Sunday, March 23, 2014

በግፊያ የሚነሱ አሉ…… በግፊያ የማይነሱትስ?



ግርማ ሠይፉ ማሩ
ለዚህ ፅሁፍ የሚሆን ርዕስ ያቀበለኝ ዶክተር ምህረት ደበበ ነው፡፡ በቅርቡ ብዙዎች “የተቆለፈበት ቁልፍ” በሚለው መፅሃፉ ነው የምናውቀው፡፡ ከዚያ በኋላም በሸገር ሬዲዮ ከመዓዛ ብሩ ጋር በሚያደርጋቸው ውይይቶች ሬዲዮ እንዳንዘጋ ከሚያደርጉን ጥቂት ሰዎች አንዱ ሆኖዋል፡፡ የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የደፋሮች መፈንጫ ሆነው ባሉበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለልብ የሚሆን መልዕክት ከሚያስተላልፉልን አንዱ እንግዳ እንደ ነበር መመስከር ግድ ይለኛል፡፡ በቅርቡ ታዲያ ብዙዎቻችን በግፊ ካልተነሳን በስተቀር ተልዕኮ ኖሮን የምናሳካው ነገር እጅግ አነስተኛ ወይም የሌለ መሆኑን ሲነግረን ነበር፡፡ ይህንን መልዕክት ተንተርሼ ነው ለዛሬ በተለያየ መልኩ በግፊ ሰለመነሳት ለማንሳት እና ሲከፋም ተገፍተው የማይነሱም መብዛታቸው ይህችን ሀገር ምን ያህል ከባድ ፈተና እንደተጋረጠባት ለማሳየት የምሞክረው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ ቦርድ
ምርጫ ቦርድ አሉኝ ብሎ ከሚላቸው 75 ፓርቲዎች ግማሾቹን ደግሞ ደግሞ የሚቆጥራቸው ቢሆኑም ራዕይ ኖሯቸው ሊደርሱበት ወደሚፈልጉት ግብ እንዴት እንደሚደርሱ ሃስበው ይህን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚሰሩ ፓርቲዎች ቢቆጠሩ የአንድ እጅ ጣት አይሞሉም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የሚንቀሳቀሱት ወይ ገዢው ፓርቲ አበል አለ ብሎ ሲጠራቸው፣ አሊያም አንድ የፖለቲካ ትርፍ የሚያስገኝ ኩነት ተገኘ ሲባሉ ነው፡፡ አብዛኞቹ ግን መኖራቸው የሚታወቀው ምርጫ የሚባል ነገር ሲመጣ ነው፡፡ በዚያን ሰሞን አለን ለማለትም ገፊ የሚሆነው ምክንያት ምርጫ ቦርድ የሚያድላት ገንዘብ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ከዘህ ውጭ ሌላ ብዙ ገፊ ምክንያት ብናስብም ለእኔ በተግባር የገጠመኝ ግን ከፓርቲ መዝገብ ላለመሰረዝ ምርጫ መወዳደር የግድ ስለሚል ነው፡፡ መሰረዝ የማይፈልጉበትን ምክንያት ግን እዚህ ማንሳት ተገቢ አይደለም በሚል ባልፈው መረጥኩ፡፡ ላነሳው ያልፈለኩት ጉዳይ በእውነቱ ዋነኛው ገፊ ምክንያት እንደሆነ ግን ይታወቃል፡፡ ለአንባቢያን አይመጥንም በሚል ነው የማልፈው፡፡
በግፊ የሚነሱ ፓርቲዎች ለዚህች ሀገር የመድበለ ፓርቲ ሰርዓት ግንባታ የሚመጥኑ እንዳልሆኑ እነርሱም ያውቃሉ ህዝቡም ያውቃል፡፡ ገዢው ፓርቲም በደንብ አውቆ ከግፊ ውጪ እንዳይነሱ ቆመው እንዲከርሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ዋናው ግን ቆመው ለመክረም የወሰኑት እራሳቸው መሆናቸውን ሳንዘነጋ ነው፡፡ በኢህአዴግ ማሳበብ ማቆም ይኖርባቸዋል፤ ይኖርብናል፡፡ ለውጥ ለማምጣት ከሆነ ግን ከግፊ ወጥተን በራስ ተነሳሽነት በልምድ ከተሰመረው መስመር ውጭ መንቀሳቀስ ግድ ይላል፡፡
የምርጫ ቦርድ መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ ለልዩ ልዩ ጉዳይ ጎራ ብዬ አውቃለሁ፡፡ የሚፈልጉትን ሠራተኛ በመንግሰት የስራ ሰዓት ማግኘት ዘበት ነው፡፡ የቦርዱ አባላት በቋሚ ሰራተኛነት መገኘት ባይኖርባቸው በቀጠሮ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ምን ያደርጋል ቢገኙስ መፍትሔ የሚባል ነገር ሊሰጡ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ዝም ብሎ ምርጫ ቦርድን ለመክሰስ እንዳይሆን ማሳያ ላቅርብ፡፡ ነጋዴ ችግር ሲገጥመው ንግድ ሚኒስትር እንደሚሄደው እኛም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ችግር ገጥሞናል መፍትሔ ስጡን ብለን የምንሄደው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ፖሊስ በየመንገዱ የፖለቲካ ስራ ልንስራ እየከለከለን ነው፤ አዳራሽ የሚያከራዩ ሰዎች ፈቃድ ይሉናል ፈቃድ ሰጪ አካል ደግሞ የለም ምን እናድርግ፤ ማተሚያ ቤት የንግድ ፈቃድ አምጡ ይላል እኛ ነጋዴ አይደለንም ይህን ጉዳይ በአዋጅ መሰረት መፍትሔ ስጡን፤ ወዘተ. ለምርጫ ቦርድ በግንባር ቀርበን ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ናቸው፤ አንድም መፍትሔ የለም፡፡ መልሳቸው አነጋግረን መልስ እንሰጣችኋለን ይሉናል፡፡ መልስ ግን የለም፡፡ ይልቁንም በአውራ ፓርቲ መኖር ተገቢነት ላይ በሚቀርብ የገዢው ፓርቲ መድረክ ላይ በተሳታፊነት ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ በግፊም አይነሳም ወይም ገፊውን ይመርጣል ማለት ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በአሰተዳደራዊ መስመር አልፈታ ሲለን ነው እንግዲህ ሌላ ተቋም ለመፈተሽ ወደ ፍርድ ቤት የተሄደው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን በግፊ ይነሱ አይንሱ እዚህ ማንሳት አያስፈልግም፡፡ ይደር ብለን እንለፍ፡፡

