Thursday, October 2, 2014

የወታደራዊና አንባገነን መንግሰታት መኖሪና ባህሪያቸው

ዛሬ እንድ ፍልስፍና ብጤ አስኝቶኝ ነው ለመፃፍ የተነሳሳሁት፡፡ የወታደራዊ እና/ወይም አንባገነናዊ መንግሰታት መገላጫ በመኖሪያ አካባባያቸው ይገለፅ እንደሆን በሚል፡፡ ከዚህ ቀጥዬ የማነሳቸውን የወታደር መኖሪያዎች እና የቤተ መንግሰት ሁኔታን ይመለከታል፡፡ ዘወትር እነዚህን ግቢዎች ባየኋቸው ቁጥር የሚመጣብኝ አሳብም ስለሆነ ነው፡፡ ለነገሩ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ አዲስ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚክስ ትምህርት መጀመሪያ የሆነው አንድ በላተኛ፣ አንድ አቅራቢ፣ አንድ ገበያ የሆነው ከአንድ ሰው ጀምሮ፣ ወደ ቤተሰብ እና ሀገር የሚያድገው ሞዴል ተፅህኖሞ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገሮችን ከቀላል በመነሳት ወደ ውስብሰብ ደረጃ ለማጥናት ይረዳል የሚል እምነትም አለኝ፡፡
በወታደራዊ አገዛዝ ውስጥ የሆኑ ሀገሮች መጨረሻቸው እንዴት እንደሚሆኑ መረዳት የሚፈልግ ሰው በቦሌ መንገድ ከቦሌ ወሎ ሰፈር አደባባይ ከመድረሳችን በፊት በሚገኘው የመጨረሻ መታጠፊያ ላይ የሚገኘውን የፌዴራል ፖሊስ የ ”ቪ.አይ.ፒ ጥበቃ” ማረፊያ መመልከት ነው፡፡ ይህ ቤት በደርግ ጊዜ የከፍተኛ ባለስልጣን መኖሪያ እንደነበር የሚነገር ሲሆን፣ ዘመናዊ ቪላ እንደነበር ግን ብዙዎቻችን ምስክር ነን፡፡ ይህ ቪላ በአሁኑ ወቅት በአይናቸን እያየነው ፈራርሶ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሶዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የብሎኬት አጥር እና በፍፁም ለአካባቢው የማይመጥን የቆርቆሮ ግንባታ ተደርጎበታል፡፡ ህገወጥ ግንባታ የሚባለው እነሱን አይመለከትም፡፡ በአጠቃላይ ይህ ጊቢ ከነበረበት ደረጃ አሁን ወዳለበት ደረጃ የወረደው በእኔ እምነት የወታደር መኖሪያ በመደረጉ ነው፡፡ አንዲት ሀገርም በወታደራዊ አስተዳደር ውስጥ ስትወድቅ እንደዚህ እንደምትወርድ ማሳያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ አሁን በግቢው ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ይህ ቤት ቀደም ሲል ምን ይመስል እንደነበር ስለማያውቁ ይህ የምሰጠው አስተያየት ሊገርማቸው ይችላል፡፡ እጅግ የሚያሳፍር ነው፡፡ ኪራይ ቤቶች ይህን ቤት በቅጡ መዝግቦ መያዙንም እጠራጠራለሁ፡፡ በእኔ እምነት ይህ ቤት አሁን ባለው የከተማ የሊዝ ዋጋ ቢሸጥ ለአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ደረጃውን የጠበቀ ፅ/ቤት ሊሰራ የሚችል ገንዘብ ሊያስገኝ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ በከተማው ውስጥ ከግለሰቦች ተወርሰው ለፖሊስ ማረፊያ የተደረጉ ቤቶችን መመልከት ተመሳሳይ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ለምንድነው ግን ከመሻሻል ይልቅ ወደኋላ መሄድ የሚቀናን? የእነዚህ ቤቶች አያያዝ ወታደራዊ መንግሰት ሀገርን እንዴት አድርጎ እንደሚያቆረቁዝ ማሳያ ይመስለኛል፡፡
