Wednesday, April 29, 2015

የኦሮሞ ጉዳይ …. መፅሃፍ እና የፀሃፊው የሰለሞን ሰዩም የኦነግ ፍቅር

ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com, girmaseifu.blogspot.com
እውነቱን ለመናገር የሰለሞን ሰዩምን የመጀመሪያ ክፍል መፅሃፍ ሳነብ ትዝ ያለኝ በአንድ ወቅት “ኮንዶም ኤች.አይ.ቪ አይከላከለም” የሚል መፅሃፍ የፃፈውን እብድ ሰው ነው ያስታወሰኝ፡፡ ፀረ ኮንዶም የሆነ አሰተሳሰብ ያላቸው አብዛኞቹ የሀይማኖት አክራሪና “ፕሮ ላይፍ” በመባል የሚታወቅ የአሰተሳሰብ ዘርፍ ደጋፊ ሰዎች የፃፉትን ሰብሰቦ በማስረጃ የተደገፈ በሚል ነበር ኮንዶም ኤች አይ ቪን አይከላከልም እያለ ህዝቡን ለማሳሰት የሞከረው፡፡ አሁንም ሰለሞን ሰዩም ፅንፈኛ የኦሮሞ ነፃነት አቀንቃኞች እና “አማራ ጠል” አስተሳሰብ አራማጆችን እየጠቀሰ ኦሮሞ በእቅድና በዝግጅት ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር አማራ በሚባል ገዢ መደብ ስትረገጥ ነበር ሊለን ይሞክራል፡፡ እግረ መንገዱንም በእርግጥ ይህን የሚፅፈው እኔ የማውቀው ሰለሞን ሰዩም ነው? የሚል ጥያቄም ጭሮብኛል፡፡
ሌላው ጥያቄ የጫረብኝ ሰለሞን ስዩም መፅሃፍ ፅፎ ግዙ ካለ በኋላ ሃሳቤን ለመቅረፅ ነው ያለውን ዘመነኞቹ “ላይክ” አድርጌዎለሁ የሚሉት አይነት ፌዝ ይጋብዛል፡፡ ለማነኛውም እኔ ደግሞ የወደድኩለት የፈለገውን ብሎም ቢሆን ኢትዮጵያችን በኦሮሞነት የበለጠ የምታምር መሆኑን ለማሳየት መሞከሩ ነው፡፡ እርሱም የዚሁ አባል እንደሆን በገደምዳሚ የነገረን በጋራ ቤት የመኖራችን ሚስጥር ገልጦልኛል፡፡
ሰለ ኦሮሞ ብሔርተኝነት እና የአማራ ገዢ መደብ
ሰለሞን ሰዩም የአማራ የበላይነት ሲባል ገዢ መደቡን ነው ብሎ በመግቢያ ላይ ቢነግረንም እዚህም እዚያም የአማራ የበላይነት ለመታገል በሚል የኦሮሞ ብሔርተኝነትን የሚገልፅበት መንገድ አማራን እንደማያሸማቅቅ ሊነግረን አይችልም፡፡ የትግራይ ነፃ አውጪዎች ትግል የአማራ ገዢ መደብ ሲሉ ሊደግፋቸው የተሰበሰበው ህዝብ እንዴት አድርጎ “አማራ ጠል” እንዲሆን እንዳደረጉት አብሮን ያለ እውነት ነው፡፡ ሰለሞንም በገፅ 153 ላይ በግልፅ “የሆነው ሆኖ የገዢ መደብ ቡድኑ የተገኘባቸው ዘውጌዎች፣ ቁሳዊ ጥቅም ባያገኙም ሰነ-ልቦናዊ ገዥነት መላበሳቸው ተፍጥሯዊ በመሆኑ ምንም ነገር አልተጠቀመሙ ማለት አይቻልም፡፡” በሚል አስቀምጦታል፡፡ ይህ ደግሞ በመግቢያው ላይ “የአማራ ገዢ መደብ፣ ከአማራ ህዝብ ጋር አንድ አድርጋችሁ አትውሰዱ” ካለው ጋር ይቃረናል፡፡
