Thursday, March 10, 2016

መንግሰታችን ለመጪው ግንቦት ሃያ አብዮት ይጠራ ይሆን?



የካቲት 21 2008 በኢትዮጵያ ታሪክ ተመዝግቦ አልፏል፡፡ ቀጣዩ ታሪካዊ ቀን ደግሞ የሚመጣው ግንቦት 20 2008 ነው፡፡ የግንቦት 20 ማግሰት ምን አዲስ ነገር እንደሚመጣ ግን ማንም የሚያውቅ የለም፡፡ መገመት ግን ይቻላል፡፡ የመጪው ግንቦት ሃያ ቀደም ብለን እንድንነጋገርበት ያሳሰበኝ በቅርቡ የአዲስ አበባ የትራንሰፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ያደረጉት የሰለማዊ ተቃውሞ/የስራ ማቆም አድማ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአዲስ አበባ አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች መደዳ ቁጥር ሰላሣ ሺ የደረሰ ሲሆን በእርግጠኝነት በስራ ላይ የሚገኙት ግን ከግማሽ የሚበልጡ አይደለም፡፡ በተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡትን ታክሲ ያልሆኑ ሚኒባሶች ሲጨመሩ ሃያ ሺ የሚሆኑ መኪኖች በአግልግሎት ውስጥ ናቸው የሚል ታሳቢ መውሰድ ይቻላል፡፡ እነዚህ የትራንሰፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በሰራቸው የሚተዳደረውን በመቶ ሺ የሚቆጠረ ቤተሰብ አባል ችግር ላይ ሊጥል የሚችል እርምጃ በመውሰድ መንግሰትን የተጋፈጡ ሲሆን፣ በማህበራቸው በኩል ተደረገ በተባለ ድርድር ለተቃውሞ መነሻ የሆነው መመሪያ ለሶሰት ወር ተግባራዊ እንዳይሆን ከስምምነት በመደረሱ ተቃውሞ ተቋርጦዋል፡፡ ሶሰት ወር የሚሞላው ደግሞ ግንቦት 20 2008 ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መነሳት ያለበት ጥያቄ ከሶሰት ወር በኋላስ? የሚለው ነው፡፡ በተለይ ጥያቄውን ከአሸከርካሪዎች አንፃር የተወሰኑ መሰረታዊ ነጥቦችን በማንሳት እንመልከተው፤
 የመጫኛ እና ማውረጃ ቦታ በቂ ያለመሆን
እንደሚታወቀው ለታክሲ ማቆሚያና ማውረጃ በቂ ቦታዎች በከተማው ውስጥ የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ታክሲዎች ባመቻቸው ቦታ ይጭናሉ ያወርዳሉ፡፡ ተሳፈሪውም በየአስር ሜትሩ ወራጅ አለ ብሎ መውረድ ይፈልጋል፡፡ ተሳፋሪን በየቦታው ለማውረድ ብቻ ሳይሆን ለመጫንም ይቆማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በመንገድ ዳር የቆሙ መኪኖችን ደርበው መጫንና ማውረድ መደበኛ የታክሲ ስራ አካል ነው፡፡ ይህ ድርጊት አሁን በወጣው መመሪያ መሰረት ከፍተኛ ቅጣት የሚያስጥል ነው፡፡ ሰለዚህ በሚቀጥለው ሶሰት ወር ውስጥ  መንግሰት ይህን ችግር ለመፍታት እና መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅምም ፍላጎትም የለውም፡፡ አማራጩ ደርቦ መጫንና ማውረድ ትክክለኛ ተግባር ተደርጎ እንዲወሰድ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ሌላው አማራጭ ደግሞ ለታክሲ ማቆሚያ ሲባል በመንገድ ላይ መኪና ማቆም መከልከል ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንገድ ተከትለው የተሰሩት ህንፃዎች እና የተከፈቱ የንግድ ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የፊት ለፊቱ ችግር ሲሆን መንገድ ላይ ፓርክ ማድረግ መከልከል ከዚህ የከፋ ሌላም ችግር እንደሚኖረወ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ለማነኛውም መንግሰት ይህን ችግር እንደማይፈታው ታውቆ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡
የትራፊኮች የሰነ ምግባር ጉዳይ
የትራፊኮች የስነ ምግባር ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ሁሉም ይረዳዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት መንግሰት መፍትሔ ብሎ ያሰቀመጠው አቅጣጫ ግን ከህግም ከሞራልም አንፃር ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ትራፊክ ላይ ከጠቆመ ትራፊኩ ከስራ ይባረራል፡፡ ምን ማለት ነው? የትራፊኮች የሰነ ምግባር ችግር በሌሎች ዜጎች የሌለ ይመስል ሌሎችን አምኖ እርምጃ መውሰድ የህግ መሰረት የለውም፡፡ ትራፊክ ያለጥፋት ሊቀጣን ይችላል የሚል ስጋት ሲቀርብ ትራፊኩን ያለጥፋቱ የሚያስቀጣ አስራር ይፈጠር ማለት አይደለም፡፡ አንድ ትራፊክም ቢሆን ያለጥፋቱ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ለምንል ሰዎች ግን ይህ ህገወጥ ነገር ግን በአደባባይ እየተነገረ ያለ የእርምጃ ዓይነት ዜጎችን አሸማቃቂ ነው፡፡ ለማነኛውም ዋነኛው ችግር ግን ትራፊኮች በዚህ ዓይነት ህግ ውስጥ ምን ያህል ሊቆዩ ይችላሉ? የሚለው ሲሆን የትራፊኮች የስራ ማቆም አድማ መንገድ ከመዝጋት አልፎ የተለየ ነገር ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ እርምጃ ሰዎች በትራፊኮች ላይ ጥቆማ ከማድረግ ይልቅ ትራፊክና አሸከርካሪ ተጣምረው ለበለጠ ውስብስብ ችግር የሚዳርግ ነው የሚሆነው፡፡ ልብ ማለት ያለብን ትራፊኮቹም ቢሆኑ የማህበረሰቡ አካል መሆናቸው እና ለትራፊክነት ፍላጎት ያላቸው ከሰራ ፍቅር ወይም ከደሞዙ አማላይነት የተነሳ አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት ሪፖርት ጋዜጣ ያወጣው ዜና ትዝ የሚለኝ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች በጉምሩክ ለፈታሽነት ስራ በሺዎች መመዝገባቸው የስራ ፍቅር እንዳልሆነ ግልጥ ከመሆን አልፈን ወጣቶቻችን የደረሱበትን የገንዘብ ማግኛ ፍላጎት መስመር የሚያጋልጥ ነው፡፡ ሃሳቤ ግልፅ ይመስለኛል፡፡ ዲግሪ ይዞ ኬላ ላይ ፈታሽ መሆን መመኘት የጤና አይመስለኝም፡፡
የቅጣቶች ተደራራቢነት
