ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
የጣና ሀይቅ የጎንደር ነው ወይስ የጎጃም? የሚል የይገባኛል ጥያቄ
እንዳለ ያወቅሁት በደርግ የመጨረሻ ዘመን ምስራቅ ጎጃም እና ምዕራብ ጉጃም የሚል የአሰተዳደር አካባቢ የተመሰረተ ሰሞን ነው፡፡
በዚያን ጊዜ ጢስ አባይ ፏፏቴን ለማየት እየሄድን እያለ አብሮን ያለው ጎንደሬ ጓደኛችን አካባቢው የጎንደር መሆኑን ለማረጋገጥ ማየት
ያለብን እረኛውን መሆኑን ነገረን፡፡ እረኛን አይቶ መሬቱን የጎንደር ወይስ የጎጃም ተብሎ እንዴት ይለያል ብለን በአግራሞት ተመለከትነው፡፡
እረኛው የሚጠብቃቸው በጎቹ እረኛቸውን ተከትለው የሚሄዱ ከሆነ ጎንደሬዎች ናቸው አለን፡፡ እንዳለንም በጎቹ እረኛውን ተከትለው ሲሄዱ
ተመልክተን፡፡ ፈጠን ብዬ ሄጄ እረኛውን ጎንደሬ ነህ ወይስ ጎጃሜ? ስለው ጎንደሬ ነኝ አለኝ፡፡ ታዲያ አሁን ይህ አካባቢ ጣናን
ጨምሮ ምዕራብ ጎጃም ተባለ ምን ይሰማችኋል? ብዬ ጥያቄ አሰከተልኩበት፡፡ እረኛው ለዕድሜ ልኬ የሚሆን ትምህርት ሰጠኝ፡፡ “ዋ!
ውሃም መሬቱም እዚሁ ድሮ ያለበት አይደለ?” አለኝ በሚያስደንቅ ፍጥነት፡፡ የተማረው ጓደኛዬ የጎንደር መሬትና ውሃ ለጎጃም ተሰጠ
ብሎ ሲብሰለሰል እረኛው ችግር የለም የት ይሄዳል ብሎ ከተማረው ጓደኛዬ የተሻለ መልስ ሰጠኝ፡፡ የጎንደር መሬት ለትግራይ ተሰጠ
የሚለውን የክልል ድንበር ችግር ብዙም ሰሜት የማይሰጠኝ የትም ቢሆን መሬቱ በኢትዮጵያ ግዛት ክልል በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ይህ የጎንደር
እረኛ ያስተማረኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእረኛ ለመማር ዝግጁ ከሆነን ማለቴ ነው፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያዊነቴ እንጂ በዘር ተቆጥሮ
የሚሰጠኝ መሬት ስለማልፈልግ ነው፡፡ ወደዚህ ትዝታ የመረኛ በቅርቡ በአዲስ አበባ እና ፊንፊኔ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ
ማስተር ፕላን አስመልክቶ ደም አፋሳሽ ድጋፍና ታቃውሞ መነሳቱ ነው፡፡
የከተማ ኮንስትራክሽን እና ቤቶች ሚንሰትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ ለምክር
ቤት ቀርበው ሪፖርት ሲያቀርቡ ይህን ጉዳይ በሚመለከት “የአዲስ አበባና
ፊንፊና ዙሪያ ከተሞች የተዘጋጀው የተቀኛጀ ፕላን ዝግጅት ይህን ያህል ጫጫታ የፈጠረው የኢህአዴግ ፖሊሲ ውጤት ነው ብለው ያምናሉ?
