Sunday, May 25, 2014

ግንቦት 20 ያለመለስ ስንት ይቆይ ይሆን?



ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
ሰሞኑን ልባችን እሰኪጠፋ የግንቦት 20 ፍሬዎች የተባሉት “ልማትና ዲሞክራሲ” በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እንዲሁም እየተከፈላቸው በማህበራዊ ድህረ ገፅ የስድብ ናዳ የሚያወርዱትን ስዶች ጨምሮ እንደ ፍራፍሬ እየበላን እንደ ወተት እየተጋት ነው፡፡ ሚዛናዊ ሆኜ  ግንቦት 20 ያመጣልኝን ፍሬ ሳስብ የምር ግራ ይገባኛል፡፡ የእኔ ግርታ የሚመነጨው አሁን ያለንበት ደረጃ ለመድረስ በእርግጥ 23 ዓመት ያስፈልገን ነበር ወይ? የሚል ነው፡፡ በእኔ እምነት ግንቦት 20 የስርዓት ለውጥ የመጣበት ቀን እንደሆነ ለመቀበል አልቸገርም፡፡ ደርግን የተካው ዳግማዊ ደርግ በመባል የሚታወቀው ኢህአዴግ ግን ከምን ከምን አንፃር ከደርግ እንደሚሻል ሊገባኝ አልቻለም፡፡ እኔ በፍፁም የማላደርገው ኢህአዴግን ከደርግ ጋር ማወዳደር ነው፡፡ በሂሣብ ትምህርት ፍየልና በግ እንደማይደመረው ማለት ነው፡፡ ኢህአዴጎች ደስ የሚላቸው ሁሌም ውድድሩ ከደርግ ጋር እንዲሆን ነው፡፡ ሲያስፈልግም ከምኒሊክ ጋር መወዳደር የሚያሻቸው በተለይ ባቡርና ስልክ ሲነሳ ነው፡፡ ሊያፍሩበት በሚገባ ነገር ውድድር ይከጅላሉ፡፡ እኔ ኢህአዴግን እንዲመዘን የምፈልገው ስመዝነውም የሚቀልብኝ ከዓለም አቀፍ መለኪያ እንዲሁም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሚገባን ደረጃ አንፃር ነው፡፡
አፍቃሪ ኢህዴጎች “ኢህአዴግ ባይኖር ኖሮ ይህች ሀገር ትፈራርስ ነበር” ለማለት አፋቸውን እንኳን ያዝ አያደርጋቸውም፡፡ ይህንን መፈራረስ የገታው ደግሞ “የኢህአዴግ የብሔር ብሔረሰብ ፖሊሲ ነው” ይሉናል፡፡ በእኔ እምነት የመፈራረስ ሟርትም ሆነ የሟርቱ ማፍረሻ ፖሊሲ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ኢህአድጋዊያች ለዚህም ማሳያው የሚሉት በሽግግር ኮንፈረንስ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት ውስጥ ከአስር በላይ የሚሆኑት መገንጠል አለብን የሚሉ ነበሩ በማለት ነው፡፡ ልክ ነው በዚህ ማህበር ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ሃሣብ የሚያራምዱ ቢበዙ እንጂ የዚህ አቀንቃኞች ሊያንሱ አይችሉም፡፡ ህወሃትን ጨምሮ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ የመሳሰለሉት ከስማቸው ጭምር የመገንጠል ደቀ መዝሙሮች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በእነርሱ ጋባዥነት የሚመጣ ድርጅት እንዴት አድርጎ ከዚህ የተለያ ሃሳብ ሊያራምድ ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ለዚያውም እነዚህ ጋባዦች በለስ ቀንቷቸው መሣሪያ ታጥቀው አራት ኪሎ ቁጭ ብለው ባሉበት ወቅት፡፡ ይህ ግን በፍፁም የኢትዮጵያ ህዝብ ለመገንጠል ዝግጁ ነበር የሚያስብል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከኢህአዴግ በፊትም በቋንቋቸው ይናገራሉ፣ ይዘፍናሉ፣ ያለቅሳሉ፡፡ በኢህአዴግ ጊዜ የተጨመረልን “ቁቤ የሚበል” ፊደል እና ወጣቱ በተለይ በኦሮሚያ አካባቢ ኢትዮጵያዊ ራዕይ እንዳይኖረን መደረጉ ነው፡፡ የዚህ ፍሬ ምስራቹን በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ደርሶ ተመልክተነዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ችግር በኢትዮጵያ ጥላ ስር ይፈታል ጥቅሙም ይረጋገጣል ብዬ ነው የማምነው የሚለው ኦህዴድ፤ አባል የሚመለምለውና የሚያደራጀው በኦነግ ፕሮግራም እንደሆነ ያጋለጠ ክስተት ነበር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር አሉት የሚባለው “ኦህዴድ ሲፋቅ ኦነግ ነው” የሚባው በዚህ ክስተት ኦህዴድ ሳይፋቅም ኦነግ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ይህ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሀገራት ለውህደት በሚሰሩባት ዓለም የመገንጠል ጥያቄ በወጣቶች ላይ የዘራው ኦህዴድ/ኢህአዴግ ያሰገኘልን የግንቦት 20 ፍሬ ነው፡፡ ኢቲቪም ሆነ ተሳዳቢዎቹ የማህበራዊ ድህረ ገፅ ካድሬዎች ይህን የግንቦት 20 ፍሬ አያነሱትም፡፡
ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በአንድ ሳምንት ተበጥብጦ የሚጠጣ አይደለም የሚል አዲስ መፈክር መጥቶዋል፡፡ በእኔ እምነት ሃያ ሶስት ዓመት ሙሉ ተዓማኒነት ያለው እና ተቀባይነት ያገኘ ምርጫ ማካሄድ ያለመቻልን የሚያክል ብቃት ማነስ በዓለም ያለ አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ በብቃት ምርጫ ማጭበርበር እንደ ብቃት ከተወሰደ ደግሞ ገዢውን ፓርቲ የሚያሽልም ነው፡፡ ለልምድ ልውውጥም ብዙ አንባገነን መሆን የሚፈልጉ እንደ ጆርጅ ኦሩዌል መፅሃፍ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት ገንብቻለው የሚል መንግሰት ዜጎች በምርጫ ለመወዳደር፣ አማራጭ ይዞ በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ፣ ምርጫን ያለስጋት መታዘብ፣ የመሳሰሉትን ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለመጠቀም በፍርሃት እየራዱ ብዙዎች “አታነካኩኝ ልኑርበት” የሚሉበት ሀገር ሲሆን፤ የዲሞክራሲ ስርዓት ለማስፈን ነው ትግሉ እየተባሉ በዱር በገደል ህይወታቸውን የሰዉ ሰማዕታት ድንገት ቀና ቢሉ ምን ምን ዓይነት መልስ እንደሚሰጧቸው መገመት ያስቸግራል፡፡ የሚያሳዝነው እራሳቸውን ለመስዋዕትነት አዘጋጅተው የነበሩ በአጋጣሚ በህይወት የተረፉት ይህ ነው ዲሞክራሲው ሲባሉ እሺ ብለው መቀበላቸው ነው፡፡ ከመሰዋዕትነት መትረፋቸውን እንደ አንድ ትርፍ ቆጥረው በአንድ ወይም በሌላ የሚያገኙትን ጥቅም እያገኙ እነርሱም ቀሪ ህይወታቸውን ማጣጣም ተያይዘውታል፡፡ በህይወት ለሚገኙ ኢህአዴግ ታጋዮች ፍሬው የእነርሱ በህየወት መትረፍ ሆኖወል፡፡ የሰመሃታቱን ቃል ኪዳን መብላት ግንቦት 20 ፍሬ ነው፡፡
የዛሬን ግንቦት 20 ለሃያ ሶስተኛ ጊዜ ተከብሮዋል፡፡ ዋና የቡድን መሪያቸውን አጥተው እውር ድንብር መሄድ ከጀመሩ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ያከበሩት ኢህአዴጎች ዛሬም ሃሳብን በነፃነት መግለፅን ማረጋገጥ አልቻሉም፡፡ ከዚህ በኋላ ስንት እንደሚቆዩ አይታወቅም፡፡ ለዚህ ነው ስንት ይቆዩ ይሆን ብዬ መጠየቅ ያማረኝ፡፡ ኢህአዴግ በእርግጥ የተሳካለት ይህን መብት መረጋገጡ ላይ ነው፡፡ በህገመንግሰት ውስጥ ወርቃማ ነፃነቶችን ለማስቀመጥ ያልፈራው ኢህአዴግ በጠመንጃ ለማነጋገር ከተዘጋጁት ይልቅ በብዕራቸው ጉድለቱን ሊያሳዩት የሚጥሩትን ጋዜጠኞች ዓይናችሁን ላፈር ብሎ እያሳደደ ነው፡፡ ኮምፒዩተር ላይ ቁጭ ብለው ሃሣባቸውን በነፃነት እዚህ ግባ ለማይባል ማህበራዊ ገፅ ተጠቃሚ ስላካፈሉ ብሩዕ ተሰፋ ያላቸውን ወጣቶችን እስር ቤት ያጉራል፡፡ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሽት ታዬ፣ እስክንድር ነጋ አንድም ጥይት የላቸውም፡፡ የሚያስገርመው ጠመንጃ ከያዙት ይልቅ ግን ገዢውን ፓርቲና መንግሰትን ያርበደብዱታል፡፡ “ዞን ዘጠኞች” በምን መለኪያ ነው ብጥብጥ የማስነሳት አቅም ያላቸው፡፡ የእነሱ አቅም የነበረው ሃሣብን በነፃነት ገልፆ በሰላም መተኛት ነው፡፡ ለነገሩ እነርሱም ወደ ሌላ ዞን ተዛወሩ እንጂ ሀገሪቱ እራሷ እስር ቤተ መሆኗን ለማመላከት ነው “ዞን ዘጠኝ” ብለው እራሳቸውን የሰየሙት፡፡ ኢህአዴግ እነዚህ ወጣቶች በሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ብለው ስለተንቀሳቀሱ እስር ቤት አጎራቸው፡፡ በተቃራኒው ግን እነዚህ ወጣቶች በየካፍቴሪያው ተጎልተው ቢውሉ፣ በየጫት ቤቱ ሺሻ ሲያጨሱ ቢውሉ እና ዲቪ ሲሞሉ ወይም ከሀገር መውጫ መንገድ ሲቀይሱ ቢውሉ፣ ስለዚህች ሀገር አያገባንም ብለው ቢጦምሩ ጫፋቸውን አይነካም፡፡ ዝንባቸውን እሽ አይልም ነበር፡፡ የግንቦት 20 ፍሬያችን ከሃያ ሶስት ዓመት በኋላ ያገኘነው በግልፅ በህገ መንግሰት የተደነገገን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የማይከበርበት ስርዓት መገንባት ነው፡፡ የስርዓት ለውጥ ብቻ፡፡ ከደርግ ወደ ዳግማዊ ደርግ በመጀመሪያው ዘመናቸው ቡድናዊ አንባገነንነት፡፡ በኋላም ወደ ግለሰብ አንባገነንነት ማለትም ከመንግስቱ ሀይለማሪያም ወደ መለስ ዜናዊ መሸጋገር ነው፡፡ይህን ኢቲቪ ሊያሳየን አቅም የለውም፡፡ ተከፋይ የድህረ ገፅ ተሳዳቢዎችም አይሞክሯትም ለምን ቢባል እንጀራ ነው፡፡
ግንቦት 20 እንደ መሰከረም 2 ወደ መቃብር እንዳይወርድ በቀጣይ የሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ባህል ይሆን ዘንድ ግን ኢህአዴግ አሁንም እድል አለው፡፡ ሃያ ሶስት ዓመት ዘግይቶም ቢሆን ሰመዓታቱን ሊያስከብር የሚችለውን የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥን የዲሞክራሲ ስርዓት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው፤ ይህንንም ለማሳካት እኛ ሰላሣ እና አርባ ዓመት መግዛት አለብን የሚለው ተረት ተረት ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን በዚህች ሀገር ሌላ አብዮት የሚጠራ ገፊ ምክንያት ነው፡፡ ይህ አብዮት ሲመጣ ደግሞ መሰከረም ሁለት እንደተፈነገለው ግንቦት 20 ይፈነገልናል ሌላ ከዓመቱ አንድ ቀን ሌላ የድል የለውጥ ቀን ይመጣል፡፡ ለዲሞክራሲ ለፍትህ ሲባል ሰማዕታት ለሆኑት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሲባል ግንቦት 20 የድል ቀን ሊሆን የሚችልበት እድል ያለው በኢህአዴግ እጅ ነው፡፡ በማንኛውም ምክንያት ኢህአዴግ በክብር ሳይሆን በውረደት ከወደቀ ግንቦት 20 የዓመቱ አንድ ቀን ከመሆን አልፎ የድል ቀን ሆኖ ሊከበርበት የሚችልበት አንድም ምክንያት አይኖርም፡፡ አሁን ባለው ሁኔት ያለፉት 23 ዓመታት ለኢህአዴጋዊያን የድል ቀን ሲሆን ለእኛ እንደማነኛውም የዓመቱ አንድ ቀን ሆኖ ተገደን ከሰራ የምንቀርበት ቀንም ጭምር ነው፡፡ እንደ አሁኑ ደግሞ አርብ ቀን ሲውል ለረዥም የሳምንት መጨረሻ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል እንጂ በመጀመሪያው ግንቦት 20 ጠዋት የሰማነውን ለህዝብ ጥቅም ሲባል የተሰራ አንድም ድል አይሸተኝም፡፡
ዐፄ ሀይለስላሴ ሰማኒያኛ የልደት ባህላቸውን፤ ደርግ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዮት ያቀረበለትን የስልጣን ይልቀቁ ጥያቄ ገፍተው እንደተዉት ሁሉ ኢህዴግም እሰከ ዛሬ ካሳለፋቸው እድሎች በተጨማሪ መቼ እንደሆነ በቅርብ ባይታወቅም እሩቅ ባልሆነ ጊዜ እድሉን ገፍቶ ይጥለዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከዋናው የቡድኑ መሪ መለስ ዜናዊ እልፈት በኋላ ለረዥም ጊዜ በሴራም በእውቀትም የሚመራው ሰው ያለው አይመስለኝም፡፡ ይህ ግን ከግምት በላይ ነው፡፡ ወንበሩን የወሰዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን ፍንጭ አላሳዩንም ይልቁንም ሌጋሲ ማስቀጠል በሚል የወይን ፋብሪካ ምረቃን ጨምሮ ተቀባይነት የሌላቸው በምረቃ ስራ ተጠምደው መዋላቸው ለሌላ ሰትራቴጂክ ሰራ ጊዜ እንደሌላቸው የሚያሳብቅ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ደምረን ስናይ ግንቦት 20 እንደ መስከረም 2 ሳይዋረድ ከመለስ እልፈት በኋላ ስንት ዓመት ይቀጥላል? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግንቦት 20 በግራዋ ዛፍ ላይ የበቀለ መራራ አፕል ነው፡፡
ቸር ይግጠም!!!!
ግርማ ሠይፉ ማሩ