ቅጣቶች ተደራራቢ ከመሆናቸው አንፃር አንድ የቤት መኪና አሸከርካሪ ሰድስት ወር ወይም ሁለት ዓመት ቢቀጣ በትራንስፖርት መሄድ አማራጭ ሲሆን አቅም ካለው ደግሞ በሾፌር መሄድ ይችላል፡፡ በአሸከርካሪነት የሚኖር ለመደበኛ አሸከርካሪ በስራው ፀባይ የተነሳ ደንብ ለመተላለፍ የተጋለጠ አሸከርካሪ ግን ዲግሪውን ነው የሚቀማው፡፡ ለምሳሌ እኔ ዲግሪ ብቀማ የምሰራውን ስራ የሚከለክለኝ ነገር ስለሌለ ተቀጥሬ መስራት ብቻ ነው የሚቀርብኝ፡፡ አንድ አሸከርካሪ ግን መንጃ ፍቃዱ ከተቀማ ከሰራ መስኩ ነው የሚባረረው፡፡ ለስድስት ወር ለሁለት ዓመት ምን እየበላ እንዲኖር እና ቤተሰቡን እንዴት እንዲያስተዳደር እንደታሰበ መመሪያው አይገልፅም፡፡ በትራፊክ አደጋ ሰው እንዳይሞት በረሃብ ግን ይሙት የሚል ይመስላል፡፡ አንድ ቀደም ሲል በህገወጥ ተግባር ሲሰማራ የነበረ፣ ነገር ግን ፀባዩን አርቆ ስርዓት ይዞ የታክሲ ረዳት ከዚያም ሁለተኛ፣ ሶሰተኛ ብሎ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ በስራ ላይ ያለ አሸከርካሪ ቃል በቃል አለ የተባለው “ችግር የሌም ተመልሼ ወደ ቀድሞ ስራዬ እገባለሁ” ነው፡፡ ማጅራት እየመታ ሰው ገድሎ እንዲኖር ማለት ነው፡፡ ሌሎች ሀገሮች የዚህ ዓይነት ህግ ሲተገብሩ በሀገራቸው ስራ የሌለው ሰው የማህበራዊ ዋስትና የሚባል ክፍያ የሚያገኝ በመሆኑ ስራ አጥቼ ምን ልሁን አይልም፡፡ ይህን ስናስብ ህጎችን ስንቀዳ በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ማድረግ ይኖርብናል፡፡ አሁንም መነሳት ያለበት ጥያቄ የዛሬ ሶሰት ወር መንጃ ፍቃዱን  የተቀማ አሽከርካሪ ምን ይሁን? ፈቃድ የማይጠይቁ ስራዎች ገቢ የሚያስገኙ አማራጭ ካሉም ይነገረን፡፡ አንዱ የገዢው ፓርቲ አባልነት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ከአባልነት በመለስ ማለቴ ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ካለው የድርድር ባህሪ አንፃር ለማሳያ ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ሊፈታቸው አይችልም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሊያደርግ የሚችለው ብዙ ቢሆንም ከልምድ ግን የተወሰኑትን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንደኛ ይህን ተቃውሞ ሲመሩ የነበሩትን በተለያየ መንገድ በመደለል የተደረገውን የስራ ማቆም አድማ በድጋሚ ሊጠራ የማይችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ለዚህም  እነዚሁኑ ሰዎች የአገልግሎት ሰጪ ሾፌሮችና ረዳቶችን በመከፋፈል ባቀደው መሰረት ከሶሰት ወር በኋላ መመሪያውን በማን አለብኝነት ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህም ሲሆን ከዚህ ቀደም የተደረገውን ድርጊት እንዲያወግዙ ጭምር በማድረግ ሞራላቸውን ማኮላሸት ዋናው ግብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በንግድ ባንክ ሰራተኞች ላይ የተወሰደውን እርምጃ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
በቀጣይ ደግሞ ተጨማሪ ታክሲዎች በመንግስት ድጋፍ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ወይም ይገባሉ እያሉ በማስወራት አሁን ያሉትን አገልግሎት ሰጪዎች ከጫወታ ሊያሰወጣን ነው ወደሚል የሰነ ልቦና ጦርነት መፍጠርና ማሰጨነቅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደምም ተሞክሮ የሰራ ሲሆን በቀጣይ በተመሳሳይ መልኩ ስራ ላይ አይውልም አይባልም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ከዚህ ቀደም በባለ ታክሲዎች የተደረጉ የስራ ማቆም አድማዎች ናቸው፡፡
እኔ ከዚህ የስራ ማቆም አድማ በግሌ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ ዋነኛው ነገር ህዝቡ ከተባበረ ማንኛውም መብቱ የተነካ ስብስብ መብቱን ማስከበር እንደሚቻል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የታክሲ ሾፌሮች ዘወትር በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚደርስባቸው ዘለፋ አዘል አስተያየቶች በተቃራኒው የእነርሱ መኖር በሁሉም እንቅስቃሴ ውስጥ ሞተር መሆኑን ለዘነጋው ዜጋ ትምህርት አስተላልፈዋል ብዬም አምናለሁ፡፡ በቀጣይ ሁሉም በጋራ የማይቆሙ ቢሆን እንኳን ጉዳዩ የበለጠ የከነከናቸው አሸከርካሪዎች በተናጥል መኪናውን ለባለቤቱ አስረክበው ዋነኛ የሰራ ሰርተፊኬት ከማሰረከብ ይህ ህግ እስኪሻሻል በሾፌርነት ላለመስራት ቢወስኑ ባለንብረቶች መኪናው በፈረስ ስለማያሰጎትቱት መንግሰትም ባለቤቶቹን ለማስገደድ አቅም አይኖረውም፡፡ ሰለዚህ ጫናውን ማስቀጠል ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሌላው መንገድ ደግሞ ሾፌሮች ሰራቸውን ለመስራት አሁን ከሚከፈላቸው በላይ የሚመጣውን የወደፊት አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል ደሞዝ እና የቀን አባል ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ታሪፍ ሲሻሻል እና ገቢው ሲጨምር ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አዲሱ ተግባራዊ የሚሆነው መመሪያ ወደ ህዝቡ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ይጠራል ማለት ነው፡፡ ህዝቡ ደግሞ አሁንም ያለው ዋጋ መሸከም አልቻለም እና በሌሎች ዕቃዎችም ላይ የዋጋ ንረት ሊጠራ ይችላል፡፡ እነዚህ ሲደመሩ ደግሞ ሌላ ጦስ ላለመጥራታቸው ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡
የዛሬ ሶስተ ወር አጭር ጊዜ ነው፡፡ አሸከርካሪ፣ የመኪና ባለቤቶች፣ ተጠቃሚው ህዝብ፣ በተለይም መንግስት ከፍተኛ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ግንቦት 20 2008 በሚያበቃው ሶሰት ወር መንግሰት ምን ይዞ እንደሚመጣ በጉጉት እንጠብቃለን፡፡ መንግሰታችን ለመጪው ግንቦት ሃያ አብዮት ይጠራ ይሆን?
ቸር ይግጠመን
ግርማ ሠይፉ ማሩ

Monday, February 29, 2016

የግል ባንኮችና የተቃዋሚዎች ምዕዳር ጥበት ሲነፃፀር!!!.



ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ በሪፖርተር ጋዜጣ የካቲት 13/2008 እትም እስጢፋኖስ ሲሜ የተባሉ ፀሃፊ “የመወዳደሪያ ምህዳር የጠበበባቸው የግል ባንኮች ተግዳሮት” በሚል የፃፉት ፅሁፍ በማንበቤ ነው፡፡ ፀኃፊው በመግቢያቸው ላይ የገለፁትን “የፖለቲካ ምዕዳር ጠቧል አልጠበበም የአንድ ሰሞን የኢህአዴግና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሩ መከራከሪያ አጀንዳ ነበር፡፡ ኢህአዴግ አለመጥበቡን፣ ተቃዋዋሚ ፓርቲዎችም  መጥበቡን ሳያሳዩን እንዲሁ ጠቧል፣ አልጠበበም በሚል ደረቅ ክርክር ብዙ “እድሜ ገዙ”” በሚል የተነሱበትን ፍሬ ነገር ፍሬ የሚያሳጣ ሀሳብ ደንቅረው ሲያበቁ ይህን ለፖለቲካ ተንተኞች እተዋለሁ በማለታቸው እንደ ፖለቲከኛ ለመልሱ አቤት ለማለት ነው፡፡ የመወዳደሪያ ሜዳው ለግል ባንኮች ቢጠብም አሁንም በህይወት አሉ፤ የምዕዳሩ ጥበት አማራጭ ሜዳ መፈለግ እስኪያስመኝ የጠበበው ግን በፖለቲካው በኩል መሆኑን እግረ መንገድም ለማሰታወስ ነው፡፡
አቶ እስጢፋኖስ ለባንኮች ምዕዳር መጥበቡን የገለፀላቸው አዕምሮ ግን የፖለቲካ ጉዳይ ሲሆን መስመር ይዞ አቋም ለመውሰድ ሲያቅተው ማየት የፖለቲካ ምዕዳሩ በዜጎች ሃሳብ በነፃነት በመግለፅ ላይ ያሳረፈውን ጫና የሚያሳይ ነው፡፡ አቶ እስጢፋኖስ የግል ባንኮች ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶች ብለው ያነሱዋቸው ነጥቦች በሙሉ የፖለቲካ መልእክት እንዳለው ለመረዳት የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ የባንክ ባለሞያ ከሆኑ መንግሰት ለምን በግል ባንኮች ላይ አላሰፈላጊ ጫና እንደሚያደርግ በፊት ለፊት ከሚሰጠው የብሄራዊ ባንክ ከሚያወጣቸው መመሪያዎች የፊት ገፅ መግላጫ ጀርባ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካል- ኢኮኖሚ ትንተና  መስመር እንደሚቃኝ ማወቅ አለባቸው፡፡
ለዛሬው አቶ እስጢፋኖስ አውቀው ካልተኙ በኢትዮጵያ ውስጥ እሳቸው የአንድ ሰሞን መከራከሪያ ከነበረበት ጊዜ በላይ የፖለቲካ ምዕዳሩ መጥበቡን ለማሳየት የተወሰኑ ነጥቦችን አንስቼ ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የምዕዳሩ መጥበብ ሌሎች አንባቢዎችም እንዲያስታውሱት ያግዛል ብዬ ሰለማምን በአጭር በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡
ኢህአዴግ የፖለቲካ ምዕዳሩን መለካት የሚፈልገው በሀገሪቱ ውስጥ የተፃፈ ህገ መንግሰት በመኖሩ፣ ይህን መሰረት አድርገው የወጡ የምርጫ ህጎች ከመኖራቸው ጋር ነው፡፡ በተጨማሪ ኢህአዴግ ዓይናችሁን ጨፍኑ ብሎን ፍርድ ቤት ብትሄዱ ሁሉ መፍትሄ አለ ሊለን ይሞክራል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የህግ የበላይነት ብሎ ነገር የለም፡፡ ሰለዚህ ጉዳይ ሁሉ የሚያልቀው በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ነው፡፡ ህገ መንግሰቱ እንኳን በፈለጉት ጊዜ በሚያወጡት አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ እንደሚሻር የእለት ከዕለት ምስክርነት የምንሰጥበት ነው፡፡

በእኔ እምነት በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ለማካሄድ የሚያስችል የፖለቲካ ምዕዳር ፈፅሞ የለም፡፡ ገዢው ፓርቲ በአውራ ፓርቲነት ለመቀጠል ወስኖ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ደፍጥጧቸዋል፡፡ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ለማካሄድ ከገዢው ፓርቲ በተጨማሪ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖር የግድ ይላል፡፡ በእኛ ሀገር አሉ እንደሚባሉት 73 ፓርቲዎች ዓይነት ሰርተፍኬት በቦርሳ ይዘው ምርጫ ቦርድ በሚያዘጋጀው ግብዣ ላይ የሚገኙትን ማለት አይደለም፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲ ማለት አማራጭ ያለው በህዝብ ውስጥ ገብቶ ለመስራት አባላትን ለመመልመልና ለማደረጃት ከዚህ ውስጥም ብቃት ያላቸውን የፖለቲካ መሪዎች ለማውጣት የሚችል ፓርቲ ማለት ነው፡፡ ይህን መንገድ ይዞ የነበረውን አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መንግሰት ምን እንዳደረገው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የፖለቲካ ምዕዳሩ ጠቧል ከሚሉት ፓርቲ አንዱ ስለነበር ሰለ መጥበቡ ለማሳየት ለፖለተካ ፓርቲ ዋና ምሶሶ ናቸው በሚባሉት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የአንድነት ፓርቲን ምሳሌ በማድረግ ብቻ ላስረዳ፡፡
ሕዝባዊ ስብሰባዎችና ሰለማዊ ስልፉችን ማድረግ
አንድ ፓርቲ ከደጋፊዎችና ከሌሎች የህብረተሰብ ከፍሎች ጋር የቅርብ ግንኙነት የሚያደርገው ህዝቡን ለለውጥ እንዲነሳሳ የሚያደርገው በተመረጡ እና ለህዝብ ልብ ቅርብ ናቸው ያላቸውን አጀንዳዎች በማንሳት ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሰለማዊ ሰልፉችን በማድረግ ነው፡፡ ይህ በመንግሰት ቀጥተኛ ተሳትፎ ማንነታቸው ባልታወቀ የደህንነት ሰዎች ጭምር በመታገዝ ተግባራዊ እንዳይሆን ይደረጋል፡፡ አንዱ በመንግሰት በቀጥታ የሚደረገው ማደናቀፊያ የሚያደረጉት ማነኛውም ህዝባዊ ስብሳባዎች እና ሰላማዊ ስልፎች እውቅና በመከልከል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የመንግሰት ሰራተኞች ሳምንት ሙሉ ስራ የማይገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ከፍ ሲል ደግሞ ከፍተኛ ሹም ተብዬዎችም ከቢሮ ውጭ በመሆን ውሳኔ እንዳይሰጥ ያደርጋሉ፡፡ በከፍተኛ ወጭ በግል ሆቴሎች ለሚደረግ ስብሰባም ፈቃድ አይገኝም ፈቃድ ሲገኝ ባለቤቶቹ “እንኑርበት” የሚል የፍርሃት መልስ ይሰጣሉ፡፡ ኢህአዴግ በፈለገው አዳራሽ በፈለገው አደባባይ ስብሰባ ይጠራል፡፡ አቶ እስጢፋኖስ ይህ ሜዳው እኩል መሆኑ ያሳያል?

