Saturday, December 20, 2014

ጀግኖቻችን እና የፍርድ ቤት ነፃነት!!!

ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; girmaseifu.blogspot,com
በቅርቡ የሚካሄደውን የ2007 ምርጫን  አስመልክቶ የፓርቲዎችን ዝግጅት ምን እንደሚመስል ለመረዳት ኢህአዴግ፣ አንድነት እና ኢዴፓ የወከሉ ሰዎች በፋና ሬዲዮ ባለፈው እሁድ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ መኖሩ ትርጉም ስለአልነበረው ነው እንጂ ሌላም አንድ ፓርቲ ወክያለሁ ያለ ሰው እንደነበር ዘንግቼው አይደለም፡፡ የኢህአዴጉ ወኪል በመጨረሻ ላይ ያቀረቡትን ሃሳብ ሳደምጥ የኢህአዴግ ፓርቲ ወኪል ማንም ቢሆን ተመሳሳይ እንደሆነ መረዳት የምንችለው ነገር አንዳቸውም በተነገራቸው እንጂ በራሳቸው መርምረው ሊደርሱበት የሚፈልጉት ሀቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ በፓርቲው ስብሰባ ከሚሰበካቸው ውጭ ዋነኛ የመረጃ ምንጫቸው የኢትዮጰያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ገፋ ሲል ደግሞ ፋና ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንድደርስ ያደረገኝ ነጥብ ደግሞ የአንድነት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ የነበረው አንዱዓም አራጌ እና ሌሎች የህሊና እሰረኞች ላይ የተፈረደውን የፍርድ ቤት ውሳኔ መቀበልና አለመቀበል ከፍርድ ቤት ነፃነትና ለፍርድ ቤት እውቅና ከመስጠት ጋር ማያያዛቸው ነው፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ባለመስማማት የምንይዘውን አቋም መረጃ የሌለው ነው ብለው የሚያቀርቡት ጉንጭ አልፋ  ክርክር እጅግ አስገራሚ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም አንዱዓለም አራጌ ይፈታ በሚል አንድ ፅሁፍ ፅፌ ነበር አንዱዓለም የታሰረው በ “አሸባሪነት” ነው ለሚሉን መስሚያ የሌለን መሆኑን ብቻ አይደለም የታሰረው የኢህአዴግ ጉምቱ ባለስልጣናት ከእቅዳቸው በፊት ከስልጣን የሚነቀንቃቸው ሰላማዊ ታጋይ መሆኑን በመጠርጠራቸው ነው የሚል ነበር፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙት ደግሞ በምርጫ ሁለት ሺ ሁለት ክርክር ወቅት ተናዳፊ ተከራካሪ ሆኖ በመቅረቡ ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ አንዱዓለም ንቢቱን አስንቆ በስልጣን ሲናገሩ የነበሩትን በመረጃ አስደግፉ ሲያጋልጣቸው ቂም ይዘው እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህን እንድንገምት ያደረገን ደግሞ አንዱዓለም በተከሰሰበት ወንጀል ለዕድሜ ልክ እስር አይደለም ለምክር የሚገብዝ ጥፋት ማጥፋቱን የሚያስረዳ ማስረጃም አልቀረበበትም ምስክርም አልተሰማበትም፡፡ አዳፍኔ ምስክሮችም ቢሆኑ ከእስር ቤት ለመውጣት ቃል የሰጡ ቢሆንም በፍርድ ቤት ገብተው ግን አንዱዓለም ለሸብር ተግባር ወጣት ሲያደረጅ ነበር ብለው ሊመስክሩ አልቻሉም፡፡ የኢህአዴግ ሹሞች በቦታው አልነበሩም፤ እኛ ግን በቦታው ነበርን፡፡
ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠበት መዝገብ በአሁኑ ወቅት ማንም ሰው ሊያገኘው እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ የኢህአዴግ አባላትና ሹማምንት ደግሞ ይህን መረጃ ለማግኘት ከማነኛችንም በላይ እድሉ አላቸው፡፡ እነዚህ የኢህአዴግ አባላትና ባለስልጣናት ይህን የምናቀርበውን ጩኽት ልክ መሆኑን ለማጣራት ለምን ይህን የፍርድ ቤት መዝገብ መርምረው አቋም አይዙም? የሚል ብርቱ ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህ ሹሞች ከላይ እንደገለፅኩት በኢህአዴግ ስብሰባ ወቅት ከሚሰሙት ማብራሪያ እና በመንግሰት ሚዲያ ከሚሰሙት ውጭ ሌላ ነገር አንብበው ለመረዳት ዝግጁ አይደሉም፡፡ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ቢሆኑም ከዚህ ጭፍን መስመር ውጭ አይደሉም፡፡ አንዱዓለም ይፈታ በሚል በፃፍኩት ፅሁፍ እንዲ ብዬ ነበር፤
