ጥቅምት 3/2007
ክቡር የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት በምክር
ቤቱ ደንብ መሰረት መሰከረም 26/2007 ዓ.ም ለሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ንግግር በማቅረባቸው ምሰጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በተለይ
ባልተለመደ ሁኔታ የተሟላ ባይሆንም በመብራት መቆራረጥ ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ ለመጠየቅ ድፍረት በማሳየታቸው ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡
ይህን ስናበረታታ ከፍ ወዳለው ተጠያቂነትን ወደ መውሰድ ያድጋል የሚል ተሰፋ ስለአለን ነው፡፡
ክቡር ፕሬዝዳንቱ ባቀረቡት የመክፈቻ
ንግግር ላይ የተካተቱ እና ተገቢ ያልሆኑ ወይም ያልተሟሉ እና መሻሻል የሚገባቸው ያልኳቸውን ነጥቦች አቀርባለሁ፣
F በየዘርፉ በቀረበው ሪፖርት ያለፈውን
አራት ዓመት አፈፃፀም ያካተተ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአብዛኛው የቀረበው መንግሰት ተሳክቶልኛል ብሎ በሚያምነው አካባቢ ነው/ ያለመሳካታቸው
የታመነው ከወጪ ንግድና ከውሃ አቅርቦት የመሳሰሉት በስተቀር/፡፡
በሪፖርቱ መግቢያ ላይ ባለፉት አራት ዓመታት ሁለት አሀዝ እድገት እንደተመዘገበ በያዝነው ዓመትም 11.4 እንደሚሆን ይገልፃል፡፡
ይህም ማለት በእድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተቀመጠው 11.2 ግብ አሳክተናል እንደማለት ነው፡፡ አሁን በመሬት ላይ ያለው
ሀቅ ግን፣
o
የባቡር
መስመር ከታቀደው 2395 ኪሎሜትር100 ኪሎ ሜትርም አይጠናቀቅም (ሁላችንም እንድናተኩር የሚፈለገው በአዲስ አበባ 34 ኪሎ ሜትር
ላይ ብቻ ነው)፤
o
662
ሚሊዮን ዶላር በዓመት የውጭ ምንዛሪ ያስገባል የተባለለቻው የሰኳር ፋብሪካዎች፣ ወደ ውጭ መላኩ ቀርቶ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከውጭ
ግዥ እየተከናወነ ነው፤
o
የማንፋክቸሪን
ሴክተር እየተሰፋፋ አይደለም፣በዚህ ዘርፍ ለመሳተፍ የሚመጣ ባለሀብት ቢኖር እንኳን ሊያስተናግደው የሚችል የሀይል አቅርቦት የለም
(8000 ሜጋ ዋት ይኖረናል ተብሎ የነበረው በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 3500 መድረስ ከተቻለ ትልቅ ስኬት ነው)፤
o
የመንገድ
ግንባታ ከታቀደው ግማሽ መሰራት የሚቻል አይመስለንም፤
o
የትላልቅ
ዘመናዊ እርሻዎች ታቅደው የነበረው 3ሚሊዮን ሄክታር ለአልሚዎች ለመስጠት አስር በመቶ እንኳን የተሳካ አይደለለም፣ የተሰጣቸውም
ቢሆኑ በአግባቡ እየሰሩ እንዳልሆነ ይታወቃል፤
o
በምግብ
እህል እራሳችንን ጭለናል የሚል ፕሮፓጋንዳ ቢኖርም ሰንዴ አሁን ከውጭ እየገዛን ለዋጋ ማረጋጋት በሚል እየቀረበ ነው እየቀረበ ነው፤
እነዚህን ዋና ዋና የልማት ግቦች
ማሳካት ባልተቻለበት ሁኔታ በዕቅዱ የመጀመሪያ ሶስት ዓመታት የነበረውን እጅግ አሳሳቢ የዋጋ ንረት ጋር ተደምሮ የእድገቱ ቁጥር ለዕቅዱ ሊቀንስ ያልቻለው ምን የተለየ እነዚህን ጉድለቶች
ማካካሻ ተገኝቶ ነው? የሚል አጠቃላይ አሰተያየት አለኝ፡፡ የእነዚህ ጉድለቶች ለእድገት ምጣኔ ትርጉም የላቸውም አንባልም ብዬ ነው፡፡
F በሪፖርቱ ገፅ 4 ቁጠባ በእድገትና
ትራንሰፎሜሽን ከታቀደው በላይ መድረሱን ነገር ግን ከዚህ በላይ መስራት የሚያስችል አቅም እንዳለ ይገልፃል፡፡ አሁን የተገኘውም