ከላይ ወታደራዊ መንግሰት መገለጫ ያልኩትን ሞዴል ለማሳየት የሞከርኩ ሲሆን፡፡ የአንባገነን መንግሰታት ደግሞ መገለጫ ሊሆን ይቸላል ብዬ ያልኩትን ላካፍላችሁ፡፡ በአጋጣሚ ሆኖ በቀን አንድ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ፅ/ቤት በጀርባ መግቢያ በር ማለፌ አይቀርም፡፡ በፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ደግሞ በመኪና ብቻ ሳይሆን በእግር ጉዞ ምክንያትም በሳምንት አንድ ሁለቴ አልፋለሁ፡፡ እነዚህን ጊቢዎች ስትመለከቱ መታዘብ የምትችሉት በጊቢያቸው ያደገውን ሙጃ ሳር ብቻ ሳይሆን የንፅህና ጉድለቱን ጭምር ነው፡፡ እነዚህ መሪዎቻችን የሚኖሩበት ጊቢ በዚህ ደረጃ የቆሸሸ እንዲሆን ሲፈቅዱ የሚመሩትን ሀገር እንዴት አድርገው ገነት ሊያደርጉት እንደሚችሉ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከእነዚህ ጊቢዎች የሚወጣው ፍሳሽ መንገድ አቋርጦ የሚሄድ ሲሆን አስፋልቶቹን እና የእግረኛ መንገዶቹን አበላሽቶ ስንመለከት ማዘናችን የማይቀር ነው፡፡ እርገጠኛ ነኝ መሪዎቹ የሚሄዱባቸው አካባቢዎች ምንጣፍ እንደሚሆኑ እና ሀገሩ ሁሉ እንደዚሁ እንዲመስላቸው እንደሚፈለግ፡፡ በእነዚህ ጊቢዎች አጥር ተጠግቶ መሄድ ግን አይቻልም፡፡ እሳት የሚተፋ ጠብመንጃ ያነገቱ ሰዎች ውክቢያ ይከተሎታል፡፡ ይህች ሀገር እነዚህን ጊቢዎች በንፅህና ለመያዝና ለተመልካች ማራኪ ለማድረግ አቅም የላትም ቅድሚያ የምንሰጠው ሌላ ነገር አለን ሊሉን አይችሉም፡፡ በእኔ እምነት የእነዚህ ትልቅ የሀገር ገፅታ ግንባታ የሚገለፅባቸው ጊቢዎች በሙጃ ተውጠውና ንፅህናቸው ተጓድሎ ከጊቢው አልፎ ሌሎችን ያበላሹበት ምክንያት በውስጡ ያሉት መሪዎች መገለጫ ነው፡፡
ለንፅፅር እንዲሆን ሁልጊዜ በቴሌቪሽን የምንመለከተውን የባራክ ኦባማን ቤተመንግሰት ልብ ይሏል፡፡ ማንም መጠራጠር የሌለበት በተግባርም እንዲሁ ግልፅ እና ንፁህ ማራኪ ነው፡፡ ውጭ ከሚገኘው ክፍት አጥር እስከ ቤቱ ድረስ ያለአንድ ግርዶሽ ፅድት ብሎ ይታያል፡፡ በቅርቡ ሰላም የሚነሱ ጠብመንጃ የታጠቁ ሰዎች አይታዩም፡፡ ይህ ማለት ጥበቃ አይካሄድም አይደለም፡፡ ለዚህም ፅሁፍ መነሻም የሆነኝ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጊቢ በአንድ ሰው መደፈሩን (አጥር ዘሎ መግባት) አስመልክቶ የግቢው የፀጥታ ሃላፊ ከስልጣን መልቀቅ ነው፡፡ ለምን እንደ ኢትዮጵያ ቤተመንግሰት ጠባቂዎች አላስፈራራችሁም በሚል አይደለም፡፡ ወደፊትም ጊቢውን ማጠር እንደመፍተሄ አይወሰድም፡፡ እንደወትሮ ለህዝብ ዕይታ ክፍት ይሆናል ጥበቃው ግን በስርዓት ይጠናከራል፡፡ የህዝብ መብት በማይነካ መልኩ፡፡ በእኛ ሀገር አንድ ሰው አምልጦ ቢገባ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ግንባሩን በጥይት ይባላል፡፡ በዚህም ምክንያት የቤተ መንግሰት የጥበቃ ኃለፊ የሚወስደው አንድም ኃላፊነት  አይኖርም፡፡ ከኃላፊነት ይለቃልም ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይህ ነገር  በእኛ ሀገር ስልጣን እንጂ ተጠያቂነት የሚባል ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው፡፡ ተረኛ ጠበቂው ግን ዘሩ ተጣርቶ ከአንዱ ድርጅት ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ መከራውን ይበላል፡፡ ኦሮሞ ከሆነ ኦነግ፣ አማራ ከሆነ ግንቦት 7፣ ወዘተ. ….