ፓርቲዎች የሚሰሩበት ቢሮ አለማግኘት
አንድ ፓርቲ የዕለት ከዕለት ስራውን ለማከናወን ቢሮ እንሚያስፈልገው ግልፅ ነው፡፡ ባንክ መቼም ቢሮ ለመከራየት ችግር አልተፈጠረበትም ይልቁንም ህንፃው ሁሉ ባንኮችን ነው የሚጠብቀው፡፡ ፓርቲዎች ቢሮ ለመከራየት በሚያደርጉት ጥረት አከራዮችን ቢሮ እንዳያከራዩ ከፍተኛ ጫና በመንግሰት መዋቅርና በደህንነት ተብዬ ሰዎች  ይደረግባቸዋል፡፡ በሚስጥር ውስጥ ለውስጥ ቢሮ ኪራይ ከተፈፀመ በኋላ ውል እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ አንድነት በአብዛኛው በቢሮነት የሚጠቀምባቸው ቦታዎች በአባላት በጎ ፈቃድ ለሌላ ጉዳይ ቢያከራዩት ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኙበትን በመልቀቅ እና በአባላት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ አንድነት በአዲስ አበባ በዋና ቢሮነት ሲጠቀምበት የነበረው ቢሮ በወር ብር35000/ሰላሳ አምሰት ሺ/ ለመከፍል ግዴታ ገብቶ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ኢህአዴግ ግን በየወረዳ መስተዳደሩ እና በየቀበሌው የያዛቸው ቢሮዎች ኪራይ እንኳን መክፈሉን እርግጠኞች አይደለንም፡፡ በአንድ ወቅት በሰበታ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ያየሁት የኦህዴድ ፅ/ቤት፤ ዛሬም በአዲስ አበባ ካዛንችስ የኢህዴግ ፅ/ቤቶች በመስተዳድር ጊቢ ውስጥ ናቸው፡፡ መቼም አቶ እስጢፋኖስ እነዚህን ነጥቦች ሲያነቡ ንግድ ባንክ እና ሌሎች የግል ባንኮች ትዝ እንደሚሎት አልጠራጠርም፡፡ የፖለቲካ ምዕዳር ለማጥበብ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መስሪያ ቦታ ከማሳጠት የበለጠ አሳማኝ ነገር ማቅረብ ይቻላል?
የፓርቲ ጋዜጣ ለማተምና ለማስራጨት መቸገር
አንድነት ፓርቲ የሚያትማቸውን ጋዜጦች በየትኛውም ማተሚያ ቤት ማትም እንዳይቻል ተደርጎዋል፡፡ ይህን መልስ ለመስጠት ብለን የገዛነው የማተሚያ ማሸን እና ጄኔሬተር ፓርቲያችን እንዲፈርስ የደህንነት መስሪያ ቤት ውሳኔ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ፓርቲያችን በምንም ምክንያት የጠበበውን ምዕዳር በራሳችን መንገድ ለማስፋት የወሰድነው ቆራጥ እርምጃ ምዕዳሩን ባጠበቡት አካላት በኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው፡፡ ጋዜጣ አዙዋሪዎች በግልፅ እንዳያሰራጩ ይከለከላሉ፡፡ ሰብሰባ ማድረጊያ ቦታ፣ የመስሪያ ቦታ ብሎም ጋዜጣ ፅፎ ዜጎች በገንዘባቸው ገዝተው ምን እንደምናስብ ለማወቅ ከመከልከል በላይ የፖለቲካ ምዕዳር መጥበብ በምን ሊለካ ይችላል?
የፓርቲ አባላት ምልመላና ማደራጀት ማደናቀፍ
አቶ እስጢፋኖስ አንድ ባንክ ተቀማጩን ማሰፋት እንዳለበት ያምናሉ፡፡ አንድ ፓርቲም አባላትና ደጋፊዎቹን ማስፋት ግዴታው ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ለመሆኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የፓርቲውን ጊቢ ረግጠው ሲወጡ በደህንነት ሰዎች በሚደረግባቸው ክትትልና ማስፈራሪያ በድጋሚ ላለመምጣት ይወስናሉ፡፡ ማስፈራሪያ የሚደረገው በቀጥታ አባል ለመሆኑ ፍላጎት ላሳየው ግለሰብ፣ ለቤተሰቦቹ በሚሰራበት መስሪያ ቤት በኩል ጭምር ነው፡፡ ብዙዎች ይህን ተቋቁመው አባል ሲሆን ከሚሰሩበት መስሪያ ቤት ይባረራሉ፡፡ የኢህአዴግ አባል ከሆኑ ግን ሹመት ያገኛሉ፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ለፖለቲካ ስልጣን የሚወዳደሩ ሁለት አካላት በተለያየ ሁኔታ ሲዳኙ ምዕዳር ጠቧል ካልተባለ ምን ሊባል እንደሚችል አላውቅም፡፡ ወደ ሌላ ከመሄዴ በፊት አቶ እስጢፋኖስን አንድ ጥያቄ ልጠይቃቸው፣ እርሶ ወይም ጓደኞቾ ለምን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ለመሆን “ፈራችሁ”? መልሶ ምንም ይሁን ምን የረፋችሁት የሚያስፈራራ ስለአለ እና እርሶም ስለሚፈሩ ነው፡፡ ምዕዳር ማጥበብ ማለት ማስፈራራት ማለት ነው፡፡

የፓርቲ ፋይናንስ
ኢህአዴግ አቶ እስጢፋኖስ በግልፅ እንደሚረዱት ብዙ የገንዘብ ምንጭ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ከፍ ሲልም በቀጥታ ነጋዴዎች ተሰብሰበው በመቶ ሚሊዮኖች እንደሚሰጡት ይታወቃል፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲ ድጋፍ የሚያደርግ ነጋዴ ቢኖር ግን ይህች ሀገር የእርሱ ልትሆን አትችልም፡፡ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ነጋዴዎች በፓርቲ አባላት ስም ብቻ ነው ድጋፍ ሊያደርጉልን የሚችሉት፡፡ ይህንንም ቢሆን በከፍተኛ ሚስጥርና ስጋት፡፡ ተመጣጣኝ የፋይናንስ ምንጭ የሌላቸው አካላት እኩል ይወዳደሩ ማለት ፌዝ ከመሆኑ የሚዘል አይደለም፡፡ ያለ ውዴታ መቶ ሚሊዮኖች መስጠትም ሆነ ተደብቆ መስጠት የፖለቲካ ምዕዳሩ ውጤት ነው፡፡ የሚያስቀው ነገር ግን ከየት አምጥታችሁ ነው ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ የምታደርጉት? የሚለው የፍርሀት ወለድ ጥያቄ ነው፡፡ በመቶ ሚሊዮኖች ገንዘብ መድቦ የሚፏልል ገዢ ፓርቲ በሳምንት ሁለት ጋዜጣ ለዚያውም አንባቢ ገዥቶ የሚያነበውን ከየት አመጣችሁ ገንዘብ? ብሎ እንቅልፍ ያጣል፣ ነውረና አፈና ይፈፅማል፡፡
ሚዲያ አጠቃቀም
ሁለት ተወዳዳሪዎች እኩል ለመውዳደር ለሚመርጣቸው አካል እኩል ቅርብ መሆን አለባቸው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አንዱ ሚዲያ ነው፡፡ የመንግሰት ሚዲያዎች ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ሰሞን ከሚከፍቷት ውስን ቀዳዳ በስተቀር ዘወትር የሚተጉት የገዢውን ፓርቲ በማወደስ ላይ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ የሚፈጠርን ኮሽታ እንደመሃት በማውራት ህዝቡ ከተቃዋሚዎች እንዲርቅ አበክረው በመስራት ነው፡፡ በየትኛውም የመንግሰት ሚዲያ ተቃዋሚዎች የሚያደርጉት በጎ እንቅስቃሴ አይዘገብም፡፡ ይባስ ብሎ በተቃዋሚዎች ላይ የተቀነባበረ ዘጋቢ ፊልም እየተሰራ ይሰራጫል፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ በኢህአደግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለው የፖለቲካ ምዕዳር እኩልነት፡፡
ለማጠቃለል ከዚህ በላይ የተነሱት ነጥቦች በኢትዮጵያ ውስጥ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ለማካሄድ በሩ የተዘጋ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የመድበለ ፓርቲን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ ባለመቻሉ ሌሎች የሀይል አማራጮች በጠጴዛው ላይ ቀርቧል፡፡ ቀላል የማይበለው ዜጋም ይህን አማራጭ እንደምርጫው እየወሰደ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በኦሮሚያ የምንመለከተው እንቅስቃሴ ሰልፍ ለማድረግ ከዞን ወረዳ ፈቃድ ጠይቀው አይደለም፡፡ እነዚህ ዓይነት ብሶት ማቅረቢያ መንገዶች ፈቃድ መጠየቅ እያበቃ መመጣቱን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ሚዲያው ሲታፈን አማራጭ ሚዲያ መፈለግ የግድ ይላል፡፡
ገዢው ፓርቲ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን የምር የሚፈልጉት ላይ በር መዝጋቱ እንደሚፈልገው በአውራ ፓርቲ ስም እድሜወን የሚያረዝምለት ሳይሆን እድሜውን የሚያሳጥረው መሆኑን መካሪ ካለው ቢመክረው ካልሆነም የእኛንም ግፉዋን ምክር ቢሰማ ጥሩ ነው፡፡ የፖሊቲካ ምዕዳሩ ሲሰፋ እና መድበለ ፓርቲ እውን ሲሆን በባንኮች ላይ ከጀርባው የሚሸረበው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካል- ኢኮኖሚ ቦታውን ያገኛል፡፡ ከዚህ ውጭ የባንኮችም የመወዳደሪያ ምዕዳር ወደፊትም ከዚህ በላይ ይጠባል፡፡ የባንኮች መወዳደሪያ ፍታሃዊ እንዲሆነ የፖለቲካ ምዕዳሩ መስፋት የግድ ነው፡፡
ቸር ይገጠመን!!!!!

