Friday, March 7, 2014

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በምሽት አትንዱ!! ዘመኑን መረዳት ያቃተው የሰነፍ ውሳኔ!!



በጥር አጋማሽ አካባቢ ምክር ቤቱ ለዕረፍተ ከመበተኑ በፊት አስቸኳይ ያላቸውን ጉዳዮች ለመጨረስ በሚል ከስዓት በኋላ በሰምንት ሰዓት ለመገናኘት ቀጠሮ ይዞ ምክር ቤቱ ሲበተን ወደ ቢሮዬ ተጠግቼ ምሳ ለመብላትና እግረ መንገዴንም በቢሮ አንድ አንድ ነገር አድርጌ ለመመለስ ሳዘግም ፒያሳ ላይ ያለው የትራፊክ ጭንቅንቅ መላወሻ ሲያሳጣኝ ፌቴን አዙሬ ወደ ጣይቱ ሆቴል አመራው፡፡ ብቻዬን ምግብ ቤት መመገብ ባልወድም የግዴን አንድ ጥግ ይዤ ቁጭ እንዳልኩ አንድ ሰው መጥቶ ቅር ካላለህ አብሬህ ብቀመጥ ብሎኝ ፈቃድ ሲጠይቀኝ በደስታ ብዬው አብረን ምሳ በላን፡፡ ጋበዘኝም! ግብዣውን ላለመቀበል  ስግደረደር አይዞህ አንተ ባለስልጣን አይደለህም ካንተ ምንም አልፈልግም ብሎ ካሰፈገገኝ በኋላ ወግ ጀመርን፡፡ እዚህም እዚያም እያልን ብዙ ጠቃሚ ውይይቶች ለማድረግ ዕድል አገኘሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ለእንደኔ ዓይነቱ መረጃ ቃራሚ ጠቃሚ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡
ካነሳናቸው ጉዳዮች አንዱ በምሽት አገልግሎት እንዳይሰጡ የታገዱትን ሚኒባስ እና መስል መኪኖችን የሚመለከት ሲሆን፤ በዛሬ ፅሁፍ ይህን ርዕስ እንዳደርግ ጫና ያደረገብኝ ደግሞ ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተዛማጅ የሆነ ዘግናኝ ዜና በጠዋት በመስማቴ ነው፡፡ ይህውም በምሽት የሚደረግ ትራንስፖርት አሁንም ባለመቆሙ፣ ይልቁንም በድብቅ በህገወጥ መንገድ የሚደረግ መሆኑ ያስከተለው አደጋ ነው፡፡ በጥር 27  ሊነጋ ሲል ከጎንደር አዲሰ አበባ ሰዎች ጭኖ ሊገባ ሲል ነጋ አልነጋ ብሎ ሲከንፍ ለጉዳያችን በፍጥነት እንደርሳለን ያሉ ሰድስት ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ ብዙዎች ለከባድና ቀላል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በሀገራችን በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው የሚያልፈው ቁጥሩ አሁን እየቀረበ ካለው እንደሚልቅ ደግሞ አንድ ባለሞያ በማግስቱ በሚዲያ ሲናገሩ ሰማሁ፡፡ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ከጥቂት ቀናት በኋላ ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች በመረጃው ውስጥ እንደማይካተቱ ነው ያስረዱን፡፡ በሀገራቸን የሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ዝቅ ብሎ የሚቀርበውም መረጃ ቢሆን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው ማንም ይስማማል፡፡ ዛሬ የትኩረት አቅጣጫ ማድረግ የፈለኩት ግን የምሽት ትራንስፖርት የተከለከለው በእርግጥ አደጋ ለመቀነስ ነው? ወይስ ሌላ ውስጠ ወይራ አለው?
በምሳ ላይ ያጫወቱኝ ግለሰብ እንደሚያምኑት ከሆነ በምሽት በሚኒባስ የሚደረግ ጉዞ የተከለከለው አንድም የቴክኒክም ሆነ የህግ መስረት ኖሮት ሳይሆን ይልቁንም በዋነኝነት ሚኒባሶች በሚሰሩበት መስመር የሚንቀሳቀሰው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ  “ሰላም ባስ” በመባል የሚታወቀው ድርጅት ባለቤትነቱ የኤፈርት ድርጅት ገቢ በመቀነሱ ነው የሚል ነው፡፡
ይህ ምንም እውነት የሌለው ግምት ወይም አሉባልታ ነገር ነው ተብሎ የማይተው ቢሆንም ግን ሚኒባስ ከ150 ኪሎ ሜትር በላይ መሄድ አይችልም ብሎ ብቃቱ ላይ ምስክርነት የሰጠው ማን ነው? አንድ ሚኒባስ ከአዲስ አበባ ናዝሬት ሶስት ጊዜ ደርሶ መልስ ሄደ ወይም ቀጥ ብሎ ባህርዳር፣ጎንደር ወይም ድሬዳዋ ሄደ ለውጡ ምን እንደሆነ የሚያስረዳኝ ሰው ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ተመሳሳይ የሆኑ መኪኖች ነገር ግን ባለቤታቸው ግን መንግሰት ወይም የቱሪስት ድርጅት ከሆነ በፈለጉት መንገድንና ጊዜ መጓዝ የሚከለክላቸው የለም፡፡ ተመሳሳይ መኪና ባለቤቱ ብቻ ስለተለያየ እንዴትና ወዴት መሄድ እንዳለበት ገደብ ይጣልበታል፡፡ የቴክኒክ ብቃት ከሆነ ምክንያቱ በማንም ባለቤትነት ይያዝ እገዳው መፅናት ይኖርበታል፡፡
ብዙ ሰዎች በተለይ በኤፍ.አም ሬዲዮ ስልክ ተደውሎላቸው (ደውለው ማለት ስለሚከብደኝ ነው) በዚህ ጉዳይ የምሽት ጉዞ መከልከል እንዳለበት አበክረው የሚገልፁበት ምክንያታቸው በምሽት በሚደረግ ጉዞ በሚፈጠር አደጋ የተማረሩ የሚመስሉ ናቸው፡፡ እንደው ለነገሩ በቀን አደጋ ቢበዛ በቀንም ይከለከል ይሆን? ሀገራችንን ቀን ከሌሊት ሰርተንም ቢሆን ለውጥ ለማምጣት መድከም ሲኖርብን በቀጭን ትዕዛዝ በምሽት መስራት አይቻልም የሚባልበት ሀገር መሆኗ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አሳኝም ነው፡፡ በሚኒባስ ሳይሆን በአውቶሞቢል ሀገር እያቋረጡ መሄድ በሚቻልበት የቴክኖሎጂ እና የተሻለ የሚባል መንገድ ባለበት ዘመን የዚህ ዓይነት መመሪያ አስገራሚነቱን ያጎላዋል፡፡ ሚኒባሶች መብራት የተሰራላቸው በምሽት መጓዝ ስለሚችሉና ስለአለባቸው ጭምር ነው፡፡ የምሽት ጉዞ በተለይ በጥሩ የአየር ሁኔታ ላይ ለመኪናም ሆነ ለተጓዥ እጅግ ምቹ እንደሆነ የሚታመን ነው፡፡ የየምሽት ጉዞ የሚፈልጋቸውን ጥንቃቄዎች መደረጋቸውን ማረጋገጥ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ በምሽት ተጉዞ፣ በቀጣዩ ቀን ጉዳዩን አጠናቆ በቀጣዩ ምሽት ወደ ቤቱ ተመልሶ ወደ ስራ ለመግባት የሚተጋን ሰው ከዚህ ትጋት የሚያደናቅፉ የኤፍ.ኤም ጀግኖች ተዉ የሚላቸው መኖር አለበት፡፡ ያለበለዚያ ግን እንደሚባለውም የገዢዎች ንብረት እና ተጠቃሚነትን የሚነኩ ድርጅቶች እጅ አለበት የሚባለውን ለማመን እንገደዳለን፡፡
ይህንን ሀሳብ ሳቀርብ በምሽት ጉዞ የሚደርስ አደጋን መከላከያው መንገድ ጉዞውን ማስቀረት አይደለም ከሚል መነሻ እንጂ በምሽት ጉዞ ላይ ምንም ዓይነት ቁጥጥር መደረግ የለበትም ከሚል መነሻ አይደለም፡፡ በምሽት መስራትም ሆነ መጓዝ የሚፈልጉ ዜጎች መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፡፡ ይህ መብት ፀኃይ ስለ አለችና ስለሌለች መሆን የለበትም፡፡ ጉዞው በህግ የሚገዛና ስርዓት ያለው ይልቁንም የዜጎችን ደህንነት በሚያረጋግጥ ደረጃ ላይ መሆኑን መቆጣጠር በሚያስችል መስመር ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሚኒባስ 12 ሰው መጫን ካለበት ከ12 ስው በላይ ጭኖ ቢገኝ የሚቀጣው ባለመኪናው ብቻ ሳይሆን በትርፍ ለመጫን ፈቃደኛ የሆነው 13ኛ ሰው ሲከፋም ይህን በመመልከት ምን ይደረግ ብለው ዝም ያሉት ሌሎቹ ተሳፋሪዎች ጭምር መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ስንችል ሰርዓት ያላው አገልግሎት ሰጪ ብቻ ሳይሆን ሰርዓት ያለው ተገልጋይም ማፍራት ይቻላል፡፡ ሌላው የፍጥነት ገደብ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ የመኪና ባለንብረቶች እንዲያስገጥሙ ማድረግ አሁን ባይቻልም፣ መንግሰት በየመቶ ኪሎሜትር ቲኬት መቁረጫ ማሽኖችን በማስቀመጥ አሽከርካረዎች የደረሱበትን ሰዓት በመመልከት ከፍጥነት ገደብ ውጭ የተጓዙት ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በየባንኮችና ቢሮዎች ወረፋ ለመያዣነት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ማሽን ዓይነት ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው አሽከርሪዎች በጉዞ ላይ የሚጠቀሙተን ጫትና ሌሎች ደባል ሱሶች እንዲያቆሙ በፍፁም ቁርጠኝነት መመሪያውን ለመተግበር በመወሰን እንጂ፤ ሰራ የምትሰሩት ፀኃይ ስትኖር ብቻ ነው የሚለውን የሰነፍ መንገድ ተገቢ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ችግር ብልዓትን ይፈጥራል የሚለውን ብሂል ከመተግበር እና ዜጎችን ቴክኖሎጂ ለመጠቀምና ለፈጠራ ከማንቃት ወደ ቁጥጥር ማድለት የመንግሰትን ደካማነት እንጂ ለዜጎች ሃሳቢነትን አያሳይም፡፡