ሰለሞን በኦሮሞ ላይ የደረሰውን ግፍ ለማጉላት ከ30 ሚሊዮን ኦሮሞ የሶስተኛ ደረጃ ትምህርት ያገኘው 0.01 ከመቶ በታች ነው ብሎ ያልተሟላ ማስረጃ ቢጠቅስም የሌሎች ብሄሮችንም የመቶኛ ድርሻ ማሰቀመጥ ይገባ ነበር ብሎ የሚጠይቅ እንዳለ አልተረዳውም፡፡ በኦሮሞ ላይ የደረሰ በደል ጥልቀት ለማሳየት “ኦሮሞ በአበርክቶው እንዳይኮራ፣ ብሔረተኝነቱ እንዳያብብ፣ ባህሉን የማናናቅ፣ በራስ የመተማመን ሰሜት የመሸርሸር ስራ የተተገበረው በተጠና ዘዴ እንደነበር የሚናገሩ አሉ፡፡” ይልናል፡፡ ነገር ግን ይህን ጥናት ማን አስጠና? ማን አጠና? የጥናቱ ሰነድ አለ ወይ? ተብሎ ሳይጠየቅ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት ወደፊት አለማለት የአማራ ገዢ መደብ በሚል አማራን ለመክስስ እጅ መጠንቆል ከሰለሞን የሚጠበቅ አልመሰለኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ ፅንፈኛ የኦሮሞ ነፃ ሀገርነት የሚደግፉ ሰዎችን ፅሁፍ መጥቀስ ሚዛናዊ አያደርግም፡፡ የበለጠ ያስገረመኝ “በተለይ እስከ 19983 ድረስ የኢትዮጵያ መንግሰት የአማራ ገዢ ልሂቃን መንግስት ብቻ ነበር፡፡” (ገፅ 22/23) የሚለው የሰለሞን ድምዳሜ ኢህአደግ ተጨፈኑ ላሞኛቹ እንደሚለው ዓይነት ሆኖብኛል፡፡ ሁሉን ትተን ደርግ ዘውጊያዊ ማንነት የነበረው ስብሰብ ነበር ለማለት የምናውቀው ሀቅ ይተናነቀናል፡፡ በሳበ ፊደልም ቢሆን ኦሮምኛ ይፃፍ እንደነበር በግሌ አውቃለሁ፡፡ የኦሮምኛ ሬዲዮ ፕሮግራም ነበር፡፡ በቂ አልነበረም ያስማማናል፡፡ በሰለሞን መፅሃፍ ውስጥ የቁቤ ፊደል ከሳባው ፊደል የተመረጠበትን እውነተና ምክንያት አግኝቻለሁ፡፡ ይህም ክፍሌ ጆቴ “በኦሮሞ ህዝብ የስነ-ልቦና ነፃነት ወሳኝ ነው፡፡” በሚል የቀረበው ነው፡፡ አማራ ገዢ መደብ ጨቋኝ ተደርጎ በተሳለበት አግባብ አማርኛ በሚፃፍበት የሳባ ፊደል ኦሮሚፋን መፃፍ የሚፈለገውን የሰነ ልቦና ነፃነት አይሰጥም ሰሜት ይስጣል፡፡  
የኦሮሞ ጠልነትና የኦሮሞ ጥላቻ በተደራጀ ከላይ በጠየቁት መሰረት በጥናት ባይሆንም በምድር ላይ ያልነበረ ውሸት ነው ብዬ ልሞግት አልችልም፡፡ አንድ አንድ ጓደኞቼ እኔ የኦሮሞ ደም እንዳለኝ ሳያውቁ፣ አንድ አንዶች አውቀው ለነገር ፍላጋ የሚናገሩት ነገር እንዳለ አውቃለሁ፡፡ የግል ገጠመኞቼም ነገር ከማባባስ አልፍ ድምዳሜ ስለማያደርሱ እዚህ መጥቀስ ተገቢ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ግን በኦሮሞዎች ዘንድ ኦሮሞ ከሁሉም የሚበልጥ ምርጥ ነው፣ የተፈጥሮ ሀብት በተለየ ሁኔታ ያለው፣ ሌላው ለዝንብ ማረገፊያ ቅጠል የሌለው እስኪመስል ድረስ ፅንፍ የያዙ ነገሮች አሉ፡፡ አሁንም በግልፅ በኦሮሚያ ክልል