Sunday, May 18, 2014

ዘላለም ስንት ነው?



አውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሰርዓት ሲኖር ተጠቃሚ የሚሆኑት ለዚህ ሲሉ ክቡር ህየይወታቸውን ለመሰዋዕትነት ያዘጋጁትና ይህንን መራራ ፅዋ በክብር የከፈሉት ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁንም የነፃነት፣ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ ሰርዓት መሰፈን ደስ የሚያሰኘው የተጠቃሚ ምርጫ ለመሰዋዕትነት በመዘጋጀት እና በመክፈል አድልዖ ያለማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ ዓይነት ሰርዓት  የሚጠቀሙትም እነዚህን መሰረታዊ የሰው ልጅ መብቶችን ለማስከበር በሚደረግ ትግል ወቅት እራሳቸውን በፍርሃት ውስጥ ያኖሩትን ብሎም እራሳቸው ጨቋኞቹን ጭምር መሆኑ ነው፡፡ ለመሰዋዕትነት እራሳቸውን ያዘጋጁ ዜጎች ለምን እንዲህ ሆነ ብለው የሚቆጩበት ጊዜ የላቸውም፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት በሌለበት በመንግሰት የሚመራ ቁሳዊ ዕድገት አስተማማኝ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ የተገለፀ ሀቅ ነው፡፡ በሀገራችን ዕድገት አለ የለም ክርክር ጉንጭ አልፋ ከሆነም ቆይቶዋል፡፡ በሀገራችን ቁሳዊ ዕድገት እንዳለ ምንም ጥርጥር የለም፡፡ የዚህ ዕድገት ተቋዳሾችም ጥቂቶች እንደሆኑ ማመን የግድ ይላል፡፡ እነዚህ ደልቃቆች ውኃ ስለማይጠጡ የውሃ ችግር ችግራቸው አይደለም፤ መብራት ቢጠፋ ጄኔሬተር ያስነሳሉ፣ ሞባይልም ቢሆን ባለ ሳተላይት ይኖራቸዋል (እነዚህ ብዙ አይደሉም)፣ ሌላም ሌላም ልንዘረዝር እንችላለን፡፡ እነዚህ ኪሳቸውን በገንዘብ ሞልተው፤ ነፃነታቸውን በፍርሃት በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ያደረጉ ሰዎች ሌሎች በሚከፍሉት መስዋዕትነት ነፃ የሚወጡ ናቸው፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ገፊ የሆነው ምክንያት የሆነው ግን እነዚህ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያሉ ሰዎች ፍርሃትን አበደባባይ ሲሰብኩት መስማቴ ነው፡፡
ይህ ቀን እስኪያልፍ ድረስ ተዉኝ ልኑርበት እየተባለ በድፍረት መፎከር ተጀምሮዋል፡፡ ድሮ በድብቅ ይፈራል ሲባል ነው የምናውቀው አሁን በድፍረት ስለ ፍርሃት የሚወራበት ዘመን ደረስናል፡፡ ይህን የሰማሁት ባለቤቴ ክሊኒክ ወረፋ ሆና ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ድንገት እግር ጥሎኝ አልፎ አልፎ ጎራ ከምልበት “መዝናኛ” ቤት እንደተቀመጥኩ ነው፡፡ መቁሰያ ቢባል ይሻላል፡፡ አንድ ወደ ጎልምሳና የተጠጋ የሰላሣ ሰምንት ዓመት ሰው ስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የማውቀው