“መደበቅ የሌለብኝ ዕውነት ግን ከአንዱዓለም ጋር ከምናደርገው የሠላማዊ ትግል ውይይት (አንዳንዴም ጭቅጭቅ የሚባል ቦታ ሊደርስ የሚችል) በተቃራኒ አንድ የሆነ ሠይጣን አሳስቶት - ይህ ሠይጣን ኢህአዴግ ሊሆን ይችላል፤ ማለትም የሠላማዊ መንገዱን ሁሉ እያጠበበ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ - አንዱዓለም ተገዶ ሌላ አማራጭ ፍለጋ ሄዶ ይሆን በሚል የመረጃ ፍለጋ ጉጉቴ አልጨመረም ልላችሁ አልችልም፡፡”
ይህ የሚያሳየው አንዱዓለም ጓደኛ የትግል ጓዴ ቢሆንም ሊሳሳት ይችላል ብዬ መጠራጠሬ አልቀረም ነበር፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትርም ክምር ማስረጃ አለ ብለውን ነበር፡፡ ፍርድ ቤት ከቀረበው ማስረጃ እና ከቀረቡት ምስክሮች ግን አንድም ውሃ የሚቋጥር ነገር ስናጣ፤ ክምር ቀርቶ አንድ ገፅ ወረቀት ሲጠፋ ፍርድ ቤት ወስኖዋል ብለን ከህሊናችን ጋር ተጋጭተን እንደ ኢህአዴጎቹ አንዱዓለም አሽባሪ ነው እንድንል መፈለጋቸው አስገራሚ ብቻ ሳይሆን እነዚህ የኢህአዴግ ሹሞች እንዴት አድርገው እንደሚሰሯቸው መረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡
ይህን ሁሉ በድጋሚ እንድል ያስባለኝ ኢህአዴግን ወክሎ የቀረበው የውይየት ተሳታፊ “በእስር ቤት የሚገኙትን አመራሮችና አባሎች ጅግኖቻችን ማለታችሁ አሁንም በሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ህጋዊና ህገወጥ መስመር እያጣቀሳችሁ ለመሄድ ያላችሁን ዝግጅት የሚያሳይ ነው፡፡” የሚል አስተያየት ሲሰጡ መስማቴ ነው፡፡ የሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ሰላማዊ ሊሆን የሚችለው ሀቅን በመደፍጠጥ እና ፍርድ ገምድል ውሳኔን አሜን ብሎ በመቀበል ሳይሆን ኢህአዴግ በስልጣኑ የመጡበትን ያለምንም ይልኝታ እድሜ ልክም ቢሆን እስር ቤት ለመጎር ደንታ የሌለው መሆኑን በማጋለጥ ነው፡፡ ይህንን ሀቅ ለመመርመር ድፍረት ያገኙ የኢህአዴግ አባላትም ሆኖ ሹሞች በዚህ አይነት ስርዓት ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን ለመረዳት አይቸገሩም፡፡ ይህን ስርዓት በመለወጥ የሚገኘው ትንሳኤ ማንም በግፍና በፍርደ ገምድል ውሳኔ ሰጋት ላይ እንዳይወድቅ የሚያድርግ ነው፡፡ የዚህ ደግሞ ትሩፋት ለኢህአዴግ አባላትም የሚሆን ነው፡፡
የኢህአደግ ሹሞች በዚህ ዓይነት ውይይት ወቅት ከፓርቲያቸው በተቃራኒ መስመር ይቁሙ የምል የዋሃ አይደለሁም፡፡ ይልቁንም እነዚህን ነጥቦች መከራከሪያ ሆኖ ቢመጣ እንኳን ችላ ብለው በማለፍ ከትዝብት ሊተርፉ ይቻላሉ የሚል እምነት ስለ አለኝ ነው፡፡ በሀገራችን ያሉትን ተቋሞች የምናከብራቸው በህንፃቸው ግዝፈት ወይም በቀጠሩት የስው ሀይል ብዛት ሊሆን አይችልም፡፡ ፍርድ ቤቶች ሊከበሩ የሚችሉት በሚያሰፍኑት ፍትህ ነው፡፡ ዜጎች መብቴ ፍርድ ቤት ሄጁ አስከብራለሁ የሚል ደረጃ ሲደርሱ ነው፡፡ በሀገራችን ያለው የፍትህ ስርዓት ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በቤተስብ ውርስ ጉዳይ እንኳን አፋጣኝ ፍትህ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በፍትሃብሔር ጉዳይም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው ደረጃ የወረደ ነው፡፡ ይህ እንዲሻሻል ማሳሰብ እና መታገል ፍርድ ቤቶቸን እውቅና እንደመንፈግ መቁጠር ተገቢ ነው ለማለት አይቻለም፡፡ በተመሳሳይ ፍርድ ገምድል ውሳኔዎችን እንድንቀበል መገደድም የለብንም፤ ብንገደድም ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡ ለዚህ ነው የህሊና እስረኞችን ጅግኖቻችን የምንለው፡፡
እኔም እላለሁ የአንድነት ፓርቲ አባላት ላይ እየተለጠፈ ያለው “የአሸባሪነት” ታፔላ በፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው ደግመን ደጋግመን ማሳሰብ እንፈልጋልን፤ መፍተሔውም ፖለቲካዊ ውሳኔ በመስጠት መፍታት እና ለሰላማዊ ትግል የፖለቲካ ምዕዳሩን ማስፋት ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል መድረኩ በጠበበ ቁጥር ደግሞ ዜጎች አማራጭ የትግል ስልት መፈለጋቸው የግድ ነው፡፡ በጠረጴዛ ላይ ያለው ሌላኛው አማራጭ ሀገርን ህዝብን ከመጉዳት ውጭ ገዢዎችንም ሊጠቅማቸው የሚችልበት አንድም መንገድ አይታይም፡፡ ሁሉም አሽናፊ ሆኖ የሚወጣበት ስርዓት መዘርጋት ለፍትህ ስርዓቱም ትንሳኤ ስለሚሆን ጅግኖቻችንን በመፍታት ለፍትህ ስርዓቱ ትንሳኤ በጋራ እንድንቆም መንግሰት ኃላፊነት አለበት፡፡
ምርጫ ሁለት ሺ ሰባት ለለውጥ!!!
ቸር ይግጠመን



No comments:

Post a Comment