Sunday, May 25, 2014

ግንቦት 20 ያለመለስ ስንት ይቆይ ይሆን?



ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
ሰሞኑን ልባችን እሰኪጠፋ የግንቦት 20 ፍሬዎች የተባሉት “ልማትና ዲሞክራሲ” በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እንዲሁም እየተከፈላቸው በማህበራዊ ድህረ ገፅ የስድብ ናዳ የሚያወርዱትን ስዶች ጨምሮ እንደ ፍራፍሬ እየበላን እንደ ወተት እየተጋት ነው፡፡ ሚዛናዊ ሆኜ  ግንቦት 20 ያመጣልኝን ፍሬ ሳስብ የምር ግራ ይገባኛል፡፡ የእኔ ግርታ የሚመነጨው አሁን ያለንበት ደረጃ ለመድረስ በእርግጥ 23 ዓመት ያስፈልገን ነበር ወይ? የሚል ነው፡፡ በእኔ እምነት ግንቦት 20 የስርዓት ለውጥ የመጣበት ቀን እንደሆነ ለመቀበል አልቸገርም፡፡ ደርግን የተካው ዳግማዊ ደርግ በመባል የሚታወቀው ኢህአዴግ ግን ከምን ከምን አንፃር ከደርግ እንደሚሻል ሊገባኝ አልቻለም፡፡ እኔ በፍፁም የማላደርገው ኢህአዴግን ከደርግ ጋር ማወዳደር ነው፡፡ በሂሣብ ትምህርት ፍየልና በግ እንደማይደመረው ማለት ነው፡፡ ኢህአዴጎች ደስ የሚላቸው ሁሌም ውድድሩ ከደርግ ጋር እንዲሆን ነው፡፡ ሲያስፈልግም ከምኒሊክ ጋር መወዳደር የሚያሻቸው በተለይ ባቡርና ስልክ ሲነሳ ነው፡፡ ሊያፍሩበት በሚገባ ነገር ውድድር ይከጅላሉ፡፡ እኔ ኢህአዴግን እንዲመዘን የምፈልገው ስመዝነውም የሚቀልብኝ ከዓለም አቀፍ መለኪያ እንዲሁም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሚገባን ደረጃ አንፃር ነው፡፡
አፍቃሪ ኢህዴጎች “ኢህአዴግ ባይኖር ኖሮ ይህች ሀገር ትፈራርስ ነበር” ለማለት አፋቸውን እንኳን ያዝ አያደርጋቸውም፡፡ ይህንን መፈራረስ የገታው ደግሞ “የኢህአዴግ የብሔር ብሔረሰብ ፖሊሲ ነው” ይሉናል፡፡ በእኔ እምነት የመፈራረስ ሟርትም ሆነ የሟርቱ ማፍረሻ ፖሊሲ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ኢህአድጋዊያች ለዚህም ማሳያው የሚሉት በሽግግር ኮንፈረንስ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት ውስጥ ከአስር በላይ የሚሆኑት መገንጠል አለብን የሚሉ ነበሩ በማለት ነው፡፡ ልክ ነው በዚህ ማህበር ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ሃሣብ የሚያራምዱ ቢበዙ እንጂ የዚህ አቀንቃኞች ሊያንሱ አይችሉም፡፡ ህወሃትን ጨምሮ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ የመሳሰለሉት ከስማቸው ጭምር የመገንጠል ደቀ መዝሙሮች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በእነርሱ ጋባዥነት የሚመጣ ድርጅት እንዴት አድርጎ ከዚህ የተለያ ሃሳብ ሊያራምድ ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ለዚያውም እነዚህ ጋባዦች በለስ ቀንቷቸው መሣሪያ ታጥቀው አራት ኪሎ ቁጭ ብለው ባሉበት ወቅት፡፡ ይህ ግን በፍፁም