መቼም ይህን ጉዳይ በተቃዋሚዎች አያሳብቡም” የሚል አሰተያየት
አዘል ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ሚኒሰትሩ መልስ ሲሰጡ ለልማት በጋራ መቆም እንዳለብን ገልፀው በአሁኑ ጊዜ እገሌ ነው ጥፋተኛ ማለት
ተገቢ እንዳልሆነ ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዕይታ መነፅር ውስጥ መሆናችንን በመጥቀስ በተፈጠረው ሁኔታ ደሰተኛ
እንዳልሆኑ የሚገልፅ ሰሜታቸውን መደበቅ ተሰኖዋቸው ነበር፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ከቅላፂያቸው ተቃዋሚን ለመከሰስ ፍላጎታቸውን መረዳት
አያሰቸግርም ነበር፡፡ በእኔ እምነት ለዚህ ለተነሳው ተቃውሞ መንስዔዎች የኢህአዴግ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
አሁን በዩኒቨርሲት የሚገኙት ወጣቶች በሙሉ ማለት ይቻላል የኢህአዴግ
ትውልዶች ናቸው፡፡ በኢህአዴግ የትምህርት ፖሊሲና አጠቃላይ ፖሊሲ አቅጣጫ ኢትዮጵያዊነትን እያኮሰሰ ጎጠኝነትን እያሞገሱ የመጡ ናቸው፡፡
የኦሮሚያ ልጆች ከክልላቸው ወጥተው ከሰሜን እሰከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ተቀጥረው መስራት እንዲሁም ኢንቨስት አድርገው
ቀጣሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አልተማሩም፡፡ አብዛኛዎቹ ክልሎችም እንደዚሁ ናቸው፡፡ በተለየ ሁኔታ ይህ እየተመቻቻላቸው ካሉት በስተቀር፡፡
ይህ በኢህአዴግ አገላለፅ ጠባብነት የሚለው ሲሆን የዚህ ምንጩ ደግሞ እራሱ የኢህአዴግ ፖሊሲ ነው፡፡ እነዚህ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች
ከዚህ አሰተሳሰብ ተነስተው የአዲስ አበባ መሰተዳድር ከፊንፊኔ ዙሪያ ከተሞች ጋር የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተዘጋጀ ሲባሉ የእኛ የሚሉት
የኦሮሚያ መሬት የእኛ በማይሏቸው ሌሎች ኢትዮጵያዊያኖች መሬታቸው የመቀማት ስሜት ቢያድርባቸው ልንፈርድባቸው አይገባም፡፡ ልክ ናቸው
ማለት ግን አይደለም፡፡ የዛሬዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የወደፊት ሀገር ተረካቢዎች ጢስ አባይ ፏፏቴ ዳር ከሚገኘው እረኛ ባልተሻለ
ደረጃ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የኢህአዴግ የትምህርት እና የፖለቲካ ስርዓት በትውልድ ገዳይነት መጠየቅ ካለበት አንዱ በዚህ መሆኑ መታወቅ
አለበት፡፡ አቶ መኩሪያ የዚህ ስርዓት አሰፈፃሚ ሰለሆኑ ጥያቄዬን ለመመለስ በመረጡበት አግባብ ወደፊት ታሪክ ይፈርደናል ብለዋል፡፡
ለታሪክ ፍርድ እንዲመች እነዚህን ጥያቄዎች እናንሳ፡፡ በትግራይ ክልል ስንት ኦሮሞ ኢንቨሰተሮች አሉ? በኦሮሚያ ስንት ትግሬ ኢነቨሰተሮች
አሉ? ብለን ብንጠየቅ መልሱ ግልፅ ነው፡፡ በጋምቤላ ውስጥ ካሉት ኢንቨሰተሮች ምን ያህል ኦሮሞዎች አሉ? ለነዚህ ጥያቄዎች የሚገኘው
መልስ ግልፅ ነው፡፡ ከነዚህ ጥያቄዎች የሚገኘው መልስ የተሳሳቱ የኦሮሞ ብሔረተኞች ኢትዮጵያ የጋራችን እንዳልሆነች የሚያደርጉት
ቅስቀሳና ተግባር መገለጫ ነው፡፡ የኦህዴድ ጎምቱ ባለስልጣናት ትልቁ ግባቸው በፌዴራል ስልጣን ወይም ኦሮሚያ ብቻ ነው አማራጫቸው፡፡