መንግስት /አሰፈፃሚ አካል
መንግሰት የሚባለው አካል ሰራውን የሚያሰራው የሲቪል ሰርቪስ ወይም የመንግሰት ሰራተኞች በመባል በሚታወቁት በአብዛኛው የባለሞያዎች ስብስብ ነው፡፡ በአብዛኛው እነዚህ ሰራተኞች ጠዋት 2፡30 ወደ ሰራ ገብተው ማታ 11፡30 ከስራ የሚወጡ መሆናቸውን ከግንዛቤ አስገብተን (በቀን ሰምንት ሰዓት ማለት ነው) ይህን ሁሉ ሰዓት በስራ ገበታቸው ተገኝተው የተጣለባቸውን ሃላፊነት ሲከውኑ ነው የሚውሉት ብለን ስናስብ ግን መልሱ አዎንታዊ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ለዚህም ነው መንግስት የሚባል አካል የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ መርዓ ግብር ብሎ የሚዳክረው፡፡ ግን ለምንድነው እነዚህ ሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞች በግፊ ካልሆነ በስተቀር የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለመስጠት ዳተኛ የሆኑት ማለት ይኖርብናል፡፡ ለማነኛውም ያለግፊ የሚሰሩ ከተሰመረላቸው መስመር ወጥተው የሚያገለግሉ የሉም ማለት አይደለም፡፡ የአብዛኛው መገለጫ ግን በግፊ መነሳት መሆኑ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው መንግሰት የሚባለውን አካል የሚያዋቅረው እና የሚመራው ደግሞ ገዢው ፓርቲ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ደግሞ እንቅስቃሴው ጎልቶ የሚታየው ልክ እንደተቃዋሚዎቹ ሁሉ በምርጫ ሰሞን መሆኑ ነው፡፡ ለገዢው ፓርቲ ገፊው ምርጫ የሚሆነው ግን እንደ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ከምርጫ ቦርድ የሚያገኘው ገንዘብ አይደለም፡፡ ከምርጫ ቦርድ የሚያገኘውን ገንዘብ ከህግ አግባብ ውጭ በምርጫ ቦርድ በኩል ለሌሎች ፓርቲዎች እንደሚያድለው እናውቃለን፡፡ ለገዢው ፓርቲ ምርጫ ገፊ የሚሆነው ለመግዛት የሚያስችለውን ውጤት አግኝቻለሁ ብሎ አለማቀፍ ማህበረሰቡን ለማሳመን እንዲቻለው በማሰብ ነው፡፡ ለዚህም ህዝቡን በልማት ስም የልማት አርበኛ ነኝ ብሎ ድምፅ ለማግኘት ያስችለኛል ያለውን ከመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ እስከ የልማት ሰራዎች ሳይጠናቀቁም ቢሆን ምርቃ ለማድረግ ደፋ ቀና የሚለው፡፡ እንግዲህ ሰሞኑን በምርጫ ግፊ እነዚህን ክስተቶች እስኪያነገሸግሸን እንሰማለን፡፡ በነገራችን ላይ የ1997 ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ምርጫ እንደዋዛ የማይመለከተው ገዢ ፓርቲ በግፊ የሚሰራቸውንም ቢሆን ህዝቡ አሁን ድረስ እድሜ ለቅንጅት እንደሚል መረጃ አለን፡፡ በተለይ በጉራጌ ዞን ከቅንጅትም አልፎ የአንዳንድ ቅንጅት ግንባር ቀደም ሰዎችን ስም በማንሳት ነው በአካባቢያቸው ሰለሚጀመሩ ልማቶች ምስጋና የሚያቀርቡት፡፡ አዲስ አበባም ቢሆንም ወጣቱን ከአደገኛ ቦዘኔ ከሚል ፍረጃ በማንኛውም ሁኔታ ወጣቱን መያዝ ወደሚል ገዢውን ፓርቲ ያሸጋገረ ገፊ ጉዳይ ምርጫ ነው፡፡ ይህ ወጣቱን የማቀፍ አቅጣጫ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ግን በግፊ የሚነሳና ቁም ነገር የሚሰራ ነው ተብሎ በብዙዎች ዘንድ አይወሰድም፡፡ በነገራችን ላይ በግፊ የሚነሱ ሰዎችም ቢሆኑ የተለየ ነገር ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ገዢው ፓርቲም የሰዎች ስብስብ ነው፡፡ ዶክተር ምህረት ደበበ እንደነገረን ከሆነ “በግፊ የሚነሱ ሰዎች ሰራ ሲቀጠሩ እንዲያከናውኑ ከተሰመረላቸው መስመር ዘለግ አድርገው ሰራ ለመስራት ብዙም ተነሳሸነት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ልዩ ፈጠራ በማድረግ ሰራን ለማሻሻል አቅም የላቻውም፡፡ ሰራቸውንም ለመስራት ሁልጊዜ ጎትጓች ይፈልጋሉ በጉትጎታ ደግሞ ፈጠራ የለም፡፡” ነው የሚለው፡፡ ገዢው ፓርቲ ደግሞ የሰዎች ስብስብ ነው ብለናል፡፡ እነዚህ አባላቱ ደግሞ አብዛኞቹ ሰለግል ነፃነት ግድ የሌላቸው ብሎም የሚያደርጉት ነገር ሁሉ በግምገማ እና ግምገማን ተከትሎ በሚከተላቸው ቁንጥጫ ፍርሃት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ከነዚህ በግፊ ከሚንቀሳቀሱ አባላት ደግሞ አዲስ ነገር መጠበቅ የዋህነት ነው፤ ፈጠራ ከነፃነት የሚመነጭ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በግፊ የሚነሱ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች እሰከተሰመረላቸው መስመር ድረስ ሊሰሩ እንደሚችሉ እሙን ነው፤ ይህም የሚሆነው ገፊው አካል ወይም ሁኔታ በሚያደርሰው የግፊት መጠን እና ገፊው በተገፊው ላይ ባለው ኃይል የሚወሰን መሆኑን መረዳት ይኖርበናል፡፡ የሚገርመው ግን ሀገራችን የሚያስፈልጋት ያለ ግፊ የሚሰሩ ሰዎችና ተቋማት ቢሆንም አሁን ግን በግፊም በደንብ የማይሰሩ ሲከፋ ደግሞ በግፊም የማይነሱ መብዛታቸው ነው፡፡
ስንቶቻችን የሰዓት ፊርማ ባይኖር በሰራ ሰዓት በስራ ቦታችን እንገኛለን? ብሔራዊ የሆኑ የበዓል ቀናት ቅዳሜና እሁድ ሲውሉ የማይበሳጭ ስንቱ ነው? የስራና የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜ ባይኖር ሪፖርት የሚባል ነገር ይኖራል ወይ? ተማሪዎች ፈተና ባይኖር ለዕውቀት ብሎ ጥናት ይኖር ነበር ወይ? ወዘተ ብለን ስንጠይቅ በሁሉም መስክ ግፊት የግድ የሚለን ጉዳይ ሆኖዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ሆኖ ግን የማይንቀሳቀስ ብዙ ሰው እንዳለ ሳይዘነጋ፡፡
በሀገራችን ጭቆናው በዝቶብኛል የሚለው ዜጋ እጅግ ብዙ ነው፤ ይህ የጭቆና መብዛት ገፊ ሆኖ እምቢ ለነፃነቴ ብሎ ግን የሚነሰው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ነፃነትን ለማግኘት ከጭቆና መብዛት የተሻለ ገፊ ሁኔታ ከየት ሊመጣ ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ጭቆና እምቢ የሚባልበት መንገድ አንዱ የምርጫ ካርድ መውሰድ ሲሆን፤ የምርጫ ካርድ ወስዶ የሚመርጠው አማራጭ ካጣ ደግሞ ካርዱን ቤቱ ይዞ በመቀመጥ ጨቋኞችን እምቢ ማለት የግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ አብዛኛው ግን አማራጭ ከሌለ ካርድ መውሰድ ምን መልዕክት እንዳለው አይረዳም፡፡ ሌሎችም ጭቆና እምቢ የሚባልባቸው መንገዶች እንዳሉ ባለመዘንጋት ነው፡፡ እምቢኝ ብሎ ቤት ከመቀመጥ ጅምሮ ጎዳና ወጥቶ እምቢ ብሎ እስከመጮህ፡፡ እምቢኝ ለማለት ግፊው አልበቃንም ወይም ቢገፉንም አንነሳም ብለናል ማለት ነው፡፡
በግፊ አልነሳ ያሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ አካለት ወዘተ ለመዘርዘር በሃሳቤ ቢመጣም ወደ ዝርዝሩ ገብቼ መሄድ አልፈቀድኩም እሰኪ ይህን ፅሁፍ ለማንበብ እድል የገጠማቸሁ ሁሉ እራሳችሁን ገምግሙት፡፡ በራሳችሁ ተነሳሽነት የምትንቀሳቀሱ ፣ በግፊ የምትነሱ መሆኑን ወይም በግፊም ቢሆን ለመነሳት ባትሪያችሁን የጨረሳችሁ መሆኑን ፈትሹ መልሱን ስታገኙ ቢያንስ በዚህ ዓመት ካላችሁበት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት ውሳኔ አድርጉ ግፊን እምቢ በሉ፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

