Saturday, December 27, 2014

አንድነትና ምርጫ ቦርድ


ዛሬ በምርጫ ቦርድ ጉዳይ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ነገር ማንም ይረዳዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ፀረ አንድነት ዘመቻ ከተጀመረ ቢቆይም እያለፈ እያለፈ ብቅ ማለቱ ብዥታ ስለፈጠረብኝ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከአንድነት ጋር የሚያድርግ ያለውን ዝርዝር ከማውራቴ በፊት ግን ለአንባቢ ማስጨበጥ ያለብኝ ነገር አለ፡፡ አንድነት ፓርቲ ምርጫ እሳተፋለሁ ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚለውን ብዙዎች እነደፈለጉ ይልቁንም እነሱ ለመረጡት የሰነፍ መንገድ በሚመቻቸው መንገድ እየተረጎሙት ይገኛል፡፡
አንድነት ፓርቲ ምርጫ እገባለሁ ብሎ ሲወስን አንድነት በምንም መመዘኛ ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከመንግሰት መዋቅሮች የተለየ ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ በማሰብ አይደለም፡፡ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ይልቁንም አሁን ባለው ሁኔታ ማለትም ከዋና አዛዣቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እልፈት በኋላ ለመጀሚረያ ጊዜ የሚያካሂዱትን ሀገራዊ ምርጫ ከቀድሞ በተለየ ለመሸነፍ ዝግጁ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ማለትም በ1997 እንዳደረጉት ለሙከራም ቢሆን የጫወታ ሜዳውን ሊከፍቱት አይችሉም፡፡ ባጠቃላይ የአንድነት ፓርቲ ግምገማ ገዢው ፓርቲ ከምን ጊዜውም በላይ ዘግቶ መጫወት እንደሚፈልግ ከግንዛቤ ያሰገባ ነው፡፡ ሰለዚህ መድረኮች በቅርቡ እንዳሉት እንዲሁም አንድ እንድ ፓርቲዎች ሲሉት እንደነበረው ኢህአዴግ በሩን ለውይይት የዘጋው እንደ አንድነት ፓርቲ ምርጫ እንገባለን ስለአልን አይደለም፡፡ ኢህአዴግ አሁን ካለበት ነባራዊ ሁኔታ ተነስቶ ምንም ክፍተት እንደማይሰጥ በመረዳት ከወዲሁ መላውን ህዝብ አንቀሳቅሰን ለማስከፍት የወሰንን መሆኑን ማውቅ ይኖርባቸዋል፡፡
አንድነት ምርጫ እሳተፋለሁ ሲል ደግሞ ለተሳትፎ እንዳልሆነ ደግሞ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ የመጀመሪያው በር ማስከፈቻው ደግሞ ህዝቡ አማራጭ የለም ከሚል ፕሮፓጋንዳ እንዲላቀቅ በማድረግ አማራጭ ማሳየት ዋነኛው ሲሆን፣ አማራጭ መኖሩን ከተረዳ ደግሞ በነቂስ ወጥቶ ለመራጭነት እንዲመዘገበ፣ እንዲመርጥ እና ድምፁን እንዲያስከብር ማስተማር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሩን ክፈቱ ከሚል ጉንጭ አልፋ ጭቅጭቅ ተላቀን እንዴት እንክፈተው ላይ ማተኮር የሚል ስትራቴጂ ነው፡፡ ሚሊዮኖች በዚህ መስመር ከተሰለፉ ደግሞ ማንም ውሳኔያቸውን እንደማይቀለብስ እርግጠኞች ነን፡፡ ይህ ደግሞ በህዝብ ኃያልነት መተማመን ነው፡፡ ህዝቡ ከተባበረ ይህን በመንግሰት መዋቅሮች የሚደርሰውን አፈና ሊበጥሰው እንደሚችል ማመን