አሁን በማን አለብኝነት ወይም ደግሞ ከአንድ ሰፈር በተፈጠረ የጥቅም ግጭት ምክንያት በተሰጠ ጥቅሻ ብዙ መቶ ሺ ብር አውጥተው ሰርተን እናድጋለን ቤተሰቦቻችንን እናስተዳድራለን ብለው ወደ ትራንስፖርት ዘርፍ የገቡተን ዜጎች እጅግ አሳዝኖዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም መንግሰት ሊወስዳቸው የሚችላቸው ቁጥጥሮች እና የሚያወጣቸው መመሪያዎች ተገማችነት የሌላቸው በመሆናቸው በማነኛውም የስራ ዘርፍ ተሰማርቶ መስራት አደገኛ ነው ወደሚል መደምደሚያ የሚወስድ ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ይህን ተማምነው ከውጭ መጥተው ሰራ የጀመሩ ቢሆንም አሁን ደግሞ በኪሳራ ሸጠው ወደ ውጭ ለስደት ተሰጋጅተዋል፡፡ በዚህ ገንዘብ ትልቁ ልጄን ውጪ ልኬ መኪናው የሚያመጣውን ያህል እርሱ ይልክልኛል ብለው ያጫወቱኝ ጎልማሳ አሉ፡፡ የመንግሰታችን መልስ ይሞክሩት እንደሚሆን አለመጠርጠር ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ ባለንብረቶች የምሽት ጉዞ ንብረታቸውን ሲያሰማሩ የሾፌሮችን ብቃትና የመኪናቸውን ደህንነት እያረጋገጠ ሰምሪት የሚሰጥ አንድ ማህበር በማቋቋም ንብረታቸውን በህገወጥ መንገድ ለአደጋ እና እንዲሁም ዜጎችን አደጋ ላይ የሚጥል አገልግሎት እንዲቆም ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውን ማሳየት እና በህገወጥ መንገድ የተጣለባቸውን የምሽት አገልግሎት የመስጠት መብት ለማስከበር መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሰትም ከፍተኛ ንብረት ወጥቶበት የተገነቡት መንገዶች 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ ለማመቻቸት ከክልከላ የተሻለ ዘዴ ለመቀየስ መስራት ይኖርበታል፡፡ ክልከላው የሰነፍ መንገድ ነው፡፡ 
ይህን ፅሁፍ እንድከትብ ያነሳሳኝ የጥር 27/2006 አደጋ መሆኑን በመግቢያዬ ገልጫለሁ፡፡ ስለዚህም ይህ መኪና ከጎንደር ተነስቶ አዲስ አበባ ሊገባ 20 ኪሎሜትር ሲቀረው ነው የተገለበጠው፤ የተገለበጠውም ሳይነጋ ትራፊክ ሳይዘው ለመግባት በሚያደርገው ጥረት እና በነበረው ፍጥነት ምክንያት ነው፡፡ ይህን ሁሉ ኪሎ ሜትር አቋርጦ የተጣለውን ክልከላ ጥሶ ሲመጣ መቆጣጠር ማሰቆም ያልተቻለው ለምንድነው? በዚህ ሁሉ መንገድ የነበሩ ይህን መመሪያ እንዲያስከብሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ክፍሎች ሁሉ በህግ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በሹፌር ላይ ጥፋቱን አላኮ መቆም የለበትም፡፡ ይህ በጥቅሻ እንቅስቃሴን ማስቆምና ማሰቀጠል ተጠያቂነት ሊኖርበት ይገባል፡፡ የዜጎች ህይወት በከንቱ እንዲጠፋ ምክንያት የሆኑት ሁሉ ለህግ እንዲቀርቡ ሁሉም ይጩኽ፡፡
በመጨረሻም እንደነገሩ የምንፅፋቸው ፅሁፎች አንባቢ እንዳላቸው እርግጠኛ ብሆንም የሚመለከታቸው አካላትም እንደሚያነቡት የሚያሳይ ሁለት የእግረመንገድ ነጥብ ላንሳ፡፡  በአንድ ወቅት ቃሊቲ ሄጄ ባነበብኩት ማሰታወቂያ መሰረት በመንግሰት ሀብት የብአዴን በዓል እንደሚከበር ገልጬ ነበር፡፡ የካቲት 2/2006 አንዱዓለም አረጌን ለመጠየቅ ሲሄድ ምንም ዓይነት ማስታወቂያ በሩ ላይ መለጠፍ ክልክል መሆኑን አንብቤ መጥቻላው፡፡ ይህ የሚያሳየው ፅሁፉን እንዳነበቡት ሲሆን የወሰዱት እርምጃ ግን የመንግሰትን ንብረት ለፓርቲ መጠቀሚያ እንዳይውል ማድረግ ሳይሆን አሁንም የመከልከል ዜዴያቸውን ነው የተጠቀሙት፡፡ የሰነፉን መንገድ፡፡
ሌላው ለፅሁፋችን ተነባቢነት ማሳያው አቶ አሰራት ጣሴ በአዲስ ጉዳይ ላይ ባሰፈሩት ሀሳብ ምክንያት ፍርድ ቤት ደፍረዋል ተብለው ለእስር መዳረጋቸውን ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ሊማሩ የሚገባ የነበረው፤ የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል የሚለውን ወርቃማ አባባል ሲሆን በተቃራኒው ከመንግሰታቸው ባልተለየ የማስፈራሪያ ዘዴያቸውን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ትላንት የተሰጠውን ውሳኔ መሰረት አድርጌ ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡
ለማነኛውም የዚህ ፅሁፍ አንባቢ የሆናችሁ የትራንስፖርት ዘርፍ ሹሞች ሀገራችን ኢትዮጵያ ሃያ አራት ሰዓት ሰርተን ዓለም ከደረሰበት ለመድረስ ብዙ እንደሚቀረን ተገንዝባችሁ ለሰራ የሚያነሳሳ ዘዴ እንድታሰቡ አደራ እላለሁ፡፡ ያለበለዚያ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የቀኑንም ትራንሰፖርት አስቁሙና የትራፊክ አደጋ በመቀነስ ከዓለም አንደኛ ለመሆን ሞክሩ፡፡ በትራንስፖርት ኤኮኖሚክስ ከአደጋ ነፃ የሚባለው ዜሮ ርቀት ነው፡፡
ቸር ይግጠመን

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሰላኝ ከእውቀት እና እውነት ጋር የሚጋጭ ትንተና ለምን?



ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በቅረቡ ወደ ሚዲያ የመጡት የኤርትራው ወዲ ኢሳያስ አፈወርቂ በሚዲያ ቀርበው አንድ አንድ ነገር በማለታቸው፤ ከማን እናንሳለን በሚል ነው የሚሉ ሰዎች ጋር መስማማት የለብንም፡፡ አጋጣሚ ነው ብለን ማለፍ ካልፈለግን አጋጣሚ ባይሆንም አጋጣሚውን ለእኛም እንድ አንድ “እውቀት” የሚጨምር ነገር ልናገኝበት የምንችል አጋጣሚ አድርጎ መውስድ ግድ ይለናል፡፡ እውቀት የሚለውን ነገር ግን ልብ ልንለው የሚገባ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ ተከትሎ ብዙ አስተያየት የተሰጠ ቢሆንም፣ የግል ዕይታዬን ማካፈል የተደጋገመ ቢሆን ጥሩ ነው ብዬ አመንኩ፡፡ ምክንያቱም በመሬት ላይ ካለና ከምናየው እውነትና እውቀት ጋር የተጋጨ ስለመሰለኝ፡፡
የቡድን አመራርን በተመለከተ
የቡድን አመራር ነው ለሃያ ዓመት በፓርቲያችን ያለው ማለት አቶ መለስ እያሉም አመራር ላይ ነበርን ሊሉን ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ ከህወሃት ክፍፍል በፊት (እነ ሰዬ፣ ገብሩ፣ ተወልድ፣ ወዘተ) በሚመክሩበት አጀንዳ እኛም ነበርን ሊሉን አይችሉም፡፡ በዚያን ጊዜ የቡድን አመራር በህወሃት ውስጥ እንደ ነበር እናውቃለን፣ ይህ በኢህዴግ ውስጥም ዘልቆ ገብቶ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ይልቁንም አንድ አንድ የህወሃት ሰዎች በየክልሉ ተቀምጠው የህወሃት ውሳኔ ያስፈፅሙ ነበር፡፡ ከህወሃት ክፍፍል በኋላ ነገሮች እንደተቀየሩ እሙን ነው፡፡ ከህወሃት የቡድን አገዛዝነት ወደ አቶ መለስ ዜናው እጅ ስልጣን ተጠቃሎ ነው የገባው፡፡ ለዚህም ነው አቶ መለስ ዜናዊን “ጠቅላይ” የሚባሉት፡፡ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ቦታውን ከያዙት በኋላ በጠቅላይነት የሚያማቸው የለም፡፡ እንደ እኔ ዓይነቱ ወደ ቡድን አሰራር ገብተዋል የሚል ግምት የያዝን አለን፡፡ ሌሎች ደግሞ ወደቀድሞ ቦታ ተመልስው ህወሃት ነው ከጀርባ ሆኖ ማርሽ የሚቀይረው ብለው ይጠራጠራሉ፡፡ እንዲህ ያለህ የተምታታ ግምት ስለአለ ነው በዘዴ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ነዎት?የሚል ሽንቋጭ ጥያቄ ያስነሳው፡፡
ኢህአዴግ በግልፅ እንደሚናገረው ተግባራዊ ነገር አድርጊያለሁ ብሎ የሚያምነው ከተሃድሶ በኋላ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ከተሃድሶ በኋላ ደግሞ አቶ መለስ ጠቅላይ የነበሩበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት አቶ ኃይለማሪያምም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ሹመት እንጂ ስልጣን አልነበራችሁም፡፡ ለምሳሌ አቶ ኃይለማሪያም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ጠቅላዩ የነበራቸው መረጃ በሙሉ ነበረኝ ምክንያቱም የቡድን አመራር ስለምንከትል ብለው አይዋሹኑም፡፡ ቢሉም በፍፁም አናምኖትም፡፡ በዚያ ደረጃ ተተኪ ልሆን እችላለሁ ብለው ዝግጅት እንዳልነበሮት የሚያሳብቀው እውነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ ሞት ቦታውን ሲይዙ ከሚሰጡት መግለጫ ለመረዳት የሚቻል ነበር፡፡ ለማነኛውም በቅጡ የኢህአዴግ የቡድን አመራር እንዲኖር ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ወሳኝ ስብዕና ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር የሚጠበቅ መሆኑን ተረድተው የቡድንም የግለሰብም ወሳኝነት ተመጣጥነው የሚሄዱበት መስመር የግድ እንደሚል ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የአሜሪካው ፕሬዝደንት በግላቸው እንደፈለጋቸው አይወስኑም፡፡ ይህን ለመረዳት ቢንላደንን ለመያዝ የተደረገውን ዘመቻ እንዴት በቡድን እና እንዴት በግል ኃላፊነት ወስደው እንደወሰኑ የሚያሳየውን ፊልም ይመልከቱት፡፡
ቴሌ እና የሚታለብ ላም
ይህን በተመለከት ዶክትር ካሱ ኢላላ ብለውት እስከ ዛሬ ድረስ ካደረጉት ስህተት እንደ አንዱ የሚቆጠር የነበረ ነው፡፡ ኢህአዴግ አፍ እንጂ ጆሮ የለውም የሚለውን በሚያጠናክር ሁኔታ ቃል በቃል ሲደግሙት በግሌ አዝኛለሁ፡፡ ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ቴሌ “በመንግሰት እጅም” ሆኖ አትራፊ ነው፡፡ ቴሌ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነገሩን መረጃ መሰረት በመንግሰት እጅ ሆኖ 6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ለልማት ያውላል ብለውናል፡፡ ያልገባቸው ነገር ግን ቴሌ በግል ይዞታ ቢሆንም ከዚህ ሶሰት እጥፍ የሚሆን ትርፍ ሊያተርፍ እንደሚችል ነው፡፡ ከዚህ ትርፍም መንግሰት ድርሻውን ያገኛል፡፡ በኢህአዴግ ሰፈር ያለው ችግር የልማት ባለቤት ህዝብ ይሁን ወይስ መንግሰት የሚለው ነው፡፡ የግል ባለይዞታዎች ከቴሌ ትርፍ ካተረፉ የብር ኖት አይበሉም መልሰው አዋጭ ነው ብለው ባሉት መስመር ኢንቨስት ያደርጉታል፡፡ ምን አልባትም ከመንግሰት በተሻለ አዋጭ መስመር ነው ስራ ላይ የሚያውሉት፡፡ ለዚህ ጉልዕ ምሰሌ በመንግሰት እጅ የሚገኙ የነበሩትን የቢራ ፋብሪካዎች አሁን ለመንግሰት እየከፈሉ ያሉትን ታክስና በኢኮኖሚ ውስጥ እየፈጠሩ ያሉትን መነቃቃት ነው፡፡ እነዚህ ተቋሞች በመንግሰት እጅም እያሉ አትራፊ ነበሩ፤ አሁን ግን የበለጠ አትራፊ ናቸው፡፡
በዋነኝነት የቴሌ በመንግሰት እጅ መቆየት የሚፈለገው ለልማት ካለው ፋይዳ እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ በስልጣን ለመቆየት ግን እንዲህ ያለን ህዝቦችን የሚያስተሳሰር ቴክኖሎጂ በግለሰብ እጅ አስገብቶ የነፃነት በር ሆኖ እንዲያገለግል አይፈለግም፡፡ ለሃምሳ ዓመት መግዛት የሚፈልግ ፓርቲ በዚህ ደረጃ ወርዶ ለማፈን ቢሞክር ባህሪው ነው ብሎ መውሰድ ነው፡፡ በልማት ስም በተለይ ለገጠሩ ህዝብ ለማስፋፋት ብለው ሰበብ ከሰጡ በኋላ ግን የቴሌ ገንዘብ ለባቡር መስመር ዝርጋታ እየዋለ ነው ብለው የገጠሩን ህዝብ ለመጠቀሚያ ብቻ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል፡፡ የቴሌው የህዝብ ግንኙነት በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሁን በተያዘው ማስፋፊያ  85 ከመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ክፍል በኔትወርክ ይሸፈናል ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ጠቅላላ ሀገሪቱን ለመሸፈን የቀረው ጥቂት ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን ከመንግሰት በተሸለ ጥራት ለሚሰጡ የግል ድርጅት አስተላልፉ፣ መንግሰት የመሰረተ ልማት ማስፋፊያና ቁጥጥር ላይ ለምን አይገባም የሚለው መከራከሪያ አሁንም ለፊት ለፊት ጉንጭ አልፋ ጭቅጭቅ እንጂ ይህ ሊሆን የሚችለው በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መቃብር ላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ይዘገይ ይሆናል እንጂ ይህ እንደሚሆን ግን ጥርጥር የለውም፡፡ ማለትም አብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ወደ መቃብር ይወርዳል፡፡
እዚህ ጋ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር የግል ባለሀብቱን ስብሰባ እየጠሩ የግሉ ዘርፍ ምትክ የሌለው እንደሆነ እናምናለን፤ ከግል ዘርፉ ጋር ጠብ የለንም የሚል መንግሰት ጠቅላይ ሚኒስትር “መንግሰት ብቻ ነው ይህን ትርፍ ለልማት የሚያውለው” ማለት እንዴት ያለ ተቃርኖ እንደሆነ ነው፡፡ በግለሰቦች (ሲደመሩ ህዝብ የሚሆኑት) እምነት የሌለው መንግሰት፤ የህዝብ ወኪል የሚሆን አይደለም፡፡ በህዝብ ስም ግን ይነግዳል፡፡ መንግሰት ብቻ ነው የሚያለማው የሚለውን ከወሰድን የአሜሪካ መንግሰት ከመከላከያ እና ከተወሰኑ ፓርኮች በስተቀር የመንግሰት የሚባል ነገር የለውም፡፡ በአሜሪካ ልማት የለም በቻይና ነው ያለው እንደማይሉ ተሰፋ አደርጋለሁ፡፡ ብዙ ሰው ቻይና ከአሜሪካ ቀጥሎ ግዙፉ ኢኮኖሚ እያሉ ሲሳሳቱ አሜሪካ ቻይናን 10 ዕጥፍ እንደምትበልጣት የምናውቅ አይመስላቸውም፡፡ ቻይና ከጃፓን በለጠች እንጂ አሜሪካ ጋር አልደረሰችም፡፡ ይህችን እንደ እግረ መንገድ ያዙልኝ፡፡ እርግጥ ነው የቻይና መንግሰት ሀብታም ነው፣ ህዝቡ ግን ድሃ፡፡ ምክንያቱም ፍልስፍናው መንግሰት ብቻ ነው የሚያለማው የሚል እና የኛዎቹም ቅጂያቸው እንደዚያ ስለሆነ ነው፡፡ ሰትራቴጂው ገጠሩን እዚያው ገጠር ለማሰቀረት እቅድ ከሌለ በስተቀር የገጠሩ ህዝብ አሁን የሚፈልገው ስልክ እና መብራት ይዛችሁለት በጫካ ስር መኖር ሳይሆን ከተሜነት ነው፡፡ ወደ ስልኩ እና መሰረተ ልማቱ መምጣት ይኖርበታል፡፡
የታክስ ምጣኔ እና የታክስ መሰረት ማሰፋት
ግብር በማይከፈልበት የቦርድ ክፍያ እና ሌሎች ገቢዎች ለሚደጎም ባለስልጣን ብዙ ግልፅ ያልሆነ ግን ደሞዝተኛውን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ ያለው ከፍተኛ ታክስ የሚከፈልበት የደሞዝ ጣሪያ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አለመሆኑ ነው፡፡ በጋዜጠኞች የቀረበውም ጥያቄ ይህን የሚመለከት እንጂ አጠቃላይ የታክስ ሪፎርም እየተባለ ለረዥም ጊዜ የተያዘ የተሰፋ ፕሮጀክት ምንደረሰ የሚል አይደለም፡፡ ደሞዝተኛውን ደሞዝ ጨመርንልህ ብሎ በግብር ከመቀማት በተግባር የታክስ ምጣኔውን ማስተካከል የዘገየ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን የስራ ተነሳሸነት እየገደለ ያለ በምድር ላይ ያለ ሀቅ ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ጨመረ ብሎ በየጊዜው የነዳጅ ዋጋ የሚጨምር ፣ ይህንንም ተከትሎ የትራንስፖርት ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያደርግ መንግስት በቀጥታ ከደሞዝተኛ ላይ የደሞዝ መቀነስ እንደሆነ መረዳት አዳጋች አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ ሲቪል ሰራተኞች የመነሻ ደሞዝ ከፍ ማድረግ (ዝቅተኛ የደሞዝ መጠን መወሰን) እና የግብር ማሰከፈያውን የገቢ መጠን ከፍ ማድረግ አፋጣኝ ምላሽ የሚሻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዜጎች የሚያገኙትን ገቢ እየተከታተለ የሚቀማቸውን አይፈልጉም፡፡ መንግሰትም ቢሆን፡፡ በታክሰና ግብር ስም እየቀሙ እኔ ለልማት አውለዋለሁ ማለት ከስድብ አይተናነሰም፤ ዜጎችም ሰርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ለልማት ለዚያውም ለዘላቂ ልማት ነው የሚያውልቱ፡፡ ከዜጎቹ እየቀማ ዜጎችን በማደኽየት የሚበለፅግ መንግሰት ልማታዊ ነኝ ሊል አይችልም፡፡