Sunday, March 16, 2014

ዜና ውህደት



ዛሬ በመኢህአድ ፅ/ቤት የመኢህአድ እና የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት የጋራ ስብሰባ አድርገው አንድ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህውም ለቀጣይ ሐሙስ መጋቢት 11/2004 ዓ/ም የቅድመ ውህደት ሰምምነት እንዲደረግ እስከ አሁን ውህደቱን ለማዘግየት የተወሰደው ጊዜ ከበቂ በላይ በመሆኑ አጅግ አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ ይህን ጉዳይ አጠናቆ የጋራ ጉባዔውን የሚያመቻች ኮሚቴም በእለቱ ይፋ እንዲደረግ ከስምምነት ተደርሶዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ውህድ በሚሆኑበት ወቅት ፈታኝ ይሆናሉ የተባሉ የፕሮገራም እና የደንብ ልዮነቶች የሚባሉት ውሕዱን ፓርቲ የተሻለ ደንብና ፕሮግራም እንዲኖረው ከማድረግ የዘለለ ውህደቱን ለማዘግየት ምክንያት እንዳይደሉ መግባባት ላይ ተደርሶዋል፡፡  የውህዱን ፓርቲ ስያሜ በተመለከተም ተሳታፊዎቹ በአዲስ መሆን እንዳለበት እና ይህም ተጠንቶ ለጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ የሚወሰን እንደሆነ ግንዛቤ ተይዞዋል፡፡ ትልቁ ነጥብ የነበረው በሁለቱም ፓርቲዎች በኩል አመራሮች በምንም ሁኔታ ውህደቱን ለማዘግየት ቢሞክሩ አባላት ተዋሕደው አመራሮች ተንጠልጥለው እንደሚቀሩ በተደጋጋሚ የገለፁ ሲሆን ይህም በከፍተኛ ጭብጨባ ድጋፍ አግኝቶዋል፡፡ እውነት እውነት እላችኋለው ይህ ጉዳይ ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ እውን ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የፈረሰው ቅንጅት ሶስት አራተኛው እንደተመለሰ ይሰማኛል፡፡ ቸር ወሬ ያሰማን፡፡ የመጋቢት 11 ሰው ይበለን፡፡

የአፍሪካ መሪዎችና አፍሪካዊያን ግርማ ሠይፉ ማሩ



በቅርቡ ለስብሰባ የመካከለኛ አፍሪካ በምትገኘው ካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ ተገኝቼ ነበር፡፡ ያውንዴ በነበርኩበት ጊዜም አጋጣሚ ሆኖ ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሚከበርበት ስለነበር አከባበሩን አሰመልክቶ የአፍሪካ መሪዎች እንዴት በዓል እንደሚያከብሩ ለመታዘብ ዕድል ሰጥቶኛል፡፡ ለአምባገነንት የሚጠቀሙበት መመሪያም አንድ መሆኑን ለማወቅ ጊዜ የሚወስድ አልነበረም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ደግሞ ከጎረቤት ሀገር ተሳታፊዎች ጋር ለመገናኘት እና ለመወያየት ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ በተለይ ከኤርትራዊ ወንድሞቻችን እና እህቶች ጋር የነበረን ቆይታ ከእነርሱ  ከራሳቸው በስተቀር ከኢትዮጵያ የሚለያቸው ነገር የሚያውቅ እንደሌለ አፍጥጦ የሚታይ ሀቅ ነበር፡፡  ከሱማሊያ ከመጣው ወጣት ጋር የነበረን ውይይትም በፍፁም የማይታመን ነበር፡፡ የእኛ ጎምቱ ባለስልጣናት አብረውን ካሉት ጋር እንዴት እንደሚያጋጩን ሲያስላስሉ እዚያ ማዶ ያሉት ግን የእኛ ናፍቆት አላቸው፤ የአብሮነትን ጥቅም በደንብ ተረድተውት እንዴት እንደሚሆን ግን ግራ የተጋቡ ይመስላሉ፡፡ ይህን መፈላለግ ለመግለፅ ግን ከአንድ ጥግ ወደ ሌላ ጥግ መሄድ ለምን እንዳስፈለገን ተወያይተን የደረስንበት በእኛ በህዝቦች መካከል  ምንም የሚያለያይ ነገር እንደሌለ ነው፡፡ ለአብሮነታችን ግን አምባገነኖችን ከመክስስ በዘለለ ሁላችን የበኩላችንን ማድረግ ይኖርበናል፡፡
እንደ መግቢያ
የማርች 8 ባህል በካሜሮን ከተማ ያውንዴ ድል ባለ ሁኔታ ሲከበር የዓይን ምስክር ሆኜ ተመልክቻለሁ፡፡ ባህሉ ያለ ብዙ ወንዶች ተሳትፎ የሀገሪቱ ቀዳማዊ እመቤት በተገኙበት የተከበረ ሲሆን በእኛ ሀገር ለቀዳማዊ እመቤት በዚህ ደረጃ የደህንነት ጥበቃ ሲደረግ አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ የባሰ አለ ሀገር አትልቀቅ የሚባለው ይኼን ጊዜ ይመስለኛል፡፡ የማርች 8 በዓልን ለማድምቅ የወጡት ሴቶች እንደኛው ሀገር በመስሪያ ቤት ተደራጅተው የወጡ ሲሆን፤ ከበዓሉ በኋላ ግን እንደ እኛዎቹ ሴቶች ወደቤታቸው ነጠላቸውን በአናታቸው ላይ አድርገው ጠውልገው ሲመለሱ አላያሁም፡፡ በየደረሱበት አረፍ ብለው ቢራ እየተጎነጩ ሲመሽም ተሳክረው በየጎዳናው ሲደንሱ አጀብ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ይኼ ነው እኩልነት ብዬ ታዝቤያቸው መጥቻለው፡፡ የሰልፉ ዝግጅት፣ የጦር ሰራዊት ጋጋታው፣ ወዘተ… በሀገራችን የሴቶች ሊግ የሚያደርገው ዓይነት እና በመንግሰት የሚደገፉ ሰልፉች ጋር አንድ ሲሆንብኝ ተሳስቼ መስቀል አደባባይ የተገኘው እንጂ በዚህ ሁሉ ኪሎ ሜትር ርቀት ልዩነት በዚህ ደረጃ መመሳሰል ይኖራል ብዬ ለማመን እራሴን ተጠራጠርኩ፡፡
ኢትዮጵያ (ከኤርትራ እና ያለ ኤርትራ)
ኤርትራዊያን ብዬ ለመፃፍ ወይም ለመጥራት የምር ምቾት አይስጠኝም፡፡ ያራቅኳቸው እኔም ከኢህአዴጎች ጋር ሆኜ አንድ አይደለንም የሚለውን የመደገፍ ሰሜት እየመጣብኝ ይፈታተነኛል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን አሁን ያለውን እውነት ለመቀበል ስል እንደ ሁለት ሀገር አድርጌ ለመፃፍ እገደዳለሁ፡፡ ልቤ ግን ይህን እያለኝ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ያለ ኤርትራ፤ ኤርትራም ያለ ኢትዮጵያ መኖር እንደሚችሉ ባሳለፍናቸው ሃያ ዓመታት በላይ የተረጋገጠ እና የተመዘገበ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን አብረን ብንሆ ከዚህ የተሻለ ልንሆን እንደምንችል ከምን ጊዜውም የበለጠ አሁን የተሰማን ይመስለኛል፡፡ እኛ ከተከዚ ደቡብ የምንገኝ ህዝቦች አስመራ፣ ምፅዋ ሄደን ለመዝናናት ቢያስፈልግም ሰርተን ለመኖር ከኢሳያስ መሞት ቀጥሎ ከዚህ ከእኛ ሰፈር የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መፍረስ የግድ የሚለን ይመስለኛል፡፡ ይህ “ጦርነትም ሰላምም የለም” በሚል ግርግዳ ታጥረን መኖራችን፤ ከአሰመራም ከአዲስ አበባም በኩል የመራራቅን ግድግዳ እያጠናከረ እንደሚሄድ ግን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በዚሁ ከቀጠልን አዲሱ ትውልድ የእኛን ያህል አስመራንም ሆነ ምፅዋን የመጎብኘት ጉጉቱ ባያድርበት መገረም አይኖርብንም፡፡ በተለይ በአሰመራ በኩል አዲስ ታሪክ በመስራት ፕሮጀክት ውስጥ ኤርትራ በጎረቤት ሀገሯ ኢትዮጵያ ቅኝ ተይዛ እንደነበረ በሰፊው ተፅፎ እየተሰጠ እንደሚሆን መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ ከአቶ መለስ እና ጓዶቻቸው በስተቀር እኛም ሳናውቅ አንድ በቅኝ የገዛነው ሀገር እንዳለን በአስመራ በኩል ይመዘገብ ይሆናል፡፡ አቶ መለስ ፅፈውታል ተብሎ የሚታመነው “ኤርትራ ከየት ወዴት?`` የሚለው መፅኃፍ ኢትዮጵያን ቅኝ ገዢ አድርጎ ነው የሚያቀርበው፡፡ የኤርትራ ጉዳይም ከቅኝ ግዣት ነፃ የመውጣት ነው ብለው ነው የደመደሙት፡፡ ለዚህም ነው ኤርትራ ነፃ ሀገር እንድትሆን ቀድመው ደብዳቤ የፃፉት፡፡ እርግጠኛ ነኝ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ታሪክ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ መገንጠሏን የሚነግር እንጂ በቅኝ ይዘናት የነበረን ሀገር እንዳስረከብን አይደለም፡፡ ለምሳሌ እንግሊዝ ኬኒያን ለቃ እንደወጣችው ዓይነት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተገነጠለች እንጂ ከሱዳን ቅኝ ግዛት አይደለም ነፃ የወጣችው፡፡
የዚህ ፅሁፍ ዓላማም ይህ እየተጠናከረ ወደ አዲሱ ትውልድ በመሄድ ላይ ያለውን የሚያራርቅ ግንብ የኢሳያስንም ሆነ የእኛን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሞትና ግብዓተ መሬት ሳይጠብቅ ህዝብ ለህዝብ በሚደረግ ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረግ እንዳለብን ከውስጤ ስለተሰማኝ ፍላጎቱና አቅሙ ላላቸው ሰዎች እረ ጎበዝ አንደ እንበል ለማለት ነው፡፡ ይህን እንዴት ማድረግ ይኖርብናል የሚለው ብዙ ሰዎች ብዙ የሚሉት ነገር እንደሚኖር ባምንም በእኔ ግምት በቅርቡ መጀመር ያለባቸው ብዬ የማምናቸው በማህበራዊም ሆነ በመደበኛ ሚዲያ ወጣቱ ትውልድ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን የባሕል፣ የቋንቋ፣ የሰነልቦና፣ ወዘተ አንድነት የሚያሳዩና አዲሱን ትውልድ ከቀድሞ ጋር የሚያስተሳስሩ ሰራዎችን መስራት የግድ ይለናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰራዎች በፍፁም በአንድ ወገን ብቻ የሚሰሩ መሆን የለባቸውም፡፡ የኢየትዮጵያና የኤርትራ ቴሌቭዝኖች እንዲህ ዓይነት መልካም ሰራ ቢጠበቅባቸውም የማያምርባቸው ስለሆነ ከውጭ የሚተላለፉ ለምሳሌ ኢሳት እና “ኢቢሴ” በዚህ ጉዳይ ላይ ቢሰሩ የሚጠቀሙ እንጂ የሚጎዱ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ተግባራት በፍፁም ከፖለቲካ አመለካከት ጋር የሚገናኙ መሆን የለባቸውም፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን የጋራ ፎረሞችን በማዘጋጀት በአብሮነታችን ዙሪያ ምክክር በማድረግ ከእንደዚህ ዓይነት መድረኮች የሚገኙ ሃሳቦች በሰፊው ህዝቡ እንዲያውቀው በማድረግ የህዝብ ለህዝብ መቀራረብን ልናጎለብት ይገባ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፖለቲከኞች በፈጠሩት ግጭት ባለሞያዎች በሚገናኙበት መድረክ ላይ ለመሳተፍ አንድ ኤርትራዊ አውሮፓ ድረስ ተጉዞ ሶስት አራት ቀን መንገድ የሚያድርበት ቀን ለማሳጠር መሰረት መጣል ያለብን ይመስለኛል፡፡ ይህን ለማድረግ በመግቢያዬ ላይ እንዳልኩት የኢሳያስ መሞትና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መፍረስ ከጠበቅን የመለያየታችን ግንብ በልጆቻችን ውስጥ ሰርጾ መቼ አንድ ነበርን ሊሉን ይችላሉ፡፡