ይኖርብናል፡፡ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የምንለየው በዚህ ነው፡፡ ሌሎች ኢህአዴግ በሩን ይክፈትና እንግባ ሲሉ እኛ ደግሞ ከፍተን እንግባ ብለናል፡፡ ኢህአዴግ ልብ ቢገዛና ሜዳውን ለሁሉም እኩል እንዲሆን ቢያደርገው ምርጫው ፍጥጫ ሳይኖርበት ሊጠናቀቅ እንደሚችል የሁላችንም እምነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በሩን ከፍተን እንግባ ያልነው እኛ ብቻ አይደለንምን የሀይል አማራጭ የሚከተሉትም ይህን ከፍቶ መግባት ይስማሙበታል፡፡ ልዩነታችን እኛ በሰላማዊ መንገድ ህዝብን አስተባብሮ ማሰከፈት እና መግባት ይቻላል ማለታችን ነው፡፡
ወደ ምርጫ ቦርድ ጉዳይ ስንመለስ፣ ምርጫ ቦርድ አንድነትን ምን አድርግ እያለው እንደሆነ ለሁላችን ግልፅ አይደለም፡፡ ከምርጫ ቦርድ ሰዎች ጋር በግንባር ቀርበን ስንወያይ በአክብሮት እንደሚያስተናግዱን መካድ ተገቢ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በተለያየ ጊዜ በሚዲያ ብቅ እያሉ የሚሰጡት መግለጫ ስንመለከት አንድነት ፓርቲን ለምን በዚህ ደረጃ እንደሚፈታተኑት ለመረዳት ይከብዳል፡፡ በቅርቡ በአንድነት ውስጥ በአመራር አሰያየም ችግር እንዳለ አስመስለው ያቀረቡት ነገር በጣሙን አሳኝ ብቻ ሳይሆን በተለይ አንድነት ፓርቲ የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫን በንቃት ለመሳተፍ በቂ ዝግጅት አድርጎ መንቀሳቀስ በጀመረበት ወቅት መሆኑ ጋር ተራ ግጥምጥሞሽ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው በሚዲያ ምንም ዓይነት ቅስቀሳ ሳያካሂድ፣ በየሰፈሩም የህዝብ ታዛቢ ምርጫ እንደሚካሄድ በይፋ ጥሪ ሳይደረግ፣ በሚስጥር በደብዳቤ በተጠሩ የቀበሌ ነዋሪዎች የህዝብ ታዛቢ ምርጫ ማድረጉን ስንታዘብ፣ ምርጫው ፕሮፌስር መርጊያ በቃና በተደጋጋሚ ምርጫን በተሻለ ሁኔታ ለማካሄድ አቅም ፈጥረናል ይበሉ እንጂ ሁሉንም እኩል ለማጫወት ዝግጁ ናቸው ብለን ለማለት አቅም እያነሰን፣ እነሱም እምነታችንን እየሸረሸሩት ይገኛል፡፡
ምርጫ ቦርድ አንድነት ፓርቲን ከሌሎች ፓርቲ በተለየ ሁኔታ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ብዛት አሰገቡ ይህም በደንባችሁ ውስጥ ይካተት ብሎ ሲል በግልፅ ባይሆንም በገደምዳሜ ጠቅላላ ጉባዔ ካልጠራችሁ ይህን ማድረግ አትችሉም ማለቱ ነበር፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ደግሞ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ይህን ማድረግ አይችልም የሚል ታሳቢ ያደረጉ ይመስላል፡፡ አንድነት ግን ይህን ግምት መና ባስቀረ መልኩ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ በደመቀ ሁኔታ ለ2007 ምርጫ መሰረት ጥሎ ሲለያይ ምርጫ ቦርድ እሰይ ተፎካካሪ የሚሆን ፓርቲ መጣ ብሎ መደሰት ሲገባው በተራ የአስተዳድር ስራዎች መሰረት አድርጎ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ በሳምንት ጊዜ እንድታስታውቁ የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት በማስተላለፍ ህዝቡን ግራ ማጋባት ተገቢ እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ ይህን ጉልበታቸውን ለፓርቲዎች አቅም ግንባታ ቢያውሉት የሚጠቀሙ ይመስለኛል፡፡ ሀገርም ከዚህ ይጠቀማል፡፡