ሊስትሮም ሁን ብባል ወረዳም ሂድ ከተባልኩ አደርጋዋለሁ፤
ሊስትሮም ሁን ብባል ወረዳም ሂድ ከተባልኩ የምሄድ ወታደር ነኝ፡፡ ይህ አባባል በኢህአዴግ ሰፈር የግል ነፃነት ስለሌለ ምን ያህል እውቀት እንደሚባክን ነው የሚያሳየው፡፡ ልክ ነው በሚቀጥለው ዙር ወደ ክልል ቢባሉ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ አሁኑ በምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር ማዕረግ የሚያገለግሉት ቱባ ባለስልጣን ወደ ክልል ብሎም ወደ ዞን ሲላኩ እሺ ብለው መሄዳቸው የዚሁ ማሳያ ነው፡፡ ከክልል ፕሬዝደንትነት ወደ ጠቅላይ ሚኒሰትረ አማካሪነት ተመሳሳይ የምደባ ዝውውር ነው፡፡ ይህ ግን በምንም ምክንያት ተገቢ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ ቅዱስ መፅሐፍ ምሳሌ 4፡18 “የጻድቃን መንገድ እንደ ንጋት ብርሃን ነው፤ ሙሉ ቀን እሲከሆን ድረሰም እየጨመረ ይበራል” ይላል፡፡ ምን ነው የኛ መሪዎች ቁልቁል ማየት ፈለጋችሁ፡፡  የሌሎች ሀገር መሪዎች ከመሪነት ሲለቁ ተከታይ ቦታቸው ሊሰትሮ መሆን ወይም የእርሱ ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አማካሪነት ነው፡፡ ዛሬ ክሊንተን አንድ ሰዓት ንግግር አድርገው የሚያገኙት ገንዘብ ከወረዳ በጀት በስንት እጥፍ እንደሚልቅ ነጋሪ የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ይህን ብቃት አረጋግጫለሁ ያለ ሰው ወረዳ ለመሄድ አያስብም፡፡ በምደባ የተገኘ ስልጣን ግን በምደባ ሊነሳ ይሚችል ነው፡፡ በምደባ ከሚገኝ ስልጣን ያድነን፡፡ እኔ ግን ከዚህም በላይ የገባኝ፣ የጋራ አመራር አለ ብሎ ከግል ተጠያቂነት ለመሽሽ እንዳይሆን የሚል ፍርሃትም አለኝ፡፡ ሌላው ግን አብዛኛው ሹመኛ ነገ ወረዳ ልወረወር እቻላለሁ በሚል ስጋት ተግቶ በዘረፋ ይሰማራል፡፡ የብቃት ከግምት መውጣትና የምደባ ሹመት የሚያመጣው ጣጣ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለዛሬ ይብቃን ቸር ይግጠመን፡፡