ኢትዮጵያና ሱማሊያ
ኢትዮጵያና ሱማሊያ በሱማሌ ቅኝ ገዜ የነበሩት በተለይ እንግሊዞች በቀበሩት የግጭት መንፈስ የተነሳ በተደጋጋሚ የድንበር ግጭት ብሎም ደም አፋሳሽ የሆነ ሙሉ ጦርነቶች ውስጥ ገብተን እንደነበር እሙን ነው፡፡ ይህን እውነት የምናውቅ የሁለት ሀገር ዜጎች ግን ካሜሮን ላይ ስንገናኝ እንደ ድሮ ሰፈር ልጅ በፍቅር ስንጫወት ነው የከረምነው፡፡ ከሱማሌው ተወካይ መሃመድ ጋር መጀመሪያ የተግባባነው ኢትዮጵያዊ መስሎን ነበር፡፡ እኔን እና መሃመድን የሚለየን መሃመድ ትንሽ  ትንሽ አማርኛ ይሞክራል እኔ ሱማልኛ ስለማልሞክር ይበልጠኛል ማለት ነው፤ መሃመድ ተግባቢ እና በደንብ እንደምናውቃቸው ሶማሊዎች ቴክኖሎጂ የሚወድ ነው፡፡ በእጁ የያዛት ብላክ ቤሪ ስልክ ሁሉንም ወሬ ታቀብለዋለች፡፡ መሃመድ እንደሚለው “ይህች ስልክ ሱማሌ ውስጥ በተለይ በአልሻባብ እጅ ከገባህ ሞት ታስከትላለች” ይላል በተደጋጋሚ፡፡ ቴክኖሎጂን እና ሌሎች የህዝብ መጠቀሚያዎችን በመከልከል አፍነው ሊገዙ የሚንቀሳቀሱ የአልሻባብ ሰዎች በፍፁም ምንጫቸው ሱማሌ እንዳልሆነ እና ከውጭ የመጣ አካራሪነት እንደሆነ ያምናል፡፡ በዚህ ሰበብ ግን በኢትዮጵያ በኩል እየተወሰደ ያለው እርምጃ በደንብ ታስቦበት ካልሆነ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን እንደሚጎዳ አበክሮ ይናገራል፡፡ እርግጥ ነው አሁን ያለው መንግስት ደካማ ስለሆነ የኢትዮጵያ እርዳታ በተለይ ወታደራዊ ድጋፍ ይፈልጋል፤ እንደዚያም ሆኖ ግን ህዝቡ ይህን ሳይረዳ ይቀርና እንደ ወራሪ ሀይል በመቁጠር አልሻባብን ይቀላቀላል፡፡ ይህ ደግሞ ወደፊት ተባብረን እና ተደጋግፈን  የምንኖርበትን  ጊዜ ያርቀዋል ይላል፡፡ መሃመድ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያና በሱማሊያ መካከል የተደረገውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በታሪክነት ነው እንዲዘጋ የሚፈልገው፡፡ ይህ ጦርነት “ሁለት አንባገነኖች ንፁዓንን ያስፈጁበት በኋላ ደግሞ እነርሱ የተቃቀፉበት ነበር” ይላል መሃመድ፡፡ ሁለቱም አሁን የሉም ይህን ታሪክ አድርጎ ወደፊት መሄድ ነው ያለብን ነው የሚለው፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ድንበር አርቴፊሻል ነው ብሎ ያምናል፡፡ ኢትዮጵያዊያኖች ባህር ዳር ሆነው ለመዝናናት ከሞምባሳ የእኛ ይቀርባል ይላል፤ ሶማሌዎችም ኢትዮጵያ ቤታችን ነው ብለው ያምናሉ እንደ መሃመድ እምነት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሁሉን ነገር ትተው በችግራችን ጊዜ እንደ ሀገራችን እንድንኖር ማድረጋቸው በፍፁም የሚረሳ ውለታ እንዳልሆነ ነው መሃመድ የሚተርከው፡፡
መሃመድ ይህን ሁሉ ባጫወተኝ ማግስት የኢትዮጵያ ጦር ወደ ደቡብ ጁባ ላንድ ሊገባ መሆኑን በተለመደ የመረጃ ቃራሚነቱ ሰምቶ ግርማ አሁንም የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ መግባቱ ለህዝቡ በደንብ እንዲያውቀው ካልተደረገ መንግሰት ለመንግሰት ብቻ በሚደረግ ሰምምነት መሆኑ ችግሩን ከማባባስ አልፉ አልሻባብን ያጠናክራል የሚል ስጋት አለኝ ብሎ ፍርሃቱን አጋራኝ፡፡ እውነት ነው ደካማ የሱማሌ መንግሰት የሚያግዘው ጉልበተኛ ያስፈልገው ይሆናል፤ ለሀገር ዘላቂ ጥቅም ሲባል ግን ለአልሸባብ የሚወረወሩ ጥይቶች ሰላማዊ ዜጋ፣ ሴቶች እና ህፃናትን እንዳይጎዱ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡
ቸር ይግጠመን