አንባቢ እንዲረዳ የምንፈልገው ዋና ቁምነገር አንድነት ፓርቲ እንደ ፓርቲ ሁሉንም ህጋዊ መስመሮች አሟልቶ በተደጋጋሚ በሆደ ሰፊነትና በቅንነት በህግ ከሚጠበቅብን በላይ በመሄድ ከግብግብ ግንኙነት ወደ ውይይት ለማምረት ሙካራ እያደረግን መሆኑን አውቆ አንድም የህግ ክፍተት ፈጥረን ከጫወታ ለመውጣት ሰበብ እንደማንሰጣቸው ነው፡፡ ይህ ማለት ግን እንዲያንበረክኩን እድል እንሰጣለን ማለት አይደለም፡፡ ለማነኛውም ምርጫ ቦርድ ህዳር 19 ቀን በፃፈልን ደብዳቤ መሰረት የሚጠበቅብን የጠቅላላ ጉባዔ ቁጥር በደንብ አካታችሁ አምጡ የሚል ሲሆን ይህን ደግሞ ታህሳስ 3 የተሰበሰበው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲካተት አድርጎ ሪፖርቱ ታህሳስ 10 2007 ለቦርዱ ፅ/ቤት ገቢ ተደርጎዋል፡፡ ታህሳስ 10 ማለት ቦርድ ስብሰባ ያደረገበት ዕለት እና በሚዲያ የቀረበበት ቀን ስለሆነ ሪፖርቱን ከማየቱ በፊት ያሳለፈው ውሳኔ ነው ብለን በቅን ልቦና በመውሰድ በህዝቡ ዘንድ የፈጠሩት ብዥታ በሚያጠራ መልኩ የፈለጉት ሪፖርት በአንድነት በኩል የቀረበ መሆኑን በሚዲያ ይገልፃሉ ብለን አሁንም በቅንነት እንጠብቃልን፡፡
አንድነት ፓርቲ ላይ ምርጫ ቦርድ ከዚህም የከፋ ጫና ሊያደርስብን እንደሚችል መጠበቅ ትጥቃችንን ጠበቅ ለማድረግ እንደሚረዳን መገንዘብ አለብን፡፡ በቀጣይ በሚኖሩት ተደጋጋሚ ምርጫ ተኮር እንቅስቃሴዎች በቁጥር ብዙ የሚባሉ ለውጤት ሳይሆን ለተሳትፎ የሚገቡ ፓርቲዎች ይህን ጫና ለማድረግ አብረው መሰለፋቸውም የግድ ነው፡፡ ለለውጥ የተነሳው ህዝብ ግን ትኩረቱን ማን ላይ ማድረግ እንዳለበት ግን ጠንቅቶ ያውቃል፡፡ በቅርቡ በምርጫ ቦርድ በተሰጠው የሚዲያ መግለጫም አብዛኛው ሕዝብ ይህ ዘመቻ አንድነት ላይ ለምን በዛ? ብሎ ጠይቆዋል፡፡ መልሱም ግልፅ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ ቁርጥ አቋም ይዞዋል፣ በቀጣይ ምርጫ ሚሊዮኖች ተንቀሳቅሰው ድምፃቸውን ይስጣሉ፣ የሰጡትን ድምፅ ደግሞ ያስከብራሉ ብሎ ያምናል፡፡ አምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለአምሳ ሰው ጌጡ እንደሚባለው፣ አንድነት ፓርቲ እያንዳንዱ ዜጋ ነፃነቱን ለማስከበር ዘብ ከቆመ የሚሊዮኖች ድምፅ ይከበራል ብሎ በማመን የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ቀኝ ኋላ ዙር ሊሉ የሚፈልጉትን በሙሉ ወደፊት በማለት ለማሸነፍ የስነ ልቦና ዝግጅት እናድርግ እላለሁ፡፡ ምርጫ የገባ ነው ምርጫ ቦርድን አምነን ሳይሆን የህዝብን ሀያልነት ተገንዝበን ስለሆነ ማሸነፋችን ሳይታልም የተፈታ ነው፡፡ መንገዱ ምንም ያህል ጎርባጣ ቢሆንም ለድል የተነሳን መንፈስ ማሸነፍ ይከብዳል፡፡ ይቻላል ብለን እንደጀመርነው ከግብ ለማድረስ ቀበቶዋችንን ጠበቅ ነው፡፡ ቀላል ነው፣ የመጀመሪያው ሰራ ለመራጭነት መመዝገብ ነው፡፡ ቀዳሚ ይሁኑ ካርዶን በእጆ ያስገቡ!!!
ቸር ይግጠመን!!!!


No comments:

Post a Comment