Tuesday, March 29, 2016

የጠቅላይ ሚኒሰትሩ የለበጣ ስብሰባዎች!!!



ጠቅላይ ሚኒሰትር ኃይለማሪያም ሰሞኑን ስራ በዝቶባቸው እንደከረሙ ሁላችን እንረዳለን፡፡ የስራው ውጤታማነት የሚለካው ግን በሚያሰገኘው ፍሬ ነው፡፡ በእኔ  ግመገማ ስራቸው ለውጤት እንዳልሆነ የተረዳሁት ዘግየት ብዬ “ከተቃዋሚ ፓርቲ” ተብዬዎች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከንግድ ማህበረሰብ ቀጥሎም ከምሁራን ጋር ውይይት አድረጉ ሲባል የምር እኚህ ሰው የሚመሩት ድርጅት ልብ ገዛ ብዬ ተሰፋ ማድረጌ አልቀረም ነበር፡፡ ምን ያደርጋል በተመሳሳይ ለህዝብ ግንኙነት ሲባል የሚያደርጉት መሆኑን ያጋለጠ ስብሰባ መጋቢት 14 ቀን 2008 በማድረግ ተስፋዬ አጨለሙት፡፡ የብዙ ሰው ሰሜት እንደሚሆንም ተሰፋ አደርጋለሁ፡፡ ለነገሩ ከሁሉም ጋር የሚያደርጉት ስብሰባ የኢህአዴግ ክፉ መንፈስ የተጫነው ነበር፡፡ ከአቋም ፍንክች እንደማይሉ፣ እነርሱም ሌቦች ሌላውም ሌባ (የመንግሰትና የግል ሌቦች) መሆኑን በሚያስረግጥ መንፈስ የተካሄዱ ናቸው፡፡
ነጋዴዎችን ሰብሰበው ያስተላለፉት የመጨረሻ መልዕክት መንግስት ማሰር ቢፈልግ ሁሉም ከእስር ሊተርፍ እንደማይችል አስጠንቅቀው እና በተቻለ መጠንም አሸማቀው ነው፡፡ መልዕክቱ አሁንም ቢሆን ፀባይ ካሳመራችሁ የምናስረው እስር ቤት ሟቋቋም ድረስ የደረሱትን ብቻ ነው የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትራችን ነጋዴዎች እስር ቤት እንዳላቸው የነገሩን ነገር ብዙ የሚገርም አይደለም፡፡ በእኛ ሀገር አንድ የውጭ ኤምባሲ እስር ቤት እንደነበራው ይውራ ነበር (የኤርትራ ኤምባሲ)፤እፍኖም ይወስድ ነበር፡፡ ይህ ይሆን የነበረው ግን በመንግሰት የደህንነት ሰዎች ድጋፍና ትብብር ጭምር ነው፡፡ በእኔ እምነት አሁንም እስር ቤት ያቋቋመው ነጋዴ የደህንነት ድጋፍ አልነበረውም ብዬ አላምንም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም የትኛው ነጋዴ የት ቦታ እስር ቤት አደራጅቶ ከማን ጋር ይስራ እንደነበር በግልፅ በስም ሊገልፁልን ግድ ይላቸዋል፤ በዚሁ ሁኔታም ክስ ተመስርቶ ማየት እንፈልጋል፡፡ (Name and Shame)፡፡  በዚህ አጋጣሚ ፕሮፌስር መስፍን ይህን አስመልክቶ በፌሰ ቡክ ገፃቸው ላይ ማለፊያ ነገር አስነብበውናል፡፡ የሚገርመው በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ይህ መነገሩ ነው እንጂ፤ አንባገነን ስርዓት ባበት ማንም ይህን ሊያደርግ ይቸላል የሚል ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው በሶማሊያ ብዙ የጎበዝ አለቆች በነጋዴዎች የሚታዘዙ ማሰሪያዎች አሉዋቸው፡፡ ፀጥታም የሚያስከብሩት እነዚሁ የጎበዝ አለቆች ናቸው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ይህ የቀረ አይመሰለኝም፡፡
የነጋዴውን ስብሰባ ጉዳይ ከመቋጨቴ በፊት “ነጋዴ በሙሉ ሌባ ነው” የሚል እንደምታ ያለውን ንግግር ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ሲያደርጉ ነፃነቱ ያለው እና ነፃነቱን የሚያስከብር የንግድ ምክር ቤት ተወካይ ቢኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ እንዲጠይቁ ማስገደድ ባይችል ለወጉ ለማረጉም ቢሆን ጥያቄ ያቀርብ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ነጋዴ ግብር እየከፈለ ያቆማትን ሀገር ሁላችሁም ሌቦች ናችሁ፤ ማሰር ብንፈልግ የሚቀር የለም የሚል መልዕክት ማስተላለፍ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ከጠቅላይ ሚኒስትር የማይጠበቅ ንግግር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንድም ቀን በንግድ ተሳትፈው ስለማያውቅ ነጋዴዎች ትርፍ ለማሳደግ የሚወሰዷቸው የተለያዩ እርምጃዎች በሙሉ “የሌብነት ስራ” ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ህጋዊ የሆነ የታክስ መቀነስ እንቅስቃሴ በትምህርት/በህውቀት (Legal Tax Evation) የተደገፈ መሆኑን የሚነግራቸው አማካሪ የላቸውም፡፡ አማካሪዎች ተብለው የተሰየሙት ተመሳሳይ በመሆናቸው ለውጥ ሊመጣ አይችለም፡፡
ከነጋዴዎች ቀጥለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምሁራን ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ሰምተናል፡፡ ነጋዴዎቹን ሲያነጋግሩ እንደነበረው ሁሉ ከምሁራኑ ጋር የነበረው መንፈስም ያው የኢህአዴግ ክፉ መንፈስ የተጫነው ነበር፡፡ ይህን ስብሰባ ከነጋዴዎቹ ልዩ የሚያደርገው ነገር “ከፈለጋችሁ ፓርቲ አቋቁሙና እንጋጠም” ማለታቸው ነበር፡፡ በእለቱ ስብሰባ የተገኙ ተሳታፊዎች የዋዛ የማይባል ጥያቄ ማንሳታቸውን እኛ አድማጮች ደግሞ በተሰጠው ኢህአዴጋዊ ማብራሪያና ማፈራሪያ ሳይሆን በጥያቄዎቹ መስመር ላይ መሆናችንን ማሳታወስ ግድ ነው፡፡ ምን ማለት ነው? ብሎ ለሚጠይቅ “ይህች ሀገር ነፃነት ያለው ህዝብ መኖሪያ አይደለችም፡፡ ጋዜጣኛም፣ ነጋዴም፣ ፖለቲከኛም፣ ተማሪም፣ ወዘተ በነፃነት የሚኖርበት ሀገር አይደለም፡፡” የሚለውን የምሁራን አስተያየት የምንደግፍ መሆኑን ለመግለፅ ነው፡፡
ከምሁራኑ ስብሰባ ከተሰነዘሩት አስተያየቶች አንዱ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ “ደረታችሁን ነፍታችሁ የምትሄዱት” በሚል ከናይሮቢ ጋር ያደረጉት ንፅፅር ሲሆን ይህ ንፅፅር በምንም መመዘኛ ትክክልም ተገቢም ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እውነቱን ለመናገር ለአንድ ኬኒያዊ የኬኒያ መንግሰት ስጋቱ አይደለም፡፡ እኛ ግን መንግሰታችን ስጋታችን ነው፡፡ በእኛ ሀገር ሀፈና የሚፈፀመው ሊጠብቅን በሚገባ መንግሰት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ እስከ ዛሬ ከሸብርተኛ ቡድን ነፃ የሆነችውን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ስምም ፆታም አልገልፅም ብለው ነገር ግን እስከ አያት ስሟ የነገሩን ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ጉቤቦን በግፍ በማሰራቸው አይደለም፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ደረጃ ለሸብር የደረሰ ሰነ ልቦና ስለሌለን ነው፡፡ ርዕዮትን የፈቷት በግፊት መሆንን ማመናቸው አንድ ነገር ሆኖ፤ በህገወጥ ሁኔታ በእስር እንደነበረች ግን የምንረሳው አይደለም፡፡ (የፍርድ ቤቶች ውሳኔ ልክ ነው ቢባል እንኳን የእስር ጊዜ ጨርሳ አንፈታም ብለው ከህግ ውጭ አስረው ነበር ያስቀመጧት) በኋላ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በግፊት እንደተፈታች ያመኑትን ማለት ነው፡፡