ብሎ እንዲህ ብሎ ፎከረ፤

“ፈሪና ተራራ ዘላለም ይኖራል፤
ብርሌና ደፋር ቶሎ ይሰበራል፡፡”
ስለዚህ ተዉኝ ልኑርበት ብሎ የሱን ፍርሃት እንደ ተራራ ሲያገዝፈው፡፡ ለነፃነታቸው ቀናዔ የሆኑትን እና በተፈጥሮ ያገኙትን ነፃነት አናሰነካም የሚሉትን ደግሞ ከተራ ድፍረትና ብርሌ ጋር አነፃፅሮ ለፍርሃቱ ማወራረጃ ውሲኪውን ተጎነጨበትም፡፡ ይኼኔ ነው የቆሰልኩት እና ይህን ለመክተብ ማሰታወሻ የያዝኩት፡፡
እንግዲህ የሳላሣ ስምንት ዓመት ጎልማሳው በከተሜነት ዕድሜው ስሌት በአስራ ሁለት ዓመቱ ሰለፈሪነት ገብቶት እሰከ ዛሬ ለሃያ ስድስት ዓመት አብዛኛውን ደግሞ በኢህአደግ የአገዛዝ ዘመን አንገቱን ደፍቶ እየኖረ ነው፡፡ ለዘላለምም ከነፍርሃቱ ይኖራል፡፡ ፍርሃትም ተራራም ዘላለም ሊኖሩ ይችላሉ ይህ ወንድማችን ግን ከአሁን በኋላ ስንት ሊኖር ብሎ ነው የፍርሃት ፉከራ የሚያወርደው? የሚል ጥያቄ ጫረብኝ፡፡ ዘላለም ለእንዲህ ዓይነት ፈረዎች ስንት ነው? ሰዎች በምድር ላይ በፍርሃት ተውጠው በተጎለቱበት አይደለም ዘላለማዊ የሚሆኑት፡፡ ብዙ ቁም ነገር የሰሩ ጀግኖች የሚዘከሩት በሰሩት ቁም ነገር ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ጆኔፍ ኬኔዲ፤ ወዘተ ከሀገራቸው አልፈው እኛ እንደመደበኛ እውቀት የምናውቃቸው ሰዎች በለጋ ዕድሜያቸው ይህችን አለም ተሰናብተዋል ነገር ግን ለዘላለም ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ በላይ ዘለቀ ስቅላት ሲፈረድበት አርባ ዓመት ያልሞላው ጎልማሳ ነበር እንቢኝ ውርደት ብሎ የሞትን ፅዋ ተጎነጨ ነገር ግን በላይ ዘለቀ “የበላይ ናት እሷስ” እየተባለ በዘፈን ይወደሳል፣ ቅኔ ይቀኙለታል፡፡ ዘላለም ስንት ነው ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡ በፍርሃት አንገት ደፍቶ በቁም ሞቶ እድሜ መቁጠር? ወይስ በድፍረት አንገት ቀና አድርጎ መኖር?
ተማም አባቡልጎ የሚባል የህግ አማካሪኛ ጠበቃ መቼም የማያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ በአንድ አጋጣሚ በፍርድ ቤት ቅጥር ጊቢ ሆነን ስንጫወት እንዲህ አለኝ “እሰር ቤት ስለ መግባት እና ሰለመገደል ማሰብ የእኛ ስራ መሆን የለበትም፡፡ የእኛ ተግባር መሆን ያለበት በድፍረት፣ በስርዓት፣ በነፃነት አንገት ቀና አድርጎ መኖር ነው አለኝ፡፡” እውነቱን ነው አሳሪና ገዳዮች እንዴት፣ መቼ እና በምን ሁኔታ እንደሚያደርጉት ያስቡበት እንጂ እኛ ምን በወጣን ሰለ እሰርና ሞት እናስባለን፡፡ በተቃራኒው ግን ፈሪ ሁልጊዜ በትክክል መፍራቱን እያረጋገጠ መኖር አለበት፤ ያለበለዚያ ሰው መሆኑ በሚፈጥርበት የነፃነት ስሜት ተነሳስቶ ደፋር ሆኖ ገዢዎችን እንዳያሰቀይም መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ ፍርሃቱን በትክክል መፍራቱን ማረጋገጥ የፈሪ ሃላፊነት ነው፡፡ ያለበለዚያም እንዴት ዘላለም ይኖራል፡፡ ድንገት ድፍረት ይመጣና እንደ ብርሌ መሰበር ይመጣል፡፡ አንባቢዎች ፍረዱኝ ፈሪ ነው ወይስ ከፍርሃት ውጭ ያለ በሰጋት የሚኖር?
የሀገራችን ሁኔታ ጉራማይሌ መሆኑን ማሳያው ይህን የፍርሃት ቀረርቶ የሰማሁት ሚያዚያ 26/2006 ካደረግነው ሰልፍ በተመለስን ሶስት ቀን ሳይሞላው መሆኑ ነው፡፡ ፍርሃትን እንቢ ብለው “እመነኝ አልፈራም” ሲሉ የነበሩ ወጣቶች ድምፅ በተለይ የወጣት ሀብታሙ አያሌው ድምፅ ጆሮዬ ላይ እያቃጨለ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ “መብትን መጠየቅ አሸባሪነት አይደለም”፣ “ማዕከላዊ ይዘጋ፣ ማዕከላዊ ጓንታናሞ”፣ ወዘተ. የሚሉ መፈክሮች በሰማሁበት ጆሮ መሆኑ ነው፡፡ “አንገድለም ግደሉን” እየተባለ በአደባባይ ሲፈክር ከነበረ ብዙ ሺ ህዝብ በተለየ በአንድ “መዝናኛ” በተባለች ጠባብ ክፍል ውስጥ የፍርሃት ፉከራ ምን የሚሉት እነደሆነ ለእኔ ግልፅ  አይደለም፡፡ ፍረዱኝ የቱ ነው ለመኖር ጣዕም የሚሰጠው? ተዉኝ ልኑርበት ብሎ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሆኖ ቀንና ምሽት ሳይለዩ በአልኮል ውስጥ፣ ግራና ቀኝ ያለን ሁሉ እየፈሩና እየተጠራጠሩ የእነ ማቱሳላህ ዕድሜ ቢገኝ እንኳን ዘላለም መኖርን ያስመኛል?
የዚህ ፅሁፍ ዋና ዓለማው ፈሪን መውቀስ አይደለም ይልቁንም ፍርሃትን ስለመፍራት እንድንወያይ እና ከዚህም የሚገኘውን የተሻለ የዘላለም ትርጉም የሚገኝበትን መንገድ መሻት ነው፡፡ በድፍረት ውስጥ ስለ አለ የነፃነት ጣዕምን ሰዎች እንዲያጣጥሙት ማሳየት ያለብኝ ስለመሰለኝ ነው፡፡ ድፍረት ሲባል በፍፁም ከጀብደኝነት ጋር ተገናኝቶ አላስፈላጊ ትርጉም እንዲሰጠው አልፈልግም፡፡ ውሃ ዋና የማይችል ሰው፣ ደፋር ነኝ ብሎ ቢዋኝ እንደሚሰምጥ ማወቅ አለበት፡፡ ሁሉም እርግጠኛ መሆን ያለበት ፈንጂ ላይ የመረማመድ ድፍረት እየሰበኩ አይደለም፡፡ ተፈጥሮዋዊ መብታችንን ላለማስናካት የሚያስፈልገውን ወኔ በአሰፈላጊ ጊዜ መጠቀም ይኖርብናል የሚል ሃሳቤን ለማጋራት ነው፡፡ እንደዚህም ሆኖ ግን መፍራትም፣ ከፍርሃት ጋር ተዋዶ መኖርም ምርጫ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ምርጫ እናከብራለን የምንል ከሆነ ደግሞ የተሳሳተ ምርጫም ቢሆን ምርጫውን ማክበር የግድ ይላል፡፡ ሰው ከሆነ ግን ምርጫው ልክ እንዳልሆነ ሲረዳ ምርጫውን ያስተካክላል፡፡ ሰው የመሆን ጥቅሙ ይህ ነው፡፡ ነፃነት ለእኔ ከእግዜር የተሰጠኝ መክሊት እንጂ በማንም የተቸርኩት አይደለም፡፡ ይህን መክሊቴን ቀብሬ መኖር አብዝቼ መጠቀም የእኔ ድርሻ ነው፡፡ በተሰጠን መክሊት ልክ እንጠየቃለን፡፡