ውጤት በከተማ የቤቶች ግንባታ እና በቦንድ ሸያጭ የተገኘው ከፍተኛ ነው፡፡ ሪፖርቱ የግብርናው ሴክተር የኤኮኖሚው የጀርባ አጥንት
ሆኖ ቀጥሎዋል በተለይም አነሰተኛ ማሳ በሚያካሄደው የአርሶ አደር ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አሰቀምጦዋል፡፡ ከዚህ ሴክተር ቁጠባን በተገቢ
ሁኔታ ማግኘት ያልተቻለው እና ለሀገር ውስጥ ገቢም ይህ ነው የሚባል ድርሻ ያልታየበት ምክንያት በሪፖርቱ ውስጥ አልተገለፀም፡፡
አሰተያየቴን ግልፅ ለማድረግ ሚሊየነር አርሶ ሀደሮች በቁጠባና በግብር ከፋይነት ያላቸው ሚና ምን ያህል እንዲሆነ አይታወቅም ለማለት
ነው፡፡ ሁሌም ሲሸለሙ እንጂ ግብር ከፈሉ ሲባል ሰለማንሰማ ነው፡፡
F በሪፖርቱ ገፅ 4 ላይ “… ሀገራቸን
ምንም እንኳን በመንግሰት ዋስትናም ሆነ ከዚያ ውጭ የምትወስደው የብድር መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም በተለያዩ የዕዳ
ጫና መለኪያዎች መሰረት ዝቅተኛ የዕዳ ጫና ካላቸው ሀገሮች ተርታ ትገኛለች፡፡….. ይህም ተጠብቆ ይቀጥል፡፡” ይላል፡፡ በቅርቡ
የኢንተርሸናል ሞነተሪ ፈንድ ያቀረበው ሪፖርት እንዲሁም የዓለም ባንክ የሚያወጣቸው ፅሁፎች ከዚህ በተቃራኒ መንግስት ለመሰረተ ልማት
ግንባታዎች የሚወሰዳቸውን ብድሮች ተጠቃለው የማይታዩ በመሆናቸው እነዚህ ብድሮች ጫናቸው ከፍተኛ ነው ብሎዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ
ሰምምነት መድረስ አለመቻሉም ተዘግቦዋል፡፡ መንግሰት የሚገነባቸው የመሰረተ ልማት አውታሮች ከመንግሰት በጀትም ሆነ የብድር ዕዳ
ውስጥ ለማሳየት ያልተፈለገበት ምክንያት ተቀባይነት ያለው አይመስለኝም፡፡ ሪፖርቱም ከዚህ አኳያ ሙሉ ነው ማለት አይቻለም፡፡
F በሪፖርቱ ገፅ 6 “… ሀገራዊ ባለሀብቱ
አሁንም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው ተሳትፎ አነሰተኛ ነው፡፡ በያዝነው ዓመት ማነቆዎችን ለመፍታት ተዋናዮችን ያሳተፈ ጥረት ይደረጋል፡፡”
ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር እጅግ ተሰፋ ሰጪ የሆነ የሀገር ውስጥ ቁጠባና ኢንቨሰትመንት በሚያበረታታ መልኩ በአክሲዮን ተቋቁመው ወደ
ሰራ ለመግባት በጅምር ላይ የነበሩ ለምሳሌ ሀበሻ ሲሚንቶ፤ ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስም የጠቀሱት ህብር ስኳር ለመሳሰሉት
ትላልቅ የግል ባለሀብት ለሚመጡ ተነሳሸነቶች በቂ ትኩረትና ድጋፍ አለመስጠቱን ስናይ ሪፖርቱ በተግባር ካለው ጋር የሚጋጭ ነው የሚል
አስተያየት አለን፡፡ አሁንም በዚህ ዓይነት ከመንግሰት ውጭ ለሚመጡ ተነሳሽነቶች ምንም ዝግጅት አይታይም፡፡
F በቤቶች ልማት በሪፖርቱ የቀረበው
ቁጥር እና በሚሊዮን ከሚቆጠረው ቤት ፈላጊ ጋር ሲነፃፀር አሁንም ተመጣጣኝ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ
ወቅት እንዳልኩት መንግሰት የተመዝጋቢዎቹን ፍላጎት በማርካት ተሰፋቸውን ያለመልማል ብዬ አላምንም፡፡ ይህ ፕሮግራም መንግሰት ባለው
አቅምና ቁርጠኝነት ላይ የሚፈተንበት እንደሚሆን አሁንም እምነቴ ነው፡፡ በሪፖርቱ ውስጥ “ በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩ ዜጎች በተያዘው
አቅጣጫ መሰረት የሚሰተናገዱ ይሆናል፡፡” ይላል፡፡ ይህ አቅጣጫ ምንድነው? ዜጎች ተበድረው ገንዘብ ባንክ ካሰገቡ በኋላ የመንግሰት