የኢትዮጵያ ህዝብ ለመገንጠል ዝግጁ ነበር የሚያስብል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከኢህአዴግ በፊትም በቋንቋቸው ይናገራሉ፣ ይዘፍናሉ፣ ያለቅሳሉ፡፡ በኢህአዴግ ጊዜ የተጨመረልን “ቁቤ የሚበል” ፊደል እና ወጣቱ በተለይ በኦሮሚያ አካባቢ ኢትዮጵያዊ ራዕይ እንዳይኖረን መደረጉ ነው፡፡ የዚህ ፍሬ ምስራቹን በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ደርሶ ተመልክተነዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ችግር በኢትዮጵያ ጥላ ስር ይፈታል ጥቅሙም ይረጋገጣል ብዬ ነው የማምነው የሚለው ኦህዴድ፤ አባል የሚመለምለውና የሚያደራጀው በኦነግ ፕሮግራም እንደሆነ ያጋለጠ ክስተት ነበር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር አሉት የሚባለው “ኦህዴድ ሲፋቅ ኦነግ ነው” የሚባው በዚህ ክስተት ኦህዴድ ሳይፋቅም ኦነግ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ይህ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሀገራት ለውህደት በሚሰሩባት ዓለም የመገንጠል ጥያቄ በወጣቶች ላይ የዘራው ኦህዴድ/ኢህአዴግ ያሰገኘልን የግንቦት 20 ፍሬ ነው፡፡ ኢቲቪም ሆነ ተሳዳቢዎቹ የማህበራዊ ድህረ ገፅ ካድሬዎች ይህን የግንቦት 20 ፍሬ አያነሱትም፡፡
ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በአንድ ሳምንት ተበጥብጦ የሚጠጣ አይደለም የሚል አዲስ መፈክር መጥቶዋል፡፡ በእኔ እምነት ሃያ ሶስት ዓመት ሙሉ ተዓማኒነት ያለው እና ተቀባይነት ያገኘ ምርጫ ማካሄድ ያለመቻልን የሚያክል ብቃት ማነስ በዓለም ያለ አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ በብቃት ምርጫ ማጭበርበር እንደ ብቃት ከተወሰደ ደግሞ ገዢውን ፓርቲ የሚያሽልም ነው፡፡ ለልምድ ልውውጥም ብዙ አንባገነን መሆን የሚፈልጉ እንደ ጆርጅ ኦሩዌል መፅሃፍ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት ገንብቻለው የሚል መንግሰት ዜጎች በምርጫ ለመወዳደር፣ አማራጭ ይዞ በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ፣ ምርጫን ያለስጋት መታዘብ፣ የመሳሰሉትን ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለመጠቀም በፍርሃት እየራዱ ብዙዎች “አታነካኩኝ ልኑርበት” የሚሉበት ሀገር ሲሆን፤ የዲሞክራሲ ስርዓት ለማስፈን ነው ትግሉ እየተባሉ በዱር በገደል ህይወታቸውን የሰዉ ሰማዕታት ድንገት ቀና ቢሉ ምን ምን ዓይነት መልስ እንደሚሰጧቸው መገመት ያስቸግራል፡፡ የሚያሳዝነው እራሳቸውን ለመስዋዕትነት አዘጋጅተው የነበሩ በአጋጣሚ በህይወት የተረፉት ይህ ነው ዲሞክራሲው ሲባሉ እሺ ብለው መቀበላቸው ነው፡፡ ከመሰዋዕትነት መትረፋቸውን እንደ አንድ ትርፍ ቆጥረው በአንድ ወይም በሌላ የሚያገኙትን ጥቅም እያገኙ እነርሱም ቀሪ ህይወታቸውን ማጣጣም ተያይዘውታል፡፡ በህይወት ለሚገኙ ኢህአዴግ ታጋዮች ፍሬው የእነርሱ በህየወት መትረፍ ሆኖወል፡፡ የሰመሃታቱን ቃል ኪዳን መብላት ግንቦት 20 ፍሬ ነው፡፡
