣ አሊያም አንድ የፖለቲካ ትርፍ የሚያስገኝ ኩነት ተገኘ ሲባሉ ነው፡፡ አብዛኞቹ ግን መኖራቸው የሚታወቀው
ምርጫ የሚባል ነገር ሲመጣ ነው፡፡ በዚያን ሰሞን አለን ለማለትም ገፊ የሚሆነው ምክንያት ምርጫ ቦርድ የሚያድላት ገንዘብ ሳትሆን
አትቀርም፡፡ ከዘህ ውጭ ሌላ ብዙ ገፊ ምክንያት ብናስብም ለእኔ በተግባር የገጠመኝ ግን ከፓርቲ መዝገብ ላለመሰረዝ ምርጫ መወዳደር
የግድ ስለሚል ነው፡፡ መሰረዝ የማይፈልጉበትን ምክንያት ግን እዚህ ማንሳት ተገቢ አይደለም በሚል ባልፈው መረጥኩ፡፡ ላነሳው ያልፈለኩት
ጉዳይ በእውነቱ ዋነኛው ገፊ ምክንያት እንደሆነ ግን ይታወቃል፡፡ ለአንባቢያን አይመጥንም በሚል ነው የማልፈው፡፡
በግፊ የሚነሱ ፓርቲዎች ለዚህች
ሀገር የመድበለ ፓርቲ ሰርዓት ግንባታ የሚመጥኑ እንዳልሆኑ እነርሱም ያውቃሉ ህዝቡም ያውቃል፡፡ ገዢው ፓርቲም በደንብ አውቆ ከግፊ
ውጪ እንዳይነሱ ቆመው እንዲከርሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ዋናው ግን ቆመው ለመክረም የወሰኑት እራሳቸው መሆናቸውን ሳንዘነጋ ነው፡፡ በኢህአዴግ
ማሳበብ ማቆም ይኖርባቸዋል፤ ይኖርብናል፡፡ ለውጥ ለማምጣት ከሆነ ግን ከግፊ ወጥተን በራስ ተነሳሽነት በልምድ ከተሰመረው መስመር
ውጭ መንቀሳቀስ ግድ ይላል፡፡
የምርጫ ቦርድ መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ
ለልዩ ልዩ ጉዳይ ጎራ ብዬ አውቃለሁ፡፡ የሚፈልጉትን ሠራተኛ በመንግሰት የስራ ሰዓት ማግኘት ዘበት ነው፡፡ የቦርዱ አባላት በቋሚ
ሰራተኛነት መገኘት ባይኖርባቸው በቀጠሮ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ምን ያደርጋል ቢገኙስ መፍትሔ የሚባል ነገር ሊሰጡ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ዝም ብሎ ምርጫ ቦርድን ለመክሰስ
እንዳይሆን ማሳያ ላቅርብ፡፡ ነጋዴ ችግር ሲገጥመው ንግድ ሚኒስትር እንደሚሄደው እኛም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ችግር ገጥሞናል መፍትሔ
ስጡን ብለን የምንሄደው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ፖሊስ በየመንገዱ የፖለቲካ ስራ ልንስራ እየከለከለን ነው፤ አዳራሽ የሚያከራዩ ሰዎች
ፈቃድ ይሉናል ፈቃድ ሰጪ አካል ደግሞ የለም ምን እናድርግ፤ ማተሚያ ቤት የንግድ ፈቃድ አምጡ ይላል እኛ ነጋዴ አይደለንም ይህን
ጉዳይ በአዋጅ መሰረት መፍትሔ ስጡን፤ ወዘተ. ለምርጫ ቦርድ በግንባር ቀርበን ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ናቸው፤ አንድም መፍትሔ የለም፡፡
መልሳቸው አነጋግረን መልስ እንሰጣችኋለን ይሉናል፡፡ መልስ ግን የለም፡፡ ይልቁንም በአውራ ፓርቲ መኖር ተገቢነት ላይ በሚቀርብ
የገዢው ፓርቲ መድረክ ላይ በተሳታፊነት ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ በግፊም አይነሳም ወይም ገፊውን ይመርጣል ማለት ነው፡፡
ምርጫ ቦርድ በአሰተዳደራዊ መስመር አልፈታ ሲለን ነው እንግዲህ ሌላ ተቋም ለመፈተሽ ወደ ፍርድ ቤት የተሄደው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን
በግፊ ይነሱ አይንሱ እዚህ ማንሳት አያስፈልግም፡፡ ይደር ብለን እንለፍ፡፡
መንግስት /አሰፈፃሚ አካል
መንግሰት የሚባለው አካል ሰራውን
የሚያሰራው የሲቪል ሰርቪስ ወይም የመንግሰት ሰራተኞች በመባል በሚታወቁት በአብዛኛው የባለሞያዎች ስብስብ ነው፡፡ በአብዛኛው እነዚህ