ከላይ ሰለ ሚያዚያ 26 ሰልፍ ካነሳሁ አይቀር ሁለት ትዝብቶኝ ማሰፈር ይገባኛል ብዬ አመንኩ፡፡ በሰልፉ ላይ ሆኜ የታዘብኩት አንድ የወታደሮችን መኖሪያ የሚጠብቅ ዘብ ያሳየውን የተለየ ባህሪ ነው፡፡ ጠብ መንጃውን የታጠቀው ዘብ መቼ እንደሚተኩስ እና እንደሚገድል አይታወቅም ወይ? ለህውቀት እንዲረዳኝ መሳሪያ የያዘ ወታደር በፈለገ ሰዓት መሳሪያውን የመጠቀም መብት አለው ወይ? ይህን ጥያቄ እንዳነሳ የገፋፋኝ በወታደሮች መኖሪያ ቅጥር ጊቢ መግቢያ ላይ በስሜት የተነሱ ሰዎችን ከመግቢያው በር እንዲርቁ እየተከላከልን እያለ አንድ መሣሪያ የታጠቀ ዘብ ጠጋ ብሎን “አልሄድም ነው የሚሉት!!” ብሎ መሳሪያውን ከቃታው ላይ ሲያደርግ ተመልክቼ እንዴት አንደዘገነነኝ ማሰረዳት ስለምቸገር ነው፡፡

ለምሣሌ መዝገብ ቤት ያለ ሰራተኛ ማህተም ሳይፈቀድ እንደማያደርገው፣ ገንዘብ ቤት ያለ ገንዘብ ያዥ ሳይታዘዝ እንደማይከፍለው ሁሉ ጠመንጃ የያዘ ወታደር ሆነ ፖሊስ ተራ ግርግር ተፈጠረ ብሎ መተኮስ፣ ሲተኩስም አንገት ላይ ተኩሶ መገድል ይችላል ወይ? ለወታደርና ፖሊስ አሰገዳጅ የሚባሉ ሁኔታዎች እንዳሉ እረዳለሁ፡፡ የሰለፉ ዕለት የተመለከትኩት የዘብ ሰሜት እጅግ ያስደነገጠኝ ነገር ሰለሆነ ነው፡፡ እግረ መንገዱን በሲግናል በኩል ስናልፍ አንድ አንድ ሰልፈኞች ያሳዩት ያልተገባ ድርጊት በግሌ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብኛል፡፡ በህንፃ ላይ ሆነው የድጋፍ እንዲሁም የሰድብም ምልክቶች ይተላለፉ ነበር እነዚህን ሁሉ በትዕግሰት እና በፍቅር መመለስ ነበረባቸው፡፡ “መከላከያ የኛ!!” የሚል መፈክር መኖር ነበረበት በእርግጥም መከላከያ የእኛ ነው፡፡ ጥቂቶች መጠቀሚያ ስላደረጉት የእኛ መሆኑን መካድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያማዝናል፡፡ ኢህአዴግ ለስልጣን እየቀረበ ሲመጣ “የጭቁን መኮንኖች እና ጭቁን ወታደሮች” ማህበር መመስረቱ የማይረሳ ነው፡፡ በመጨረሻው ግን ሁሉንም መበተን ነበር የወሰነው፡፡ ኢህዴግ የደርግን መንግሰት ካስወገደ በኋላ ከሰራቸው ትልቅ ሰህተቶች አንዱ የኢትዮጵያን መከላከያ ሀይል የደርግ ሰራዊት ብሎ መበተኑ ነው፡፡ ይህ የማይታረም ስህተት ከአሁን በኋላ መደገም ያለበት አይደለም፡፡ ከሌላው ሰህተት መማር መቻል ይኖርብናል፡፡
በመጨረሻም “ማዕከላዊ ይፍረስ፣ ጓንታናሞ ነው!!” ሲባል የነበረውን የሚያዚያ 26 መፈክር ድጋሚ ብቻዬን ማለት አማራኝ፡፡ ምክንያቱም “ዞን 9” በመባል የሚታወቁትን ወጣት ጦማሪዎች በፍርድ ቤት ቀርበው ግርፋትና ድብደባ ደርሶብናል ብለው አቤት ማለታቸውን ሰምቼ ነው፡፡ የፀረ ሽብር ህግ ለመርማሪዎች ከገደብ በላይ በሚስጥር የመመርመር እና መረጃ የመሰብሰብ ስልጣን የሰጣቸው (የወሰዱት) መረጃን በበቂ አሰባሰበው ወንጀለኛ ለመያዝ ነው ቢባልም ይህን ከመጠቀምና መረጃ ለፍርድ ቤት ከማቅረብ ይልቅ የመረጡት መንገድ በአሰራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የሚሰራበትን የግፍ ምርመራ ዘዴ ነው፡፡ተጠርጣሪን አጣርተው መያዝ ሲገባቸው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቅ ተጠርጣሪንም ቤተሰብንም ማንገላታት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው መንግሰት በተደራጀ መልክ መረጃ አሰባሰበው ክስ መመስረት እንደማይችል፤ ይልቁንም በጉልበት በመጠቀም ማሰፈራራትን መምረጡን ነው፡፡ ተፈጥሮዋዊ ነፃነታቸውን በህውቀታቸውና በልምዳቸው መሰረት ህዝብ እንዲያውቅ ሲተጉ ከነበረ ወጣቶችና በባንኮኒ ውስጥ ተዉኝ ልኑርበት ከሚለው ማን ክብር አለው? ምርጫው የግል ነው፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!

Monday, May 12, 2014

የኢህዴግ ብሔርተኝነትና የተቀናጀ ማሰተር ፕላን ……..?



ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
የጣና ሀይቅ የጎንደር ነው ወይስ የጎጃም? የሚል የይገባኛል ጥያቄ እንዳለ ያወቅሁት በደርግ የመጨረሻ ዘመን ምስራቅ ጎጃም እና ምዕራብ ጉጃም የሚል የአሰተዳደር አካባቢ የተመሰረተ ሰሞን ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ጢስ አባይ ፏፏቴን ለማየት እየሄድን እያለ አብሮን ያለው ጎንደሬ ጓደኛችን አካባቢው የጎንደር መሆኑን ለማረጋገጥ ማየት ያለብን እረኛውን መሆኑን ነገረን፡፡ እረኛን አይቶ መሬቱን የጎንደር ወይስ የጎጃም ተብሎ እንዴት ይለያል ብለን በአግራሞት ተመለከትነው፡፡ እረኛው የሚጠብቃቸው በጎቹ እረኛቸውን ተከትለው የሚሄዱ ከሆነ ጎንደሬዎች ናቸው አለን፡፡ እንዳለንም በጎቹ እረኛውን ተከትለው ሲሄዱ ተመልክተን፡፡ ፈጠን ብዬ ሄጄ እረኛውን ጎንደሬ ነህ ወይስ ጎጃሜ? ስለው ጎንደሬ ነኝ አለኝ፡፡ ታዲያ አሁን ይህ አካባቢ ጣናን ጨምሮ ምዕራብ ጎጃም ተባለ ምን ይሰማችኋል? ብዬ ጥያቄ አሰከተልኩበት፡፡ እረኛው ለዕድሜ ልኬ የሚሆን ትምህርት ሰጠኝ፡፡ “ዋ! ውሃም መሬቱም እዚሁ ድሮ ያለበት አይደለ?” አለኝ በሚያስደንቅ ፍጥነት፡፡ የተማረው ጓደኛዬ የጎንደር መሬትና ውሃ ለጎጃም ተሰጠ ብሎ ሲብሰለሰል እረኛው ችግር የለም የት ይሄዳል ብሎ ከተማረው ጓደኛዬ የተሻለ መልስ ሰጠኝ፡፡ የጎንደር መሬት ለትግራይ ተሰጠ የሚለውን የክልል ድንበር ችግር ብዙም ሰሜት የማይሰጠኝ የትም ቢሆን መሬቱ በኢትዮጵያ ግዛት ክልል በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ይህ የጎንደር እረኛ ያስተማረኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእረኛ ለመማር ዝግጁ ከሆነን ማለቴ ነው፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያዊነቴ እንጂ በዘር ተቆጥሮ የሚሰጠኝ መሬት ስለማልፈልግ ነው፡፡ ወደዚህ ትዝታ የመረኛ በቅርቡ በአዲስ አበባ እና ፊንፊኔ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላን አስመልክቶ ደም አፋሳሽ ድጋፍና ታቃውሞ መነሳቱ ነው፡፡
የከተማ ኮንስትራክሽን እና ቤቶች ሚንሰትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ ለምክር ቤት ቀርበው ሪፖርት ሲያቀርቡ ይህን ጉዳይ በሚመለከት “የአዲስ አበባና ፊንፊና ዙሪያ ከተሞች የተዘጋጀው የተቀኛጀ ፕላን ዝግጅት ይህን ያህል ጫጫታ የፈጠረው የኢህአዴግ ፖሊሲ ውጤት ነው ብለው ያምናሉ? መቼም ይህን ጉዳይ በተቃዋሚዎች አያሳብቡም”  የሚል አሰተያየት አዘል ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ሚኒሰትሩ መልስ ሲሰጡ ለልማት በጋራ መቆም እንዳለብን ገልፀው በአሁኑ ጊዜ እገሌ ነው ጥፋተኛ ማለት ተገቢ እንዳልሆነ ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዕይታ መነፅር ውስጥ መሆናችንን በመጥቀስ በተፈጠረው ሁኔታ ደሰተኛ እንዳልሆኑ የሚገልፅ ሰሜታቸውን መደበቅ ተሰኖዋቸው ነበር፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ከቅላፂያቸው ተቃዋሚን ለመከሰስ ፍላጎታቸውን መረዳት አያሰቸግርም ነበር፡፡ በእኔ እምነት ለዚህ ለተነሳው ተቃውሞ መንስዔዎች የኢህአዴግ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
አሁን በዩኒቨርሲት የሚገኙት ወጣቶች በሙሉ ማለት ይቻላል የኢህአዴግ ትውልዶች ናቸው፡፡ በኢህአዴግ የትምህርት ፖሊሲና አጠቃላይ ፖሊሲ አቅጣጫ ኢትዮጵያዊነትን እያኮሰሰ ጎጠኝነትን እያሞገሱ የመጡ ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ልጆች ከክልላቸው ወጥተው ከሰሜን እሰከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ተቀጥረው መስራት እንዲሁም ኢንቨስት አድርገው ቀጣሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አልተማሩም፡፡ አብዛኛዎቹ ክልሎችም እንደዚሁ ናቸው፡፡ በተለየ ሁኔታ ይህ እየተመቻቻላቸው ካሉት በስተቀር፡፡ ይህ በኢህአዴግ አገላለፅ ጠባብነት የሚለው ሲሆን የዚህ ምንጩ ደግሞ እራሱ የኢህአዴግ ፖሊሲ ነው፡፡ እነዚህ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከዚህ አሰተሳሰብ ተነስተው የአዲስ አበባ መሰተዳድር ከፊንፊኔ ዙሪያ ከተሞች ጋር የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተዘጋጀ ሲባሉ የእኛ የሚሉት የኦሮሚያ መሬት የእኛ በማይሏቸው ሌሎች ኢትዮጵያዊያኖች መሬታቸው የመቀማት ስሜት ቢያድርባቸው ልንፈርድባቸው አይገባም፡፡ ልክ ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ የዛሬዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የወደፊት ሀገር ተረካቢዎች ጢስ አባይ ፏፏቴ ዳር ከሚገኘው እረኛ ባልተሻለ ደረጃ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የኢህአዴግ የትምህርት እና የፖለቲካ ስርዓት በትውልድ ገዳይነት መጠየቅ ካለበት አንዱ በዚህ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አቶ መኩሪያ የዚህ ስርዓት አሰፈፃሚ ሰለሆኑ ጥያቄዬን ለመመለስ በመረጡበት አግባብ ወደፊት ታሪክ ይፈርደናል ብለዋል፡፡ ለታሪክ ፍርድ እንዲመች እነዚህን ጥያቄዎች እናንሳ፡፡ በትግራይ ክልል ስንት ኦሮሞ ኢንቨሰተሮች አሉ? በኦሮሚያ ስንት ትግሬ ኢነቨሰተሮች አሉ? ብለን ብንጠየቅ መልሱ ግልፅ ነው፡፡ በጋምቤላ ውስጥ ካሉት ኢንቨሰተሮች ምን ያህል ኦሮሞዎች አሉ? ለነዚህ ጥያቄዎች የሚገኘው መልስ ግልፅ ነው፡፡ ከነዚህ ጥያቄዎች የሚገኘው መልስ የተሳሳቱ የኦሮሞ ብሔረተኞች ኢትዮጵያ የጋራችን እንዳልሆነች የሚያደርጉት ቅስቀሳና ተግባር መገለጫ ነው፡፡ የኦህዴድ ጎምቱ ባለስልጣናት ትልቁ ግባቸው በፌዴራል ስልጣን ወይም ኦሮሚያ ብቻ ነው አማራጫቸው፡፡ ልጆቻቸውን ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጭ እንዲኖሩ አድርገው እያዘጋጁ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኢህአዴግ ያስተማራቸውን ብሄረተኝነት ልክ መስሎዋቸው ይሁን ወይም በማነኛውም ምክንያት የፈለጉትን ሃሣብ የመደግፍና የመቃወም መብት አላቸው፡፡ ይህን መብታቸውን በስላማዊ መንገድ እስከገለፁ ድረስ ኢህአዴግ የሚውስድው የግድያ፣ እስር፣ ከትምህርት የማፈናቀልና የማፈን ተግባር በምንም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አሰቀያሚው የመንግሰት ምክንያት ደግሞ የተገደሉት ባንክ ሲዘርፉ ነው መባሉ ነው፡፡ሰዎች ከሚሞቱ የአምቦ ባንክ ቢዘረፍ ይሻል ነበር፡፡ ዜጎች የተሳሳተ ሃሳብንም ቢሆን የመደገፍ መብት የግል ውሳኒያቸው መሆን አለበት፡፡ ከተሳሳተ መንገድ መመለሻው መንገድም ውይይትና የሃሳብ ፍጭት እንጂ በጠመንጃ የሚታገዝ ጡጫ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ ዓይነት የግጭት አፈታት ሰልት እንዲሁም የእኔ ብቻ መንገድ ልክ ነው ከሚል አሰተሳሰብ መውጣት ለዚህች ሀገር ትንሳዔ አንድ እርምጃ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ገድለው ሲያበቁ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች መፅናናትን መመኘት ሌላ አቁስል የሆነ ሰልቃ ነው፡፡
የኢህአዴግ መንግሰት ምን ታይቶ እንደሆነ ባይታወቅም  የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ከእራሱ የኦህዴድ/ኢህአዴግ አባላትን ጨምሮ በኦሮሚያ ስም የተደራጀን ፓርቲ ነን የሚሉ በሙሉ ተቃውመውታል፡፡ ለተቃውሞው መነሻ በእርግጥ የህዝብ ጥቅም ከሆነ ህዝብ የሚጠቀመው እነዚህ ከተሞች ተቀናጅተው በጋራ ተመጋግበው ለማደግ ሲወሰኑ ብቻ ነው፡፡ አሁን ያለው ዓለም አቅፍ ተሞክሮ በአንድ ሀገር ክልል አይደለም በሁለት ሉዓላዊ ሀገሮች ማዕክልም የጋራ የመልማት ሰትራቴጂ የግድ የሚል ሆኖዋል፡፡ የኢህአዴግ የተቀናጀ ልማት ስትራቴጂ ምፀት የሚመስለው በኦህዴድ ጋሻ ጃግሬነት የተገነባው የጠባብነት መገላጫ “አኖሌ” ሀውልት ምረቃ ማግሰት መሆኑ የኢህአዴግ ዘላቂ ሰትራቴጂው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሰር ማሰተባበር ይሁን ማለያየት ግልፅ አለመሆኑ ነው፡፡ ኢህአዴግ ግራ ገብቶት ግራ የሚያጋባ ሰርዓት ነው፡፡