የዛሬን ግንቦት 20 ለሃያ ሶስተኛ ጊዜ ተከብሮዋል፡፡ ዋና የቡድን መሪያቸውን አጥተው እውር ድንብር መሄድ ከጀመሩ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ያከበሩት ኢህአዴጎች ዛሬም ሃሳብን በነፃነት መግለፅን ማረጋገጥ አልቻሉም፡፡ ከዚህ በኋላ ስንት እንደሚቆዩ አይታወቅም፡፡ ለዚህ ነው ስንት ይቆዩ ይሆን ብዬ መጠየቅ ያማረኝ፡፡ ኢህአዴግ በእርግጥ የተሳካለት ይህን መብት መረጋገጡ ላይ ነው፡፡ በህገመንግሰት ውስጥ ወርቃማ ነፃነቶችን ለማስቀመጥ ያልፈራው ኢህአዴግ በጠመንጃ ለማነጋገር ከተዘጋጁት ይልቅ በብዕራቸው ጉድለቱን ሊያሳዩት የሚጥሩትን ጋዜጠኞች ዓይናችሁን ላፈር ብሎ እያሳደደ ነው፡፡ ኮምፒዩተር ላይ ቁጭ ብለው ሃሣባቸውን በነፃነት እዚህ ግባ ለማይባል ማህበራዊ ገፅ ተጠቃሚ ስላካፈሉ ብሩዕ ተሰፋ ያላቸውን ወጣቶችን እስር ቤት ያጉራል፡፡ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሽት ታዬ፣ እስክንድር ነጋ አንድም ጥይት የላቸውም፡፡ የሚያስገርመው ጠመንጃ ከያዙት ይልቅ ግን ገዢውን ፓርቲና መንግሰትን ያርበደብዱታል፡፡ “ዞን ዘጠኞች” በምን መለኪያ ነው ብጥብጥ የማስነሳት አቅም ያላቸው፡፡ የእነሱ አቅም የነበረው ሃሣብን በነፃነት ገልፆ በሰላም መተኛት ነው፡፡ ለነገሩ እነርሱም ወደ ሌላ ዞን ተዛወሩ እንጂ ሀገሪቱ እራሷ እስር ቤተ መሆኗን ለማመላከት ነው “ዞን ዘጠኝ” ብለው እራሳቸውን የሰየሙት፡፡ ኢህአዴግ እነዚህ ወጣቶች በሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ብለው ስለተንቀሳቀሱ እስር ቤት አጎራቸው፡፡ በተቃራኒው ግን እነዚህ ወጣቶች በየካፍቴሪያው ተጎልተው ቢውሉ፣ በየጫት ቤቱ ሺሻ ሲያጨሱ ቢውሉ እና ዲቪ ሲሞሉ ወይም ከሀገር መውጫ መንገድ ሲቀይሱ ቢውሉ፣ ስለዚህች ሀገር አያገባንም ብለው ቢጦምሩ ጫፋቸውን አይነካም፡፡ ዝንባቸውን እሽ አይልም ነበር፡፡ የግንቦት 20 ፍሬያችን ከሃያ ሶስት ዓመት በኋላ ያገኘነው በግልፅ በህገ መንግሰት የተደነገገን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የማይከበርበት ስርዓት መገንባት ነው፡፡ የስርዓት ለውጥ ብቻ፡፡ ከደርግ ወደ ዳግማዊ ደርግ በመጀመሪያው ዘመናቸው ቡድናዊ አንባገነንነት፡፡ በኋላም ወደ ግለሰብ አንባገነንነት ማለትም ከመንግስቱ ሀይለማሪያም ወደ መለስ ዜናዊ መሸጋገር ነው፡፡ይህን ኢቲቪ ሊያሳየን አቅም የለውም፡፡ ተከፋይ የድህረ ገፅ ተሳዳቢዎችም አይሞክሯትም ለምን ቢባል እንጀራ ነው፡፡
