Friday, April 24, 2015

በዚህ ጊዜ እንኳን ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንቁም …. ማለትም የፖለቲካ ቁማር ይቅር

ወዳጄ ከበደ ካሰ ዘወትር ወዳጄ ስልህ በግል ጠብ የሌለን የሀሳብ መስመራችን ግን አንድ አለመሆኑን በማስታወሰ ነው፡፡ ይህን አንተ እንደምትረዳው አውቃለሁ፡፡ አንድ አንድ አብረውህ በቡድን በሚመስል መልኩ የሚሳደቡትን ግን እንዳተ በግንባር ባላውቃቸውም ወዳጅነት ግን የሚኖርኝ አይመስለኝም፡፡ የሃሳብ ሳይሆን እነርሱ ጥቁረቴን ሁሉ የሚጠሉት ይመስለኛል፡፡ እጥረቴም ኢህአዴግን ለመቃወም ሆን ብዬ ይመስላቸዋል፡፡ ለማነኛውም በሪፖርተር ላይ  “ከአይኤስ” እኩል የማወግዛቸው …” በሚል ርዕስ ያሰፈርከውን ፅሁፍ አንብቤ በተረዳሁት መልክ መልስ ልሰጥህ ወደድኩ፡፡ ይህ በአስራ ሰድስት አንቀፅ ተክፍሎ የተፃፈን ፅሁፍ እንዲህ አድርጌ አየሁት፡፡
አንቀፅ አንድ ላይ በሰፈረው በሙሉ ተሰማምቻለሁ፡፡ በአንቀፅ ሁለት ላይ “በየትኛውም ሁለተኛ ሀገር በሰደት መኖር በሰላም ወጥቶ በሰላም ለመግባት ዋስትና አይሰጥም” በሚል መደምደሚያ የጀመርከው ግን በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡ ለማሳያ ያቀረብካቸው ሀገሮች ላይ ትክክል ነህ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት አይቻልም፡፡ በዓለም ግን እጅግ በጣም ብዙ ሀገሮች የሰው ዘር በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባባቸው ናቸው፡፡ በተለይ እናነትተ አብዮታዊ ዲሞክራቶች፤ ኒዎ ሊብራል እያልችሁ በምትሰድቧቸው ሀገሮች “ዜጋ” አይደለም ባጠቃላይ የሰው ልጅ በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባባቸው ሀገሮች ናቸው፡፡ ይልቁንም ብዙዎቻችን በሀገራችን በሰላም ወጥተን በሰላም እንድግገባ ሃላፊነት ያለባቸውን የደህነነትና የፖሊስ ሀይሎች የምንፈራበት ሀገር ውስጥ የምንኖር መሆናችን ትንግርት የሚያሰኝ በምድር ላይ ያለ ሀቅ ነው፡፡ ይህ አስተያትህ ከልምድ ማነስ ነው ብዬ ለመውሰድ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ አንድ ወዳጄ በውጭ ሀገር የሚኖር በአሜሪካን ሀገር የነጮች ዘረኝነት በግልፅ ይታየኛል፣ ነገር ግን በሀገሬ እንደሚሰማኝ ዓይነት በፖሊስና ደህንነት ክትትል እየተደረገብኝ አደጋ ላይ እወድቃለሁ የሚል ስጋት የለበኝም ነው የሚለው፡፡ በሀገራችን ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው የሚል ህገመንግሰታዊ ድንጋጌ ቢኖርም ከቤ አንተ እና አለቆችህ በህግ ፊት እኩል ናችሁ? በስልክ የሚያሳስሩ፣ በስልክ የሚያስፈቱ አለቆች አታውቅም? እውነት ብቻ ተናገር መወሻሸት አያስፈልግም፡፡
በሶሰተኛው አንቀፅ ላይ አሁን በሊቢያ የተፈጠረውን ጉዳይ የሙስሊም ጉዳይ አድርገው ሊያጣሉን ከሚፈልጉ ሀይሎች መጠበቅ እንዳለብን ያስቀመጥከው ትክክል ነው፡፡ ከዚህ የከፋም ሊመጣ ስለሚችል በፅናት በአንድነት መኖር ይኖርብናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የእነዚህ ሰማዕታት ደም ለአንድነታችን ማጠናከሪያ በማድረግ ጠላቶቻችንን ማሳፈር ይኖርብናል፡፡ ከአይኤሰ እኩል የማወግዛቸው ያልከው እነዚህን ስለሆነ ተሰማምቻለሁ፡፡ በማስከተል የፖለቲካ ቁማርተኞችን እንደምታወግዝ በትክክል አስቀምጠህ ቁማርተኛውን መረጣ ላይ ግን አድልዎ አሳየተሃል፡፡ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ተገዥነትህን በግልፅ አስቀመጥክ፡፡ አሁን ድረስ በእነዚህ ወንድሞቻችን ደም የፖለቲካ ቁማር እየተጫወተ ያለው ማን ነው?