የሚታይ “ኦሮሞ ያልሆነን ጠልነት” የምንታዘበው ነው፡፡ ለማነኛውም ሰለሞን ሰዩም “ግማሽ መንገድ የመጣውን ኦሮሞ፣ የአንድነት ሀይሎችም ግማሽ መንገድ ሄደው ይቀበሉት” ቢልም አሁንም ሰለሞን መምጣቱ ልክ ቢሆንም ኦሮሞ እንደ ህዝብ ወደ ግማሽ እንዲመጣ የማይፈልጉ፣ ሌላውም መጥቶ በፍቅር መኖራችን የሚያባንናቸው እንዳሉ መርሳት የለብንም፡፡ እንደ አንደ ኦሮሞ እና እንደ አንድነት ሀይል አቀንቃኝ እኔ በማራምደው አስተሳሰብ አንድ የኦሮሞ ልጅ የሚጎዳ ከሆነ አንገቴን እሰጣለሁ፣ ኦሮሞ ስለሆነ ሳይሆን ሰው ስለሆነ ብቻ፡፡ እርግጠኛ መሆን ያለብን ግን ጉዳዩ የአማራና የኦሮሞ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እና ኢትዮጵያችን ነች፡፡ ይህን የምለው በፍፁም የአማራ ገዢ መደብ ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ስለማልስማማ ነው፡፡ አማራም አማራነቱን ሳይተው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ኦሮሞም ኦሮሞነቱን ሳይተው ኢትዮጵያ ነው፡፡ ለእኔ የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት የምጠይቀው የሚስጠኝ ምንም ገዢ መደብ የለም፤ ወዘተ ….
ለማነኛውም ሰለሞን ሰዩም ማለት የፈለገው በትክክል ገብቶኝ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ የሚባል ነገር ተወው ባክህ የሚባል አይደለም፡፡ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ሊስተናገድ የሚገባው የፖለቲካ አጀንዳ ነው ለማለት ነው፡፡ ዋናው ምሳሌ የኦሮሚያ ጉዳይ ቢሆንም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከአንድ ዓይነት ብሎኬት እንደተሰራ ቤት አይደለችም እያለን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ለመሆንም ማንነትን መልቀቅ አያስፈልግም የሚል ነው፡፡ ይህ የገባኝ ቢሆንም በኢትዮጵያ ብሔርተኛ ወይም ደግሞ የአንድነት ደቀመዝሙሮች ያላቸውን ደግሞ ባልተገባ ሁኔታ ለራሱ በገባው ወይም ደግሞ አክራሪ የኦሮሞ ነፃነት አቀንቃኞች የሰጡትን አስተያየት እያጣቀሰ ተገቢ ያልሆኑ ድምዳሜዎች ላይ እንደንደርስ ሊገፋን ሞክሯል፡፡ እኔ የአንድነት ደቀ መዝሙር ነኝ፡፡ በፍፁም የማንንም ማንነት ተለውጦ አንተ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነህ እንዲባል አልፈልግም፡፡ አሜሪካዊ ሲባል አይሪሽ መሆኑን፣ አፍሪካ አሜሪካ መሆኑን ደብቅ ተብሎ ያውቃል፣ እኛስ ለምን?