Tuesday, January 26, 2016

የአባይ ፀሃዬ የለውበትም የት ያደርስ ይሆን?



ወዳጆች መቼም የዚህ ሀገር ነገር ግራና ቀኙ ጠፍቶዋል እንበል እንዴ? የፌዴራል ሹሞች የበታች ሹሞችን በፖለቲካ ውሳኔ በሚመጡ ጉዳዮ ጭምር እጃቸውን ወደታች መቀስር ጀምረዋል፡፡ ይህ ጉዳይ አዲስ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም አማርኛ ተናጋሪዎች ተለይተው ከመኖሪያቻው ሲፈናቀሉ፣ ተጠያቂ የተደረጉት “ጥቂት ኪራይ ስብሳቢ” የተባሉ የበታች ሹሞች ናቸው፡፡
አሁን ደግሞ የአዲስ አበባና በዙሪያ ያሉ ከተሞች የተቀኛጀ ማስተር ልማት ይዞት የመጣው ጦስ በቀላሉ የሚገላገሉት አይመስልም፡፡ ጎምቱ የሚባሉት ባለስልጣናትም ቢሆን ስህትት ከመስራት የሚያግዳቸው ኃይል ሊገኝ አልቻለም፡፡ የዛሬ ፅሁፌ መነሻ የሆነው ደግሞ አቶ አባይ ፀሃዬ በሚዲያ የሰጡት የመከላከያ መልስ እጅግ ስለአስገረመኝ ነው፡፡
ባጠቃላይ መንግሰት የሚባለው አካል እንደ አካል ይህ ጦሰኛ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ግራ አጋብቶታል፡፡ ግራ ተጋብቶ ግራ እያጋባን ይገኛል:: የአዲስ አበባ መሰተዳደር በግሉ ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ ያደርጋል የሚል ዜና የሰማነው የኦሮሚያ/የኦህዴድ ሰራ አስፈፃሚ የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ እንዳይሆን ውድቅ ባደረገ ማግስት ነው፡፡ አዲስ አበባ በተናጥል ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ ሲያደርግ በዙሪያ ያሉት ከተሞች ላይ የሚያሰከትለው በጎም ሆነ አሉታዊ ተፅህኖ እንዴት እንደሚታይ የነገረን የለም፡፡ ለማነኛውም ይህን እናቆይ እና ለፅሁፌ መነሻ ወደ ሆነው ጉዳይ ልግባ፡፡
በእኔ እምነት በኦሮሚያ አካባቢ ለተነሳው ንቅናቄ ዋነኛው ነገር ቆስቋሽና አቀጣጣይ የነበሩት አቶ አባይ ፀሃዬ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ኦቶ አባይ ፀሃዬ እጅ እና እግር የለሌለው ክስ በየደረጃው ወደሚገኙት የኦሮሞ ካድሬዎች ላይ አቅርበዋል፡፡ ወደዚህ ጉዳይ በዝርዝር ከመግባቴ በፊት ግን በዚህ ጦሰኛ ማስተር ፕላን ነገር ቆስቋሽና አቀጣጣይ ያልኩበትን ምክንያት ማስረዳት ይኖርብኛል፡፡
አቶ አባይ ፀኃዬ በአሁኑ ሰዓት ያላቸው ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በፖሊሲና ጥናት ጉዳዮች ማማክር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ስልጣና በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ዘመን የነበረ አይደለም፡፡ ኦቶ አባይ ይህንንም ስልጣናቸውን የገለፁበት መንገድ ጠብ የሚፈልግ ካለ ወይም ከተገኘ ለጠብ የሚመች ነው፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስትር የእለት ተእለት ስራ ስለሚበዛባቸው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እንደንስራ ተመደብን” ሲሉ በመጀመሪያ ያድረኩት የህገ መንግሰቱን አንቀፅ 79 መመልከት ነበር፡፡ ይህ ህገ መንግስት ካልተቀየረ በሰተቀር የፖሊሲ ጉዳዮችን ሸክም የሚወስድላቸው ሌላ ሰው መድበው እርሳቸው በሌላ የእለት ተዕለት ስራ መጠመድ አይገባቸውም ነበር፡፡ አቶ አባይ ፀሃዬ በዚሁ ስልጣናቸው መነሻ ባለፈው ሁለት ዓመት ግድም በኦሮሚያ በተለይ አምቦ አካባቢ በተነሳው ግርግር ማግስት ቆም ብሎ የነበረውን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጉዳይ ከምርጫው በኋላ በአሸናፊነት መንፈስ ከኦህዴድ ካድሬዎች ጋር ባደረጉት ውይይት “ይህንን ፕላን በግዳቹ ትተግባራለችሁ ብለዋል የሚለው ነው”፤ ይህን አይሉም ሊባል የማይችለው የኦህዴድ ባለስልጣናትም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበራቸው አቋም ተግባራዊ ለማድረግ ምን እናድርግ? የሚለው እንጂ ተግባራዊ አናደርግም የሚል ሰለ አልነበረ ነው፡፡
ይህች በግድ የምትል ቃል እልህ አስገብታ ይህን ሁሉ እሳት የጫረች እንደሆነች መገንዘብ አያሰቸግርም፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ እልፈት በፊት ኦሮሚያ በእጅ አዙር ይቆጣጠሩት እንደነበር፤ ለዚህም እንደ አለማየሁ አቶምሳ እና ሙክታር የመሰሉ የመለስ ቀኝ እጆች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ሉሎችም አሉ፡፡ ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የኦሮሚያ ባለስልጣናት ከህውሃት ሰዎች ጋር ትከሻ መለካከት እንደጀመሩ ብዙ ማሳየዎች አሉ፡፡ አቶ አባይ ፀሃዬ ከመለስ ሞት ማግስት ጀምሮ ከአንገታቸው ቀና ካሉት ሰዎች አንዱ ቢሆኑም በኦሮሚያ ሰፈር የተፈጠረውን ትከሻ መለካካት ያጤኑት አይመስለኝም፡፡ይህን ትከሻ መለካካጽ ልብ ብለውት ቢሆን ኖሮ “በግዳችሁ ትተገብራላችሁ” የምትለው ጦሰኛ ቃል አትውጣም ነበር፡፡ በግድ ማርም ቢሆን አይጥምም!!!