የፍርድ ቤት ያለህ ……



በታሕሳስ ወር አጋማሽ አንድ የፌዴራል ፖሊስ መኮንን ችሎት በመድፈር ተከሰው አሁንም ጉዳይ በፍርድ ሂደት ላይ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ፖሊሶቹ አድመው አሁንም ማን እንደሆነ አላወቅንም ብለው አለቃቸው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አስደርገዋል፡፡ አሁን አላውቅም ድሮ የመኮንን ማዕረግ የሚሰጣቸው ሰዎች ከፖሊስነቱ በተጓዳኝ የህግ ትምህር እውቀት እንዳላቸው ለማንም ግልፅ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ድፍረት መዳፈር አይቻልም፡፡ ይህን ጉዳይ ያነሳሁት በመፅሔት ላይ በተሰጠ አስተያየት ተደፍርኩ ያለ ችሎት አቶ አስራት ጣሴን የአምስት ወር የእስር ቅጣት በሁለት ዓመት ገደብ መወሰኑን ታዝቤ ነው፡፡ ከአምሰት ወሩ ይታሰብ አይታሰብ ባይታወቅም ለአስር ቀን በወህኒ ቤት እንዲቆዩም ተደርጎዋል፡፡ ለህግ ልዕልና ሲባል ፍርድ ቤት እንዲከበር ከዚህ የበለጠ መሰዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀን ሰው ችሎት ደፍረሃል ማለት ግን ጠብ ያለሽ በዳቦ ነው፡፡
ለማነኛውም መኮንኑ ይግባኝ ሰለጠየቁ በሚል በገንዘብ ዋስትና ከእስር ያሰፈቱት የፌዴራል የመመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንት አቶ አስራትን ግን ሊያስፈቱ አልቻሉም፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ የሚሰበሰቡት ዳኞች የፖለቲካ ታማኝነት እንጂ የህግ እውቀታቸው ዝቅተኛ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ስለዚህ ለገዢው ፓርቲ ያዳላሉ ማለት እንዴት ሆኖ ነው ችሎት መድፈር የሚሆነው፡፡ በቅርቡ የፍትህ ሰርዓቱን የመልካም አስተዳደር መርዓ ግብር በቀረበበት ወቅት አቅመ ቢስ ያለውን ፍርድ ቤት እኛስ ብንለው ምን ይለዋል፡፡ አቅም የሌላቸው ዳኞች ተገቢውን ፍትህ ይሰጣሉ ብለን አለማመን መብታችን ነው፡፡
የፖለቲካ ትግል ውስጥ የገባነው ትክክለኛ የፍትህ ሰርዓት እንዲዘረጋ ጭምር ነው፡፡ መንግሰትን ፍርድ ቤት ገትረን መብታችንን የሚጠብቅልን ፍርድ ቤት ቢኖር በእውነት ወደ ፍርድ ቤት እንጂ የፖለቲካ ትግል ምን አመጣው፡፡ የዚህ ጊዜ ፖለቲካ የሚሆነው መሪ ለመሆን ዕጩ ሆኖ መወዳደር ብቻ ነው፡፡ ትግል የታባቱ፡፡
የፀረ ሙስና እና ሰነምግባር ኮሚሽን ባስጠናው ጥናት ተዓማኒነት ከጎደላቸው ተቋማት አንዱና ዋነኛው ፍርድ ቤቶች እንደሆኑ ገልፆዋል ይህን ተቋም ትክክለኛ ፍትህ ሊሰጠኝ አይችልም ብዬ ማመን በምን መንገድ ነው ችሎት መድፈር የሚሆነው፡፡ በግሌ በፍርድ ቤት ላይ እምነት ቢኖረኝ ኖሮ ያለ ስሜ የአሸባሪነት ዶክመንተሪ መስሪያ ስሆን በማግሰቱ ነበር ፍርድ ቤት የምገትራቸው፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ከፖለቲካ ጥቅሻ ነፃ ነው ብዬ ስለማላምን አላደረኩትም፡፡ አንድ ቀን እንዳውም በዚሁ ዶክመንተሪ እኔው ልከሰስ እችላለሁ፡፡ ፍርድ ቤትም ጥፋተኛ ነህ ተከላከል ብሎ ዕድሜ ልክ ሊፈርድ ይችላል፡፡
በአቶ አሰራት ጣሴ ክስ መነሻ ዳኛዋ በሌላ ክስ የማይፈለጉ ከሆነ ልቀቋቸው ብለው ለፖሊስ ሲያዙ፤ ፖሊሱ ያለምንም ማንገራገር አለቅም ሲል ደነገጥኩ፡፡ ፖሊሱ ይዞት የመጣውን እሰረኛ የሚለቅበት ሰርዓት ቢኖርም ክብርት ዳኛ ማዘዣው በፅሁፍ ሲደርሰን በህጉ መሰረት እንፈፅማለን የሚል ለፍርድ ቤት የሚገባን ክብር የማይስጥ ፖሊስ ይህን እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ፍርድ ቤት ነፃ ነኝ ቢለኝ መብቱ ቢሆንም፤ እኔ ደግሞ አይመስለኝም ነፃ አለመሆናችሁን ብዙ ምልክት አለ ማለት መብቴ ነው፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽነር አሊ ሱሌይማን እንደተናገሩት “በአሁኑ ወቅት ጠበቃ የሚመረጠው በሙያ ብቃትና በምስጉን ስነ ምግባሩ  ተከራክሮ እውነት ያወጣል በሚል ሳይሆን ምን ያህል ደላላ አለው? ዳኛና ባለስልጣናትን ያውቃልን? በሚሉ መስፈርት ነው” ብለዋል (አዲሰ ዘመን ጋዜጣ የካቲት 2/2006)፡፡ ይህ አሰተያየት ጠበቆችን ለመዝለፍ ቢመስልም ትክክለኛው ግን ደላሎች የሚያገናኙት ዳኞች፣ በባለስልጣን ጥቅሻ የሚሰሩ ዳኞች መኖራቸውን ነው፡፡ የጠበቃ፣ የዳኛ እና የባለስልጣናት ህገወጥ ግንኙነት የሰፈነበት የፍትህ ሰርዓት ትክክለኛ ፍትህ አይሰጠንም ብሎ ማመን እንዴት አድርጎ ነው ችሎት/ፍርድ ቤትን መድፈር የሚሆነው፡፡

“ፍትህ ከኢህአዴግ ፍርድ ቤቶች ይገኛል ተብሎ ሳይሆን ለታሪክ ምስክርነት ነው” ብሎ ጥርጣሬን መግለፅ ነው ወይስ “በደላላና በባለሥልጣን ጥቅሻ ይስራል” ማለት፡፡ ሁለቱም እውነት ከሆነ እውነት ነው፡፡
ሌባ ዳኞች ብለው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በምክር ቤት ሲሳደቡ እረ በህግ ማለት ያልቻለ ፍርድ ቤት ዛሬ ደግሞ ችሎት በአንድ መጣጥፍ ውስጥ በተሰጠ አሰተያየት ተደፈረ ማለት እንዴት እነዴት ነው ነገሩ፡፡