የሰለሞን ግራና ቀኝ ትንተና
የሰለሞን ግራና ቀኝ ትንተና የራሱ በገባው ያሰመረው እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባቦት የተደረሰበቱ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ስል የተለየ ንባብ ሳያስፈልገኝ አሁን ባለው ሁኔታ ቀኝና ግራ ትንተና የማውቀው “ግራ” የሚባሉት ወደ ኮሚኒስት አስተሳሰብ የሚያዘነብሉ ሲሆን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ፖለቲካ ትንተናቸው ይህንኑ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ “ቀኝ” የሚባሉት ደግሞ በካፒታሊሲት ርዕዮት የሚከተሉ ወይም ወደዚያ የሚያጋድሉ ናቸው፡፡ እነርሱም የኤኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ትንተናቸው ይህንኑ መስረት ያደረገ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ጥጎች አማካይ የሚባል ቦታ አለ፡፡ ይህ ማዕከል ግን ሀሳባዊ ነው፡፡ አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ የሶሻሊሰት/ኮኒሚኒስት የሚባሉ ሀገሮች በብዛት/በተግባር የሉም ካሉም በእጅ ጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሰለዚህ በዓለም ላይ የሚደረጉ ቀኝና ግራ ዘመም ትንተናዎች ከአሳባዊው አማካይ ተነስቶ ወደ ቀኝ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የእኛው ሀገር አብዮታዊ ዲሞክራሲም ምናልባት በተግባር ሃሳባዊው አማካይ አካባቢ ቢገኝ እንኳን በሀሳባ ግን በአካባቢው የለም፡፡ ምን አልባለት ግራ ሰፈር ሊገኝ ይችላል/አልባኒያ ሶሻሊዝም እያሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሰለሞን ሰዩም ትንተና ኢህአዴግ ግራ የገባው ግራ አንጂ ቀኝ ሊሆን አይችለም፡፡
ሰለሞን ስዩም በተጨማሪ “የ1960ዎቹን በጅምላ ግራ ዘመም ማለት ልክ አይደለም”(122)ይላል፡፡ ልክ ለመሆን የፈለገ ሁሉም የሶሻሊስት/የኮሚኒዝም አቀንቃኝ ነበሩ ስለዚህ ግራ ዘመም ብቻ ሳይሆን ግራዎች ናቸው፡፡ ሰለሞን እንደ መነሻ የወሰደው ግራኞች ተራማጆች፣ ቀኞች ደግሞ አድሃሪያን (ሪአክሽነሪ) የሚለው ፍረጃን ነው፡፡ ይህ ፍረጃ የግራዎቹ ኮሚኒስት አስተሳሰብ ያላቸው ለራሳቸው ያወጡት የተሳሳተ ሰያሜ ነው፡፡ ሰለሞን በምሳሌ ያቀረባቸው “ኮንሰርቫቲቭ” እና “ሌበር” የሚባሉት ሁለቱም ከሴንተር/ከአማካይ በስተቀኝ ባለው ሰፍር በተወሰነ ርቀት የሚለያዩ ናቸው፡፡ በውስጣቸው ግራና ቀኝ ዘመም ሲባል እንኳን ከአማካዩ ባላቸው ርቀት እንጂ በፍፁም ሶሻሊስት/ኮሚኒስታዊ ርዕዮት ቅርበት አይደለም፡፡ የእኛዎቹ ኢህዴጎች ግን ከአማካዩ በግራ ብቻ ሳይሆን እዛም ውስጥ ግራ የገባቸው መሆኑ ነው፡፡ ግራ መሆናቸው ማሳያው ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ያላቸው ግዴለሽነት/አስመሳይነት፣ ለነፃ ኢኮኖሚ የመንግሰት ጣልቃ ገብነት ፍቅር፣ አጭበርባሪ የሆነ ህዝባዊ ህዝባዊ የሚሉት ምሽግ፣ ብዙ ሊባል ይችላል፡፡