በህገ መንግሰት ድንጋጌ አዲሰ አበባ በኦሮሚያ ክልል ዙሪያ መገኘቷን ተቀብሎ አዲስ አበባና ኦሮሚያን በሚያሰተሳሰሩ ጉዳዮች ኦሮሚያ ልዩ  ጥቅም እንደምታገኝ እና ይህም በህግ እንደሚወሰን ተደንግጎዋል፡፡ የኦሮሚያን ክልል ተጠቃሚነት በተሻለ ማረጋገጥ የሚችላው የመስረተ ልማትና ሌሎች ሰትራቴጂክ ትብብሮች ማሰብ ካልተጀመረ የኦሮሞን ህዝብ እንዴት ለመጥቀም እንደሚታሰብ አይገባኝም፡፡ በኦሮሚያ ጉዳይ ላይ ለጊዜውም ቢሆን ወሳኝነት ያለው ኦህዴድ ሁል ጊዜ ሀገራዊ ዕይታውን በጠባብነት ሰሜት (በተሳሳተ ያለን በቂ ነው በሚል ትልቅነት መኮፈስ) የተጀቦነ ነው፡፡ ለምሳሌ የግል የፋይናንስ ድርጅቶችን ለመገዳደር ከመንግሰት ባንኮች በተጨማሪ በክልል መንግሰታት የሚታገዙ “የግልባንክ ተብዬዎች” ተቋቁመዋል የእዚህን ባንኮች ሰያሜ ስንመለከት የአማራ ክልል ድጋፍ ያለው “አባይ ባንክ” አማራ ባንክ የሚል አማራጭ ቀርቦ ውድቅ መደረጉን በመድረኩ ላይ ከነበሩ ሰዎች ሰምተናል፣ ትግራይ ክልል እንደ ሁሌም ትግራይ ባንክ በአሳባቸውም አልመጣም “አንበሳ ባንክ” ነው ያሉት፡፡ በተመሳሳይ የደቡብ ክልልም “ደቡብ ግሎባል ባንክ” ይበል እንጂ ጉራጌ፣ ሲዳማ ወይም ወላይታ ለማለት አልፈለጉም የደቡብ በራሱ የዚህ ዓይነት ሰያሜ ለመስጠት አስቸጋሪ መሆኑ ሳይዘነጋ ማለቴ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ስትራቴጅስቶች ግን “ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል” በማለት ከአዲሰ አበባና ከኦሮሚያ ውጭ የመንቀሳቀስ እድሉን የሚያጠብ ጠባብ ውሳኔ ወሰኑ፡፡ ኦሮሚያን ሊገልፅ የሚችል ሌላ ተራራ፣ ወንዝ፣ ታሪካዊ ቦታ ወይም የገበያ መስፋፋትን የማይገድብ ስያሜ የሌለ ይመስል ማለቴ ነው፡፡ የኦሮሚያ ስትራቴጂስቶች በዚህ ደረጃ ሲሳሳቱ በኢህአዴግ ዘመን በጠባብ ብሔረተኝነት ያደጉት ወጣቶች የተቀናጀ እቅድ ቢቃወሙ ሊገርመን አይገባም፡፡ ኢህአዴግም የዘራወን እያጨደ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡
ዮኒቨርሲቲዎች በፌዴራል መንግሰት ስር ሆነው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆኑ ቢታወቀም ለዚህ ጉዳይ በተቃውሞ የተነሱት ለምን በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ብቻ ሆኖ? ብሎ መጠየቅም ያሰፈልጋል፡፡ በዚሁ የዘር ፖለቲካ የተነሳ የኦሮሚያ ክልል ልጆች ምርጫቸው በአብዛኛው በክልላቸው እንዲሆን ይፈልጋሉ፣ ከምራቃም በኋላ መመደብ የሚፈልጉት በኦሮሚያ ክልል ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ለኦሮሞ ልጆች ይጠቅማል ወይ? የኦሮሞ ብሔርተኛ ነን የሚሉ ሁሉ መልስ ሊሰጡበት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው በቤቴ የገጠመኝን ታሪክ በአጭሩ ላካፍላችሁ፡፡ የአክሰቴ ልጅ እኔ ቤት እየኖረ ሰበታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ይመጣል፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ በምርጫ ኦሮሚፋ እና አማርኛ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ኦሮሚፋ አቀላጥፎ የሚናገረው የአክሰቴ ልጅ አሁንም ኦሮሚፋ ክፍለ ጊዜን እንደመረጠ ሲነግረኝ ለምን? ብዬ ሞገትኩት፡፡ መልሱም “ቋንቋውን ንቆ የነፍጠኛ ቋንቋ መረጠ ብለው ይጠምዱኛል” ነው ያለኝ፡፡ ኦሮሞ ያልሆኑት የሰበታ ልጆች ምን መረጡ?  አልኩት አሰከትዬ፡፡ “እነርሱም ኦሮሚፋ ነው የመረጡት” አለኝ፡፡ ልዩነቱን አስረዳሁት አማርኛ በደንብ የሚችሉት ኦሮሚፋ ሲመርጡ እነርሱ የወደፊት ዕድላቸውን ወደ ሙሉ ኢትዮጵያ ሲያሳድጉ አንተ ግን እጣ ፈንታህን በኦሮሚያ ላይ ብቻ አደረከው፡፡ ምርጫው ያንተ ነው አልኩት፡፡ በምርጫው ቀጠለ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲጨርስም ጅማ ዩኒቨርሲቲ መረጠ፡፡ ጅማ ለስራ ሄጄ ከዩኒቨርሲቲ አሰጠርቼ ከጓደኞቹ ጋር ሳገኘው ሁሉም ጓደኞቹ ኦሮሚፋ ተናጋሪ ናቸው፡፡ አንድ አንዶቹ በፍፁም አማርኛ የሚጠየፉ፡፡ እነዚህ ልጆች እንዴት አድርገው የኢትዮጵያዊነት ፕሮጀክት ሊጥማቸው ይችላል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞችን በድጋሚ ልጠይቅ ይህ ተግባር የኦሮሚያ ልጆችን ይጠቅማል ወይ? ለአክሰቴ ልጅና ለጓደኞቹ በወቅቱ የነገርኳቸው መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን የሚመራው ከትግርኛ አሰበልጦ ወይም እኩል አማርኛ ስለሚናገር ነው፡፡ በኢትዮጵያችን የኦሮሞ ልጆች ትልቅ የሚባለውን ቦታ ለማያዝ አማርኛን መጠየፍ የሞኝ ምርጫ ነው ነበር ያልኳቸው፡፡
በተመሳሳይ የኦህዴድ ካድሬዎች የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጅ ማስተር ፕላንን ለምን ተቃወሙት? የሚለውን መመርመር ይኖርብናል፡፡ እነዚህ ከተሞች በፈራቃ ካድሬዎች እየተመደቡ የድርሻቸውን የሚመዘብሩበት፣ ሲበቃቸው በዝውውር ስም የሚነሱበት እና ካድሬው ሁሉ ተራ ቢደርሰኝ ብሎ የሚጠብቅባቸው መሆናቸው አንዱ ነው፡፡ የተቀናጃ ማስተር ፕላን የሚባለው ይህን ዕድል ሊዘጋ ይችላል፡፡ ምን አልባትም በካድሬነት ሳይሆን በእውቀት የሚተገበር ሊሆን ስለሚችል ፍርሃታቸውን በህገ መንግሰት ይቃረናል በሚልና ለህዝብ መፈናቀል ይፈጥራል በሚል የሸፍጥ ሽፋን ነው የሚቃወሙት፡፡ እነዚህ ካድሬዎች መቼ ነው ስለ ህገ መንግሰትና የህዝብ ጥቅም ቆመው የሚያውቁት? አሁን ግን ለግል ጥቅማቸው ህዝብና ህገ መንግሰትን ከለላ አድርገው ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡ ተማሪዎችን ከለላ አድርገው፡፡ ለማነኛውም የካድሬ ተቃውሞ አንዴ ተጠርቶ እሰኪገመገም እና ከዚህ በፊት የሰራውን ወንጀል እስኪያስታውሱት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይታገሳል፡፡ በተቃወመበት አፉ ውዳሴ ሲያወረድ በቅርቡ እንሰማለን፡፡ አሳዛኙ ግን ምንም ውስጥ የሌሉትን፣ በጠባብ ብሔረተኝነት ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች ለአደጋ እንዲጋለጡ ማድረጋቸው ነው፡፡ የመንግሰትንም ትዕግሰት አልባነት የሚያጋልጥ ድርጊት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡
ለማነኛውም የአዲስ አበባና በዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ ልማት ብዙ ነገር እንድንማር የሚያደርግ ነው፡፡ ኢህአዴግ ዜጎችን በኢትዮጵያዊነት እና በብሔረተኝነት የማሰተባበር ፈተና ውስጥ መውደቁን፤ የዘራው የጠባብ ብሔረተኝነት ፖሊሲ በተለይ በኦሮሚያ ነብስ ዘርቶ ለእድገት እንቅፋት መሆኑን፤ ቋንቋ መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ወደ ፊትም ከዚህ ዓይነት ችግር የሚላቀቅ እንዳልሆነ፤ ወዘተ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ኦህዴዶች የኦሮሞ ልጆች በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኤኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ ግንኙነቶች የላቀ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረጋቸውን በዚህ አጋጣሚ ልናስታውሳቸው ይገባል፡፡ የኦሮሞ ልጆች ጠቅላይ ሚኒሰትር ለመሆን መዘጋጀት ይኖርባቸዋል …… ፕሬዝዳንት መሆን ይበቃቸዋል፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!

