Sunday, December 14, 2014

ህገ መንግሰቱን የሚንደው ማን ነው?




ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; girmaseifu.blogspot.com
በአገባደድነው ሳምንት መጀመሪያ ህዳር 29 ቀን በከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የ “ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች”  ቀን ተክብሮ ውሎዋል፡፡ “ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች” የሚሉት ሶሰት ቃላቶች ቢሆኑም በህገ መንግስት ውስጥ አንድ ትርጉም የተሰጣቸው ቢሆንም ባለቤቶች ነን የሚሉትም ቢሆኑ በውል ያልተረዷቸው ተምኔታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ ወጣም ወረደ ግን እነዚህ ቃላቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልዕ ቦታ ያላቸው እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ እኛም እነዚህን ቃላቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉልዕ ቦታ የያዞ መሆናቸውን አምነን ተቀብለናል፡፡ ይህ ማለት ግን ገብቶናል ማለት አይደለም፡፡ ይህ በየክልሉ በዙር የሚከበረው ባህል ታስቦበት ህገ መንግሰት ከጸደቀበት እለት ጋር የተገናኘ ስለሆነ እለቱን ከህገ መንግሰት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የሚነሱበት ብናደርገው ክፋት የለውም፡፡ ስለዚህ ባለፉት 20 ዓመታት ይህ ህገ መንግሰት ምን ሰጠን ምንስ ነፈገን ብለን መጠየቅ እና የተወሰኑ ማሳያዎች ማቅረብ ተገቢነት ያለው ይመስለኛል፡፡
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ባለፈው ሳምንት ዕትም በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ እንዳስቀመጠው ህገ መንግሰታችን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የህግ ግዴታ ለማይጣልባቸው “ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” ለሚባል ሃሳባዊ ስብስብ ተሰጥቶ ህገ መንግሰቱ የናንተ ነው ተብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ህገመንግሰቱ የማንም እንዳይሆን ተደርጎዋል ብሎናል፡፡ ይህ የሆነው ግን በስህተት የሚመስለው ካለ ተሳስቶዋል፡፡ የማንም ያልሆነን ማለትም ባለቤት የሌለወን ነገር በአደራ ለመጠበቅ በሚል ለረዥም ጊዜ በስልጣን ለመቆየት የተደረገ ደባ እንደሆነ መረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የዚህን ሴራ ማሳያ የሚሆን ምሳሌ ከዚህ በታች ማቅረብ ጉዳዩን ግልፅ ያደርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፕሬዝዳንትነት የጀመሩትን በታሪክ አጋጣሚ የተገኘ ሀገር የመምራት ተልዕኮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያወርዱት በፕሬዘደንታዊ ስርዓት (በቀጥታ የህዝብ ምርጫ ስልጣን የሚይዝ) ፕሬዝዳንት መሆን ጠልተው አይደለም፡፡ በዛን ጊዜ በነበረው ነባራዊ ሁኔታ አቶ መለስ ዜናዊን ማንም ሀገር ወዳድ ተነስቶ ዕጩ ሆኖ ቢቀርብ ሊያሸንፋቻው እንደሚችል ስለሚያውቁ ከዚህ የተለየ አደረጃጀት መከተል ነበረባቸው፡፡ ይህም በድርጅታዊ አሰራር በሚስጥር ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የሚያሰችል ዘዴ መከተል ነው፡፡ ይህ ህውሃት እንደ ቡድን አቶ መለስ ዜናዊ በግል ያለባቸውን ያለመመረጥ ስጋት ካነሱት ነጥቦች አንዱ በ1987 አይደለም ዛሬ ከሃያ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያዊያን የባህር በር አጥተው መታነቃቸውን ለመዘንጋት አልተቻላቸውም፡፡
ከዓለም የባህር በር ከሌላቸው ሀገሮች በህዝብ ብዛት አንደኛ መሆናችን ብቻ ሳይሆን በቅርብ ርቀት በባሕር በር ላይ ተገኝተን የበይ ተመልካች መሆናችን ታሪክ ይቅር የሚለው ስህተት አይደለም፡፡ የዚህ ታሪካዊ ስህተት መሃንዲስ ደግሞ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ሌላው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮ-ኤርትራ የወንድማማቾች ጦርነት ተከትሎ ህዝቡ ለባንዲራ ያሳየውን ፍቅር ተመልክተው የባንዲራ ቀን እንዲከበር አረንጓዴ መብራት ቢያሳዩም፤ እራሳቸው በስታዲየም ተገኝተው “ጨርቅ” ነው ብለው ያጣጣሉትን ባንዲራ በክብር ቢሰቅሉትም ህዝቡ ባንዲራ “ጨርቅ” ነው የሚለውን የአፍ ወለምታ ሊዘነጋው አልተቻለውም፡፡ በእነዚ እና ሌሎች ብዙ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት ዜጎች በቀጥታ የሚመራቸውን መሪ እንዳይመርጡ ያደረገ ህገ መንግስት ነው፡፡