ከላይ የነበሩትን ስብሰባዎች የለበጣ እንደነበሩ ግምት እንድወስድ ያደረገኝ ስብሰባ የተካሄደው መጋቢት 14/2008 “ከተቃዋሚ ፓርቲ” ተብዬዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ነው፡፡ በእኔ እምነት የውይይቱ ዋልታና ማገር የነበረው እነዚህ ፓርቲዎች በሀገራችን ከሚያመጡት የዲሞክራሲ ትሩፋት ይልቅ ለሆዳቸው መሙያ የሚሆነውን ቀለብ አስፋፈር ላይ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ተሳታፊዎቹ በሙሉ በሚባል መልኩ ደስተኛ የሆኑት ኢህአዴግ ከመንግሰት ካዝና ከሚደርሰው ገንዘብ ግማሹን ሊያካፍላቸው ፈቃደኝነቱን በጥቂቱም ቢሆን በማሳየቱ ነው፡፡ ለእነዚህ ተቃዋሚ ተብዬዎች ከዚህ ውጭ መልካም ዜና የለም፡፡ በስብሰባው ያልተገኙትም ቢሆን ያናደዳቸው ገንዘቡ ለፓርቲዎች የጋራ መድረክ አባላት ብቻ መሰጠቱ ነው፡፡ በክፍያው ላይ ቢካተቱ አብረው ጮቢ እንደማይረግጡ መረጃ የለንም፡፡ ከዚህ ውጭ መልካም ጅምር ብለው የኢዴፓው መሪ የገለፁት ምርጫን አስመልክቶ ይደረጋል ያሉት ለውጥ ነው፡፡ ይህ አባባል በእውነቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለቆየ ሰው ፓርቲዎች ስልጣን የማይዙት ወይም ተወካይ የማይኖራቸው ህዝቡ ተቃዋሚዎችን በአብልጫ ስለአልመረጠ እና “አብላጫ ድምፅ ያገኘ ያሸንፋል” በሚለው የምርጫ ህግ ምክንያት ያስመስለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩም “ምን አባታችን እናድርግ ህዝቡ ሲመርጠን” ያሉትን እንደመደገፍ የሚቆጠር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ትልቁ ችግር እኩል መወዳደሪያ ሜዳ ያለመኖሩን አለመቀበል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከኢህአዴግ ጋር እንደመቆም የሚቆጠር ነው፡፡ ለነገሩ ኢዴፓ ከኢህአዴግ ጋር ለምን ቆመ አይባልም፣ ከዚያ ውጭ የት ሊቆም ይቸላል፡፡ ግቡም ትንሸም ቢሆን የፓርላማ ወንበር ማግኘት ነው፡፡
ለማነኛውም ጠቅላይ ሚኒሰትሩ “ተቃዋሚ ተብዬዎች” ምን እንደሚፈልጉ ገብቶዋቸዋል፡፡ ሆዳቸውን የሚሞሉበት ገንዘብ እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ “ተቃዋሚ ተብዬዎችም” ምን እንደማይችሉም አውቀዋል፡፡ መሻሻል የሚገባቸውን አዋጆች አጥኑና አምጡ በህጉ መሰረት ይታያል ብለዋቸዋል፡፡ እነዚህ አንደ ገፅ ሰርዓት ያለው መግለጫ መፃፍ ለማይችሉ ተቃዋሚዎች ጥናት አጥኑና አምጡ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ሌላው ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ያልገባቸው ደግሞ የሰበሰቧቸው “ተቃዋሚዎ ትብዬዎች” በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ አንድም ቦታ የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡
ሰለዚህ በቀጣይም ከህዝቡ ጋር የሚካሄትዱትም ሆነ የተካሄዱት ስብሰባዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ የፎረም እና የኢህአዴግ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ውሰጥ በንቃት የሚሳተፉ ሰዎች ተገኝተው ድራማ የሚካሄድባቸው እንደሆነ ግምት ወስደና ወይም ገብቶናል፡፡ ይህ ደግሞ የነፃነት ቀን መምጫውን ያዘገየው እንደሆን እንጂ ጨርሶ አያስቀረውም የሚል እምነት አለኝ፡፡ መፍትሄው ከዚህ በፊት ፀረ-ህዝብ፣ ጸረ -ምናም እያላችሁ ያገለላችሁትን ቡድኖችና ግለሰቦች በንቃት ማስተፍና ትክክለኛውን ሁኔታ መገንዘብ ነው፡፡ በተጨማሪ ያለምንም ቅድመ ሁኔተ ያለ አግባብ በእስር ላይ የሚገኙት ታጋዮች መፍታት ነው፡፡ ስብሰባም ካስፈለገ …….
ቸር ይግጠመን
ግርማ ሠይፉ ማሩ

Monday, March 14, 2016

የጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ሪፖርት መድረሻው “የመልካም አስተዳደር ችግር እንፈታለን፤ ሰልጣን ግን አንለቅም” መሆኑ ነው?



የጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ሪፖርትን በወፍ በረር ስንቃኛው የሚከተለው ይዘት እንዳለው መረዳት እንችላለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓመቱ ከመጠናቀቁ ቀደም ብለው የዕድገት ቅናሽ እንደሚኖር በሰበብ ደግፈው አምነዋል፡፡ ይህም ደግሞ ገዢው ፓርቲ ከአስራ አንድ በመቶ የእድገት ልክፍት በግድም ቢሆን መላቀቁን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የፈለገውን ያህል ተግዳሮት ቢፈጠር ያልተተገበሩ ግዙፍ ዕቅዶች ዝርዝር ቢቀርብም “ቢሆንም 11 ከመቶ አድገናል” እንደ ነበር አንዘነጋውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የእድገት ቅናሽ መኖሩን  ቢያምኑም “ትንሽ ቅናሽ ያሳያል” በሚል ማለፋቸው ዝናብ ከዘነበ መልሶ ለማቅራራት ዝግጅት እንዳለ አመላካች ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ማጠቃለያ ሪፖርት ሲያቀርቡ የሰበታ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ጥቅምት/2008 ላይ እንደሚጠናቀቅ ተናግረው የነበረ መሆኑን ሳንዘነጋ ዛሬም 97 ከመቶ ተጠናቆዋል ብለውናል፤ ይህ አፈፃፀም ስራ ለመጀመር የሚያስችል እንደሚሆን ቢታመንም ባቡሩ አሁንም ስራ አልጀመረም፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በኤሌትሪክ ችግር ፈተና እየገጠመው ጄኔሬተር ሊገዛ ነው እየተባለ ባለበት ሁኔታ አሁን ባለው የኤሌትሪክ አቅርቦት ችግር ከ700 ኪሜ በላይ መስመር እንዴት ሊያደርጉት እንደሆነ የጠየቃቸውም የለ፤ ጠቅላይ ሚኒሰትሩም መረጃ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ ከባቡር መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ የቀረበው አስቂኝ ነገር “በዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ” በሚል ሰበብ ሌሎች በዕቅድ የተያዙ መስመሮች ስራ ሊጀመር እንደማይችል ፍንጭ ስጥተውናል፡፡
በተመሳሳይ የስኳር ነገር ለኢህአዴጎች ገዳቸው አይደለም፡፡ ከታቀደው ተቀንሶ በተወሰኑት ትኩረት ይሰጥ የሚል ሃሳብ መያዙን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ይፋ አድርገዋል፡፡ ደስ የሚለው የጠቅላይ ሚኒሰትሩ አባባል ደግሞ “ጓጉተን የምናወጣው ዕቅድ የማሰፈጸም አቅማችንን ጋር አልተመጣጠነም” የሚለው ነው፡፡ እኛም እያልን የነበረው አሁንም የምንለው አቅም የላችሁም ነው፡፡ የገንዘብ ብቻ አይደለም - ገንዘብ የማሰባሰብ አቅም ማለት ነው፡፡ የዕውቀት ብቻ አይደለም - እውቀት የማሰተባበር አቅም ነው፡፡ ተገባብቶ አሰተባብሮ የመስራት አቅም የላችሁም ነው ያለነው፡፡ ጉጉት ብቻ ናቸሁ!!!
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገር ውስጥ ቁጠባን ከማሳደግ አንፃር ዋነኛ ያልዋቸውን የመኖሪያ ቤት እና የጡረታ መዋጮ በሪፖርታቸው ውስጥ አንስተዋል፡፡ በእርግጥም ቆጥቦ ህዝቡ የሚጠቀምባቸው ሳይሆን መንግሰት ከአቅሙ በላይ እየለጠጠ ለሚይዛቸው ፕሮጀክቶች ፋይናንስ ማድረጊያ እንደሆኑ ከጅምሩም ግልፅ ነበር፡፡ ለምሳሌ 40/60 በሚል ቆጥቡ ቤት ታገኛላችሁ ተበሎ በጉጉት የቆጠቡ ሰዎች ፕሮግራሙን 100/0 በማድረግ የዜጎችን ሀበት ይዞ በኋላ ብር አትሞ ለመመለስ የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ ሌላው ጡረታን በሚመለከት አብዛኛው በአነሰተኛ ስራ ላይ የተሰማራ ዜጋ ትክክለኛ የግብረ ከፋይ መለያ በሌለበት ሁኔታ ከድሆች ላይ በጡረታ ስም ገንዘብ መንግሰት እየዘረፈ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ በሰተናጋጅነት የሚሰራ ሰራተና ሰድሰት ወር ጡረታ ከፍሎ የሚሰራበትን ድርጅት ቢለቅ ጡረታ ስለመክፈሉ የሚሰጠው ምንም መረጃ የለም፡፡ ቀጣይ የሚገባበት ድርጅት እንደ አዲስ ጡረታ እየቆረጠ ለመንግሰት ገቢ ያደረግል፡፡ ይህ ዜጋ በምንም ሁኔታ የዚህ የጡረታ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ደግሞ አሁን በግልፅ የሚታይ ዘረፋ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች በግል ዘርፍ ውስጥ በጡረታ መዋጮ ስም እየተዘረፉ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው በቅጡ መረጃ ሳይስጡ ያለፉት የውጭ ኢንቨስትመንት የሚመለከተውን ክፍል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳውን ንቅናቄ አሰመልክት በኢንቨስትመንት ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተፅዕኖ ያብራራው ስለሆነ እዚህ መድገሙ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ለማነኛውም አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ኢንቨሰትመንት የተሻለ ነው በሚል አልፈውታል፡፡ በምንም መለኪያ ግን አሁን