ልጅ ሆኜ በቢቢሲ የሰማሁት ነገር ታወሰኝ፡፡ ጋዜጠኛው ዲሞክራሲ የሌለባቸው መንግሰታት ሰር ያሉ ሀገራትን በምን እነለያለን? የሚል ጥያቄ  ያቀረበለት አንድ የፖለቲካ ተንተኛ እነዚህ ሀገራት በአብዛኛው “ዲሞክራቲክ” የሚል ቅጥል አላቸው ሲል ሰምቻለሁ፡፡ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ …….፡፡ ለምሳሌ የእኛን ጉድ ብንመለከት “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ” እንደሚለው ማለት ነው፡፡ በተግባር ዲሞክራሲም ፌዴራሊዝምም እንዳልሆነው ማለት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ዛሬ የምለው ሀገራት ዲሞክራት መሆናችው እና አለመሆናቸው የሚለየው በቤተመንግሰት ጊቢ አያያዝና ጥበቃ ሰርዓታቸው ነው ቢባልም ሊያስኬድ ይችላል ነው፡፡ ይህን ሞዴል ወደሌላ አፍሪካ ሀገር ሰፋ አድርጎ የሚያየው ቢገኝ በንፅህና የሚጠበቅ ቤተ መንግሰት እና ለህዝብ ግልፅ የሆነ ቤተ መንግሰት ያላቸው ሀገሮች የተሸለ ዲሞክራቲክ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡  አስተሳሰብ በአካባቢ ከሚኖር ሁኔታ ሊመነጭ ይችላል፡፡ አካባቢውንም እንዲህ እንዲሆን የሚፈቅዱት ውስጡ የሚገቡት ሰዎች ናቸው፡፡ ለነገሩ ቤተ መንግሰትን ለማስተዳደር ኃለፊነት የሚሰጣቸው ሰዎች የሚመረጡበት መስፈርት እኮ …….
ሁለት ሺ ሰባት የቤተመንግሰት ጊቢውንም ሆነ ከዚያ ውጭ ያለውን አስተዳደር የምንሻሽልበት እንዲሆን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል፡፡
መልካም አዲሰ ዓመት ….መልካም መስቀል ….መልካም …..
ቸር ይግጠመን!!!!!