ሰራተኞች ጠዋት 2፡30 ወደ ሰራ ገብተው ማታ 11፡30 ከስራ የሚወጡ መሆናቸውን ከግንዛቤ አስገብተን (በቀን ሰምንት ሰዓት ማለት
ነው) ይህን ሁሉ ሰዓት በስራ ገበታቸው ተገኝተው የተጣለባቸውን ሃላፊነት ሲከውኑ ነው የሚውሉት ብለን ስናስብ ግን መልሱ አዎንታዊ
እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ለዚህም ነው መንግስት የሚባል አካል የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ መርዓ ግብር ብሎ የሚዳክረው፡፡ ግን
ለምንድነው እነዚህ ሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞች በግፊ ካልሆነ በስተቀር የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለመስጠት ዳተኛ
የሆኑት ማለት ይኖርብናል፡፡ ለማነኛውም ያለግፊ የሚሰሩ ከተሰመረላቸው መስመር ወጥተው የሚያገለግሉ የሉም ማለት አይደለም፡፡ የአብዛኛው
መገለጫ ግን በግፊ መነሳት መሆኑ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው መንግሰት የሚባለውን አካል የሚያዋቅረው እና የሚመራው ደግሞ ገዢው
ፓርቲ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ደግሞ እንቅስቃሴው ጎልቶ የሚታየው ልክ እንደተቃዋሚዎቹ ሁሉ በምርጫ ሰሞን መሆኑ ነው፡፡ ለገዢው ፓርቲ
ገፊው ምርጫ የሚሆነው ግን እንደ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ከምርጫ ቦርድ የሚያገኘው ገንዘብ አይደለም፡፡ ከምርጫ ቦርድ የሚያገኘውን
ገንዘብ ከህግ አግባብ ውጭ በምርጫ ቦርድ በኩል ለሌሎች ፓርቲዎች እንደሚያድለው እናውቃለን፡፡ ለገዢው ፓርቲ ምርጫ ገፊ የሚሆነው
ለመግዛት የሚያስችለውን ውጤት አግኝቻለሁ ብሎ አለማቀፍ ማህበረሰቡን ለማሳመን እንዲቻለው በማሰብ ነው፡፡ ለዚህም ህዝቡን በልማት
ስም የልማት አርበኛ ነኝ ብሎ ድምፅ ለማግኘት ያስችለኛል ያለውን ከመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ እስከ የልማት ሰራዎች ሳይጠናቀቁም
ቢሆን ምርቃ ለማድረግ ደፋ ቀና የሚለው፡፡ እንግዲህ ሰሞኑን በምርጫ ግፊ እነዚህን ክስተቶች እስኪያነገሸግሸን እንሰማለን፡፡ በነገራችን
ላይ የ1997 ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ምርጫ እንደዋዛ የማይመለከተው ገዢ ፓርቲ በግፊ የሚሰራቸውንም ቢሆን ህዝቡ አሁን ድረስ እድሜ
ለቅንጅት እንደሚል መረጃ አለን፡፡ በተለይ በጉራጌ ዞን ከቅንጅትም አልፎ የአንዳንድ ቅንጅት ግንባር ቀደም ሰዎችን ስም በማንሳት
ነው በአካባቢያቸው ሰለሚጀመሩ ልማቶች ምስጋና የሚያቀርቡት፡፡ አዲስ አበባም ቢሆንም ወጣቱን ከአደገኛ ቦዘኔ ከሚል ፍረጃ በማንኛውም
ሁኔታ ወጣቱን መያዝ ወደሚል ገዢውን ፓርቲ ያሸጋገረ ገፊ ጉዳይ ምርጫ ነው፡፡ ይህ ወጣቱን የማቀፍ አቅጣጫ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ግን በግፊ የሚነሳና
ቁም ነገር የሚሰራ ነው ተብሎ በብዙዎች ዘንድ አይወሰድም፡፡ በነገራችን ላይ በግፊ የሚነሱ ሰዎችም ቢሆኑ የተለየ ነገር ያደርጋሉ
ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ገዢው ፓርቲም የሰዎች ስብስብ ነው፡፡ ዶክተር ምህረት ደበበ እንደነገረን ከሆነ “በግፊ የሚነሱ ሰዎች ሰራ
ሲቀጠሩ እንዲያከናውኑ ከተሰመረላቸው መስመር ዘለግ አድርገው ሰራ ለመስራት ብዙም ተነሳሸነት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ልዩ ፈጠራ በማድረግ