Sunday, February 9, 2014

የነሌንጮ ምልሠት ፖለቲካዊ እንድምታዎች




ግርማ ሠይፉ ማሩ
ሰሞኑን የፖለቲካ እውቀትና ይህንኑ የማከናወን ክዕሎታችንን የሚፈትኑ ብዙ ነገሮች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው የኦቶ ሌንጮ ለታ ወደሀገር ቤት የመመለስ ዜና ነው፡፡ ፋክት መፅሔት አቶ ሌንጮ ለታም እንዲመጡ፤ በእሳቸው እና ሌሎች የኦነግ አመራሮች ጦስ በሀገር ውስጥ ለእስር የተዳረጉትም ይፈቱ የሚል መልዕክት አስተላልፋ ነበር፡፡ እዚህ ጋ ልብ ማለት ያለብን የኦነግ ታፔላ ተለጥፎላቸው እስር ቤት የገቡት ሁሉ የኦነግ ደጋፊና ተላላኪ ነበሩ ማለት በፍፁም እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ሌላ እርግጠኛ መሆን የሚቻለው ግን ኦነግን በመንፈስ የሚደግፉ መኖራቸውን ጭምር ነው፡፡ ይህ ግን በምንም ዓይነት በእስር ለመማቀቅ በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም፤ ወንጀል የሚባል ውጤት እስካላመጣ ድረስ፡፡ በተጨማሪ ግልፅ መሆን ያለበት ዋና ነጥብ ደግሞ ምንም ዓይነት ምርጥ የፖለቲካ ስርዓት ለመመስረት ይሁን ለውጥ ለማምጣት በሚል ሰበብ፤ ስላማዊ ዜጎችን እይወት ለመቅጠፍ የሚደረግ ሙከራም ሆነ የተፈፀመ ተግባር ወንጀል ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት የሌለው አርመኔያዊ ድርጊት እንደሆነ ነው፡፡
የአቶ ሌንጮ ለታ ወደ አዲሰ አበባ መምጣት በብዙ መልኩ በጎ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አመጣጣቸው ግን የድሮውን የኦነግን ተረት ሊተርቱልን ከሆነ ግን ተቀባይነት የለውም፡፡ የኦነግ ታሪክ የሚያስፈልገን በመፅሀፍ መልክ ተጠርዞ ለታሪክ ምርምር መሆን አለበት፡፡ ለዚህም አቶ ሌንጮ ብቃቱ እንደሚኖራቸው አልጠራጠርም፡፡ አቶ ሌንጮ ለታ የኦሮሞ ህዝብ ቸግር በመገንጠል ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሰር ሊፈታ ይችላል በሚል እምነት  ወደ ሀገር ቤት ለመምጣት ሲወስኑ በወህኒ ቤት በኦነግ ሰም የታጎሩትን ዘንግተው ከሆነ በቅርቡ ከኦብነግ ተገንጥለው ወደ ሀገር ውስጥ በገቡ አመራሮች እንደተበለጡ መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ አቶ ሌንጮ ለታ በኢህአዴግ ሰዎች አይሞኙም ለማለት ውጤቱን መጠበቅ የግድ ይላል፡፡ የማንረሳው ግን ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅ ሀገር እንዲመሩ አቶ ሌንጮ በዕጩነት በአቶ መለስ ዜናዊ ሲጠቆሙ እንቢ ማለታቸው ግን የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የዛን ዕለት በአቶ መለስ የፖለቲካ ጫወታ እንደተበለጡ ይረዱታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሰለ ኢትዮጵያና የህወሃት ፖለቲካ ሲነሳ አንድ ልብ ማለት ያለብን ነገር ህወሃት የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት የሚለውን ስም ባለመቀየሩ አሁንም የትግራይ ሪፐብሊክ የመመስረት እቅድ እንዳለው የሚያስቡ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ስህተት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ ይህ ስህተት በሀገር ውስጥ ሳይሆን በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ነብስ ዘርቶ ይገኛል፡፡ በምድር ላይ ያለው እውነተኛ ሀቅ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ህወሃት ኢህአዴግ የሚባለውን ግንባርና ሌሎች አጋር ፓርቲዎችን ከሰሜን እሰከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እሰከ ምስራቅ በመመስረት ያጠፋውና በማጥፋት ላይ ያለው ሀይል የህወሃት መሪዎችን ለበለጠ ጥቅም የሚያበቃቸው በምኒሊክ ኢትዮጵያ በሚሏት ስር እንጂ በትግራይ ሪፐብሊክ ውስጥ እንዳልሆነ በደንብ የተረዱ መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ነው ህውሃት ኦነግንም ሆነ ኦብነግን ከተቻለ በፀባይ ካልተቻለ ምትክ በማበጀትና በጉልበት የማዳከም ስልት የሚከተለው፡፡ አቶ ሌንጮ ለታ እና ድርጅታቸው ኦነግ በሽግግር ወቅት የቀረበላቸውን እጅ መንሻ በብልዓት ይዘው አሁን የያዙትን አቋም ቢይዙ አንድ ጠንካራ ተገዳዳሪ ፓርቲ ሊሆን ይችሉ ነበር፡፡ ለኦነግ ወይም አሁን በአቶ ሌንጮ ለታ ለሚመሩት ኦሮሞ ዲሞክረሲያዊ ግንባር/ኦዴግ  እንደ ሽግግር ጊዜው በቀላሉ አማላይ የሆነ እጅ መንሻ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ በሸግግር ጊዜው ኦነግ የህወሃትን “የሚንሊክ ኢትዮጵያን” በጋራ እንግዛ ጥያቄን ቢቀበል፤ ኦህዴድን ለመሰዋትነት ለማቅረብ ብዙ አይቸገርም ነበር፡፡ አሁን ግን ኦህዴድ በፈራረሰ ኦነግ የሚለወጥ ድርጅት ነው ብሎ መገመት የፖለቲካ ቂልነት ይመስለኛል፡፡ አቶ መለስ በሌሉበት ደግሞ በኦህዴድ ቤት እንደፈለገ የሚያዝ ህውሃት ወይም ኢህአዴግ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የኦህዴድ መሪዎች አሁን ብዙ ለምደዋል፤ መሬት ይዘዋል፡፡
ለኦህዴድ የእነ ሌንጮ ለታ በፈለጉት መንገድ መምጣት፣ በሀገር ውስጥ መገኘት እና በኦሮሞ ህዝብ ውስጥ እንቅሰቃሴ መጀመር የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የመድበለ ፓርቲን አተገባበር ለመተግበር እንደመስታወት ወይም ላንቲካ ከማገልገል አልፎ የፖለቲካ ሚዛን ለውጥ እንደማያመጣ የተረዱት ይመስለኛል፡፡ ከሁሉም በላይ የኦህዴድን ትክክለኛነት ማረጋገጫ ማሕትም አድርገው የሚጠቀሙበትም ይኖራሉ፡፡ ኦህዴዶች ጥንቃቄ ካላደረጉና የኦሮሞን ህዝብ ጨዋነት ካልተጠቀሙ እነ ሌንጮ ለታን ከዚህ ቀደም በኦነግ ሰም ተፈፀሙ ለሚባሉ ጥፋቶች ሁሉ የኢቲቪ የዶክመንተሪ መስሪያ ግብዓት እንደማያደርጉዋቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ለዚህ ተግባር ሲባል በእስር ላይ ያሉትንም በመልቀቅ ጭምር ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ይህን ዓይነት ስህተት ከመስራት ኦህአዴድ/ኢህአዴግን ፈጣሪ እንዲጠብቀው እኛም ጭምር መፀለይ ይኖርብናል፡፡ ዋናው ምክንያት የዚህ ዓይነት ተግባር በሀገራችን ሀገራዊ መግባባት ልንፈጥር የምንችልበትን የመተማመን መንገድ ይዘጋዋል የሚል እምነት ስለአለኝ ነው፡፡ አቶ ሌንጮም ቀደም ብለው በዚህ መስመር ፋውል ካልሰሩ ይህን ፅሁፍ ከታናሽ ወንድም እንደተላከ መልዕክት ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ ኢህአዴግ እንደ ፖሊሲ ይህን አያደርግም አይባልም፡፡ በቅርቡ አቶ ሬድዋን ሁሴን በምክር ቤት ቀርበው የዶክምንተሪ ስትራቴጂ ልክ ነው የሚቀጥል ይሆናል ማለታቸውን ስናስብ የአቶ ሌንጮ ለታ ምርጥ የዶክመንተሪ መነሻ ኃሳብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር በኦህዴድ/ኢህአዴግም ሆነ በኦዴግ/ኦነግ ሰፈር የፖለቲካ ክዕሎታቸው የሚፈተንበት ይሆናል፡፡
ሌሎች  በሀገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆን ከፈተና የፀዱ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አንዳንዶቹ የኦዴግ አመራሮች በእነሱ መስመር እንዲሰለፉ ሲጠብቁ ሌሎቹ ደግሞ ቀደም ሲል ኦነግ ሰራው የሚባለውን ሰህተት በመንቀስ የራስን አቋም ትክክለኛነት ማሳያ መስታወት ማድረግ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚጠቅመው ገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግ/ኦህዴድ ከመሆን ዘሎ በኦሮሚያ ምድር ላይ ለሚደረግ ፖለቲካ ውሃ የሚቋጥር ነገር አያመጣም፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በዋነኝነት ማድረግ ያለባቸው ኦዴግ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ከኢህአዴግ ጋር የፖለቲካ ምዕዳሩ እንዲሰፋ ያደረገው ተሰፋ ሰጪ ድርድር ካለ፤ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው ሊጠቀሙበት የሚችሉበትን መንገድ ማሰብ ነው፡፡ ኦዴግ ትግሉ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ስትራቴጂ ሲቀበል አንዱ ቅድመ ሁኔታ በሀገር ውስጥ በምርጫ ቦርድ ምዝገባ ማድረግ አንዱ ሲሆን ሌላው ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር መድረክ አባል ለመሆን የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ (ትክክለኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሰነ ምግባር አዋጅ ነው) መፈረም የሚሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአቶ ሌንጮ ለታ ፓረቲ ኦዴግ የምርጫ ሰነምግባር ደንቡን ከፈረመ ኢህአዴግ በሀገር ውስጥ ያሉትን ፓርቲዎች በማግለል በውጭ ሆነው ከሚያስፈራሩት ጋር ለሚያደርገው ድርድር ሽፋን እንደሰጠ ነው የሚቆጠረው፡፡ ይህ ደግሞ ኦዴግን በተቃዋሚነት እና አማራጫ ያለው የኦሮሞ ህዝብን የሚወክል ፓርቲነት ሳይሆን በኦህዴድ ሀጋርነት ለመሰለፍ እንደመጣ ተደርጎ እንዲወሰድ ስለሚያደርገው ፈተናውን ያከብድበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ተቃዋሚዎችም የሚስጡት የመልስ ምት ሌላ የፖለቲካ ክዕሎት የሚጠይቅ ሆኖ ይታየኛል፡፡
ለማነኛውም በዓለም ላይ በልዩ ሁኔታ ከምንታወቅባቸው ነገሮች አንዱ የሆነው ኦነግ ሲያራምደው የነበረውን የቅርንጫፎች ጥያቄ መሆን ያለበትን ግንዶች ጠየቁት ሲባል የነበረውን የመገንጠል (የኦሮሚያ ሪፐብሊክ) ጥያቄ የሚያሻሽል እርምጃ በአዎንታዊነት መታየት ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ ትግሬ፣ ወዘተ ሰብዓዊ ክብራችንን የሚመጥን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሲመሰረት የአንድ ቡድን አባል በመሆናችን የደረሰብን የሚመስለን በደልና ግፍ ሁሉ ይወገዳል ወደሚል እየመጣን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በአንድ ቡድን ላይ ደረሰ የምንለው ግፍና በደል ያልደረሰበት ካላ የገዢው ቡድን አባል በመሆን ነው እንጂ የአንድ ቡድን አባል በመሆኑ ከግፍ አያመልጥም፡፡ ገዢዎቻችን ደግሞ አሁን የአንድ ብሔር ብቻ ናቸው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡ በኦሮሚያ ክልል የሚደርስ በደል በኦሮሚያ ካድሬዎች ነው፡፡ በትግራይ ክልል በቅርቡ በአረና አባላት ላይ የሚደርስ ያለው በደል በትግራይ ካድሬዎች ነው፡፡ የሁሉም ካድሬዎች መመሪያ ቀራጭና አሰማሪ ደግሞ በጋራ የመሰረቱት ግንባር ኢህአዴግ ነው፡፡ ትግላችን የስርዓቱ መሪ የሆነውን ፓርቲ በመቀየር ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ እንዴት? የሚለው የፖለቲካ ክዕሎታችን የሚጠየቅበት ሌላኛው ጥያቄ ነው፡፡