የተፈጠረው ሁኔታ የውጭ ኢንቨስትመንት ሊስብ አይችልም፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እንዳመኑት “ይህ ችግር ከትግራይ እስከ ደቡብ ጫፍ” መሆኑን በኦሮሚያ ቀድሞ መታየቱ ሌሎቹ ችግር የለባቸው ማለት እንዳልሆነ ማረጋገጣቸው በኢንቨስትመንት ላይ ጉልዕ ጫና አለው፡፡ ኢንቨሰተሮች ደግሞ ይህን ለማወቅ አይቸገሩም፡፡ ይህ ደግሞ የሚታየው በቀጣይ ዓመታት ሲሆን እስከ አሁን ድረስም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የጀመሩትም በሆን ቢያንስ ረዘም ያለ የዝግጅት ጊዜ መውሰዳቸው የግድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለያየ መልኩ በተግባራ ተመልክተነውል፡፡ ሰለዚህ የውጭ ኢንቨስትመንት በቅርቡ ያድጋል ብሎ መገመት አይቻለም፡፡ ሰለዚህ በሪፖርቱ በደፈናው የውጭ ኢንቨስትመንት ካለፈው የተሻለ በሚል የቀረበው ተዓማኒነት የለውም፡፡
በሀገራችን ዙራ መለስ የሚታየው ያለመረጋጋት በኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር መቀጠላችንን ስጋት ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ግምት ያላቸው ሰዎች ቀላል አይደሉም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ገዢው ፓርቲ ነገሩን ከስሩ አጥንቶ ሁሉንም ያገባኛል ባይ የሚያሳትፍ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ አሁን በተለመደ አሮጌ መንገድ መሄድ የመረጠ ይመስላል፡፡ ከወትሮ በተለይ “በሌላው አካል ላይ ጣት መቀስር ይቁም” የሚል ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ያነሱ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ግን ለመፍትሔው እሩቅ እንደሆኑ የሚያሳያው “በተሃድሶ” ጊዜ ችግር የፈቱበትን መንገድ አሁንም ሊደግሙት ያሰቡ ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ የዚህችን ሀገር ለመፍታት ከእኔ ሌላ ማንም የለም የሚል ይመስላል፡፡ አሁን ያለውን በመልካም አስተዳደር ተሸፍኖ የሚቀርብልንን መንግሰታዊ ሌብነት እና ውስልትና በቸልታ እንድናልፈው የሚጠይቁን በሚመስል ሁኔታ መቶ በመቶ ተመርጠናል ባሉበት ዓመት መቶ በመቶ ሲከሸፉ ሌላ አማራጭ ማሰብ አልተቻላቸውም፡፡ መልዕክቱ ግልፅ ነው፡፡ “የመልካም አስተዳደር ችግር እንፈታለን፣ ስልጣን መልቀቅ ግን አይታሰብም” የሚል ነው፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግሩን ደግሞ የሚፈቱት ለወጣቱ የስራ እድል የሚፈጥሩ ከዚህ ቀደም ሲዘረዝሩልን የነበሩትን “በጉጉት” ላይ የተመሰረቱ ዕቅዶችን በማቅረብ ነው፡፡ ወጣቱ ስራ ካገኘ ሌላ ጥያቄ ያለው አልመስላቸውም፡፡ የወጣቱ ጥያቄ የስራ መፍታት ብቻ አይመስለኝም፡፡ በሀገሩ እኩል እንደ ዜጋ መቆጠር እና በነፃነት የመኖር ጭምር ነው፡፡ በስራ ፈጠራ ቢሆን አሁን የሚታየውን ስራ አጥነት እንፈታለን እየተባለ በጎን ደግሞ በስራ ላይ ያሉትን የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን በመንግሰት ጣልቃ ገብነት ከስራ ለማስወጣት እቅድ እንዳለም ከሪፖርቱ ለመረዳት ከባድ አይደለም፡፡ በቅርቡ ወደ ስራ እንዲገቡ የሚታሰቡት “የቢሾፍቱ” አውቶብሶች ዋና ዓላማቸው ባለፈው የስራ ማቆም አድማ በማድረግ አንገታቸውን ቀና ያደረጉትን ዜጎች አንገት ለማስደፋት ነው፡፡ ለማነኛውም ቀኑ ደርሱ ውጤቱን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ ይህ አካሄድ የቁርጡ ቀን መቃረቡን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትራችን በሰጡት ማብራሪያ አንድ አዲስ ነገርም አስረግጠው ነግረውናል፡፡ በሀገራችን “የማንነት ጥያቄ የተመለሰ ጉዳይ ነው” ብለውናል፡፡ ማንነት “ኢቮልቭ” የሚያደርግ የሚፈጠርና የሚጠፋ መሆኑ አብቅቶለታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአሁን በኋላ አዲስ ማንነት አይፈጠርም፡፡ ይህን ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ክልሎች ተነጋግረው ቋጠሮ ማበጀት አለባቸው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህን ንግግር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገውት ቢሆን እንደ ህግ ልንወስደው እንችል ነበር፡፡ አሁን ግን እንደ የግል አስተያየት አድርገን ከመውሰድ ውጭ ህግ ነው ለማለት ውጤቱን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እነ ዳንኤል ሺበሽ “ቁጫ ቁጫ ነው ጋሞ አይደለም” በሚል በኢህአዴግ መስመር ጥያቄ በማቅረባቸው ዛሬ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢህአዴግ የማንነት ድንበር ምን ጋ ሲደርስ እንደሚቆም ዝርዝር መመሪያ ሊሰጥ ይገባል፡፡ በእግረ መንገድ የጉራጌ ብሔር/ብሔረሰብ የባህል ልብስ ደንብ ወጣ ሲባል ሰምቻለሁ …. አውነት ይሆን?
ባጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒትሩ ሪፖርት በእኔ ግምት ሪፖርት ሳይሆን አሁንም ሌላ እቅድ ነው አበክረን፣ጠንክረነት እንሰራለን የሚል፡፡አሁንም ልምድ የሚቀመርበት … የሚማሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛው ችግር ደግሞ ሰማርት ስልክ መሆኑ ተደርሶበት ሰማርት ስልክ በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ ጥረት ይደረጋል የሚል እቅድ ቀርቦልናል፡፡ በስብሰባው ላይ ህውሃት ከሞላ ጎደል የተሟላ ሲሆን የሌሎች ድርጅት ከፍተኛ ሃላፊዎች ያለመገኘት ምን ማለት ይሆን?
ቸር ይግጠመን
ግርማ ሠይፉ ማሩ

Thursday, March 10, 2016

መንግሰታችን ለመጪው ግንቦት ሃያ አብዮት ይጠራ ይሆን?



የካቲት 21 2008 በኢትዮጵያ ታሪክ ተመዝግቦ አልፏል፡፡ ቀጣዩ ታሪካዊ ቀን ደግሞ የሚመጣው ግንቦት 20 2008 ነው፡፡ የግንቦት 20 ማግሰት ምን አዲስ ነገር እንደሚመጣ ግን ማንም የሚያውቅ የለም፡፡ መገመት ግን ይቻላል፡፡ የመጪው ግንቦት ሃያ ቀደም ብለን እንድንነጋገርበት ያሳሰበኝ በቅርቡ የአዲስ አበባ የትራንሰፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ያደረጉት የሰለማዊ ተቃውሞ/የስራ ማቆም አድማ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአዲስ አበባ አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች መደዳ ቁጥር ሰላሣ ሺ የደረሰ ሲሆን በእርግጠኝነት በስራ ላይ የሚገኙት ግን ከግማሽ የሚበልጡ አይደለም፡፡ በተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡትን ታክሲ ያልሆኑ ሚኒባሶች ሲጨመሩ ሃያ ሺ የሚሆኑ መኪኖች በአግልግሎት ውስጥ ናቸው የሚል ታሳቢ መውሰድ ይቻላል፡፡ እነዚህ የትራንሰፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በሰራቸው የሚተዳደረውን በመቶ ሺ የሚቆጠረ ቤተሰብ አባል ችግር ላይ ሊጥል የሚችል እርምጃ በመውሰድ መንግሰትን የተጋፈጡ ሲሆን፣ በማህበራቸው በኩል ተደረገ በተባለ ድርድር ለተቃውሞ መነሻ የሆነው መመሪያ ለሶሰት ወር ተግባራዊ እንዳይሆን ከስምምነት በመደረሱ ተቃውሞ ተቋርጦዋል፡፡ ሶሰት ወር የሚሞላው ደግሞ ግንቦት 20 2008 ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መነሳት ያለበት ጥያቄ ከሶሰት ወር በኋላስ? የሚለው ነው፡፡ በተለይ ጥያቄውን ከአሸከርካሪዎች አንፃር የተወሰኑ መሰረታዊ ነጥቦችን በማንሳት እንመልከተው፤
 የመጫኛ እና ማውረጃ ቦታ በቂ ያለመሆን
እንደሚታወቀው ለታክሲ ማቆሚያና ማውረጃ በቂ ቦታዎች በከተማው ውስጥ የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ታክሲዎች ባመቻቸው ቦታ ይጭናሉ ያወርዳሉ፡፡ ተሳፈሪውም በየአስር ሜትሩ ወራጅ አለ ብሎ መውረድ ይፈልጋል፡፡ ተሳፋሪን በየቦታው ለማውረድ ብቻ ሳይሆን ለመጫንም ይቆማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በመንገድ ዳር የቆሙ መኪኖችን ደርበው መጫንና ማውረድ መደበኛ የታክሲ ስራ አካል ነው፡፡ ይህ ድርጊት አሁን በወጣው መመሪያ መሰረት ከፍተኛ ቅጣት የሚያስጥል ነው፡፡ ሰለዚህ በሚቀጥለው ሶሰት ወር ውስጥ  መንግሰት ይህን ችግር ለመፍታት እና መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅምም ፍላጎትም የለውም፡፡ አማራጩ ደርቦ መጫንና ማውረድ ትክክለኛ ተግባር ተደርጎ እንዲወሰድ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ሌላው አማራጭ ደግሞ ለታክሲ ማቆሚያ ሲባል በመንገድ ላይ መኪና ማቆም መከልከል ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንገድ ተከትለው የተሰሩት ህንፃዎች እና የተከፈቱ የንግድ ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የፊት ለፊቱ ችግር ሲሆን መንገድ ላይ ፓርክ ማድረግ መከልከል ከዚህ የከፋ ሌላም ችግር እንደሚኖረወ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ለማነኛውም መንግሰት ይህን ችግር እንደማይፈታው ታውቆ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡
የትራፊኮች የሰነ ምግባር ጉዳይ
የትራፊኮች የስነ ምግባር ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ሁሉም ይረዳዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት መንግሰት መፍትሔ ብሎ ያሰቀመጠው አቅጣጫ ግን ከህግም ከሞራልም አንፃር ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ትራፊክ ላይ ከጠቆመ ትራፊኩ ከስራ ይባረራል፡፡ ምን ማለት ነው? የትራፊኮች የሰነ ምግባር ችግር በሌሎች ዜጎች የሌለ ይመስል ሌሎችን አምኖ እርምጃ መውሰድ የህግ መሰረት የለውም፡፡ ትራፊክ ያለጥፋት ሊቀጣን ይችላል የሚል ስጋት ሲቀርብ ትራፊኩን ያለጥፋቱ የሚያስቀጣ አስራር ይፈጠር ማለት አይደለም፡፡ አንድ ትራፊክም ቢሆን ያለጥፋቱ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ለምንል ሰዎች ግን ይህ ህገወጥ ነገር ግን በአደባባይ እየተነገረ ያለ የእርምጃ ዓይነት ዜጎችን አሸማቃቂ ነው፡፡ ለማነኛውም ዋነኛው ችግር ግን ትራፊኮች በዚህ ዓይነት ህግ ውስጥ ምን ያህል ሊቆዩ ይችላሉ? የሚለው ሲሆን የትራፊኮች የስራ ማቆም አድማ መንገድ ከመዝጋት አልፎ የተለየ ነገር ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ እርምጃ ሰዎች በትራፊኮች ላይ ጥቆማ ከማድረግ ይልቅ ትራፊክና አሸከርካሪ ተጣምረው ለበለጠ ውስብስብ ችግር የሚዳርግ ነው የሚሆነው፡፡ ልብ ማለት ያለብን ትራፊኮቹም ቢሆኑ የማህበረሰቡ አካል መሆናቸው እና ለትራፊክነት ፍላጎት ያላቸው ከሰራ ፍቅር ወይም ከደሞዙ አማላይነት የተነሳ አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት ሪፖርት ጋዜጣ ያወጣው ዜና ትዝ የሚለኝ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች በጉምሩክ ለፈታሽነት ስራ በሺዎች መመዝገባቸው የስራ ፍቅር እንዳልሆነ ግልጥ ከመሆን አልፈን ወጣቶቻችን የደረሱበትን የገንዘብ ማግኛ ፍላጎት መስመር የሚያጋልጥ ነው፡፡ ሃሳቤ ግልፅ ይመስለኛል፡፡ ዲግሪ ይዞ ኬላ ላይ ፈታሽ መሆን መመኘት የጤና አይመስለኝም፡፡
የቅጣቶች ተደራራቢነት
ቅጣቶች ተደራራቢ ከመሆናቸው አንፃር አንድ የቤት መኪና አሸከርካሪ ሰድስት ወር ወይም ሁለት ዓመት ቢቀጣ በትራንስፖርት መሄድ አማራጭ ሲሆን አቅም ካለው ደግሞ በሾፌር መሄድ ይችላል፡፡ በአሸከርካሪነት የሚኖር ለመደበኛ አሸከርካሪ በስራው ፀባይ የተነሳ ደንብ ለመተላለፍ የተጋለጠ አሸከርካሪ ግን ዲግሪውን ነው የሚቀማው፡፡ ለምሳሌ እኔ ዲግሪ ብቀማ የምሰራውን ስራ የሚከለክለኝ ነገር ስለሌለ ተቀጥሬ መስራት ብቻ ነው የሚቀርብኝ፡፡ አንድ አሸከርካሪ ግን መንጃ ፍቃዱ ከተቀማ ከሰራ መስኩ ነው የሚባረረው፡፡ ለስድስት ወር ለሁለት ዓመት ምን እየበላ እንዲኖር እና ቤተሰቡን እንዴት እንዲያስተዳደር እንደታሰበ መመሪያው አይገልፅም፡፡ በትራፊክ አደጋ ሰው እንዳይሞት በረሃብ ግን ይሙት የሚል ይመስላል፡፡ አንድ ቀደም ሲል በህገወጥ ተግባር ሲሰማራ የነበረ፣ ነገር ግን ፀባዩን አርቆ ስርዓት ይዞ የታክሲ ረዳት ከዚያም ሁለተኛ፣ ሶሰተኛ ብሎ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ በስራ ላይ ያለ አሸከርካሪ ቃል በቃል አለ የተባለው “ችግር የሌም ተመልሼ ወደ ቀድሞ ስራዬ እገባለሁ” ነው፡፡ ማጅራት እየመታ ሰው ገድሎ እንዲኖር ማለት ነው፡፡ ሌሎች ሀገሮች የዚህ ዓይነት ህግ ሲተገብሩ በሀገራቸው ስራ የሌለው ሰው የማህበራዊ ዋስትና የሚባል ክፍያ የሚያገኝ በመሆኑ ስራ አጥቼ ምን ልሁን አይልም፡፡ ይህን ስናስብ ህጎችን ስንቀዳ በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ማድረግ ይኖርብናል፡፡ አሁንም መነሳት ያለበት ጥያቄ የዛሬ ሶሰት ወር መንጃ ፍቃዱን  የተቀማ አሽከርካሪ ምን ይሁን? ፈቃድ የማይጠይቁ ስራዎች ገቢ የሚያስገኙ አማራጭ ካሉም ይነገረን፡፡ አንዱ የገዢው ፓርቲ አባልነት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ከአባልነት በመለስ ማለቴ ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ካለው የድርድር