በእኔ እምነት አሁን በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳው በዋነኝነት “እምቢ ማስተር ፕላን” ተቃውሞ በኦሮሚያ በሚገኙ ኦህዴድ ካድሬዎች ቀጥተኛ ድጋፍ እንዳለው ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ድጋፋቸውን የሚሰጡበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም፡፡ ኦህዴድ ዛሬ እንደ ከዚህ ቀደሙ በኢህአዴግ በሚቀመጥለት አቅጣጫ የኦህዴድ ካደሬዎችን አፍሶ እስር ቤት ማሰገባት የሚችል አይመሰለኝም፡፡ ዶክተረ ነጋሶ በአንድ ወቅት እንደነገሩን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ካድሬዎችን አባረው እና እስር ቤት አስገብተዋል፡፡ የዚያን ጊዜው ኦህዴድ አሁን ያለ አይመስለኝም፡፡ የአሁኑ ኦህዴድ ያለው እድል ካድሬዎቹን ተለማምጦ በስልጣን መቆየት ነው የሚኖርበት፡፡ ሰለዚህ አቶ አባይ እንዳሉት በግድ መተግበር ሳይሆን ማስተረ ፕላኑን መሰረዝ ነው፡፡
አቶ አባይ ፀሃዬ እራሳቸውን ሲቀጥልም እናት ፓርቲያቸውን ሕውሃትን ለመከላከል ብለው የሰጡት ምለሽ በእርግጥ ሌላ ዙር ቀውስ የሚጠራ ነው፡፡ ይህ የአባይ ፀሃዬ የለውበትም መልስ የት እንደሚያደርስ ግን አላውቅም፡፡ መልሳቸው ባጠቃላይ አሁን በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳው ንቅናቄ መንስዔ “በኦሮሚያ የተለያየ እርከን የሚገኙ የኦህዴድ ሹሞች ሌቦች በመሆናቸው፣ ህዝቡ የሚጠይቀውን የመልካም አስተዳድር ምላሽ መሰጠት ባለመቻላቸው፣ ወዘተ” የሚል ነው፡፡ በዚህ የመከላከያ መልሳቸው በቀጥታ ላለመንካት የፈለጉት የኦህዴድ ከፍተኛ ሹሞችን ብቻ ነው፡፡ በእኔ እምነት ከወረዳ እሰከ ዞን ብሎም ክልል ድረስ ያሉት ሹሞች ሃላፊነት የተሰጣቸው በኦህዴድ ከፍተኛ ሹሞች ነው፡፡ በክስ ውስጥ ሊዘሏቸው ቢፈልጉም የበታቾቻቸውን መከላከል ወይም አብረው መከሰሳቸው መረዳት ግድ ነው የሚሆነው፡፡ የኦህዴድ ባለስልጣናት አቶ አባይ ፀሓዬን የሚጠይቁት ጥያቄ ያለ ይመስለኛል፡፡ ለማነኛውም አቶ አባይ ፀሓዬ ከግላቸው አልፈው ህውሃትም ሆነ ፌዴራል መንግሰት አሁን በተፈጠረው ጉዳይ አያገባውም ጉዳዩ የኦህዴድ እና የኦህዴድ ሾሞች ብቻ ነው ብለው እጃቸውን ለመታጠብ ሞክረዋል፡፡ ይህ በፍፁም የሚሳካ አይመስለኝም፡፡
በእኛ አረዳዳ ኦህዴድ የሚባል ፍጡር በኢህአዴግ በሚመራው ስርዓት ውስጥ የተለይ ነው ብለን አናምንም፡፡ ኦህዴድ የወሰዳቸው የግል ውሳኔዎች አሉ ብለን አናምንም ስለዚህ ሁሉም የኢህአዴግ አመራር አባሎች እና የፌዴራል መንግሰቱ ባለስልጣናት በዚህ ውሳኔ ውስጥ እንዳሉበት እናምናለን፡፡ ሰለዚህም አሁን አቶ አባይ ፀሃዬ ያቀረቡት መከላከያ ተቀባይነት የለውም፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት አንዳንዶቻችንም እንደምንስማማው የተቀናጀ ማስተር ፕላን በድፍኑ ክፋት የለውም፤ ክፋቱ የመጣው “በግድ ትተገብራላችሁ” የሚለው ማስፈራሪያ እና ጥቅም ካለው ማስገደድ እና ማስፈራራት ምን አመጣው? የሚለው እንደምታ ነው፡፡ ሰለዚህ ማርም ቢሆን በግድ ይመራል የምንለው!!!
በነገራችን ላይ ተጠያቂነት የሚባለው ነገር አቶ አባይ ፀኃዬ ከሃያ አራት ዓመት የስልጣን ዘመን በኋላም እንዴት ሊረዱት ተሳናቸው? ለምን ይህን የሚያክል ሀገራዊ ውሳኔ ወደ ወረዳና ዞን ሹሞች ሊወረውሩት ፈለጉ? ሌላው ደግሞ በኦሮሚያ አለ የሚሉት “መሬት መሸጥ፣ የመልካም አስተዳድር እጦት፣ ሙስና፣ ወዘተ እኛን አይመለከትም፡፡ ሕዝቡ የጠየቀው ትክክለኛ ጥያቄ ነው መልስ መስጠት ሲያቅታቸው አባይ፣ ሕውኃት፣ ፌዴራል” ይላሉ ብሎ ከሃላፊነት መሽሽ ይቻላል ወይ?ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ በእኔ እምነት አሁንም ቢሆንም ማስተር ፕላኑ ተተግብሮ ውጤት ቢገኝ ጭብጨባውን ለመውሰድ ወደኋላ እንደማትሉት ሁሉ በዚህ መነሻ ለተነሱት መሰረታዊ የመልካም አስተዳድርና የነጻነት ጥያቄ መልስ መስጠት ካቃታችሁም ተጠያቂነቱንም አብራችሁ መሆን ይኖርበታል፡፡ በመጨረሻ አቶ አባይ ፀሃዬ የኦህዴድ የበታችና የመካከለኛ አመራር ላይ ክስ አቅርበዋል፡፡ እነዚህ የኦህዴድ አመራሮች በድርጅት መስመር ሄደው ይህ ክስ በይፋ ይነሳልን፣ ስናስፈፅም የነበረው ከፍተኛ አመራሩ የሰጠን መመሪያ ነው ማለት አለባቸው፡፡ ካለበለዚያ ደግሞ በጋራ ጥያቄያቸውን በኢህአዴግ ፎረም ላይ አቅርበው ሊገማገሙበት ይገባል፤ የአቶ አባይ የግል ከሆነም ግለ ሂስ እንዲያወርዱ ማድረግ አለባቸው፡፡ መቼም ኢህአዴግም ሆነ ኦህዴድ ስልጣን መልቀቅ ስለማይወዱ ብዬ ነው ከስልጣን ይውረዱ ያላልኩት፡፡ ስልጣኑን በግድ እስኪለቁ ግለ ሂስ ያውርዱ ለማለት ነው፡፡
ቸር ይገጠመን!!!