Monday, February 3, 2014

የሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ወዴት ይመራናል?




ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
በኢህአዴግ መንደር የምርጫ ዘመቻ በይፋ መጀመሩን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ በገዢው ሰፈር ሁሉ ነገር መጠናቀቁ ጥቅሻ ሲሰጠው እንቅስቃሴ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የምርጫ ዘመቻው በተቃዋሚ ጎራ እንደምንፈልገው ነፃ፣ ፍትሓዊ እና ሁሉም ተወዳዳሪ እኩል በተዘጋጀ ሜዳ ይሆናል ማለት ከባድ ሊሆን እንደሚችል ከአሁኑ መገመት ለዝግጅት የሚረዳ ይመስለኛ፡፡ ኢህአዴግ ከጅምሩ የመጫወቻ ሜዳውን ብቻ ሳይሆን አጫዋቾችን ሁሉ ተቆጣጥሮ ጨዋታው እንዲጀመር መፈለጉን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ በዚህ ወቅት የመንግሰት አካላት የሆኑት ህግ አውጭውም ሆነ አሰፈፃሚውም በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠምደው ነው የሚገኙት፡፡ እንደ አሰፈላጊነቱም የፍትህ ስርዓቱ ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ካለን ልምድ በመነሳት ይህ ከግምት በላይ ነው፡፡
ህግ አውጭው ማለትም ምክር ቤቱ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች በምርጫ የሚሰየሙ ስለሆኑ በዋነኝነት ተግተው ለቀጣይ አምስት ዓመት በምክር ቤት በመቆየት የአዲስ አበባ ኑሮን ማጣጣም ይፈልጋሉ፤ ይህን ሀቅ መካድ አይቻለም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በኮንዶሚኒየም ስርዓት ውስጥ ቅድሚያ ለማግኘት ብዙ ሙከራዎች ይደረጋሉ፤ በቀጣዩ ካልተመረጡ ወደ መረጣቸው ህዝብ ተመልሰው በሌላ መስክ ለማገልገል ዝግጁ የሆኑት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ አስፈፃሚውም ቢሆን በቀጣይ በገዢነት ለመቆየት ቆርጦ የተነሳ ነው የሚመስለው፡፡  ስለዚህ አስፈፃሚው የሚያወጣውን ምርጫ መተግበሪያ እቅድ ነፃ ፍትዊ ይሁን ብሎ የሚከላከል አይኖርም፡፡ ይልቁንም የሚጠበቀው ተባብሮ በቁርጠኝነት መተግበር ነው፡፡ ከዚህ ዘለግ አድርገን ስናስብ ደግሞ አስፈፃሚው የሚያስበው የኢህአዴግ ዕጮዎችን ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚ ጎራ ማን? እንዴት? መወዳደር እንዳለበት ሁሉ የመወስን ፍላጎት አላቸው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ፓርቲዎችን አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ የሆኑ በአሁኑ አጠራር ልማታዊና ዲሞክራሲ አመለካከት ያላቸው፤ ከዚህ ውጭ ኒዎ ሊብራል ቢሆንም በኢህአዴግ እይታ ፅንፈኛ አይደሉም የሚባሉት ብቻ ቢወዳደሩ እና ለአበዳሪዎቻቸው እና ዕርዳታ ሰጪዎች ማስመሰያ ቢሆኑ ደስ ይላቸዋል፡፡ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት አለ እንዲባል ይህ ቻይናን እና መሰሎቿን አይጨምርም፡፡ በዚህ ጉዳይ ኢህአዴግ ማፈር ትቶዋል፡፡ ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ የሆነው ተቃዋሚዎች ሰራቸውን ስለማይስሩ ነው ብሎ ማውራትና ማስወራት ጀምሮዋል፡፡ ተገደን ነው ውስኪ የለመድነው አሉ የደርግ ባለስልጣናት ይባል ነበር፡፡ ኢህዴግም ተገዶ አውራ ፓርቲ ሆኖዋል፡፡ አንግዲህ በዚህ ዓይነት ድባብ ውስጥ ነው የሁለት ሺ ሁለት ምርጫ የሚካሄደው፡፡ ምርጫ መወዳደር ካለብን ይህን ሁሉ ተረድተን ነው፡፡ ምን እናድርግ? ብለን ማስብ የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡
በኢህአዴግ በኩል ለምርጫ ዘመቻ በእቅድ የተያዙት ዋና ዋና ተግባራት ይህችን ሀገር ሊመሩ ይችላሉ የሚባሉ ምርጥ ምርጥ ካቢኔ እና የምክር ቤት አባላትን በማቅረብና በይፋ በማስገምገም አይደለም፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ይህችን ሀገር በቁንጮነት የሚመራትን ሰው ለመምረጥ ዕድል የለንም አንድ ወረዳ የመረጠልንን ሀገር እንዲመራ ከመጋረጃ ጀርባ በሚዶልቱ ሰዎች ዕድል ይሰጠዋል፡፡ በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ትንንሽ አባላቱን በወረዳ ደረጃ ያስገመግማል፡፡ ኢህአዴግ ምርጫ ማሸነፍ የሚፈልገው በብቃቱ አይደለም፡፡ ይልቁንም ለዚህ ጉዳይ ጉልዕ ሚና ይጫወታሉ ብሎ ያመነባቸውን አካላት በማሸማቀቅ እና አንገት በማስደፋት ነው፡፡ ከዚህ በዘለለም የፓርቲው ያልሆኑ በመንግሰት ኃላፊነት የተከናወኑ ተግባራትን ለምርጫ ዘመቻ በማቅረብ ነው፡፡ እነዚህን በትንሽ በትንሹ መመልከት እንችላለን፡፡
ቀዳሚው ተግባር ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በፀረ ሰላም ሀይልነት መፈረጅ ለዚህም “የፀረ ሽብር ህጉን” እንደመሳሪያ በመጠቀም ቅስቀሳዎችን ማድረግ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ከፊት በማስቀደም ተቃዋሚዎችን በፅንፈኝነት መፈረጅ ሲሆን ተቃዋሚዎች ለዚህ ምላሽ መስጠት እንዳይችሉ ሚዲያ መከልከል፡፡ ከተቻለ የተወሰኑ አስተያየቶችን እንዲሰጡ በማድረግ እየቆረጡ ማቅረብ ናቸው፡፡
ለምሳሌ አሽባሪነት በተመለከተ ፓርቲዎች በይፋ የያዙት አቋም እና ፕሮግራማቸው ላይ ያስቀመጡትን ግልፅ አቅጣጫ ወደ ጎን በመተው ኦነግና ኢህአዴግ አብረው ሀገር ሲመሩ የተፈፀሙ ወንጀሎችን በፊልማ በማሳየት የሽብር ስራ ነው በማለት ድራማ እየሰሩ ከዚህ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ፓርቲዎች የሚወነጅልበት ፕሮፓጋንዳ ይሰራሉ፡፡ እን አንዱዓለምን ከእንዲህ ዓይነት እኩይ ተጋባሮች ጋር በማገናኘት ሌሎች የፓረቲ አመራሮቸን ተጠንቀቁ ማለት አንዱ በመተግበር ላይ ያለ ዕቅድ ነው፡፡ ሲከፋም ህዝቡ መምረጥ የሚገባው የሰላም ሀይል የሆነውን ኢህአዴግን ወይም ፀረ ሰላም የሆኑትን ተቃዋሚዎች ብሎ የተሳሳተ ምርጫ ያቀርባል፡፡ ይህን እውነት ለማስመሰል ሚዲያውን በህገወጥ መንገድ ይጠቀማሉ፣ ሚዲያውም መደበኛ ሰራው አድርጎት እየሰራው ይገኛል፡፡