ልጆቻቸውን ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጭ እንዲኖሩ አድርገው እያዘጋጁ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኢህአዴግ ያስተማራቸውን ብሄረተኝነት ልክ መስሎዋቸው
ይሁን ወይም በማነኛውም ምክንያት የፈለጉትን ሃሣብ የመደግፍና የመቃወም መብት አላቸው፡፡ ይህን መብታቸውን በስላማዊ መንገድ እስከገለፁ
ድረስ ኢህአዴግ የሚውስድው የግድያ፣ እስር፣ ከትምህርት የማፈናቀልና የማፈን ተግባር በምንም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው መታወቅ
ይኖርበታል፡፡ አሰቀያሚው የመንግሰት ምክንያት ደግሞ የተገደሉት ባንክ ሲዘርፉ ነው መባሉ ነው፡፡ሰዎች ከሚሞቱ የአምቦ ባንክ ቢዘረፍ
ይሻል ነበር፡፡ ዜጎች የተሳሳተ ሃሳብንም ቢሆን የመደገፍ መብት የግል ውሳኒያቸው መሆን አለበት፡፡ ከተሳሳተ መንገድ መመለሻው መንገድም
ውይይትና የሃሳብ ፍጭት እንጂ በጠመንጃ የሚታገዝ ጡጫ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ ዓይነት የግጭት አፈታት ሰልት እንዲሁም
የእኔ ብቻ መንገድ ልክ ነው ከሚል አሰተሳሰብ መውጣት ለዚህች ሀገር ትንሳዔ አንድ እርምጃ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ገድለው
ሲያበቁ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች መፅናናትን መመኘት ሌላ አቁስል የሆነ ሰልቃ ነው፡፡
የኢህአዴግ መንግሰት ምን ታይቶ እንደሆነ ባይታወቅም የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ከእራሱ የኦህዴድ/ኢህአዴግ
አባላትን ጨምሮ በኦሮሚያ ስም የተደራጀን ፓርቲ ነን የሚሉ በሙሉ ተቃውመውታል፡፡ ለተቃውሞው መነሻ በእርግጥ የህዝብ ጥቅም ከሆነ
ህዝብ የሚጠቀመው እነዚህ ከተሞች ተቀናጅተው በጋራ ተመጋግበው ለማደግ ሲወሰኑ ብቻ ነው፡፡ አሁን ያለው ዓለም አቅፍ ተሞክሮ በአንድ
ሀገር ክልል አይደለም በሁለት ሉዓላዊ ሀገሮች ማዕክልም የጋራ የመልማት ሰትራቴጂ የግድ የሚል ሆኖዋል፡፡ የኢህአዴግ የተቀናጀ ልማት
ስትራቴጂ ምፀት የሚመስለው በኦህዴድ ጋሻ ጃግሬነት የተገነባው የጠባብነት መገላጫ “አኖሌ” ሀውልት ምረቃ ማግሰት መሆኑ የኢህአዴግ
ዘላቂ ሰትራቴጂው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሰር ማሰተባበር ይሁን ማለያየት ግልፅ አለመሆኑ ነው፡፡ ኢህአዴግ ግራ ገብቶት ግራ የሚያጋባ
ሰርዓት ነው፡፡
በህገ መንግሰት ድንጋጌ አዲሰ አበባ በኦሮሚያ ክልል ዙሪያ መገኘቷን
ተቀብሎ አዲስ አበባና ኦሮሚያን በሚያሰተሳሰሩ ጉዳዮች ኦሮሚያ ልዩ
ጥቅም እንደምታገኝ እና ይህም በህግ እንደሚወሰን ተደንግጎዋል፡፡ የኦሮሚያን ክልል ተጠቃሚነት በተሻለ ማረጋገጥ የሚችላው
የመስረተ ልማትና ሌሎች ሰትራቴጂክ ትብብሮች ማሰብ ካልተጀመረ የኦሮሞን ህዝብ እንዴት ለመጥቀም እንደሚታሰብ አይገባኝም፡፡ በኦሮሚያ
ጉዳይ ላይ ለጊዜውም ቢሆን ወሳኝነት ያለው ኦህዴድ ሁል ጊዜ ሀገራዊ ዕይታውን በጠባብነት ሰሜት (በተሳሳተ ያለን በቂ ነው በሚል
ትልቅነት መኮፈስ) የተጀቦነ ነው፡፡ ለምሳሌ የግል የፋይናንስ ድርጅቶችን ለመገዳደር ከመንግሰት ባንኮች በተጨማሪ በክልል መንግሰታት
የሚታገዙ “የግልባንክ ተብዬዎች” ተቋቁመዋል የእዚህን ባንኮች ሰያሜ ስንመለከት የአማራ ክልል ድጋፍ ያለው “አባይ ባንክ” አማራ