የአቅጣጫ ለውጥ እና የአዳዲስ መመሪያና አቅጣጫ ፍለጋ የገባበት ምክንያት መታወቅ ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ ጋር
ተያይዞ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተያዘው አቅጣጫ ግብር ከፋዩ ዜጋ በግልፅ ሊያውቀው ስለሚገባ ግልፅ
መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡
F በሪፖርቱ ገፅ
11 “…. የሰኳር ልማት እና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎች በከፍተኛ ትኩረት እና ክትትል በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ርብርብ
ይደረጋል፡፡” ይላል፡፡ ለምንድነው ልክ የህዳሴ ግድቡ የደረሰበት ደረጃ እንደሚነገረው እነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች የደረሱበት ደረጃ
በግልፅ የማይገለፀው? በዚሁ ገፅ ላይ የመጠጥ ውሃ በተመለከተ በዕቅድ የተቀመጠው እንደማይደረስ ታምኖዋል፡፡ ስንት ለማድረስ ነው
ክለሳ የተደረገው፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ መረጃ ሲያቀርቡ የነበሩ ተጠያቂ ሆነዋል ወይ? የሚለውን ሪፖርቱ ማካተት አልቻለም፡፡
F በሪፖርቱ ገፅ 15 “በ2007 በሀገራችን
የሚካሄደው ሃገራዊ ምርጫ ነፃና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲሰሩ መንግሰት የሚጠበቅበትን ሁሉ
ያደርጋል፡፡ ሁሉም ተዋናይ ወገኖች ዋናው ፈራጁና ወሳኙ ህዝብ በሀገራቸን
የተፈጠረውን ሰፊ የሃሳብ ግብይት ዕድል በመጠቀም ደረጃ በደረጃ እየጎለበተ የመጣውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ኃላፊነት
በተሞላበት መንፈስ ወደሌላ ከፍታ ማሸጋገር ይጠበቅብናል፡፡” የሚል ነው፡፡ በእኛ እይታ
o
ኢህአዴግ
አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ መንግሰት የሚጠበቅበትን ሁሉ እያደረገ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ የኢህአዴግን ፖሊሲ
ለማስረፅ በመንግሰት ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎች ረጅም ጊዜ የወሰደ ውይይት ሲያደርግ ነበር፡፡ እኛም ያለንን አማራጭ ለመግለፅ ለአንድ
ቀን ፈቃደኛ የሆኑ ተማሪዎችና መመህራን የሚገኙበት ሁኔታ ሊያመቻችልን ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በተደረጉት ውይይቶች ለህዝቡ ከሰብሰባው
ምን እንደተማራችሁ መግለፅ ቢችሉ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
o
በምርጫ
መቼም ዋናው ተዋናይ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ እንደ አንድ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ በየወረዳው ከመንግሰት ያገኘው ፅ/ቤት
አለው፡፡ አንድነት እንደ ፓርቲ ቢሮ ለመከራየት ችግር ላይ ነው፡፡ የገንዘብ አይደለም በህዝቡ ላይ ካድሬዎች በሚፈጥሩት ስጋት ነው፡፡
ይህን እንደ መንግሰት አንድ ቢሮ ለመስጠት ፈቃደኛ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ወይም ባዶ ቦታ ቢሰጠን ደረጃውን የጠበቀ ቢሮ ልንገነባበት
የምንችል እንደሆነ ላረጋግጥሎት እችላለሁ፡፡
o
“ሰፊ
የሃሰብ ግብይት ዕድል መጠቀም” ማለትስ ምን ማለት ነው? የግል ሚዲያ እንዳይኖር ተግቶ የሚሰራ መንግሰት፣ ብሎገሮችን የሚያስር
መንግሰት፣ የመንግሰትን ሚዲያ ለገዢው ፓርቲ መጠቀሚያነት ብቻ እንዲውል ለወሰነ መንግሰት ሰፊ የሃሳብ ግብይት ተፈጥሮዋል ለማለት
ድፍረቱ ከየት እንደመጠ ግልፅ አይደለም፡፡
ሰለሆነም እነዚህ አገላለፆች ከሪፖርቱ
ውስጥ እንዲወጡ ወይም እንዲሻሻሉ ቢደረግ መልካም ነው እላለሁ፡፡
ክቡር ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ ያልተካተቱና እንዲካተት ወይም ተገቢው ትኩረት
እንዲሰጣቸው የምንፈልጋቸው ጉዳዮችን በዋና ዋና ርዕስ በማድረግ አቅርባለሁ፡፡
ፖለቲካዊ ጉዳዮች፤
F የ “ፀረ ሽብር ህግ” ሲወጣ እንደ
ምክንያት ቀርቦ የነበረው ምርመራን ለማቀላጠፍ እንደሆነ ሲገለፅ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ በፓርቲ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ
የሚያደርጉ ወጣቶችን እነ ሀብታሙን፤ ለሰላማዊ ለውጥ የሚተጉ ብሎገሮችን፤ አሰሮ ምርመራ እያደረኩ ነው ብሎ ማንገላትት ለዚህች ሀገር
የሚጠቅም አይደለም፤ከዚህ ቀደም በወህኒ ቤት የሚገኙ ጓዶቻችን እነ አንዱዓለም ናትናኤል በቀለ ገርባ እንዲሁም ጋዜጠኞች እስክንድር፣ ርዕዮት የመሳሰሉት የህሊና እስረኞች ናቸው ብለን ስለምናምን
አሁንም ፖለቲካው መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው ብለን እናምናል፤
F በአሁኑ ሰዓት መንግሰት በውጭ ከሚኖሩ
ኢትዮጵያዊያን ጋር የገጠመው አላስፈላጊ ግብ ግብ ለልማት ልናውለው የምንችለውን አቅም ከማባከን ያለፈ አንድም ፋይዳ ስለማይኖረው
በሁለቱም ወገን ስክነት በተሞላበት ሁኔታ በውይይት እንዲፈታ ማድረግ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ በግንባር ቀደምነት መውሰድ
ያለበትም መንግሰት ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ይህ ሲሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው የሚያደርጉትን
አስተዋፆ አሁን በሪፖርቱ ከተገለፀው በላይ ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት ስለአለን ነው፡፡
F ባለፈው ዓመት ሪፖርት “የመድበለ
ፓርቲ ሰርዓቱን ለማጠናከር ይቻል ዘንድም መንግሰት በህገ መንግሰታዊ ሰርዓት በተበጁ ህጋዊና ሰላማዊ ስልቶች ዓላማቸውን የሚያራምዱ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያደርጓቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡”የሚለው
በዝርዝር ተቀምጦ ለክትትል/ለመጠየቅም በሚመች መልኩ ቢቀመጥ መፍትሄ ይሆናል፡፡ የሚል አስተያየት የሰጠሁ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኝም
እንደዛ ሆኖም አንድም ነገር ሳይከናወን ዓመቱ ተጠናቆዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ በሀገር ውስጥ ለሚደረግ እንቅስቃሴ
መንግሰት የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ግልፅ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፡፡