Saturday, May 3, 2014

ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር እውነትን እናክብር …..



ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
አቶ ሀይለማሪያም ደሣለኝ ሪፖርታቸውን ካቀረቡ አስር ቀን የሆናቸው ቢሆኑም ያነሱዋቸው ጉዳዮችና መልስ ለመስጠት የመረጡት መንገድ እሰከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ ለማሳሳቻነት ለመጠቀም የኢህአዴግ ድምፅ ሆነው ስለሆነ የተናገሩት ወደፊትም በተደጋጋሚ የምንወያይበት አጀንዳ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ብዙ ሰዎች የዋህ ፖለቲከኛ ያደርጉኛል፡፡ ለምን ሲባል? እኔም ብሆን ሌሎች ለእውነትን መቆምን መርዕ ማድረግ አለብን ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ፖለቲካ ሽፍጥ እና ሴረኛነትን የሚጠይቅ ነው ብለው ስለሚያምኑ እውነትን ደግሞ ከዚህ ሰፈር ማገኘት ስለማይቻል የሚባል ስምምነት የተደረሰበት እስኪመስል ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ፖለቲከኛ መሆን የሚፈልግ የጆርጅ ኦርዌልን መፅሃፍ አንብቦ የገባው መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱም ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ አለበት ብለው የሚያምኑም ብዙ ናቸው፡፡ ይህን ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አቶ ሀይለማሪያም በሪፖርታቸው መነሻ ለቀረበላቸው መልስ የሚሰጡት ከእውነትም ከእውቀትም ሲዛነፍብኝ ለምን? የሚል ጥያቄ ስለ አጫረብኝ ነው፡፡ ፖለቲከኝነት ለሀሰት ለመገዛት ከእውነት ለመራቅ ለምን ከለላ ይሆናል፡፡
በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒሰትሩን ለማናደድ አስቤ ጥያቄ አላቀረብኩም፡፡ ይህን ሃሳቤን በመግቢያዬ ላይ ለመጥቀስ ሙከራ አድርጌየለሁ፡፡ ለሙገሳ የሚሆን ቃላቶች መደርደርም ፍላጎቴም ዓላማዬም ሰለአልሆነ አላደረኩትም፣ አላደርገውም፡፡ እኔ እንዲታወቅ የፈለኩት እርሳቸውም ከፈለጉ በመረጃ አስደግፈው እውነት እውሽት ብቻ ሳይሆን መረጃ እንዲሰጡ እና ህዝብ በቀጥታ በሚተላለፍ ሚዲያ የሚከታተል ስለሆነ ፍርድ እንዲሰጥ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ህዝቡ ፍርድ ለመስጠት እንዳይችል አሳስተው ማለፍ የፈለጓቸውን ነጥቦች ብቻ በማንሳት አሁንም ጉዳዩን ለአንባቢ ፍርደ መተው መርጫለሁ፡፡
በኢህአዴግ የሚመራው መንግሰት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያሰቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት ነው ቃል የገባው እንጂ ከ2003 እሰክ 2007 ዓመተ ምህረት ድረስ በሰራ ላይ ልምምድ የማደርግበት ነው ያለ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ከ1983 እስከ 1993 የልምምድ ጊዜያቸው፣ አቶ ሀይለማሪያምን ባይጨምርም በተልዕኮ መማሪያቸው ነበር፡፡ አሁን አቶ ሀይለማሪያም እያሉ ያሉት የአዲስ አበባውን ሳይጨምር 2395 ኪሎ ሜትር የባቡር ሀዲድ ለመዘርጋት እና ሰራ ላይ ለማዋል አቅደን ነበር፤ ይህን ስናቅድ ልምድም ገንዘብም አልነበረንም፡፡ ሰለዚህ ይህ እቅድ በዚህ የዕቅድ ዘመን አይሳካም ነው ያሉት፡፡ በእቅዱ ዘመን መጀመሪያ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክት የመፈፀም ክህሎትም ሆነ ፋይናንስ አቅም የለም ብለን ነው ዕቅዱ ላይ አስተያየት የሰጠን ሰዎች የተናገርነው፡፡ የዛን ጊዜ እኛ የዚህ ዓይነት ሃሳብ ስናነሳ ጨለምተኞች ተባልን፡፡ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጥረታችንን ከማድነቅ አልፋችሁ በኪሎ ሜትር ልትመዝኑን አትችሉም የሚል ዘለፋ አዘል መልስ መስጠት ምን አምጣው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር እንዲረዱልኝ የምፈልገው እቅድ የሚገመገመው ባሰቀመጡት መለኪያ ነው፡፡ የባቡር ሀዲድ ዕቅድ አፈፃፀም የሚመዘነው በቅድሚያ በዕቅዱ ላይ በተቀመጠው መለኪያ ነው፡፡ ይህም በተዘረጋው የባቡር ሀዲድ መስመር ነው፡፡ መልሶን በቀጣይም በዚሁ መስመር ማድረግ ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡ ካልሆነ ዕቅዱ መቀመጥ የነበረበት “የባቡር መስመር ለመዘርጋት አቅም ግንባታ” ተብሎ ለዚህም ምን ያህል የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የቁሳቁስ ዝግጅት እንደሚደረግ ብቻ ነበር፡፡ ይህ በእውነቱ ሲጀመር የሟቹ አሁን ደግሞ የእርሶ ኃላፊነት ነው፡፡ ሃላፊነቱን የወሰዱት ደግሞ ከነሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ጋር ሰለሆነ ከኃላፊነት መሽሽ አይቻልም፡፡
በተመሳሳይ በኤሌትሪክ ኃይል ዘርፍ 10 ሺ ሜጋ ዋት እናመነጫለን የሚል ግብ እንጂ ይህን ለማመንጨት የሚችል አቅም ይኖረናል የሚል አይደለም፡፡ ከ2007 በኋላ የሚመነጭ ኃይል በሙሉ ለቀጣዩ ዘመን የሚያልፍ ነው፡፡ ግልገል ጊቤ ሶሰት ካለፈው ዓመት የዞረ ነው፡፡ ለነገሩ የዚህ ዓይነት ማጭበርበር በኢህአዴግ ሰፈር የተለመደ ነው፡፡ በ2002 ምርጫ ውድድር ጊዜ ማመንጨት ያልጀመረ ፕሮጅክቶች ተደምረው ከሶሰት ሺ በላይ ደረሰናል ሲባል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይህ ማጭበርበር ግን በፍፁም እንዲደገም መፍቀድ የለብንም፤ ደጋግመን በቁጥር ማጭበርበር ይቁም ብለን እንሞግታለን፡፡ በነገራችን ላይ ግልገል ጊቤ ሶሰት በሚቀጥለው ዓመት ሰራ ይጀምራል? ወይስ አይጀምርም? ሚዲያዎች አይጀምርም እያሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖረት ይጀምራል ይላል፡፡ ይህን ጥያቄ ለምን ዘለሉት? መልሱ ስለማይጀምር ውሃ ስለማይሞላ ነው፡፡ ሰለዚህ በሁለት ሺ ሰባት መጨረሻ 10 ሺ ተብሎ ከታቀደው በእርግጥ 4000 ሜጋ ዋት ይኖረናል? ሌላ ጥያቄ ነው፡፡
በቤቶች ዘርፍ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ሰሜታቸውን ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነገር ግን ብስጭታቸው ለሁሉም ግልፅ ሆኖ የወጣበት መልስ ስጥተዋል፡፡ በ1996 ከ450 ሺ በላይ ሰዎች ለኮንዶሚኒየም ቤት የተመዘገቡ ሲሆን እነዚህ ተመዝጋቢዎች ሙሉ በሙሉ ቤት ሳያገኙ አግኝተዋል ማለት ለምን አስፈለገ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባመኑት 190ሺ ቤቶች ተገንብተው በዕጣ ለደረሳቸው እድለኞች፣ በመልሶ ማልማት ለተነሱ፣ በከንቲባዎች እና ሌሎች ሹሞች ትእዛዝ፣ እንዲሁም ለገዢው ፓርቲ ባለሟሎች ቤቶች ተሰጥቶዋል፡፡ ከዚህ ውሰጥ 100 ሺ ለተመዘገቡ ባለ ዕድለኞች ተሰጥቶዋል ብንል ቀሪው 350 ሺ ዕድለ ቢሶች ከአዲሶቹ ጋር በድጋሚ እንዲመዘገቡ ተገደዋል፡፡ እነዚህ ዕድለ ቢሶች በጠቅላይ ሚኒሰትሩ ግምት ለቀጣይ አሰር ዓመት እድላቸውን በድጋሚ እንዲሞክሩ ነው፡፡ በአዲሱ ምዝገባ የተመዘገቡት ከ850 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ከቀድሞ ተመዝጋቢዎች ልዩ የሚያደርጋቸው የቀድሞ ተመዝጋቢዎች እድል ሲደርሳቸው ገንዘብ ማፈላለግ እንጂ ቀድመው ማጠራቀም አይጠበቅባቸውም ነበር፡፡ አዲሶቹ ተመዝጋቢዎች በየወሩ በመቆጠብ እድላቸውን መጠበቅ የግድ ይላቸዋል፡፡ እነሱ በተሰፋ ቤት እየጠበቁ በሚቆጥቡት ሀብታም እንዲሁም መንግሰት ተበድሮ ይስራበታል፡፡ የእኔ ጥያቄ ከቁጠባቸው “ተገቢውን” ትርፍ ቤቱን እሲኪያገኙ የሚያገኙበት መንገድ መፈለግ ይኖርበታል፤ ባንክ ከማስቀመጥ በተሸለ ማለቴ ነው፡፡ ያለበለዚያ ይህ ቁጠባ ድሃውን የበለጠ የሚያደኽይ ነው የሚል እምተነት ነው ያለኝ፡፡