ባንክ የሚል አማራጭ ቀርቦ ውድቅ መደረጉን በመድረኩ ላይ ከነበሩ ሰዎች ሰምተናል፣ ትግራይ ክልል እንደ ሁሌም ትግራይ ባንክ በአሳባቸውም
አልመጣም “አንበሳ ባንክ” ነው ያሉት፡፡ በተመሳሳይ የደቡብ ክልልም “ደቡብ ግሎባል ባንክ” ይበል እንጂ ጉራጌ፣ ሲዳማ ወይም ወላይታ
ለማለት አልፈለጉም የደቡብ በራሱ የዚህ ዓይነት ሰያሜ ለመስጠት አስቸጋሪ መሆኑ ሳይዘነጋ ማለቴ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ስትራቴጅስቶች
ግን “ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል” በማለት ከአዲሰ አበባና ከኦሮሚያ ውጭ የመንቀሳቀስ እድሉን የሚያጠብ ጠባብ ውሳኔ ወሰኑ፡፡ ኦሮሚያን
ሊገልፅ የሚችል ሌላ ተራራ፣ ወንዝ፣ ታሪካዊ ቦታ ወይም የገበያ መስፋፋትን የማይገድብ ስያሜ የሌለ ይመስል ማለቴ ነው፡፡ የኦሮሚያ
ስትራቴጂስቶች በዚህ ደረጃ ሲሳሳቱ በኢህአዴግ ዘመን በጠባብ ብሔረተኝነት ያደጉት ወጣቶች የተቀናጀ እቅድ ቢቃወሙ ሊገርመን አይገባም፡፡
ኢህአዴግም የዘራወን እያጨደ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡
ዮኒቨርሲቲዎች በፌዴራል መንግሰት ስር ሆነው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን
መሆኑ ቢታወቀም ለዚህ ጉዳይ በተቃውሞ የተነሱት ለምን በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ብቻ ሆኖ? ብሎ መጠየቅም ያሰፈልጋል፡፡
በዚሁ የዘር ፖለቲካ የተነሳ የኦሮሚያ ክልል ልጆች ምርጫቸው በአብዛኛው በክልላቸው እንዲሆን ይፈልጋሉ፣ ከምራቃም በኋላ መመደብ
የሚፈልጉት በኦሮሚያ ክልል ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ለኦሮሞ ልጆች ይጠቅማል ወይ? የኦሮሞ ብሔርተኛ ነን የሚሉ ሁሉ መልስ ሊሰጡበት
የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው በቤቴ የገጠመኝን ታሪክ በአጭሩ ላካፍላችሁ፡፡ የአክሰቴ ልጅ እኔ ቤት እየኖረ
ሰበታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ይመጣል፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ በምርጫ ኦሮሚፋ እና አማርኛ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ኦሮሚፋ
አቀላጥፎ የሚናገረው የአክሰቴ ልጅ አሁንም ኦሮሚፋ ክፍለ ጊዜን እንደመረጠ ሲነግረኝ ለምን? ብዬ ሞገትኩት፡፡ መልሱም “ቋንቋውን
ንቆ የነፍጠኛ ቋንቋ መረጠ ብለው ይጠምዱኛል” ነው ያለኝ፡፡ ኦሮሞ ያልሆኑት የሰበታ ልጆች ምን መረጡ? አልኩት አሰከትዬ፡፡ “እነርሱም ኦሮሚፋ ነው የመረጡት” አለኝ፡፡ ልዩነቱን
አስረዳሁት አማርኛ በደንብ የሚችሉት ኦሮሚፋ ሲመርጡ እነርሱ የወደፊት ዕድላቸውን ወደ ሙሉ ኢትዮጵያ ሲያሳድጉ አንተ ግን እጣ ፈንታህን
በኦሮሚያ ላይ ብቻ አደረከው፡፡ ምርጫው ያንተ ነው አልኩት፡፡ በምርጫው ቀጠለ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲጨርስም ጅማ ዩኒቨርሲቲ
መረጠ፡፡ ጅማ ለስራ ሄጄ ከዩኒቨርሲቲ አሰጠርቼ ከጓደኞቹ ጋር ሳገኘው ሁሉም ጓደኞቹ ኦሮሚፋ ተናጋሪ ናቸው፡፡ አንድ አንዶቹ በፍፁም
አማርኛ የሚጠየፉ፡፡ እነዚህ ልጆች እንዴት አድርገው የኢትዮጵያዊነት ፕሮጀክት ሊጥማቸው ይችላል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞችን በድጋሚ