F ዛሬም እንደ ሁልጊዜው በድጋሚ መግለፅ
የምፈልገው ተቃዋሚዎች እና ገዢው ፓርቲ በማንስማማባቸው የርዕዮት ዓለምና ፖሊሲ ዙሪያ በግልፅ ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጋራ
የሀገር ጉዳይ እስከአሁን የሄድንበት ቅጥ ያጣ ፍረጃ እንዲቆም ማድረግ፤ ልዩነታችንን የምናራምድበት መድረክ በእኩልነት ማግኘት
(በአስተዳደራዊና በፀጥታ ሀይሎች በኩል የሚደርስብን በደል እንግልት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማስቀረት)፤የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው
ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡ በተለይ በዚህ የምርጫ ዓመት ለምርጫ በሚደረግ ቅስቀሳ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ብለን እናምናለን፡፡
F የፖለቲካ ምዕዳሩን መሰፋትና መጥበብ
ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ሁኔታ በመረዳት፤በጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ ከህግ ውጭ ማተሚያ ቤቶች እንዳያትሙ የሚያስፈራሩ
ካድሬዎችን፤ ከህግ አግባብ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ከውንብድና የሚለዩ ባለመሆናቸው ማሰቆም የማይችል እንዲሁም ይህንን
ድርጊት ደግ አደረጉ የሚሉ የመንግሰት ሹሞችን አደብ የማያስገዛ መንግሰት ጠመንጃ ካነሱበት ይልቅ በሃሳብ ሊታገሉት የተነሱትን እንዲመፈራ ማሳያ ብቻ
ሳይሆን በሃሳብ ለመፋለም ዝግጁ ያለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
F ምርጫ በሚመለከት ምርጫ
መወዳደር ለፓርቲዎች መደበኛ ተግባር እንደሆነ ይታወቃል፤ ለህዝብ ምርጫ እንዲሳተፍ ሲጋበዝም አማራጭ መኖሩን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፤
ከዚህ አንፃር መንግሰት አማራጭ የሌላቸው ተቃዋሚዎች የሚለውን በመተው አማራጫችንን ልናቀርብ የምንችልባቸውን በህግ የተፈቀዱትን
ስርዓቶች እንዲያሰከብርልን በድጋሚ እንጠይቃለን፤በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚመጣ ማነኛውንም ውጤት ለመቀበል ግን ገዢው ፓርቲ ዝግጁ
መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
F በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች
ዜጎች በብሔራቸውና የሚናገሩትን ቋንቋ መሰረት በማድረግ እንዲፈናቀሉ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የፌዴራል መንግሰትን ጣልቃ ገብነት
እስከ መጠየቅ ደርሶዋል፡፡ ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ቦታ የመኖር ህገ መንግሰታዊ መብት ከመቼውም በላይ አደጋ ላይ እየወደቀ
ነው፡፡ ይህ ደግሞ በህገ መንግሰት እውቅና ያገኘውን አንድ የፖለቲካ ማህበረስብ ምስረታ አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር
መንግሰት ችግሩን ከሰሩ ለመፍታት አቅም እንዳነሰው ማሳያ ነው፡፡ መንግሰት የችግሩ ምንጭ ከላሆነ ማለት ነው፡፡
ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተመለከተ
F አዲስ አበባ ከተማ ላይ እየቀረበ