በዓለም ላይ የዛሬ አስር ዓመት ቤት ለማግኘት ብሎ የሚቆጥብ የለም፡፡ የቤት ልማት ፕሮጀክት ግን ልክ ነው የአምሳ ዓመትም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ እየኖሩ “ሞርጌጅ” ይከፍላሉ እንጂ ውጭ ሆነው ለቤት ብለው አይቆጥቡም፡፡ አንድ አንድ ልባም ተማሪዎች ከተማሪ ቤት እንደወጡ ቤት ለመግዛት ሲሉ እንዲህ ዓይነት ቁጠባ በቤተሰብ ወይም በግል ቁጠባ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ አቶ ሀይለማሪያም እንዲሁም እርሳቸው የሚመሩት ፓርቲ ያልገባቸው አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ አንድ ድሃ ቆጥቦ ሀብታም ይሆናል የሚል አስተሳሰብ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ሕዝቡን እንዲህ እያሉ ማሳሳት ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሣሌ ብር 5000 የሚያገኝ ሹም ለሃያ ዓመት ሙሉ ቢቆጥብ በእድሜው መጨረሻ የሚኖረው ብር 1.2 ሚሊዮን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ገንዘብ የዛሬ አስር ዓመት ሀብታም መባል አይቻልም፡፡ የሀብት ምንጭ አዲስ ሃሳብና አሰራር ይዞ ፋይናንስ ተቋማት እና ፋይናንስ ማድረግ ከሚችሉ ግለሰቦች ጋር መገናኘት ነው፡፡ ቆጥቡና ሀብታም ትሆናላችሁ ብሎ ድሃውን የእልም እንጀራ ማብላት ቢቆም ጥሩ ነው፡፡ መቆጠብ ጥሩ ነው፡፡ ሀብታም ለመሆን ግን አይደለም፡፡ የባንኮች ስራ አንዱ ድሃ ቆጣቢዎችን ከሀብታም ተበዳሪ ኢንቨስተሮች ጋር በጥንቃቄ ማገናኘት ነው፡፡
ይህን ሁሉ ክፍተት ተመልክተን አቶ ሀይለማሪያም በምሳሌ ለማሰረዳት እንደሞከሩት ሰምንት ከአስር ያገኘ ተማሪ ሊበረታታ ይገባል ያሉትን ለመውሰድ እንቸገራለን፡፡ ኢህአዴግም ሰምንት ከአስር ስለአላገኘ፡፡ ፈተናውን ተፈታኝ ባያርመው ጥሩ ነው፡፡ ካረመውም ትክክለኛውን ማሪሚያ ቢጠቀም የተሻለ ይሆናል፡፡ አሁን በተሰጠው ማረሚያ መሰረት አምሰት ከአሰርም ማግኘቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ለምሣሌ በባቡር 3 ከአሰር፣ በኢንርጂ 4 ከአስር፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት 3 ከአሰር፣ በጨርቃጨርቅ ቆዳ ኤክስፖርት 1 ከአስር፣ በስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዜሮ ከአስር፤ በማኑፋክቸሪንግ 2 ከአሰር፣ በሰፋፊ እርሻ ልማት 2 ከአሰር፤ ወዘተ ….. ፕሮፓጋንዳውን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ያቀረቡ ዕለት ካሰገረመኝ ነገር አንዱ “አንድነት” የምትለዋ ቃል ከውስጣቸው ፈንቅላ ብትወጣም ማለትም “ግንኙነት” ብለው አሻሽለዋታል፡፡ ከኤርትራ ጋር አንድ ብንሆን ቢባል ችግሩ ምኑ ላይ ነው? የዚህን ያህል ድንጋጤ የፈጠረባቸው ለምን አንደሆነ ግራ ነው የገባኝ፡፡ ለማንኛውም የውስጥ ችግራቸውን የሚያውቁት እራሳቸው ናቸው እና ይገማገሙበት፡፡ ከዚህ ጋር የሚያያዝ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የምትለው ቃል እንዴት እንደተጠላች ሳሰብ ይገርመኛል፡፡ ይህችን ቃል የጠሉ በሙሉ ግለኝነታቸውን አስቀደሙ እንጂ ምንም ሲፈይዱ አላየናቸውም፡፡ በድንበር አካባቢ ስለሚሰጡ ሰፋፊ እርሻዎች በቂ ጥናት አድርጋችኋል ወይ? ለሚለው ጥየቀቄዬ ጥናት እንዳላደረጉበት አምነዋል፡፡ ጥናቱ ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የደራሲ ማሞ ውድነህ መፅሃፍ እንደፋሽን በሚነበብት ጊዜ ጌታ ተቀብለው ትኩረታቸውን ሁሉ መፅሃፍ ቅድሱ ላይ ስለነበር ካልሆነ፣ እስራኤሎች እንዴት አድርገው የእርሻ መሬት እየተከራዩ እስራኤል የምትባል ሀገር እንደመሰረቱ ቢያውቁ ጥያቄዬን በፌዝ አይወስዱትም ነበር፡፡ የጋምቤላ መሬት አሰመልክቶ ከሉዓላዊነት ጋር የሰጡት እጅና እግር የሌለው ማብራሪያ ስለ ጋምቤላ ህዝብ ያነሱት ነገር ሁሉ ግራ ነው ያጋባኝ፡፡ በድንበር አካባቢ ጋምቤላን ለምሳሌ አልኩ እንጂ ዑመራም ሊሆን ይችላል፡፡ ግብፆች በሰፋፊ እርሻ ሰም መሬት ወሰደው እያረሱ በድንበር ከሱዳን ጋር የኢትዮጵያን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ እንቅስቃሴ ብትጀምር ማን ይከለክላታል፡፡ መቼም ለሳውዲ ተሰጥቶ ለግብፅ ለመከልከል ጥናት የላችሁም፡፡ ለመጣ የሚቸበቸብ ከሆነ ቱርክም ከጨርቃ ጨርቅ ውጭ ለጥጥ ብሎ ድንበር ላይ መሬት ቢጠይቅ ይሰጠዋል፡፡ አሁን ማለት የፈለኩት ግልፅ ነው፡፡
በመጨረሻም ክርስቲያኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግብረሰዶማዊነትን በይፋ ላለማውገዝ ዳር ዳር ብለው ሲያልፉት እጅ ጥምዘዛው ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ መረዳት ከባድ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት እንዳልኩት ሁሉ ቴሌ፣ ባንክ የመሳሰሉትን እጃችንን ተጠምዝዘን አናደርግም በመቃብራችን ላይ የምንላቸው መሆን የለባቸውም፡፡ በመቃብራችን ላይ ከምንላቸው አንዱ በሙስሊሙም፣ በክርስቲያኑም ሆነ በዋቄ ፈታ በኢትዮጵያ ምድር ተቀባይነት የሌለውን ግብረሰዶማዊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁሉ የተለየች ብትሆን ግብረሰዶማዊያን የማይፈነጩባት መሬት እንድትሆን መስማማት ይኖርብናል፡፡ በመንግሰት በኩል የዚህ መንሽራተት እና የእጅ ጥምዘዛ ውጤት እንዳመጣ የሚያሳየው በይቅርታ አሰጣጥ ረቂቅ ህግ ውስጥ ምዕረት ከማይደረግላቸው ዝርዝር ውስጥ ገብቶ የነበረው ግብረሰዶማዊነት እንዲወጣ መደረጉ አንዱ ማሳየ ነው፡፡ አንዲህም ሆኖ ግን በተለያየ ምክንያት ለዚህ ፀያፍ ድርጊት በተለያየ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ምክንያት የተጋለጡትን ዜጎች ከዚህ ጉዳት ለመታደግ ጥረት ማድረግ የለብንም፣ የራሳቸው ጉዳይ እንበል ማለቴ አይደለም፡፡ ለመስፋፋትና ለማስፋፋት ግን መሬቱ ጭንጫ መሆኑን ማወቅ ግን ግድ ይላል፡፡ ይህ ነውረኛ ድርጊት ደግሞ በልምምድ የተገኘ እንጂ ተፈጥሮዋዊ ነው ብለው ለሚያሳስቱትም ቢሆን ቦታ እንደሌለ እና የግለሰብ መብት አራማጆች የሆንን ሰዎችም ብንሆን በዚህ ጉዳይ ግልፅ  አቋም ማንፀባረቅ ሊኖርብን ይገባል፡፡ ይህ የኒዎ ሊብራሎች ነው፡፡
ቸር ይግጠመን!!!