ግንቦት 20 እንደ መሰከረም 2 ወደ መቃብር እንዳይወርድ በቀጣይ የሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ባህል ይሆን ዘንድ ግን ኢህአዴግ አሁንም እድል አለው፡፡ ሃያ ሶስት ዓመት ዘግይቶም ቢሆን ሰመዓታቱን ሊያስከብር የሚችለውን የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥን የዲሞክራሲ ስርዓት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው፤ ይህንንም ለማሳካት እኛ ሰላሣ እና አርባ ዓመት መግዛት አለብን የሚለው ተረት ተረት ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን በዚህች ሀገር ሌላ አብዮት የሚጠራ ገፊ ምክንያት ነው፡፡ ይህ አብዮት ሲመጣ ደግሞ መሰከረም ሁለት እንደተፈነገለው ግንቦት 20 ይፈነገልናል ሌላ ከዓመቱ አንድ ቀን ሌላ የድል የለውጥ ቀን ይመጣል፡፡ ለዲሞክራሲ ለፍትህ ሲባል ሰማዕታት ለሆኑት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሲባል ግንቦት 20 የድል ቀን ሊሆን የሚችልበት እድል ያለው በኢህአዴግ እጅ ነው፡፡ በማንኛውም ምክንያት ኢህአዴግ በክብር ሳይሆን በውረደት ከወደቀ ግንቦት 20 የዓመቱ አንድ ቀን ከመሆን አልፎ የድል ቀን ሆኖ ሊከበርበት የሚችልበት አንድም ምክንያት አይኖርም፡፡ አሁን ባለው ሁኔት ያለፉት 23 ዓመታት ለኢህአዴጋዊያን የድል ቀን ሲሆን ለእኛ እንደማነኛውም የዓመቱ አንድ ቀን ሆኖ ተገደን ከሰራ የምንቀርበት ቀንም ጭምር ነው፡፡ እንደ አሁኑ ደግሞ አርብ ቀን ሲውል ለረዥም የሳምንት መጨረሻ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል እንጂ በመጀመሪያው ግንቦት 20 ጠዋት የሰማነውን ለህዝብ ጥቅም ሲባል የተሰራ አንድም ድል አይሸተኝም፡፡
ዐፄ ሀይለስላሴ ሰማኒያኛ የልደት ባህላቸውን፤ ደርግ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዮት ያቀረበለትን የስልጣን ይልቀቁ ጥያቄ ገፍተው እንደተዉት ሁሉ ኢህዴግም እሰከ ዛሬ ካሳለፋቸው እድሎች በተጨማሪ መቼ እንደሆነ በቅርብ ባይታወቅም እሩቅ ባልሆነ ጊዜ እድሉን ገፍቶ ይጥለዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከዋናው የቡድኑ መሪ መለስ ዜናዊ እልፈት በኋላ ለረዥም ጊዜ በሴራም በእውቀትም የሚመራው ሰው ያለው አይመስለኝም፡፡ ይህ ግን ከግምት በላይ ነው፡፡ ወንበሩን የወሰዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን ፍንጭ አላሳዩንም ይልቁንም ሌጋሲ ማስቀጠል በሚል የወይን ፋብሪካ ምረቃን ጨምሮ ተቀባይነት የሌላቸው በምረቃ ስራ ተጠምደው መዋላቸው ለሌላ ሰትራቴጂክ ሰራ ጊዜ እንደሌላቸው የሚያሳብቅ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ደምረን ስናይ ግንቦት 20 እንደ መስከረም 2 ሳይዋረድ ከመለስ እልፈት በኋላ ስንት ዓመት ይቀጥላል? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግንቦት 20 በግራዋ ዛፍ ላይ የበቀለ መራራ አፕል ነው፡፡
ቸር ይግጠም!!!!
ግርማ ሠይፉ ማሩ

No comments:

Post a Comment