ያለ የሊዝ ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ምንጩ አሁንም በቁጥ ቁጥ እየቀረበ ያለ የመሬት አቅርቦት ሲሆን፣ በእኛ እምነት ይህን ቦታ በዚህ
ዓይነት ዋጋ እየገዙ ያሉ ሰዎች ልማታዊ ባለሀብቶች ናቸው ብለን ለመውሰድ እንቸገራለን፡፡
ይህ ሁኔታ በመኖሪያ ቤትም ሆነ በአገልግሎቶች ላይ የዋጋ ንረት እንደሚፈጥር ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በህገ ወጥ መንገድ
የተገኙ ገንዘቦች መመሸጊያ እንዳይሆን ሰጋት አለን፡፡ 65 ሺ ብር በካሬ ገዝቶ ምን ሊነግድበት እንደሆነ ማወቅ ከባድ ነው፡፡ መንግስት
በአዲስ አበባ የሊዝ ሰርዓት ላይ ተገቢውን ማስተካከያ ማድረግ እንደሚችል ካላረጋገጥ ይህች ከተማ ለመካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው
ዜጎች መኖሪያ አይደለችም ብሎ እንደማወጅ ይቆጠራል፡፡
F ሀገራችን ኢትዮጵያ ንግድ ለመጀመር
2013 ከ 185 ሀገሮች 163 ከነበረችበት በ2014 ወደ 166 ዝቅ ብላለች፣ የሚገርመው ታክስ ለመክፈል ከነበረችበት 103 ወደ
109 ዝቅ ብላለች ይህን መንግሰት የኒዎ ሊብራል ሪፖርት ሊለውና ችላ ሊለው ቢችልም ለኢንቨሰትምንት የሚመጡ ባለሀብቶች ግን እምነት
የሚጥሉበት ሪፖርት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ኢንቨሰትመንት ለመሳብ እየሰራን ነው እየተባለ ውጤታችን ዝቅ የሚልበት ምክንያት ማወቅ
መፍተሔውን ለማግኘት ይረዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ ታክስ ለመክፍል መቸገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታክስ የምንከፍል ሰዎች እናውቀዋለን፡፡
ማሕበራዊ ጉዳዮች
F ወደ ተለያዩ ሀገሮች ለስራ በተለይ
ወደ ሀረብ ሀገራት የሚሄዱ ሰዎች ህግድ ሳይነሳ በመቆየቱ ህገወጥ ዝውውሮች እየተበራከቱ መሀኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በሀገራችን
ያለው እድገት ዜጎችን ከሰደት መታደግ እስኪችል በህጋዊ መስመር እንዲሄዱና ለዜጎች ተገቢው ጥበቃ ማድረግ የሚችል መንግስት መሻታችን
ይቀጥላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ክፍተት ያለበት ሪፖርት ነው ብዬ ነው የምወሰደው፡፡
F አሁንም ዜጎች ለህክምና ወደ ውጭ
እየሄዱ ከፍተኛ ወጪ እንደሚዳረጉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር በእድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ በተቀመጠው መሰረት ውጤት ማምጣት
አልተቻለም፡፡ ይህ ጉዳይ አሁንም ይህች ሀገር የግል ባለሀብት በዚህ መስክ ለመሳብ ካለብን ችግር ጋር የተያያዘ መሆኑን ሪፖርቱ
መግለፅ የቻለ አይደለም፡፡
በመጨረሻም
መንግሰት/በተለይም ገዢው ፓርቲ በቀጣይ
ምርጫ ከግል ቡዳናዊ አስተሳሰብ ወጥቶ ለሀገር በሚበጅ መልኩ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እየጠየቅን፤
በእኛ በኩል በኃላፊነት ሰሜት እንደምንንቀሳቀስ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅ አማራጭ እንዳለን የምናሳይበት እንደሚሆን ለኢትዮጵያ
ህዝብ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያ ሀገራችንን እና ህዝቧን
ይባርክ!!!!!!
አመሰግናለሁ
ግርማ ሠይፉ ማሩ