Saturday, March 8, 2014

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በእኔ ዕይታ ……. ግርማ ሠይፉ ማሩ



የኢህአዴግና ኣባል ድርጅቶችን እንደ ርዕሰ ጉዳይ ለማንሳት የገፋፋኝ የሰሞኑ የብአዴን መዝረክረክ ነው፡፡ ብአዴን ምን ነካው ብዬ ሃሳብ ለመሰንዘር ወስኜ ሳወጣ ሳወርድ ምን ያልተነካ የግንባር አባል ድርጅት ኖሮ ነው ብአዴን የምትለው የሚለው ሃሳብ ገዢ ሆኖ መጣብኝ፡፡ በዚህ መነሻም በነገር ቅደም ተከተል ሳይሆን ኢህአዴግ የሚባለውን ሚዛንና ቅርፅ የሌለውን ድርጅት በመመስረት ቅደም ተከተላቸው ለማየት ሞከርኩ፡፡
ሕወሓት ሁሉም እንደሚያውቀው አውራቸውን ካጡ በኋላ ዋና ስራቸው እራሳቸውን ወደ አንድ ፓርቲነት ለማሳደግ ደፋ ቀና ሲሉ እንደከረሙ እናውቃለን፡፡ የተሳካ ነገር መኖሩን የሚጠቁም ነገር የለም፡፡ ዛሬም ነገም ስብሰባ ነው፡፡ ባለሀብቶቹ ተሰብሰበው እባካችሁ ስብሰባ ቀንሱ ነው ያሉዋቸው፡፡ ህውሓት የአዲስ አበባና የመቀሌ ቡድን በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን የነፃ አውጪ ድርጅቱን የሚመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክፍፍል የሚባል የለም ብለው ለየካቲት 11 መታሰቢያ በተዘጋጀ መፅሔት ላይ ቃለ ምልልስ መስጠታቸውን ይፋ ሆኖዋል፡፡ እኛም ሰምተናል መስማት ግን መስማማት እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ይህ የሚያስታውሰን ነገር ቢኖር የጦጢትን አልበላሽምን ምን አመጣው ጫወታ ነው፡፡ ክፍፍል የለምን ምን አመጣው እንላለን፡፡ አንድ ግን ታውቆ ያደረ ነገር ቢኖር ህውሓት ሁሉ ነገሩን ለአቶ መለስ ሰጥቶ የነበረ ከመሆኑ አንፃር በተለይ በኢህዴግ ሰፈር አጀንዳ የማስቀመጡን ሰራ መስራት የሚችል ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ አሁን ህውሓት ጥንካሬ አለው ከተባለ የፓርቲ ሳይሆን ኢ-ሕገ መንግሰታዊ በሆነ መስመር የመከላከያና የደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ ባሉት ቁልፍ ሰዎች የሚተማመን ከሆነ እና እነዚህም ቁልፍ ሰዎች ቢሆኑ ይህን መተማመኛ ሰጥተው ከሆነ ነው፡፡ ዘወተር ታማኝነታችን ለህገ መንግሰት ነው በሚሉት ቃላቸው ከታመኑ ደግሞ ጠቅላይ አዛዡ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንጂ የህውሓቱ መሪ አይሆኑም፡፡ ሰለዚህ ሕውሓት በአሁኑ ሰዓት በኢህአዴግ ውስጥ አጀንዳ አሰቀማጭነት ሚና የለውም የሚል አረዳድ ነው ያለኝ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በፌዴራል መንግሰት በሚደረጉ ሹመቶች ውስጥ የህወሓት ሰዎች ከቦታ ቦታ ዝውውር እና የቀድሞ ታጋዮችን ወደፊት ከማምጣት የዘለለ አዲስ ፊት ማምጣት አልቻለም፡፡ ወጣቶቹ የህወሓት አፍቃሪ ልጆች በቢዝነሱ መስመር እንዲሁም ውስኪ በመጨለጡ እንጂ ንቁ ፖለቲከኛ የመሆን ፍላጎት ያላቸውን አይመስሉም፡፡ ባይሆን የዚህ ዓይነት ትንታግ ወጣቶች አረና ሰፈር ብቅብቅ ያሉ ይመስላሉ፡፡ እነ አብርሃ ደስታ የኢትዮጵያ አምላክ እንዲጠብቃቸው ፀሎት ሁሉ ያስፈልጋል፡፡ በትግል ከመተጋገዙ ጎን ለጎን ማለቴ ነው፡፡
በእውነቱ ከኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ውስጥ ተሰፋ ሳይበት የነበረው ብአዴን ሰሞኑን ምን እንደ ነካው ማወቅ አልቻልኩኝም፡፡ ለምን ተሰፋ ጣልክ ለሚለው ብዙ ማሳያ ቢኖረኝም በህውሓት ሰፈር ጠፍቶዋል ያልኩዋችሁን ወጣት አመራሮች ከስር ከስር ማየቴ እና ለውይየት ጋባዥ የሆኑ የቢሮ ሃላፊዎች ዋናው ሲሆን በተለይ ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ላይ ዘለግ አድርገው ሃሰበው የሚሰሩት ሰራ ወደ ሌላ የአማራ ክልል ሊሄድ ይችላል የሚል ተሰፋ ስለነበረኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሰሞኑ ከየት መጣ ሳይባል አለምነው መኮንን የሚባል ካድሬ ከልጅነት እስከ እውቀት ሌሎች ሲሰድቡት የነበረውን እራሱ መቀበሉ ሳያንሰው የአማራን ህዝብ ሙልጭ አድርጎ ሲሳደብ ሰማነው፡፡ ያስታግሱታል ብሎም በተገቢው መንገድም ይቅርታ ጠይቆ ከሃላፊነቱ ይነሳል ብለን ስንጠብቅ ይባስ ተብሎ ሚዲያ ተሰጥቶት መግለጫ ሰጪ፤ ስለ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሰኬት አብራሪ አድርገው አቀረቡት፡፡ ይህን ጊዜ የገባን ካድሬው የግል ባህሪው ሳይሆን የድርጅቱ አቋም ነው ብለን ወሰድን፡፡ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ይህን አባል ድርጅት ምንነው ጃል ማለት አልቻሉም፡፡ በኢህአዴግ ሰፈር ለምርጫ ዘመቻ ተቃዋሚዎች የቀየሱት ዘዴ ነው የሚል ማደናገሪያ ይዘው ቀርበዋል፡፡ አሁን ማን ይሙት አለምነው መኮንን የሚባል ካድሬ ሲሳደብ እንጂ በብአዴን ውስጥ መኖሩን ሰምተንም አይተንም አናውቅም፡፡ ይልቁንም የምናውቃቸው ተሰፋ የጣልንባቸው የተሳደቡ መስሎን ስናጣራ አልሰማንም እሰኪ እኛም እናጣራለን ብለውን ከዚያ በኋላ ስልክ ማንሳት ትተዋል፡፡ ተሰፋ የጣልንባቸውም ቢሆኑ ባይሳደቡም ወደውም ሆነ ተገደው ተባባሪ ናቸው፡፡
ሌላው በዚያው በብአዴን ሰፈር የተነሳው አሰቂኝ ነገር ደግሞ የህፃናት፣ወጣቶችና ሴቶች (ከጎልማሳና አዛውንት ወንዶች በስተቀር ልንለው እንችላለን) ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ ደግሞ በፍፅሙ ከአንደ በዚህ ደረጃ ካለ ኢትዮጵያዊ በተለይ ከሴት በማይጠበቅ ሁኔታ ግብረሰዶማዊነት የሚደግፍ ፅሁፍ ካሰራጩ በኋላ እኔ አይደለሁም የማህበራዊ ድህረ ገፄ ቁልፍ ተሰብሮ ሌሎች ናቸው እንዲህ ጉድ የሰሩን የሚል ማስተባበያ ሰጡ ተባለ፣ ሌላው የከተማ ብአዴን አቶ ሽመልስ ከማል ደግም እዎ ተሰርቀው ነው አሉን፡፡ የመንግሰት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት የሚኒስትሮቻችን ማህበራዊ ድህረ ገፅ እንደሚመለከተው ያወቅሁት በዚህ ጉዳይ ነው፡፡ ሚኒስተሮቹ የማህበራዊ ድህረ ገፅ መድረኮችን መጠቀማቸው የሚበረታታ ቢሆንም በምንም ሁኔታ ግን ይህ የግል እንጂ የመንግሰት ሃላፊነት ሆኖ በመንግሰት ኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት በኩል መግለጫ የሚሰጥበት አይመስለኝም፡፡
እንግዲህ እነዚህ ብአዴኖች ናቸው ኢህአዴግ የሚባለውን የሰሩልን፡፡ ለህዝብ ሰሜት ሲባል አንድ ካድሬ ከስልጣን ሊያወርዱ የማይችሉ መሆናቸውን ሳሰብ ደከሙኝ፡፡ አንድ ነገር ግን ይታየኛል፡፡ አቶ አለምነው መኮንን በግላቸው ይቅርታ ጠይቀው ከፓርቲው ቢወጡ የበለጠ ሰላም ያገኛሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያለበለዚያ ግን በፍፁም ሰላም የሚሰጥ ሰህተት እንዳልሆነ አስምሬ መናገር እችላለሁ፡፡
