Saturday, May 3, 2014

ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር እውነትን እናክብር …..



ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
አቶ ሀይለማሪያም ደሣለኝ ሪፖርታቸውን ካቀረቡ አስር ቀን የሆናቸው ቢሆኑም ያነሱዋቸው ጉዳዮችና መልስ ለመስጠት የመረጡት መንገድ እሰከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ ለማሳሳቻነት ለመጠቀም የኢህአዴግ ድምፅ ሆነው ስለሆነ የተናገሩት ወደፊትም በተደጋጋሚ የምንወያይበት አጀንዳ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ብዙ ሰዎች የዋህ ፖለቲከኛ ያደርጉኛል፡፡ ለምን ሲባል? እኔም ብሆን ሌሎች ለእውነትን መቆምን መርዕ ማድረግ አለብን ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ፖለቲካ ሽፍጥ እና ሴረኛነትን የሚጠይቅ ነው ብለው ስለሚያምኑ እውነትን ደግሞ ከዚህ ሰፈር ማገኘት ስለማይቻል የሚባል ስምምነት የተደረሰበት እስኪመስል ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ፖለቲከኛ መሆን የሚፈልግ የጆርጅ ኦርዌልን መፅሃፍ አንብቦ የገባው መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱም ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ አለበት ብለው የሚያምኑም ብዙ ናቸው፡፡ ይህን ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አቶ ሀይለማሪያም በሪፖርታቸው መነሻ ለቀረበላቸው መልስ የሚሰጡት ከእውነትም ከእውቀትም ሲዛነፍብኝ ለምን? የሚል ጥያቄ ስለ አጫረብኝ ነው፡፡ ፖለቲከኝነት ለሀሰት ለመገዛት ከእውነት ለመራቅ ለምን ከለላ ይሆናል፡፡
በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒሰትሩን ለማናደድ አስቤ ጥያቄ አላቀረብኩም፡፡ ይህን ሃሳቤን በመግቢያዬ ላይ ለመጥቀስ ሙከራ አድርጌየለሁ፡፡ ለሙገሳ የሚሆን ቃላቶች መደርደርም ፍላጎቴም ዓላማዬም ሰለአልሆነ አላደረኩትም፣ አላደርገውም፡፡ እኔ እንዲታወቅ የፈለኩት እርሳቸውም ከፈለጉ በመረጃ አስደግፈው እውነት እውሽት ብቻ ሳይሆን መረጃ እንዲሰጡ እና ህዝብ በቀጥታ በሚተላለፍ ሚዲያ የሚከታተል ስለሆነ ፍርድ እንዲሰጥ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ህዝቡ ፍርድ ለመስጠት እንዳይችል አሳስተው ማለፍ የፈለጓቸውን ነጥቦች ብቻ በማንሳት አሁንም ጉዳዩን ለአንባቢ ፍርደ መተው መርጫለሁ፡፡
በኢህአዴግ የሚመራው መንግሰት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያሰቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት ነው ቃል የገባው እንጂ ከ2003 እሰክ 2007 ዓመተ ምህረት ድረስ በሰራ ላይ ልምምድ የማደርግበት ነው ያለ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ከ1983 እስከ 1993 የልምምድ ጊዜያቸው፣ አቶ ሀይለማሪያምን ባይጨምርም በተልዕኮ መማሪያቸው ነበር፡፡ አሁን አቶ ሀይለማሪያም እያሉ ያሉት የአዲስ አበባውን ሳይጨምር 2395 ኪሎ ሜትር የባቡር ሀዲድ ለመዘርጋት እና ሰራ ላይ ለማዋል አቅደን ነበር፤ ይህን ስናቅድ ልምድም ገንዘብም አልነበረንም፡፡ ሰለዚህ ይህ እቅድ በዚህ የዕቅድ ዘመን አይሳካም ነው ያሉት፡፡ በእቅዱ ዘመን መጀመሪያ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክት የመፈፀም ክህሎትም ሆነ ፋይናንስ አቅም የለም ብለን ነው ዕቅዱ ላይ አስተያየት የሰጠን ሰዎች የተናገርነው፡፡ የዛን ጊዜ እኛ የዚህ ዓይነት ሃሳብ ስናነሳ ጨለምተኞች ተባልን፡፡ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጥረታችንን ከማድነቅ አልፋችሁ በኪሎ ሜትር ልትመዝኑን አትችሉም የሚል ዘለፋ አዘል መልስ መስጠት ምን አምጣው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር እንዲረዱልኝ የምፈልገው እቅድ የሚገመገመው ባሰቀመጡት መለኪያ ነው፡፡ የባቡር ሀዲድ ዕቅድ አፈፃፀም የሚመዘነው በቅድሚያ በዕቅዱ ላይ በተቀመጠው መለኪያ ነው፡፡ ይህም በተዘረጋው የባቡር ሀዲድ መስመር ነው፡፡ መልሶን በቀጣይም በዚሁ መስመር ማድረግ ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡ ካልሆነ ዕቅዱ መቀመጥ የነበረበት “የባቡር መስመር ለመዘርጋት አቅም ግንባታ” ተብሎ ለዚህም ምን ያህል የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የቁሳቁስ ዝግጅት እንደሚደረግ ብቻ ነበር፡፡ ይህ በእውነቱ ሲጀመር የሟቹ አሁን ደግሞ የእርሶ ኃላፊነት ነው፡፡ ሃላፊነቱን የወሰዱት ደግሞ ከነሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ጋር ሰለሆነ ከኃላፊነት መሽሽ አይቻልም፡፡
በተመሳሳይ በኤሌትሪክ ኃይል ዘርፍ 10 ሺ ሜጋ ዋት እናመነጫለን የሚል ግብ እንጂ ይህን ለማመንጨት የሚችል አቅም ይኖረናል የሚል አይደለም፡፡ ከ2007 በኋላ የሚመነጭ ኃይል በሙሉ ለቀጣዩ ዘመን የሚያልፍ ነው፡፡ ግልገል ጊቤ ሶሰት ካለፈው ዓመት የዞረ ነው፡፡ ለነገሩ የዚህ ዓይነት ማጭበርበር በኢህአዴግ ሰፈር የተለመደ ነው፡፡ በ2002 ምርጫ ውድድር ጊዜ ማመንጨት ያልጀመረ ፕሮጅክቶች ተደምረው ከሶሰት ሺ በላይ ደረሰናል ሲባል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይህ ማጭበርበር ግን በፍፁም እንዲደገም መፍቀድ የለብንም፤ ደጋግመን በቁጥር ማጭበርበር ይቁም ብለን እንሞግታለን፡፡ በነገራችን ላይ ግልገል ጊቤ ሶሰት በሚቀጥለው ዓመት ሰራ ይጀምራል? ወይስ አይጀምርም? ሚዲያዎች አይጀምርም እያሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖረት ይጀምራል ይላል፡፡ ይህን ጥያቄ ለምን ዘለሉት? መልሱ ስለማይጀምር ውሃ ስለማይሞላ ነው፡፡ ሰለዚህ በሁለት ሺ ሰባት መጨረሻ 10 ሺ ተብሎ ከታቀደው በእርግጥ 4000 ሜጋ ዋት ይኖረናል? ሌላ ጥያቄ ነው፡፡
በቤቶች ዘርፍ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ሰሜታቸውን ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነገር ግን ብስጭታቸው ለሁሉም ግልፅ ሆኖ የወጣበት መልስ ስጥተዋል፡፡ በ1996 ከ450 ሺ በላይ ሰዎች ለኮንዶሚኒየም ቤት የተመዘገቡ ሲሆን እነዚህ ተመዝጋቢዎች ሙሉ በሙሉ ቤት ሳያገኙ አግኝተዋል ማለት ለምን አስፈለገ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባመኑት 190ሺ ቤቶች ተገንብተው በዕጣ ለደረሳቸው እድለኞች፣ በመልሶ ማልማት ለተነሱ፣ በከንቲባዎች እና ሌሎች ሹሞች ትእዛዝ፣ እንዲሁም ለገዢው ፓርቲ ባለሟሎች ቤቶች ተሰጥቶዋል፡፡ ከዚህ ውሰጥ 100 ሺ ለተመዘገቡ ባለ ዕድለኞች ተሰጥቶዋል ብንል ቀሪው 350 ሺ ዕድለ ቢሶች ከአዲሶቹ ጋር በድጋሚ እንዲመዘገቡ ተገደዋል፡፡ እነዚህ ዕድለ ቢሶች በጠቅላይ ሚኒሰትሩ ግምት ለቀጣይ አሰር ዓመት እድላቸውን በድጋሚ እንዲሞክሩ ነው፡፡ በአዲሱ ምዝገባ የተመዘገቡት ከ850 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ከቀድሞ ተመዝጋቢዎች ልዩ የሚያደርጋቸው የቀድሞ ተመዝጋቢዎች እድል ሲደርሳቸው ገንዘብ ማፈላለግ እንጂ ቀድመው ማጠራቀም አይጠበቅባቸውም ነበር፡፡ አዲሶቹ ተመዝጋቢዎች በየወሩ በመቆጠብ እድላቸውን መጠበቅ የግድ ይላቸዋል፡፡ እነሱ በተሰፋ ቤት እየጠበቁ በሚቆጥቡት ሀብታም እንዲሁም መንግሰት ተበድሮ ይስራበታል፡፡ የእኔ ጥያቄ ከቁጠባቸው “ተገቢውን” ትርፍ ቤቱን እሲኪያገኙ የሚያገኙበት መንገድ መፈለግ ይኖርበታል፤ ባንክ ከማስቀመጥ በተሸለ ማለቴ ነው፡፡ ያለበለዚያ ይህ ቁጠባ ድሃውን የበለጠ የሚያደኽይ ነው የሚል እምተነት ነው ያለኝ፡፡
በዓለም ላይ የዛሬ አስር ዓመት ቤት ለማግኘት ብሎ የሚቆጥብ የለም፡፡ የቤት ልማት ፕሮጀክት ግን ልክ ነው የአምሳ ዓመትም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ እየኖሩ “ሞርጌጅ” ይከፍላሉ እንጂ ውጭ ሆነው ለቤት ብለው አይቆጥቡም፡፡ አንድ አንድ ልባም ተማሪዎች ከተማሪ ቤት እንደወጡ ቤት ለመግዛት ሲሉ እንዲህ ዓይነት ቁጠባ በቤተሰብ ወይም በግል ቁጠባ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ አቶ ሀይለማሪያም እንዲሁም እርሳቸው የሚመሩት ፓርቲ ያልገባቸው አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ አንድ ድሃ ቆጥቦ ሀብታም ይሆናል የሚል አስተሳሰብ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ሕዝቡን እንዲህ እያሉ ማሳሳት ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሣሌ ብር 5000 የሚያገኝ ሹም ለሃያ ዓመት ሙሉ ቢቆጥብ በእድሜው መጨረሻ የሚኖረው ብር 1.2 ሚሊዮን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ገንዘብ የዛሬ አስር ዓመት ሀብታም መባል አይቻልም፡፡ የሀብት ምንጭ አዲስ ሃሳብና አሰራር ይዞ ፋይናንስ ተቋማት እና ፋይናንስ ማድረግ ከሚችሉ ግለሰቦች ጋር መገናኘት ነው፡፡ ቆጥቡና ሀብታም ትሆናላችሁ ብሎ ድሃውን የእልም እንጀራ ማብላት ቢቆም ጥሩ ነው፡፡ መቆጠብ ጥሩ ነው፡፡ ሀብታም ለመሆን ግን አይደለም፡፡ የባንኮች ስራ አንዱ ድሃ ቆጣቢዎችን ከሀብታም ተበዳሪ ኢንቨስተሮች ጋር በጥንቃቄ ማገናኘት ነው፡፡
ይህን ሁሉ ክፍተት ተመልክተን አቶ ሀይለማሪያም በምሳሌ ለማሰረዳት እንደሞከሩት ሰምንት ከአስር ያገኘ ተማሪ ሊበረታታ ይገባል ያሉትን ለመውሰድ እንቸገራለን፡፡ ኢህአዴግም ሰምንት ከአስር ስለአላገኘ፡፡ ፈተናውን ተፈታኝ ባያርመው ጥሩ ነው፡፡ ካረመውም ትክክለኛውን ማሪሚያ ቢጠቀም የተሻለ ይሆናል፡፡ አሁን በተሰጠው ማረሚያ መሰረት አምሰት ከአሰርም ማግኘቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ለምሣሌ በባቡር 3 ከአሰር፣ በኢንርጂ 4 ከአስር፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት 3 ከአሰር፣ በጨርቃጨርቅ ቆዳ ኤክስፖርት 1 ከአስር፣ በስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዜሮ ከአስር፤ በማኑፋክቸሪንግ 2 ከአሰር፣ በሰፋፊ እርሻ ልማት 2 ከአሰር፤ ወዘተ ….. ፕሮፓጋንዳውን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ያቀረቡ ዕለት ካሰገረመኝ ነገር አንዱ “አንድነት” የምትለዋ ቃል ከውስጣቸው ፈንቅላ ብትወጣም ማለትም “ግንኙነት” ብለው አሻሽለዋታል፡፡ ከኤርትራ ጋር አንድ ብንሆን ቢባል ችግሩ ምኑ ላይ ነው? የዚህን