ባህሪ አንፃር ለማሳያ ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ሊፈታቸው አይችልም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሊያደርግ የሚችለው ብዙ ቢሆንም ከልምድ ግን የተወሰኑትን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንደኛ ይህን ተቃውሞ ሲመሩ የነበሩትን በተለያየ መንገድ በመደለል የተደረገውን የስራ ማቆም አድማ በድጋሚ ሊጠራ የማይችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ለዚህም  እነዚሁኑ ሰዎች የአገልግሎት ሰጪ ሾፌሮችና ረዳቶችን በመከፋፈል ባቀደው መሰረት ከሶሰት ወር በኋላ መመሪያውን በማን አለብኝነት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህም ሲሆን ከዚህ ቀደም የተደረገውን ድርጊት እንዲያወግዙ ጭምር በማድረግ ሞራላቸውን ማኮላሸት ዋናው ግብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በንግድ ባንክ ሰራተኞች ላይ የተወሰደውን እርምጃ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
በቀጣይ ደግሞ ተጨማሪ ታክሲዎች በመንግስት ድጋፍ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ወይም ይገባሉ እያሉ በማስወራት አሁን ያሉትን አገልግሎት ሰጪዎች ከጫወታ ሊያሰወጣን ነው ወደሚል የሰነ ልቦና ጦርነት መፍጠርና ማሰጨነቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደምም ተሞክሮ የሰራ ሲሆን በቀጣይ በተመሳሳይ መልኩ ስራ ላይ አይውልም አይባልም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ከዚህ ቀደም በባለ ታክሲዎች የተደረጉ የስራ ማቆም አድማዎች ናቸው፡፡
እኔ ከዚህ የስራ ማቆም አድማ በግሌ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ ዋነኛው ነገር ህዝቡ ከተባበረ ማንኛውም መብቱ የተነካ ስብስብ መብቱን ማስከበር እንደሚቻል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የታክሲ ሾፌሮች ዘወትር በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚደርስባቸው ዘለፋ አዘል አስተያየቶች በተቃራኒው የእነርሱ መኖር በሁሉም እንቅስቃሴ ውስጥ ሞተር መሆኑን ለዘነጋው ዜጋ ትምህርት አስተላልፈዋል ብዬም አምናለሁ፡፡ በቀጣይ ሁሉም በጋራ የማይቆሙ ቢሆን እንኳን ጉዳዩ የበለጠ የከነከናቸው አሸከርካሪዎች በተናጥል መኪናውን ለባለቤቱ አስረክበው ዋነኛ የሰራ ሰርተፊኬት ከማሰረከብ ይህ ህግ እስኪሻሻል በሾፌርነት ላለመስራት ቢወስኑ ባለንብረቶች መኪናው በፈረስ ስለማያሰጎትቱት መንግሰትም ባለቤቶቹን ለማስገደድ አቅም አይኖረውም፡፡ ሰለዚህ ጫናውን ማስቀጠል ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሌላው መንገድ ደግሞ ሾፌሮች ሰራቸውን ለመስራት አሁን ከሚከፈላቸው በላይ የሚመጣውን የወደፊት አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል ደሞዝ እና የቀን አባል ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ታሪፍ ሲሻሻል እና ገቢው ሲጨምር ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አዲሱ ተግባራዊ የሚሆነው መመሪያ ወደ ህዝቡ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ይጠራል ማለት ነው፡፡ ህዝቡ ደግሞ አሁንም ያለው ዋጋ መሸከም አልቻለም እና በሌሎች ዕቃዎችም ላይ የዋጋ ንረት ሊጠራ ይችላል፡፡ እነዚህ ሲደመሩ ደግሞ ሌላ ጦስ ላለመጥራታቸው ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡
የዛሬ ሶስተ ወር አጭር ጊዜ ነው፡፡ አሸከርካሪ፣ የመኪና ባለቤቶች፣ ተጠቃሚው ህዝብ፣ በተለይም መንግስት ከፍተኛ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ግንቦት 20 2008 በሚያበቃው ሶሰት ወር መንግሰት ምን ይዞ እንደሚመጣ በጉጉት እንጠብቃለን፡፡ መንግሰታችን ለመጪው ግንቦት ሃያ አብዮት ይጠራ ይሆን?
ቸር ይግጠመን
ግርማ ሠይፉ ማሩ