ኦህዴድ ኢህአዴግን ከመሰረቱት አራት ፓርቲዎች በሶስተኛ ደረጃ የሚገኝ ቢሆንም ሰሞኑን የገባበት ውጥንቅጥ ግን ለብሔር ፓርቲ አደረጃጀት ትክክል አለመሆን ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ አንድ የብሔር ፓርቲ በተደላደለ ሁኔታ አመራር ለመምረጥና ለመተካት ምን ያህል ጊዜ ያስፈልገዋል? የኦሮሞ ህዝብ በቁመቱ ልክ በኢትዮጵያ ቦታ ሊሰጠው ይገባዋል የሚሉትን ሁሉ አንገት በሚያስደፋ ሁኔታ ኦህዴድ ድርጅቱን የሚመራ ሰው መሰየም አቅቶት ሲዋትት ቆይቶ በስንት ምጥ አሁንም እዚያው በዚያው ሽግሽግ አድርገው ኦህዴድ ዲሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ የፓርቲውን መሪ መረጠ አሉን፡፡ ዲሞክራሲያዊ የሚለውን ምን አመጣው ? የጦጢት ነገር እዚህም ትዝ ቢለንም አይገርምም ለማነኛውም ግን በድርጅታዊ አሰራር የሚለው ግን ሳይፃፍ አንብበነዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ይህ ፅሁፍ እያሰናዳው እያለ ክልሉ አሁንም ርዕስ መስተዳድር የለውም፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር የቀድሞ የድሬዳዋ ከንቲባ አሁንም በፓረቲው ውስጥ ዋናም ምክትልም ሳይሆን በሞግዚትነት እሰከሚቀጥለው ምርጫ እንዲያሻግሩ የታጩ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት የሰጠሁትን ግምቴን ለማጠናከር አቶ አባዱላ ገመዳ ወደ ክልል ሊመለሱ እንደሚችሉ ይሰማኛል ወይም በምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር ማዕረግ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ  አቶ ሙክታር ከደር እንደ ከሚል ስልጣን ከነሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ጋር የክልል ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በነገራችን ላይ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የኮታ ፖለቲካ በሁሉም ሰፈር አለ፡፡ በኦሮሚያም ቢሆን የዚህ እና የዚያ ዞን የሚል የጦዘ ፖለቲካ አለ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የሁለት ሺ ሁለት ምርጫ ይዞት የሚመጣውን ማዕበል ገና ያወቀ የለም፡፡ ለማነኛውም የሰላም እንዲሆን ሁላችንም በመቻቻል መንፈስ መስራት ይኖርብናል፡፡
እንግዲህ ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ናቸው ካልን እስከ አሁን ሶስት አራተኛ የሚሆነውን አይተናል ቀሪውን አንድ አራተኛ የያዘው የደቡብ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደህዴን ሲሆን ይህ ሱሙ በአቅጣጫ የተሰየመ ፓርቲ መሪው አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒሰትር ሲሆኑ ኢህአዴግን በመመስረት መጨረሻ ቢሆንም በትረ ስልጣን ለመያዝ ግን እድለኛ የሆነ ንቅናቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያኖች በጋራ አንድ ቤት ሊኖራቸው ይገባል ይቻላልም ብለን ስንሞግት አይችልም በብሔር መደራጀት ነው ለዚህች ሀገር መፍትሔው የሚለን ኢህአዴግ ከአምሳ ሰድስት በላይ የሆኑ ብሔሮችን በአንድ ላይ በደቡብ ንቅናቄ ሲያደራጅ እና በዚህ ምክንያት የሚታየውን የአሰተሳሰብ ተቃርኖ የሚረዳ ኢትዮጵያዊ አለ ብሎ አያምንም፡፡ ሲዳማዎች በሰማችን ጥሩን ደቡብ አቅጣጫ ነው ያሉት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የብሔራቸው ተወላጅ ስልጣን ላይ ሲወጣ የሚደሰቱ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ትግሬ ሲሾም ደስ የሚለው ትግሬ ይኖራል፤ ኦሮሞ ሲሾም ደስ የሚለው ኦሮሞ ሊኖር ይችላል፤ ሌሎችም እንዲሁ፡፡ በዚህ ስሌት ከሄድን በአቶ ኃይለማሪም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ደስ የሚለው ወላይታ ሊኖር እንደሚችል ባውቅም በምንም መመዛኛ ግን ይህ ሌሎችን የደቡብ ክልል በሚባለው የታቀፉትን ብሔሮች የሚያስደስት እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡ ስልጣን የሚያዘው በብቃት ሳይሆን  እንደ ኢህአዴግ ሰሌት በዙር ከሆነ በደቡብ ውስጥ ያሉት ብሔሮች በተለይ እንደ ሲዳማ፣ጉራጌ ከምባታ ኮታቸውን ጨርሰዋል ማለት ነው፡፡ ይህ በምንም ስሌት ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡ ደህዴን ኢህአዴግ ወደ ህብረብሔራዊ ፓርቲ መቀየር ከፈለገ እንዴት ማድረግ እንዳለበት ለሙከራ የተሰራ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ስልጣንም የበቃው በውስጡ ባለው ተቃርኖ ምክንያት የያዘውን ስልጣን በማነኛውም ወቅት ቁጭ አድርግ ሲባል ቁጭ ያደርጋል በሚል ስሌት መስረት እንደሆነ እንጠረጥራለን፡፡
የእነዚህ አራት ፓርቲዎች ሰብሰብ ኢህአዴግ የሚባለውን ግንባር እንደፈጠረልን ይታወቃል፡፡ የዚህ ሁሉ መሃንዲስ የነበሩት  ከኋላ ሆነው መሪውን ለመያዝ ሲለፉ ሲተጉ የነበሩት “ባለራዕዩ” መሪ አሁን የለሙ፡፡ መሪያቻው በቀየሱላቸው መስመር ይሂዱ አይሂዱ እንደሆነ ጊዜ የሚነግረን ቢሆንም፡፡ አሁን የምንሰማቸው አንድ አንድ ነገሮች ግን ይህን የሚያሳዩ አይዳሉም፡፡ ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በፈለጉት እና በታያቸው መንገድ እየሄዱ እንደሆነ ይታያል፡፡ ፓርቲዎቹ ከኢህአዴግ ምክር ቤት በወረዳ አጀንዳ መሰረት ተወያየተው መወሰን ትተዋል፡፡ በማዕከላዊ መንግሰት ደረጃም ሟቹን ጥላ ከለላ አድርገው እንደልባቸው ሲሆኑ የነበሩትም ቢሆን ጣሪያው እንደተቀደደበት ሰው ፍሳሹ አስቸገረን እያሉ ሁሁ ሲሉ እየሰማን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ተቃዋሚውን ጎራ ምንም ሳይደግፉት ይልቁንም ሲገፉት ቆይተው አሁን ግን ምን እየሰራችሁ ነው ማለት ጀምረዋል፡፡
ሊነጋ የሚመሰል ድቅድቅ ጨለማ ሀሉም ጋ ይታያል ….. ተሰፋ መቁረጥ እንዳይመጣ መጠንከር አለብን፡፡ ኢህአዴግ ግን እንደ ግንባር አንድ ቃል የሚናገር አይመስልም አጣባቂ ሙጫ የነበሩትን “ባለራዕይ” መሪውን አጥቶ ጎዳና ተዳዳሪ የሆነ ይመስለኛል፡፡
ቸር ይግጠመን፡፡