ያህል ድንጋጤ የፈጠረባቸው ለምን አንደሆነ ግራ ነው የገባኝ፡፡ ለማንኛውም የውስጥ ችግራቸውን የሚያውቁት እራሳቸው ናቸው እና ይገማገሙበት፡፡ ከዚህ ጋር የሚያያዝ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የምትለው ቃል እንዴት እንደተጠላች ሳሰብ ይገርመኛል፡፡ ይህችን ቃል የጠሉ በሙሉ ግለኝነታቸውን አስቀደሙ እንጂ ምንም ሲፈይዱ አላየናቸውም፡፡ በድንበር አካባቢ ስለሚሰጡ ሰፋፊ እርሻዎች በቂ ጥናት አድርጋችኋል ወይ? ለሚለው ጥየቀቄዬ ጥናት እንዳላደረጉበት አምነዋል፡፡ ጥናቱ ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የደራሲ ማሞ ውድነህ መፅሃፍ እንደፋሽን በሚነበብት ጊዜ ጌታ ተቀብለው ትኩረታቸውን ሁሉ መፅሃፍ ቅድሱ ላይ ስለነበር ካልሆነ፣ እስራኤሎች እንዴት አድርገው የእርሻ መሬት እየተከራዩ እስራኤል የምትባል ሀገር እንደመሰረቱ ቢያውቁ ጥያቄዬን በፌዝ አይወስዱትም ነበር፡፡ የጋምቤላ መሬት አሰመልክቶ ከሉዓላዊነት ጋር የሰጡት እጅና እግር የሌለው ማብራሪያ ስለ ጋምቤላ ህዝብ ያነሱት ነገር ሁሉ ግራ ነው ያጋባኝ፡፡ በድንበር አካባቢ ጋምቤላን ለምሳሌ አልኩ እንጂ ዑመራም ሊሆን ይችላል፡፡ ግብፆች በሰፋፊ እርሻ ሰም መሬት ወሰደው እያረሱ በድንበር ከሱዳን ጋር የኢትዮጵያን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ እንቅስቃሴ ብትጀምር ማን ይከለክላታል፡፡ መቼም ለሳውዲ ተሰጥቶ ለግብፅ ለመከልከል ጥናት የላችሁም፡፡ ለመጣ የሚቸበቸብ ከሆነ ቱርክም ከጨርቃ ጨርቅ ውጭ ለጥጥ ብሎ ድንበር ላይ መሬት ቢጠይቅ ይሰጠዋል፡፡ አሁን ማለት የፈለኩት ግልፅ ነው፡፡
በመጨረሻም ክርስቲያኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግብረሰዶማዊነትን በይፋ ላለማውገዝ ዳር ዳር ብለው ሲያልፉት እጅ ጥምዘዛው ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ መረዳት ከባድ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት እንዳልኩት ሁሉ ቴሌ፣ ባንክ የመሳሰሉትን እጃችንን ተጠምዝዘን አናደርግም በመቃብራችን ላይ የምንላቸው መሆን የለባቸውም፡፡ በመቃብራችን ላይ ከምንላቸው አንዱ በሙስሊሙም፣ በክርስቲያኑም ሆነ በዋቄ ፈታ በኢትዮጵያ ምድር ተቀባይነት የሌለውን ግብረሰዶማዊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁሉ የተለየች ብትሆን ግብረሰዶማዊያን የማይፈነጩባት መሬት እንድትሆን መስማማት ይኖርብናል፡፡ በመንግሰት በኩል የዚህ መንሽራተት እና የእጅ ጥምዘዛ ውጤት እንዳመጣ የሚያሳየው በይቅርታ አሰጣጥ ረቂቅ ህግ ውስጥ ምዕረት ከማይደረግላቸው ዝርዝር ውስጥ ገብቶ የነበረው ግብረሰዶማዊነት እንዲወጣ መደረጉ አንዱ ማሳየ ነው፡፡ አንዲህም ሆኖ ግን በተለያየ ምክንያት ለዚህ ፀያፍ ድርጊት በተለያየ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ምክንያት የተጋለጡትን ዜጎች ከዚህ ጉዳት ለመታደግ ጥረት ማድረግ የለብንም፣ የራሳቸው ጉዳይ እንበል ማለቴ አይደለም፡፡ ለመስፋፋትና ለማስፋፋት ግን መሬቱ ጭንጫ መሆኑን ማወቅ ግን ግድ ይላል፡፡ ይህ ነውረኛ ድርጊት ደግሞ በልምምድ የተገኘ እንጂ ተፈጥሮዋዊ ነው ብለው ለሚያሳስቱትም ቢሆን ቦታ እንደሌለ እና የግለሰብ መብት አራማጆች የሆንን ሰዎችም ብንሆን በዚህ ጉዳይ ግልፅ  አቋም ማንፀባረቅ ሊኖርብን ይገባል፡፡ ይህ የኒዎ ሊብራሎች ነው፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

No comments:

Post a Comment