ባንዲራን በሚመለከት የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት በግልፅ የኢትዮጵያ ባንዲራ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ነው ብሎ ደንግጓል፡፡ በተጨማሪም አርማ እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡ አርማው ላይ ካልተስማማን በሚያስማማን የባንዲራው ይዘት ላይ አብረን መቆም እንችላለን፡፡ በግሌ ከዚህ ቀደም ከነበሩት አርማዎች የአሁኑ የተሻለ ነው የሚል እምነት ቢኖረኝም ሁሉም ዜጋ ይህ አርማ የሌለበት ባንዲራ መያዝ አለበት የሚለውን ህገ ወጥ የህግ ድንጋጌ ግን ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ መንግሰት በኤምባሴዎች፣ በመንግሰት ተቋማት አርማዬ ያለውን የማድረግ ግዴታ ቢጥል ግድ የለኝም፡፡ በግል አርማ ካላደረጋችሁ የሚል አስገዳጅ ህግ ማውጣት ግን መንግሰት ጉልበተኛነቱን ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ይህ አርማ ከልብ የሚፃፍ እና በፍቅር ሊወደቅለት የሚችል ሊያደርገው አይችልም፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት ከማነኛውም ጊዜ እና ምን አልባትም በፅሁፍ ደረጃ ከማንም ሀገር በተለየ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ህገ መንግስታዊ ዕውቅና የሰጠ ነው ቢባል ማገነን አይሆንም፡፡ ምን ያደርጋል እነዚህ ድንጋጌዎች በወረቀት ላይ የቀሩ ናቸው፡፡ በደም የተፃፈ የሚባለው ህገ መንግሰት በቾክ እንደተፃፈ መቁጠር የተሳናቸው የመንግስት ሹሞች እንደ አፈተታቸው ሲደፈጥጡት ይታያሉ፡፡ ዜጎችን በአደባባይ ከመደብደብ ጀምሮ በዓለም ላይ የቀረ ቶርች የሚደረግባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ በህገ መንግሰት እውቅና ያገኘን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች በ “ፀረ ሽብር ህግ” ተደምስሶዋል፡፡ የሰው ልጅ ክቡርነት ዋጋ አጥቶ በህዝብ ስም ስልጣን ለማቆየት ምንም ዓይነት እርምጃ የሚወሰድባት ሀገር ሆናለች፡፡ ይህ ደግሞ ባለበቤት የሌለው ህገ መንግሰት ያመጣው ትሩፋት ነው፡፡ የህገ መንግሰት ባለቤት የተባሉት “ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” የህግ ተጠያቂነት የሌለባቸው ብቻ ሳይሆኑ ሰብዓዊነትም የሌላቸው ስለሆኑ መብታችን ተነካ ሊሉ አይችሉም፡፡ እስር ቤት አይገቡም፡፡ የሚታሰረው ሰው ነው፤ ሰብዓዊ መብቱ የሚጣሰውም ሰው ነው፡፡ ዜጋው የህገ መንግስት ባለቤት ለመሆን በቡድን ውስጥ መገኘት የግድ ይለዋል፡፡ እኔ ለምሳሌ እነዚህ ቡድኖች ውስጥ ለመገኘት ፍላጎትም ምኞትም ስለሌለኝ ይህ ህገ መንግሰት የእኔ ነው ብዬ በግድ የራሴ ለማድረግ ከመታገል ውጭ ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡
ገዢው ፓርቲ በቡድናዊ አስተሳሰቡ በመወጠሩ የእኔ ዓይነት አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ህገ መንግሰቱ የእኛ እንዲሆን የምናደርገውን ጥረት ህገ መንግሰት መናድ ነው ብሎ የቡድን ጠብ ለማስነሳት ይታትራል፡፡ በዚህ ዓይነት የቡድን አስተሳሰብ ውስጥ ለሚገኙ የኢህአዴግ አባላትም ሆነ አጋሮች ማረጋገጥ የምፈልገው አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ ይህም ቁም ነገር፤
“ይህ ህገ መንግሰት ከነ እንከኑም ቢሆን እንዲከበር የምንፈልግ መሆኑን ብቻ ሳይሆን   ለማሻሻል የተቀመጡት ድንጋጌዎች ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ቢሆኑም በዚሁ መስመር ብቻ እንዲሰተካከል እንደምንታገል ማወቅ አለባቸው፡፡”
ይህ ማለት ግን በህገ መንግሰቱ በተቀመጠው መሰረት እንዳይሻሻል ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ የለም ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ዋነኛው ተጠያቂ ገዢው ፓርቲና መንግሰት ብቻ ናቸው የሚሆኑት፡፡ ገዢው ፓርቲ እና መንግሰት በዚህች ሀገር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሊኖር የሚችልበት እድል ዘግተው በነውጥ ወይም በጠመንጃ ለውጥ ከመጣ ይህ ህገ መንግሰት ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ህገ መንግሰቶች ታሪክ ሊሆን ይቸላል፡፡ ይህ እንዲሆን ፍላጎት የሌለን ሰዎች ህገ መንግስቱ ያሉበትን ችግሮች በህግ ስርዓት ብቻ እንዲሻሻል እንፈልጋለን፡፡ ይህ ባልተሟለበት ሁኔታ አንድ ፊደል በፍሉድ ሳይጠፋ ህገ መንግሰቱ እንዲከበር እንፈልጋለን፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ግን መንግሰት ህገ መንግሰቱ እንዲናድ እና ወደ መቃብር እንዲወርድ ተግቶ እየሰራ ነው፡፡ ይህን ስንታዘብ  ህገ መንግሰቱ እንዲናድ የሚሰሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአሁኑ ሰዓት እየጠየቁ ያሉት በህገ መንግስት በግልፅ የተቀመጡት ሰብዓዊና ዲሞክራሲ መብቶች ይከበሩ ነው፡፡ መብቱ የተከበረለት ዜጋ ለልማት ግብዓት እንጂ ዕዳ ሊሆን አይችልም፡፡ በቁስ በሚገለፁ እድገቶች መብታችንን አሳልፈን አንሰጥም ማለት ህገ መንግሰቱን ማስከበር እንጂ መናድ ሊሆን አይችልም፡፡ ዜጎች ህገ መንግሰታዊ መብታችንን ለማስከበር ነቅተን በምርጫ እንሳተፍ የመዝጊያ መልዕክቴ ነው፡፡
ቸር ይግጠመን




No comments:

Post a Comment