Friday, March 7, 2014

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በምሽት አትንዱ!! ዘመኑን መረዳት ያቃተው የሰነፍ ውሳኔ!!



በጥር አጋማሽ አካባቢ ምክር ቤቱ ለዕረፍተ ከመበተኑ በፊት አስቸኳይ ያላቸውን ጉዳዮች ለመጨረስ በሚል ከስዓት በኋላ በሰምንት ሰዓት ለመገናኘት ቀጠሮ ይዞ ምክር ቤቱ ሲበተን ወደ ቢሮዬ ተጠግቼ ምሳ ለመብላትና እግረ መንገዴንም በቢሮ አንድ አንድ ነገር አድርጌ ለመመለስ ሳዘግም ፒያሳ ላይ ያለው የትራፊክ ጭንቅንቅ መላወሻ ሲያሳጣኝ ፌቴን አዙሬ ወደ ጣይቱ ሆቴል አመራው፡፡ ብቻዬን ምግብ ቤት መመገብ ባልወድም የግዴን አንድ ጥግ ይዤ ቁጭ እንዳልኩ አንድ ሰው መጥቶ ቅር ካላለህ አብሬህ ብቀመጥ ብሎኝ ፈቃድ ሲጠይቀኝ በደስታ ብዬው አብረን ምሳ በላን፡፡ ጋበዘኝም! ግብዣውን ላለመቀበል  ስግደረደር አይዞህ አንተ ባለስልጣን አይደለህም ካንተ ምንም አልፈልግም ብሎ ካሰፈገገኝ በኋላ ወግ ጀመርን፡፡ እዚህም እዚያም እያልን ብዙ ጠቃሚ ውይይቶች ለማድረግ ዕድል አገኘሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ለእንደኔ ዓይነቱ መረጃ ቃራሚ ጠቃሚ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡
ካነሳናቸው ጉዳዮች አንዱ በምሽት አገልግሎት እንዳይሰጡ የታገዱትን ሚኒባስ እና መስል መኪኖችን የሚመለከት ሲሆን፤ በዛሬ ፅሁፍ ይህን ርዕስ እንዳደርግ ጫና ያደረገብኝ ደግሞ ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተዛማጅ የሆነ ዘግናኝ ዜና በጠዋት በመስማቴ ነው፡፡ ይህውም በምሽት የሚደረግ ትራንስፖርት አሁንም ባለመቆሙ፣ ይልቁንም በድብቅ በህገወጥ መንገድ የሚደረግ መሆኑ ያስከተለው አደጋ ነው፡፡ በጥር 27  ሊነጋ ሲል ከጎንደር አዲሰ አበባ ሰዎች ጭኖ ሊገባ ሲል ነጋ አልነጋ ብሎ ሲከንፍ ለጉዳያችን በፍጥነት እንደርሳለን ያሉ ሰድስት ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ ብዙዎች ለከባድና ቀላል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በሀገራችን በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው የሚያልፈው ቁጥሩ አሁን እየቀረበ ካለው እንደሚልቅ ደግሞ አንድ ባለሞያ በማግስቱ በሚዲያ ሲናገሩ ሰማሁ፡፡ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ከጥቂት ቀናት በኋላ ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች በመረጃው ውስጥ እንደማይካተቱ ነው ያስረዱን፡፡ በሀገራቸን የሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ዝቅ ብሎ የሚቀርበውም መረጃ ቢሆን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው ማንም ይስማማል፡፡ ዛሬ የትኩረት አቅጣጫ ማድረግ የፈለኩት ግን የምሽት ትራንስፖርት የተከለከለው በእርግጥ አደጋ ለመቀነስ ነው? ወይስ ሌላ ውስጠ ወይራ አለው?
በምሳ ላይ ያጫወቱኝ ግለሰብ እንደሚያምኑት ከሆነ በምሽት በሚኒባስ የሚደረግ ጉዞ የተከለከለው አንድም የቴክኒክም ሆነ የህግ መስረት ኖሮት ሳይሆን ይልቁንም በዋነኝነት ሚኒባሶች በሚሰሩበት መስመር የሚንቀሳቀሰው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ  “ሰላም ባስ” በመባል የሚታወቀው ድርጅት ባለቤትነቱ የኤፈርት ድርጅት ገቢ በመቀነሱ ነው የሚል ነው፡፡
ይህ ምንም እውነት የሌለው ግምት ወይም አሉባልታ ነገር ነው ተብሎ የማይተው ቢሆንም ግን ሚኒባስ ከ150 ኪሎ ሜትር በላይ መሄድ አይችልም ብሎ ብቃቱ ላይ ምስክርነት የሰጠው ማን ነው? አንድ ሚኒባስ ከአዲስ አበባ ናዝሬት ሶስት ጊዜ ደርሶ መልስ ሄደ ወይም ቀጥ ብሎ ባህርዳር፣ጎንደር ወይም ድሬዳዋ ሄደ ለውጡ ምን እንደሆነ የሚያስረዳኝ ሰው ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ተመሳሳይ የሆኑ መኪኖች ነገር ግን ባለቤታቸው ግን መንግሰት ወይም የቱሪስት ድርጅት ከሆነ በፈለጉት መንገድንና ጊዜ መጓዝ የሚከለክላቸው የለም፡፡ ተመሳሳይ መኪና ባለቤቱ ብቻ ስለተለያየ እንዴትና ወዴት መሄድ እንዳለበት ገደብ ይጣልበታል፡፡ የቴክኒክ ብቃት ከሆነ ምክንያቱ በማንም ባለቤትነት ይያዝ እገዳው መፅናት ይኖርበታል፡፡
ብዙ ሰዎች በተለይ በኤፍ.አም ሬዲዮ ስልክ ተደውሎላቸው (ደውለው ማለት ስለሚከብደኝ ነው) በዚህ ጉዳይ የምሽት ጉዞ መከልከል እንዳለበት አበክረው የሚገልፁበት ምክንያታቸው በምሽት በሚደረግ ጉዞ በሚፈጠር አደጋ የተማረሩ የሚመስሉ ናቸው፡፡ እንደው ለነገሩ በቀን አደጋ ቢበዛ በቀንም ይከለከል ይሆን? ሀገራችንን ቀን ከሌሊት ሰርተንም ቢሆን ለውጥ ለማምጣት መድከም ሲኖርብን በቀጭን ትዕዛዝ በምሽት መስራት አይቻልም የሚባልበት ሀገር መሆኗ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አሳኝም ነው፡፡ በሚኒባስ ሳይሆን በአውቶሞቢል ሀገር እያቋረጡ መሄድ በሚቻልበት የቴክኖሎጂ እና የተሻለ የሚባል መንገድ ባለበት ዘመን የዚህ ዓይነት መመሪያ አስገራሚነቱን ያጎላዋል፡፡ ሚኒባሶች መብራት የተሰራላቸው በምሽት መጓዝ ስለሚችሉና ስለአለባቸው ጭምር ነው፡፡ የምሽት ጉዞ በተለይ በጥሩ የአየር ሁኔታ ላይ ለመኪናም ሆነ ለተጓዥ እጅግ ምቹ እንደሆነ የሚታመን ነው፡፡ የየምሽት ጉዞ የሚፈልጋቸውን ጥንቃቄዎች መደረጋቸውን ማረጋገጥ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ በምሽት ተጉዞ፣ በቀጣዩ ቀን ጉዳዩን አጠናቆ በቀጣዩ ምሽት ወደ ቤቱ ተመልሶ ወደ ስራ ለመግባት የሚተጋን ሰው ከዚህ ትጋት የሚያደናቅፉ የኤፍ.ኤም ጀግኖች ተዉ የሚላቸው መኖር አለበት፡፡ ያለበለዚያ ግን እንደሚባለውም የገዢዎች ንብረት እና ተጠቃሚነትን የሚነኩ ድርጅቶች እጅ አለበት የሚባለውን ለማመን እንገደዳለን፡፡
ይህንን ሀሳብ ሳቀርብ በምሽት ጉዞ የሚደርስ አደጋን መከላከያው መንገድ ጉዞውን ማስቀረት አይደለም ከሚል መነሻ እንጂ በምሽት ጉዞ ላይ ምንም ዓይነት ቁጥጥር መደረግ የለበትም ከሚል መነሻ አይደለም፡፡ በምሽት መስራትም ሆነ መጓዝ የሚፈልጉ ዜጎች መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፡፡ ይህ መብት ፀኃይ ስለ አለችና ስለሌለች መሆን የለበትም፡፡ ጉዞው በህግ የሚገዛና ስርዓት ያለው ይልቁንም የዜጎችን ደህንነት በሚያረጋግጥ ደረጃ ላይ መሆኑን መቆጣጠር በሚያስችል መስመር ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሚኒባስ 12 ሰው መጫን ካለበት ከ12 ስው በላይ ጭኖ ቢገኝ የሚቀጣው ባለመኪናው ብቻ ሳይሆን በትርፍ ለመጫን ፈቃደኛ የሆነው 13ኛ ሰው ሲከፋም ይህን በመመልከት ምን ይደረግ ብለው ዝም ያሉት ሌሎቹ ተሳፋሪዎች ጭምር መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ስንችል ሰርዓት ያላው አገልግሎት ሰጪ ብቻ ሳይሆን ሰርዓት ያለው ተገልጋይም ማፍራት ይቻላል፡፡ ሌላው የፍጥነት ገደብ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ የመኪና ባለንብረቶች እንዲያስገጥሙ ማድረግ አሁን ባይቻልም፣ መንግሰት በየመቶ ኪሎሜትር ቲኬት መቁረጫ ማሽኖችን በማስቀመጥ አሽከርካረዎች የደረሱበትን ሰዓት በመመልከት ከፍጥነት ገደብ ውጭ የተጓዙት ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በየባንኮችና ቢሮዎች ወረፋ ለመያዣነት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ማሽን ዓይነት ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው አሽከርሪዎች በጉዞ ላይ የሚጠቀሙተን ጫትና ሌሎች ደባል ሱሶች እንዲያቆሙ በፍፁም ቁርጠኝነት መመሪያውን ለመተግበር በመወሰን እንጂ፤ ሰራ የምትሰሩት ፀኃይ ስትኖር ብቻ ነው የሚለውን የሰነፍ መንገድ ተገቢ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ችግር ብልዓትን ይፈጥራል የሚለውን ብሂል ከመተግበር እና ዜጎችን ቴክኖሎጂ ለመጠቀምና ለፈጠራ ከማንቃት ወደ ቁጥጥር ማድለት የመንግሰትን ደካማነት እንጂ ለዜጎች ሃሳቢነትን አያሳይም፡፡