በዚህ ፅሁፍ በግልፅ የተረዳሁት ነገር ብዕር ያነሳኽው የአሁኑ የምታገለግለውን ድርጅት ኢህአዴግን/ገዢውን ፓርቲ እና የቀደሞ መስሪያ ቤትህ ኢቲቪን ለመከላከል ነው፡፡ ይህ ግን በፍፁም አልተሳካልህም፡፡ በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ላጣራ ያለው መንግሰት እስከ አሁን እንዳላጣራ የሚያሳብቀው ሟቾች ኢትዮጵያዊያን መሆናችው ቢታወቅም አሁንም ሁሉም ክርስቲያን መሆናቸው የሚያረጋግጥ መረጃ አልወጣም ብለሃል፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በሆነ መንገድ ከተጣራ እነዚህ ሰዎች ሙስሊም ይሁን ክርስቲያን እንዴት መለየት ያቅታል? ሌላው በፍፁም መሸሽ የፈለከው የፖለቲካ ቁማር እየተጫወተ ያለው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ መሆኑን መግለፅ ነው፡፡ ይህን በፍፁም አታደርገውም፡፡ ሰደተኝነት ምንጩ በ24 ዓመት ለብሔራዊ ውርደት የዳረገንን ድህነት ማስወገድ ያልቻለው ኢህአዴግ እንጂ በ17 ዓመት በጦርነት ተወጥሮ የነበረው ደርግ ሊሆን አይችልም፡፡ አሁን በስደት የሞቱት ደግሞ የኢህአዴግ ትውልዶች ናቸው፡፡ ሀገር ጥላችሁ አትሂዱ ሰራ በሀገር ሞልቶዋል እያለ የልማት ፖለቲካ የሚነዛ ያለውም ኢህአዴግ እና መንግሰት ነው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ቁማርተኞች መሆናቸውን ማመን አልፈለክም፡፡ በቅርቡ በስደት ላይ ሜዲትራኒያን ባህር ከገቡት ሰዎች ውስጥ ሶሪያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ወዘተ በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀገሮች የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ በእኛ ሀገር የህገወጥ ደላላ ጉዳይ ብቻ የሚሆንብት ምክንያት ልታስረዳኝ ትችላለህ
ኢቢሲ/ኢቲቪን ለመከላከል የሄድክበት መስመር ከቤ አንባቢዎችን እንደመናቅ ነው፡፡ መንግሰትን መግለጫ ነው ያነበበው ኢቢሲ ብትል ያዋጣህ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይለቅም እንደሚለው፣ እነዚህ የሞቱት ኢትዮጵያዊያን ቢበዛም በአሁኑ ቋንቋን ኤርትራዊ ወንድሞቻችን እንደሆኑ እየታወቀ ይህን ስብራት እንዴት እንቻለው መባል ሲገባው፣ ህገወጥ ስደተኞች ትምህርት የሚወሰዱበት ይሆናል እየተባለን፤ ዳግም የሳውዲ ቁስላችን እየተቀሰቀሰ፤ ይህን የሚያቀርብ ኢቲቪን ከሌሎች ዓለም አቀፍ ዜና አውታሮች ጋር ለማነፃፀር መሞከር ተገቢ አልመሰለኝም፡፡ ለማነኛውም እኔም እንደፖለቲከኛ ከዚህ ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚገኝ ፖለቲካ ትርፍ ይኖራል የሚል እምነት ባይኖረኝም፡፡ የፖለቲካ ጦስ ያመጣውን ሰደት ግን በህገወጥ ደላላ ላይ ብቻ ደፍድፎ እራሰን ነፃ ማውጣት አይቻልም፡፡ ይህ የሰብዓዊነት ጉድለት ያመጣ ፖለቲካ ደግሞ ጥንብ እርኩሱ ቢወጣ ምንም ቅር አያሰኝም፡፡ በነገራችን ላይ ከቤ ፖሊስ አውጪ እና ተግባሪ ፖለቲከኞች ተጠያቂነታቸውም ይለያያል፡፡ አንተ ለአቅመ ፖሊሲ አውጭነት ያልደረስክ ስለሆነ ይህ እንደ ኢህአዴግ አባል አይመለከትህም አትጨነቅ፡፡
ለማነኛውም አህአዴግ በ24 ዓመት ጉዞ በቂ ስራ መፍጠር ያልቻለ ፓርቲ ነው፡፡ እራሱ ባመነው ስሌት ብንሄድ የዛሬ 10 ዓመት ከድህነት መውጣት ከቻልን፣ ዛሬ ከድህነት ያልወጣነው ኢህአዴግ ከ1983-1993 ባሉት አሰር ዓመታት ምንም ስራ ባለመስራቱ ነው፡፡ ብተፈልግ እነ ገብሩ እነ ስዬ አላሰራም ብለዋቸው ነው ማለት ትችላለህ፡፡ አሁንም ቢሆን ገዢዎች የራሳቸውን አቅም ለማጎልበት እንጂ ትኩረታቸው የህዝብ ችግር ለመፍታት አይደለም፡፡
ባጠቃላይ ወደጄ ከበደ ካሳ “ከአይኤስ እኩል የማወግዛቸው ….” ብለህ ርዕስ የሰጠህው ፅሁፍ በዋነኝነት ይህን አሳዛን ክስተት ህዝብ ከህዝብ በእምነት መስመር የሚያጋጩትን እና በዚህም የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱ ፖለቲከኞችን ማውገዝ እንደሆነ ብረዳም፡፡ ዋነኛ የፖለቲካ ቁማርተኞቹ አለቆችህ እና አንተው እራሰህ መሆናቸውን የዘነጋህ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ በዚህ የሀዘን ጊዜ አብረን እንዳንቆም አንድ አንድ ሀይሎች እያላቸሁ መከፋፈላችሁን ትታችሁ እኛ ኢትዮጵያዊያን በሚል እንዲተካ አደራ ጭምር እጠይቃለሁ፡፡ አሁን ለተፈጠረው ችግር ሰደት አንዱ መፍትሔ ሲሆን አሳዳጁ ደግሞ ፖለቲካ ስለሆነ የፖለቲካ መሪ የያዙ ሰዎች ተጠያቂነት እንዳለባቸውም መዘንጋት የለበትም፡፡ ከቤ ይህን ያህል ካልኩ ይበቃል፡፡ ከምስጋና ጋር ለዝርዝር www.girmaseifu.blogspot.com.


No comments:

Post a Comment