ሰራን ለማሻሻል አቅም የላቻውም፡፡ ሰራቸውንም ለመስራት ሁልጊዜ
ጎትጓች ይፈልጋሉ በጉትጎታ ደግሞ ፈጠራ የለም፡፡” ነው የሚለው፡፡ ገዢው ፓርቲ ደግሞ የሰዎች ስብስብ ነው ብለናል፡፡ እነዚህ አባላቱ
ደግሞ አብዛኞቹ ሰለግል ነፃነት ግድ የሌላቸው ብሎም የሚያደርጉት ነገር ሁሉ በግምገማ እና ግምገማን ተከትሎ በሚከተላቸው ቁንጥጫ
ፍርሃት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ከነዚህ በግፊ ከሚንቀሳቀሱ አባላት ደግሞ አዲስ ነገር መጠበቅ የዋህነት ነው፤ ፈጠራ ከነፃነት የሚመነጭ
መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በግፊ የሚነሱ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች
እሰከተሰመረላቸው መስመር ድረስ ሊሰሩ እንደሚችሉ እሙን ነው፤ ይህም የሚሆነው ገፊው አካል ወይም ሁኔታ በሚያደርሰው የግፊት መጠን
እና ገፊው በተገፊው ላይ ባለው ኃይል
የሚወሰን መሆኑን መረዳት ይኖርበናል፡፡ የሚገርመው ግን ሀገራችን የሚያስፈልጋት ያለ ግፊ የሚሰሩ ሰዎችና ተቋማት ቢሆንም አሁን
ግን በግፊም በደንብ የማይሰሩ ሲከፋ ደግሞ በግፊም የማይነሱ መብዛታቸው ነው፡፡
ስንቶቻችን የሰዓት ፊርማ ባይኖር በሰራ ሰዓት በስራ ቦታችን እንገኛለን?
ብሔራዊ የሆኑ የበዓል ቀናት ቅዳሜና እሁድ ሲውሉ የማይበሳጭ ስንቱ ነው? የስራና የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜ ባይኖር ሪፖርት
የሚባል ነገር ይኖራል ወይ? ተማሪዎች ፈተና ባይኖር ለዕውቀት ብሎ ጥናት ይኖር ነበር ወይ? ወዘተ ብለን ስንጠይቅ በሁሉም መስክ
ግፊት የግድ የሚለን ጉዳይ ሆኖዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ሆኖ ግን የማይንቀሳቀስ ብዙ ሰው እንዳለ ሳይዘነጋ፡፡
በሀገራችን ጭቆናው በዝቶብኛል የሚለው ዜጋ እጅግ ብዙ ነው፤ ይህ የጭቆና መብዛት ገፊ ሆኖ እምቢ ለነፃነቴ ብሎ ግን
የሚነሰው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ነፃነትን ለማግኘት ከጭቆና መብዛት የተሻለ ገፊ ሁኔታ ከየት ሊመጣ ይችላል፡፡ በእኔ እምነት
ጭቆና እምቢ የሚባልበት መንገድ አንዱ የምርጫ ካርድ መውሰድ ሲሆን፤ የምርጫ ካርድ ወስዶ የሚመርጠው አማራጭ ካጣ ደግሞ ካርዱን
ቤቱ ይዞ በመቀመጥ ጨቋኞችን እምቢ ማለት የግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ አብዛኛው ግን አማራጭ ከሌለ ካርድ መውሰድ ምን መልዕክት እንዳለው
አይረዳም፡፡ ሌሎችም ጭቆና እምቢ የሚባልባቸው መንገዶች እንዳሉ ባለመዘንጋት ነው፡፡ እምቢኝ ብሎ ቤት ከመቀመጥ ጅምሮ ጎዳና ወጥቶ
እምቢ ብሎ እስከመጮህ፡፡ እምቢኝ ለማለት ግፊው አልበቃንም ወይም ቢገፉንም አንነሳም ብለናል ማለት ነው፡፡
በግፊ አልነሳ ያሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ አካለት
ወዘተ ለመዘርዘር በሃሳቤ ቢመጣም ወደ ዝርዝሩ ገብቼ መሄድ አልፈቀድኩም እሰኪ ይህን ፅሁፍ ለማንበብ እድል የገጠማቸሁ ሁሉ እራሳችሁን
ገምግሙት፡፡ በራሳችሁ ተነሳሽነት የምትንቀሳቀሱ ፣ በግፊ የምትነሱ መሆኑን ወይም በግፊም ቢሆን ለመነሳት ባትሪያችሁን የጨረሳችሁ
መሆኑን ፈትሹ መልሱን ስታገኙ ቢያንስ በዚህ ዓመት ካላችሁበት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት ውሳኔ
አድርጉ ግፊን እምቢ በሉ፡፡
ቸር ይግጠመን!!!
No comments:
Post a Comment