አሁን በማን አለብኝነት ወይም ደግሞ ከአንድ ሰፈር በተፈጠረ የጥቅም ግጭት ምክንያት በተሰጠ ጥቅሻ ብዙ መቶ ሺ ብር አውጥተው ሰርተን እናድጋለን ቤተሰቦቻችንን እናስተዳድራለን ብለው ወደ ትራንስፖርት ዘርፍ የገቡተን ዜጎች እጅግ አሳዝኖዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም መንግሰት ሊወስዳቸው የሚችላቸው ቁጥጥሮች እና የሚያወጣቸው መመሪያዎች ተገማችነት የሌላቸው በመሆናቸው በማነኛውም የስራ ዘርፍ ተሰማርቶ መስራት አደገኛ ነው ወደሚል መደምደሚያ የሚወስድ ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ይህን ተማምነው ከውጭ መጥተው ሰራ የጀመሩ ቢሆንም አሁን ደግሞ በኪሳራ ሸጠው ወደ ውጭ ለስደት ተሰጋጅተዋል፡፡ በዚህ ገንዘብ ትልቁ ልጄን ውጪ ልኬ መኪናው የሚያመጣውን ያህል እርሱ ይልክልኛል ብለው ያጫወቱኝ ጎልማሳ አሉ፡፡ የመንግሰታችን መልስ ይሞክሩት እንደሚሆን አለመጠርጠር ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ ባለንብረቶች የምሽት ጉዞ ንብረታቸውን ሲያሰማሩ የሾፌሮችን ብቃትና የመኪናቸውን ደህንነት እያረጋገጠ ሰምሪት የሚሰጥ አንድ ማህበር በማቋቋም ንብረታቸውን በህገወጥ መንገድ ለአደጋ እና እንዲሁም ዜጎችን አደጋ ላይ የሚጥል አገልግሎት እንዲቆም ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውን ማሳየት እና በህገወጥ መንገድ የተጣለባቸውን የምሽት አገልግሎት የመስጠት መብት ለማስከበር መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሰትም ከፍተኛ ንብረት ወጥቶበት የተገነቡት መንገዶች 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ ለማመቻቸት ከክልከላ የተሻለ ዘዴ ለመቀየስ መስራት ይኖርበታል፡፡ ክልከላው የሰነፍ መንገድ ነው፡፡ 
ይህን ፅሁፍ እንድከትብ ያነሳሳኝ የጥር 27/2006 አደጋ መሆኑን በመግቢያዬ ገልጫለሁ፡፡ ስለዚህም ይህ መኪና ከጎንደር ተነስቶ አዲስ አበባ ሊገባ 20 ኪሎሜትር ሲቀረው ነው የተገለበጠው፤ የተገለበጠውም ሳይነጋ ትራፊክ ሳይዘው ለመግባት በሚያደርገው ጥረት እና በነበረው ፍጥነት ምክንያት ነው፡፡ ይህን ሁሉ ኪሎ ሜትር አቋርጦ የተጣለውን ክልከላ ጥሶ ሲመጣ መቆጣጠር ማሰቆም ያልተቻለው ለምንድነው? በዚህ ሁሉ መንገድ የነበሩ ይህን መመሪያ እንዲያስከብሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ክፍሎች ሁሉ በህግ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በሹፌር ላይ ጥፋቱን አላኮ መቆም የለበትም፡፡ ይህ በጥቅሻ እንቅስቃሴን ማስቆምና ማሰቀጠል ተጠያቂነት ሊኖርበት ይገባል፡፡ የዜጎች ህይወት በከንቱ እንዲጠፋ ምክንያት የሆኑት ሁሉ ለህግ እንዲቀርቡ ሁሉም ይጩኽ፡፡
በመጨረሻም እንደነገሩ የምንፅፋቸው ፅሁፎች አንባቢ እንዳላቸው እርግጠኛ ብሆንም የሚመለከታቸው አካላትም እንደሚያነቡት የሚያሳይ ሁለት የእግረመንገድ ነጥብ ላንሳ፡፡  በአንድ ወቅት ቃሊቲ ሄጄ ባነበብኩት ማሰታወቂያ መሰረት በመንግሰት ሀብት የብአዴን በዓል እንደሚከበር ገልጬ ነበር፡፡ የካቲት 2/2006 አንዱዓለም አረጌን ለመጠየቅ ሲሄድ ምንም ዓይነት ማስታወቂያ በሩ ላይ መለጠፍ ክልክል መሆኑን አንብቤ መጥቻላው፡፡ ይህ የሚያሳየው ፅሁፉን እንዳነበቡት ሲሆን የወሰዱት እርምጃ ግን የመንግሰትን ንብረት ለፓርቲ መጠቀሚያ እንዳይውል ማድረግ ሳይሆን አሁንም የመከልከል ዜዴያቸውን ነው የተጠቀሙት፡፡ የሰነፉን መንገድ፡፡
ሌላው ለፅሁፋችን ተነባቢነት ማሳያው አቶ አሰራት ጣሴ በአዲስ ጉዳይ ላይ ባሰፈሩት ሀሳብ ምክንያት ፍርድ ቤት ደፍረዋል ተብለው ለእስር መዳረጋቸውን ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ሊማሩ የሚገባ የነበረው፤ የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል የሚለውን ወርቃማ አባባል ሲሆን በተቃራኒው ከመንግሰታቸው ባልተለየ የማስፈራሪያ ዘዴያቸውን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ትላንት የተሰጠውን ውሳኔ መሰረት አድርጌ ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡
ለማነኛውም የዚህ ፅሁፍ አንባቢ የሆናችሁ የትራንስፖርት ዘርፍ ሹሞች ሀገራችን ኢትዮጵያ ሃያ አራት ሰዓት ሰርተን ዓለም ከደረሰበት ለመድረስ ብዙ እንደሚቀረን ተገንዝባችሁ ለሰራ የሚያነሳሳ ዘዴ እንድታሰቡ አደራ እላለሁ፡፡ ያለበለዚያ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የቀኑንም ትራንሰፖርት አስቁሙና የትራፊክ አደጋ በመቀነስ ከዓለም አንደኛ ለመሆን ሞክሩ፡፡ በትራንስፖርት ኤኮኖሚክስ ከአደጋ ነፃ የሚባለው ዜሮ ርቀት ነው፡፡
ቸር ይግጠመን