ብሔረተኝነት ግራ ዘመም የሚያሰኘው ነገሩን ከግለሰብ ነፃነት መልስ ከመስጠት ይልቅ እንደ ስታሊን በቡድን ሀስተሳሰብ ውስጥ  ስለተገለፀ ነው፡፡ በራሱ ግን ግራና ቀኝ መመደቢያ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይ አሁን ባለው የሃያ አንደኛ ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ አንፃር የግለሰብ መብት ሲከበር የቡድን መብት ይከበራል ከሚል ድፍን ሎጂክ ዘለል ብሎ የቡድን መብቶች በአንድ አንድ ወሮበሎች እንዳይደፈር ጥበቃ እንዲደረግለት ዋስትና መስጠት ዘመናዊነት እንጂ ቆመ ቀርነት ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህም መነሻ ብሔረተኞች ግራ ወይም ቀኝ ለመባል ሌሎች ተጨማሪ መስፈርቶች መጠየቅ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የሰካንዲኒቪያን ሀገሮች ኮሚኒሰታዊ/ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ የላቸውም ነገር ግን ወደ አማካዩ ከቀኙ የመቅረብና የመራቅ ጉዳይ ነው ግራ ዘመም፣ ቀኝ ዘመም የሚያሰኛቸው፡፡ ብዙዎች የሚሳሳቱትም በዚሁ መስመር አረዳድ ችግር ይመስለኛል፡፡ ሰለሞን “ያ አንድነት” በማለት የጠቀሰው የእኔ እና የሰለሞን አንድነት ይህን በቅጡ የተገነዘበ ፓርቲ ነበር፡፡ በኢህአዴግ ልክ ስለአልተሰፋ አደገኛ ሆኖ ተገኝቶ ፖለቲካ ውሳኔ ባይሰጥበት፡፡
የሰለሞን የኦህዴድ ጥላቻና የአለማየሁ አቶምሰ ፍቅር
ሰለሞን ሰዩም ለኦህዴድ ያለውን ጥላቻ እና ለአለማየሁ አቶምሳ የሚያሳየው ፍቅር እኔና ዳዊት ሰለሞን ክትፎ በፖፖ የምንለውን ያስታወሰኝ፡፡ ይህ አባባል በእርግጥ ያመጣው የአዲስ አበባ ህዝብ ነው፡፡ ኤርሚያስ ለገሰ የሚባል የኢህአዴግ ውስጥ አዋቂ ሰል አርከበ እቁባይ መረጃ እያወጣ ጥርጣሬ ውስት ከመክተቱ በፊት አቶ አርከበ ለአዲስ አበባ ህዝብ ጥሩ ነበሩ ይባል ነበር፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል ኢህአዴግ ናቸው፡፡ ሰለዚህ ክትፎ በፖፖ አይበላም ብሎ የአዲስ አበባ ህዝብ እርሰቸውን እንኳን በ1997 ምርጫ ሳይመረጥ ቀረ፡፡ አሁንም የሰለሞን ሰዮም ስለ አለማየሁ አቶምሳ የሚያቀርበው ተረክ መለስ ዜናዊ ከሙሰና የፀዳች ኦሮሚያ እንድትኖር ይፈልግ ነበር የሚያስብል ይመስላል፡፡ ሰለሞን ሰዩም ለሌንጮ ለታም ያለውን ፍቅርና በተለይ ለአዲሱ ፓርቲ ልቡ ክፍት አንደነበር መረዳት አይገድም፡፡ አለማየሁ አቶምሳም በህይወት ቢኖር የኦዴግ ይሆን ነበር የሚል ነው የሚመስለው፡፡ በእኔ እምነት ሌንጮ ከአዲሱ ፓርቲ ጋር በአዲስ አስተሳሰብ መጥቻለሁ ሲል የድሮ ያስከፈለውን ውድ ዋጋ ተረክ ተርኮልን፤ ካስፈለገም አፉ ብለን መሆን አለበት፡፡ ከኦህዴግ ጋር ተሻርኮ በጓሮ በር ለመግባት መሞክር ቅቡል አይመስለኝም፡፡ ሰለሞን ያንገበገበው በእስር ቤት ኦሮምኛ መስፋፋት የኦነግ ጦስ ጭምር ነው፡፡ ኦነግ እሰሩልኝ ብሎ ባይሆን እንኳን በሰሙ ጭዳ መሆናቸውን ሌንጮ ያጣዋል ብዬ አልወስደውም፡፡
ለማነኛውም የሰለሞን ሰዩም መፅሀፍ በተሟላ ሁኔታ “የኦሮሞ ነፃነት አቀንቃኞችን” የፃፉትን ፅሁፎች  በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛም ሆነ በቁቤ የተፃፉትን በሚያስባስብ መልኩ ከዚህ በተሻለ ዝርዝር ቢያቀርበልን በተለይ ቁቤ ለማይገባን ለእኛ ምስኪኖች ጥሩ ድጋፍ ይሆን ነበር፡፡ ከዚህ መለስ ያለውን የመፅሃፍ ክፍል በፋክት ላይ ቀርበው ለነበሩት ሙግቶች የተሰጠው መልስ አልተመቸኝም፡፡ አንደኛ በእርግጥ ያስፈልግ ነበር ወይ? የሚል ሲሆን፤ በማስከተልም መልሱ በእርግጥ በተደራጀ እና በሞጋች መልኩ ለማስተማር የሚረዳ ነበር ወይ? የሚል ጥያቄዎች ያስነሳል፡፡ ሌላው እነዚህ ፀሃፊዎች የአማራ ገዢ መደብ የሚባለውን ይወክላሉ? በሚል ነው ወይስ ርዝራዦች በሚል? አልገባኝም ስለዚህ የመፅኃፉን ይህን ከፍል አልወደድኩትም፡፡ መብቴ ነው!!!!



No comments:

Post a Comment