Sunday, January 17, 2016

የዶ/ር መረራ የቡዳ ፖለቲካ እና መቀበል ያቃተው መራራ እውነት



ዶክተር መረራ “የኢትዮጵያ የታሪክ  ፈተናዎች እና የሚጋጩ ሕልሞች” በሚል አዲስ መፅኃፍ አስነብቦናል፡፡ በአንድ ጋዜጣ ላይ የዶክተር መረራ ከዮኒቨርሲቲ መሰናበት ያመጣው አንድ በጎ ጎን መሆኑን አንብቤያሁ፡፡ እኔም በዚህ እስማማሀለሁ፡፡ ብዙ የሀገራችን ፖለቲካኞች ጋዜጠኛ መቅረፀ ድምፅ ይዞ በሚጠይቃቸው ጥያቄ መልስ ከመስጠት የዘለለ ብዕርና ወረቀት አገናኝተው የሚያምኑበትን የፖለቲካ መስመር እና በግላቸው ያላቸውን ምልከታ ማካፈል ይቸግራቸዋል፡፡ የዶክተር መረራ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ ለንባብ ያበቃው መፅኃፍ ጋር ይህን መፅኃፍ ሲጨመርበት ቢያንስ በፖለቲካ መስመሩ ላይ ግልፅ መረዳት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ግን በዋነኝነት ዶክተር መረራ አውቆ የሚዘላቸው አንድነትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሲሆኑ እግረ መንገዴን ከመፅኃፉ የተረዳሁትን ለማካፈል ጭምር ነው፡፡
ዶክተር መረራ በእኔ መረዳት ዛሬም መኢሶን ነው፡፡ በተቻለው መጠን መኢሶን በመከላከል እና ዋናውን ጥፋት በደርግና ኢህአፓ ትከሻ ላይ ሲጭን ነው የሚታየው፡፡ መቀበል ያቃተው መራራው እውነት መኢሶን ከደርግ ጋር ተባብሮ የደርግን ጡንቻ ማፈርጠሙ ከዚያም ተከትሎ ለተፈጠረው ጥፋት ድርሻውን ማንሳት እንዳለበት በግልፅ ሊያሳየን አለመቻሉ ነው፡፡ ድርሻ መውሰድ ስል ጥፋትን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ እና ለእርቅ ዝግጁ መሆን ማለቴ ነው፡፡ በእኔ የፖለቲካ እሳቤ ውስጥ ሂሳብ ማወራረድ የሚል የለም፡፡
ዶክተር መረራ አሁን ኢትዮጵያ የምንላትን ሀገር ቅርፅ ያሲያዙትን ምኒሊክን ጀግንነት በጥያቄ ምልክት ውስጥ በማስገባት እና ከሶማሊያ ጋር አብረው ሀገር ሲወጉ ነበር የሚባሉትን “ዋቆ ጉታን” ጀግና እያደረገ በአክራሪ ኦሮሞ ብሔርተኞች ድጋፍ የመሻት ፍላጎቱን በመፅሃፉ ውስጥ ታዝቢያለሁኝ፡፡ ዶክተር መረራ ወደ መሃል እንምጣ እያለ ጥግ ጥጉን የሚሄድ መሆኑን ማሳያም ጭምር ነው፡፡ እንደሚታወቀው የዶክተር መረራ አብረን እንስራ እስከ “ግንባር” ብቻ ነው፡፡
የዶክተር መረራ የቡዳ ፖለቲካ ብሂል በሁሉም ጉዳይ ችግሮችን ወደሌሎች ማላከክ ባለብን አባዜ ጥሩ ገላጭ ቢሆንም፤ የዚህ የቡዳ ፖለቲካ ሰለባ ዋነኛው ግን ዶክተር መረራ መሆኑ ብዙ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በተለይ መድረክ የሚባለውን ስብስብ አንዴም እንኳን ለሚፈጠሩት ችግሮች ኃለፊነት የሚወሰድ አካል አድርጎ አያቀርበውም፡፡ ዶክተር መረራ በሚመራው ድርጅት ውስጥም ያለውን ችግር ለማየት እና ለማስተካከል አይፈልግም፡፡
የዶክተር መረራ “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ሕልሞቸ” የሚለው መፅኃፍ ይህች ሀገር ከፈታና የምትወጣው እና ህልሞች ቅዠት ሳይሆኑ አውን የሚሆኑት “የኦሮሞ ልኢቃን” እና “የአማራ ልሂቃን” የያዙትን ፅንፍ ሲተዉ እና መሃል መንገድ ላይ ሲገናኙ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ እኔ በፍፁም ያልገባኝ “የአማራ ልሂቅን” የሚባለው ፍረጃ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት የሚያቀነቅኑት ለማለት ከሆነ ሌሎችም አማራ ያልሆኑ በዚህ ረድፍ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ወይም ደግሞ አማራ ማለት ኦሮሞ ያልሆነ ሁሉ ማለት እንደሆነ በግልፅ ሊነግረን ይገባ ነበር፡፡ ወጣም ወረደ እኔ በመሪነት ሁሉ የተሳተፍኩበትን አንድነት ፓርቲን በአማራ ልሂቀን የሚመራ ተብሎ ተፈርጇል፡፡ ስለዚህ ይህ መሰረታዊ ስህተት ሀገራችን ከፈተና እንድትወጣ የታዘዘላት የዶክተር መረራ መድሃኒት እንደማይሰራ የሚያመላክት ነው፡፡
ዶክተር መረራ የቡዳ ፖለቲካው ሰለባ መሆኑን በደንብ የሚያሳየው “ለአንድነት ሆዴ መቁረጥ የጀመረው፤ በ2205 ክረምት የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስብሰባዎችን በአሜሪካ ለማካሄድ ተሰማምተን ከሄድን በኋላ እነ ግርማ ሠይፉ ሙሉ በሙሉ ባልገባኝ ምክንያት የጋራ እንቅስቃሴ እንዳናደርግ ባደረጉ ጊዜ ነበር፡፡ በጊዜው ለአንድነት መሪ ለነበረው ለዶ/ር ነጋሶም ምሬቴን ገልጨ ነበር፡፡ ምሬቴ ለዶ/ር ነጋሶም የገባው ይመስለኛል፡፡ ለማረም ግን አልቻለም፡፡….”  የሚል ክስ በገፅ 147 ላይ አስፍሮዋል፡፡ ተመሳሳይ ክስ በሌለሁበት በመድረክ ስብሰባ ላይ ሰሜን ጠርቶ እንዳቀረበ ሰምቻለሁ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስብሰባዎችን በአሜሪካ ለማካሄድ ተሰማምተን የሚለው አውነት አይደለም፡፡ እኔም እርሱም በግላችን አሜሪካ እንደምንሄድ ሲታወቅ ከተቻለ በጋራ ስብሰባ ብናደርግ የሚል ሃሳብ አንሰተን ሙከራ እንድናደርግ በሚል “አዲስ ቪው ሆቴል” ተገናኝተን ተነጋግረናል፡፡ ሙከራ ደግሞ ሊሳካም ላይሳከም ይቸላል፡፡ ይህን ዶክተር ነጋሶ ለአንድነት ድጋፍ ሰጪዎች ገልፀውላቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ዶክተረ መረራ ዘወትር እንደሚያደርገው “የኦሮሞ ኮሚኒቲ” ለብቻው ሰብሰቦ ገንዘብ ያሰባሰብ ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ ለመድረክ የሚገባ አይደለም፡፡ ከዚህ በሚተርፈው ጊዜ የአንድነት ድጋፍ ሰጪዎች ስብሰባ እንዲጠሩ ጥያቄ ቀረበላቸው፡፡ የአንድነት ድጋፍ ሲጪዎች በጣም በሰለጠነ ሁኔታ ስብሰባ አድርገው በቂ ዝግጅት ሳይደረግ ድንገት የዚህ ዓይነት ስብሰባ መጥራት እንደሚቸገሩ አስታወቁ፡፡ በወቅቱ ደግሞ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል አንድነት ለጀመረው ዘመቻ ድጋፍ እያሰባሰቡ ስለሆነ ተጨማሪ ሌላ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ለማድረግ ጊዜ እንደሚወስድባቸው ምክንያታቸውን ገለፁ፡፡ ይህን ለዶክተር ነጋሶም፣ለዶክተር መረራም ተነግሯል፡፡ ዶክተር መረራ ግልፅ ሆኖ ያልገባው ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ የኦሮሞ ኮሚኒቲን ሰብሰቦ ለድርጅቱ ገቢ እየሰበሰበ፣ የአንድነትን ለመድረክ አድርጉት የሚለውን ዝግጅት ያልተደረገበትን ጥያቄ አንቀበልም ማለት ለምን እንዳሰከፋው አላውቅም፡፡ በግሌ ለመድረክ ገቢ ለመሰብሰብ ዝግጁ መሆኔን በተደጋጋሚ ገልጨለት እያለሁ ግን ለምን ሊከሰኝ እንደፈለገ አላውቅም፡፡
ሌላው ዶክተር መረራ በመድረክ ውስጥ አነድነትን የአማራ ወኪል ለማድረግ የሚሰራውን ሸፍጥ (ኦፌኮ በኦሮሚያ፤ አረና በትግራይ፤ የፕ/ሮ በየነ ድርጅቶች በደቡብ) መታገል ሳይችል “አንድነት ከመድረክ ካልወጣሁ” ብሎዋል በሚል ይከሰናል፡፡ ይህን ሸፍጥ ግልፅ የሚያደርገው መድረክ በ2007 ምርጫ አንድም ዕጩ በአማራ ክልል ያለማቅረቡ ነው፡፡ እውነቱ አንድነት እንደ ፓርቲ ከመድረክ የመውጣት ጥያቄ አንስቶ አያውቅም፤ በግለሰብ ደረጃ የመውጠት ፍላጎት ያላቻው የሉም ማለት አይቻልም፡፡ አሁን ከመድረክ ጋር ለመስራት ሽር ጉድ የሚለው ሰማያዊ ፓርቲ መስራቾች ከአንድነት የወጡበት ምክንያቱ አንዱ የመድረክ ጉዳይ ነበር፡፡ አንድነት የነበረው ጥያቄ መድረክ የእውነት “ግንባር” ወይም “ውህድ” ፓርቲ ይሁን ነበር ጥያቄው፡፡ በግልፅ ዶክተር መረራ የውህደት ተቃዋሚ ሲሆን ሁሉም የመድረክ አባል ድርጅቶች አንድነት ላይ ያላቸው የጋራ ጥያቄ የገንዘብ ምንጫችን ይዋሃድ የሚል ነበር፡፡ በመጨረሻም አንድነት “በሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በጀመረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከኢህአዴግ እኩል የተረበሹት የመድረክ አመራሮች አንድነትን ከመድረክ አግደው፣ እንደ ኢህአዴግ ይቅርታ ካልጠየቀ አይገባም ሲሉ የአንድነት አባላት ደግሞ መድረክ ሲታዘል ተንጠልጥሎ የቀረ ሰለሆነ ከጫንቃችን ይውረድ ብለው ወስነዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ ውሳኔ ነበር፡፡
አንድነት ከመድረክ መልቀቅ ብዙም ሳይወራ አንድነት በሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ላይ በያዘው ግልፅ አቋም መነሻ በስርዓቱ እንዲፈርስ ሲወሰን ከመድረክ ባንወጣ አንድነት ሳይፈርስ እንደሚቆይ እንረዳለን፡፡ ውሳኔያቸን ግን አሁን መድረክ እና አባል ድርጅቶቹ ባሉበት አቋም በፓርቲ ሰም ከመኖር ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ባሳየነው ቁርጠኝነት የበለጠ እንደሰታለን፡፡ አንድነት ከመድረክ ወጥቶም በግዛቸው ሸፈራው መሪነት ቢቀጥል መንግሰት ይህን አሳፋሪ እርምጃ አይወስድም ነበር፡፡ ምክንያቱም ባለበት የሚረግጥ ፓርቲ ማንም አይፈራውም፡፡ ግብ አስቀምጠን የምንሄድበትን አውቀን ስንሄድ ነው ፈተናው የመጣው፡፡ ዶክተር መረራ እንደፃፈው አንድነት የፈረሰው ከባለራዕይ ወጣቶች፣ ከሀረና፣ ከኦፌኮ፣ ወዘተ በመጡ አምስተኛ ረድፈኞች አይደለም፡፡ ከተለያየ ፓርቲ ወጥተው በተለይ ከብሄር ፓርቲ ለቀው አንድነትን የተቀላቀሉ ወጣቶች አንድነት ዶክተር መረራ እንደሚለው የአማራ ልሂቃን ሳይሆን የሁሉም ቤት መሆኑን በመረዳታቸው ነው፡፡ ይህን መራራ እውነት ደክተር መረራ መቀበል የግድ ነው፡፡ አንድነት የሁሉም ቤት መሆኑ ያስፈራው መንግሰት ያለምንም አፍረት አንድነትን ለማፍረስ የተነሳውም በተለይ በኦሮሚያ ስናደርገው የነበረው ያልተጠበቀ ንቅናቄ ጭምር ነው፡፡ አንድትን ለማፍረስ የተሰለፉት ሆዳሞች ደግሞ ከሁሉም ሰፈር የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የድርጅት ስራችን ክፍተት መሆኑን እናምናለን፡፡
በመጨረሻ ዶክተር መረራ የአምቦ ወጣቶች እሰኪነግሩት ተሸፍኖበት የነበረው አውነት “የከብት ሌባን የሚጠብቀው ባለቤቱ ነው፤የኮሮጆ ሌባን የሚጠብቀው ህዝብ ነው፡፡” የሚለው ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ በ2007 ምርጫ እሳተፋለሁ ሲል በአደባባይ የተናገርነው “ምርጫ ቦርድን ቁጥር ደማሪ እናደርገዋለን” የሚል ነበር፡፡ አንድም ምርጫ ጣቢያ ላይ ድምፁን የሚጠብቅ ህዝብ ካለሰለፍን ብንሰረቅም አንጮህም ብለን ተነሰተን ነበር፡፡ አሁንም ዶክተር መረራ ዘግይቶም ቢሆን እንደተረዳው የኮሮጆ ሌባን ለመጠበቅ የሚቆም መረጫ በሌለበት ምርጫ ፌዝ ነው፡፡ ለመምረጥ የተመዘገበ፤ ለሚደግፈው ድምፅ የሚሰጥ፣ የሰጠውን ድምፅ በትክክል የሚቆጥር ህዝብ ሲኖር ምርጫ ወደዲሚክራሲ መሸጋገሪያ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይሆን የሚከለክል መንግሰት ደግሞ በሌላ መንገድ ወንበሩን ለመልቀቅ መረጧል ማለት ነው፡፡
ቸር ይግጠመን!!!