ልጠይቅ ይህ ተግባር የኦሮሚያ ልጆችን ይጠቅማል ወይ? ለአክሰቴ ልጅና ለጓደኞቹ በወቅቱ የነገርኳቸው መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን የሚመራው
ከትግርኛ አሰበልጦ ወይም እኩል አማርኛ ስለሚናገር ነው፡፡ በኢትዮጵያችን የኦሮሞ ልጆች ትልቅ የሚባለውን ቦታ ለማያዝ አማርኛን
መጠየፍ የሞኝ ምርጫ ነው ነበር ያልኳቸው፡፡
በተመሳሳይ የኦህዴድ ካድሬዎች የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ
ከተሞች የተቀናጅ ማስተር ፕላንን ለምን ተቃወሙት? የሚለውን መመርመር ይኖርብናል፡፡ እነዚህ ከተሞች በፈራቃ ካድሬዎች እየተመደቡ
የድርሻቸውን የሚመዘብሩበት፣ ሲበቃቸው በዝውውር ስም የሚነሱበት እና ካድሬው ሁሉ ተራ ቢደርሰኝ ብሎ የሚጠብቅባቸው መሆናቸው አንዱ
ነው፡፡ የተቀናጃ ማስተር ፕላን የሚባለው ይህን ዕድል ሊዘጋ ይችላል፡፡ ምን አልባትም በካድሬነት ሳይሆን በእውቀት የሚተገበር ሊሆን
ስለሚችል ፍርሃታቸውን በህገ መንግሰት ይቃረናል በሚልና ለህዝብ መፈናቀል ይፈጥራል በሚል የሸፍጥ ሽፋን ነው የሚቃወሙት፡፡ እነዚህ
ካድሬዎች መቼ ነው ስለ ህገ መንግሰትና የህዝብ ጥቅም ቆመው የሚያውቁት? አሁን ግን ለግል ጥቅማቸው ህዝብና ህገ መንግሰትን ከለላ
አድርገው ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡ ተማሪዎችን ከለላ አድርገው፡፡ ለማነኛውም የካድሬ ተቃውሞ አንዴ ተጠርቶ እሰኪገመገም እና ከዚህ
በፊት የሰራውን ወንጀል እስኪያስታውሱት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይታገሳል፡፡ በተቃወመበት አፉ ውዳሴ ሲያወረድ በቅርቡ እንሰማለን፡፡
አሳዛኙ ግን ምንም ውስጥ የሌሉትን፣ በጠባብ ብሔረተኝነት ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች ለአደጋ እንዲጋለጡ ማድረጋቸው ነው፡፡ የመንግሰትንም
ትዕግሰት አልባነት የሚያጋልጥ ድርጊት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡
ለማነኛውም የአዲስ አበባና በዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ
ልማት ብዙ ነገር እንድንማር የሚያደርግ ነው፡፡ ኢህአዴግ ዜጎችን በኢትዮጵያዊነት እና በብሔረተኝነት የማሰተባበር ፈተና ውስጥ መውደቁን፤
የዘራው የጠባብ ብሔረተኝነት ፖሊሲ በተለይ በኦሮሚያ ነብስ ዘርቶ ለእድገት እንቅፋት መሆኑን፤ ቋንቋ መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም
ወደ ፊትም ከዚህ ዓይነት ችግር የሚላቀቅ እንዳልሆነ፤ ወዘተ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ኦህዴዶች የኦሮሞ ልጆች በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኤኮኖሚም
ሆነ ማህበራዊ ግንኙነቶች የላቀ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረጋቸውን በዚህ አጋጣሚ ልናስታውሳቸው ይገባል፡፡ የኦሮሞ
ልጆች ጠቅላይ ሚኒሰትር ለመሆን መዘጋጀት ይኖርባቸዋል …… ፕሬዝዳንት መሆን ይበቃቸዋል፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!
No comments:
Post a Comment