ለተቃዋሚዎች ኢህአዴግና መንግሰት ተለይተው እንደ ፓርቲ መወዳደር ካልጀመሩ ምርጫ የተወሰኑ ወንበሮች ከማግኘት በዘለለ የስልጣን መያዣ መንገድ መሆኑ እያከተመ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ነው፡፡ መድበለ ፓርቲ ስርዓት ለገዢው ፓርቲ እንደ መታጠቢያ ቤት መስታውት ፊትን መመልከቻ ሆኖ ማገልግል ነው፡፡ ይህን ዕቅድ ተግባራዊ እንዳያደርጉ ተቃዋሚዎች ከምንግዚውም በላይ ከህዝቡ ጋር በመሆን ማክሸፍ የግድ ይላል፡፡ በቀጣይ ዓመት ምርጫ ኢህአዴግ እንደ ከዚህ ቀደሙ በሙሰሊም ማህበረሰብ ድጋፍ ላይ ስለማይተማመን አሁን በከፍተኛ ደረጃ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችን ስጋት ውስጥ በመክተት ድምፃቸውን ለኢህአዴግ ድምፅ እንዲሰጡ ማድረግ አንዱ እቅድ ነው፡፡
በሌላ በኩል ኢህአዴግ ለምርጫ የሚጠቀምበት በመንግሰት በጀት የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራትን በመጠቀም ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ የሚነሱት የልማት ስራዎች፤
·        ብዙ ነጥብ ማስቆጠር ባይችልም ኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ፤
·        የስኳር ፋብሪካ ግንባታ (በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ከታቀደው 70 በመቶ ይሳካል በሚል)፤
·        የአባይ ግድብና የግብፅ እንቢተኛነት መሰረት በማድረግ፤
·        የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች፤
·        ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት (ምንም ያህል ያልተሳካ ቢሆን)፤ ወዘተ
ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ለቀጣይ ምርጫ ሚዲያዎች ሌላው የመስዋዕት በግ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ የሚተገበረው ሚዲያዎቹን የፅንፈኞች ልሳን በማለት እና ምንም ዓይነት ዕለታዊ ጋዜጣ እንዳይኖር በማድረግ ነው፤ ካስፈለገም የተወሰኑትን በመዝጋት እና እንዲሰደዱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ጭጭ ማሰኘት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ በዚህ መስመር ከአድማስና ሪፖርተር ጋር ማዝገም ነው የሚፈቀደው፡፡ እነርሱም ቢሆኑ ወደ መጨረሻው ካልሆነ ቀደም ብለው ጠንከር ያለ ነገር ማድረግ አይጠበቅባቸውም፡፡ እንደ ሪፖርተር “ያሳከከው ፓርላማ ጥርስ ያውጣ” ምክር ግን አይከለከልም፡፡ አሁን በምክር ቤት ውስጥ ያለን የምንረዳው አባላት በቀጣይ ምርጫ ይቀጥሉ አይቀጥሉ በከፍተኛ ውጥረት ላይ ነው የሚገኙት፡፡ አሁን የብዙዎቹ ጭንቅ ዕጩ ሆነው ካልቀረቡ አዲስ አበባ እንዴት እንደሚቀሩ ማሰብ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ችግር ከሌለባቸው ምርጫ ክልሎች ውስጥ የአቶ መለስ ምርጫ ክልል እና ሌሎች በሞት የተለዩ የምክር ቤት አባላት፣ በወህኒ የሚገኙ፣ እንዲሁም በስደት ከሀገር የወጡት ወንበሮች ናቸው፡፡ እንደው ለነገሩ አቶ አባዱላ አሁን ከያዙት ወንበር ወደ ክልል የሚሄዱ አይመስላችሁም፣ እኔ ግን ዝም ብሎ ይህ ይታየኛል፡፡ እሰኪ ሃሳብ ስጡበት …. ነው ጡረታ ይወጡ ይሆን?
የሲቪል ማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች በአሁኑ ሰዓት ይህ ነው የሚባል ጫና በመንግስት ላይ እያደረጉ አይደለም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን በፍፁም ዘንግተው ወደ ምርጫ 97 ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይገቡ ማስፈራራያ መሰል መልዕክቶች እየተላለፉ ነው፡፡ እነዚህ ማህበራት ደግሞ በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር ስብሰባ ተጠርተው ሌባ ሲባሉ እንኳን አይደለንም ለማለት ሞራል ያላቸው አይደለሙ፤ ባይሰረቁ እንኳን የእንጀራ ገመዳቸው ወይም የመኖር ዋስተናቸው የተመሰረተበት እንደሆነ መንግሰትን ከሚወክለው ኤጀንሲ ጋር የተዋወቁ ይመስላሉ፡፡ … በዚህ መስመር በአሰሪዎችና ሰራተኞች ፌዴሬሽን፣በወጣትና ሴቶች ሊጎች የመሳሰሉ “ነፃ” ተብዬ ማህበራ ካልሆነ በስተቀር ለመታዘብ እንኳን እንዳያሰቡ መልዕክቱ ቀድሞ እንዲደርሳቸው በመደረግ ላይ ነው፡፡

በሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ኢህአዴግ ለመከተል የመረጠው መንገድ በምንም ሁኔታ ስዕተት ባለመስራት የቀድሞ ስትራቴጂስቱም በሌሉበት ምርጫ በዝረራ የሚያሸንፍ ደርጅት እንደሆነ ማሳየት እና የቀጣዩን ዓመት የመውጫ ስትራቴጂ ለማድረግ ይመስላል፡፡ ይህ የመውጫ ስትራቴጂ ግምት በቅንነት እንጂ በፍፁም በመረጃ የተመሰረተ አይደለም፡፡
ስለዚህ አሁንም ገዢው ፓርቲ አውራ ፓርቲ በሚል አውሬ ለመሆን የቆረጠ ይመስላል፡፡ ይህ ቁርጠኝነት ግን በጎ ቁርጠኝነት እንደማይሆን መገመት ይቻላል፡፡ በደም የተፃፈውን ህገ መንግሰት፣ በደም የማስከበር ወይም የመቀየር አብዮት አማራጭን የሚያስመርጥ እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡ ይህ ምርጫ ወደ ዲሞክራሲ ስርዓት እንጂ ወደ አብዮት ባይመራን ደስታችን እጅግ የላቀ ነው፡፡ ነገር ግን ይህች ሀገር ሃምሳ ዓምት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሶስተኛ አብዮት አያስፈልጋትም ያልን ብንሆንም  ሃምሳ ዓመት ከሚዘልቅ “በምርጫ ሰበብ ከሚመጣ ባርነት” አብዮት ይሻላል የማንልበት ምንም በቂ ምክንያት የለም፡፡ ምን ዓይነት አብዮት ሌላ ቀን እመለስበታለሁ፡፡