Tuesday, September 16, 2014

ተጠያቂነት የማያረጋግጥ የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ

ባለፈው ሳምንት ማጠናቀቂያ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት የመንግሰት ከፍተኛ ባለስልጣኖች የ2006 የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ሁሉም ሪፖርት አቅራቢዎች “ፖወር ፖይንት” በሚባል የማይክሮ ሶፍት ፕሮግራም የተጠቀሙ ሲሆን አብዛኞቹ ይህን ፕሮግራም በቅጡ ለመጠቀም በግል ያላቸውን ዝቅተኛ ችሎታ ያሳየ ብቻ ሳይሆን በየመስሪያ ቤታቸው ሞያ ያላቸውን ሰዎች መጠቀም ያለመቻልና ያለመፈለግን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር፡፡ የተፈቀደላቸውን አጭር ጊዜ ያመጣጠነ ዝግጅት ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው ያዘጋጁትን የፅሁፍ ሪፖርት ሲያነቡ ጊዜ አለቀ እየተባሉ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን ቁም ነገር (ካለቸው ማለቴ ነው) ትተው በመግቢያና በሪፖርት ይዘት ጊዜ ሲያባክኑ መታዘብ አሰገራሚ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የውሃ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ በንፅፅር የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ቴክኖሎጂ የመጠቀም አስፈላጊነቱም ሰዓትን በአግባቡ በመጠቅም ተገቢውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ ረፖርት አቅራቢዎች ስዓት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ሊያቀርቡ ያሰቡትን በሙሉ ካለማቅረባቸው በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሰዓት ቁጥጥር ስራ ጨምረውባቸው ነው የዋሉት፡፡ እርግጠኛ ነኝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ ኖሮ እንዴት ሊበሳጩባቸው እንደሚችሉ፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ሚኒሰቴር ሚኒስትሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ድርጅታቸው ኢህአዴግ ንቅናቄውን እንደ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ግብዓት ለመጠቀም መወሰኑን በሚያሳብቅ ሁኔታ መሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ አና መንግስታችን በሰጡት ትኩረት በሚል ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ የመሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ በንግግሩ መግባት መልዕክት ለተሰበሰቡት የመንግስት ሹሞች ሳይሆን ጥሪ ለተደረገላቸው እና በአዳራሹ በብዛት ለታደሙት በኢህአዴግ አጣራር “የህዝብ አደረጃጀት” በመባል ለሚታወቁት የኢህአዴግ አፍቃሪዎች ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆን የስብሰባ ታዳሚዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት “ውድ” የሚል ተቀፅላ ያገኙት እነዚሁ የህዝብ አደረጃጀቶች ናቸው፡፡ እርግጥ ነው በቀጣዩ ምርጫ በአሸናፊነት ለመውጣት የእነዚህ የህዝብ አደረጃጀቶች ሚና የላቀ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ተቃዋሚዎች ተጠናክረው ታዛቢ ካስቀመጡ ምርጫ ቦርድ ያለነዚህ የህዝብ አደረጃጀት ንቁ ተሳትፎ ቢሮ ቁጭ ብሎ ኢህአዴግን ብዙ ሊረዳው አይችልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩም ሆነ ፓርቲያቸው ይህ በቅጡ የገባቸው ይመስለኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ እዚህና እዚያ የጎደሉ አግልግሎቶችን በማስተካከል ብቻ የሚያበቃ እንዳልሆነ ይልቁንም የመልካም አስተዳደር ችግር በቀጣይ የሚያመጣው “መዘዝ” ብዙ መሆኑን አበክረው ገልፀዋል፡፡ እርሳቸው “መዘዝ” ያሉትን እኛ አብዮት ስንለው የመንግሰት ሚዲያዎች ደግሞ ተቀብለው “የቀለምና የፍራፍሬ አብዮት” ይሉታል፡፡ ተመስገን ደሳለኝ አብዮት ብቻውን የማይጥም ከሆነ ብሎ ይመስለኛል “የህዳሴው አብዮት” ብሎታል፡፡ ለማነኛውም በዚህች ሀገር የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር መዘዙ ብዙ መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ከታመነ ይህ መዘዝ የተባለው ነገር ስሙ ብዙ አያስጨንቀንም፡፡ የሚያስጨንቀን ይህ መዘዝ እንዳይከተል ምን ማድረግ ይኖርብናል ነው፡፡ በተለይ መንግሰት ይህን መዘዝ ለመከላከል ብሎ ለናይጄሪያ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ልምድ ይሆናል ተብሎ የተነገረለትን “የፀረ ሽብር” ህግ እንደመፍትሔ አሰቦት ከሆነ ከመዘዙ እየራቀ ሳይሆን ወደ መዘዙ በፍጥነት እየተጠጋ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኖ ሌሎች ሚኒሰትሮች በተደጋጋሚ ያነሱት ሌላ አብይ ነገር የኪራይ ሰብሳቢነት የሚመለከት ሲሆን ይህን የኪራይ ሰብሳቢነት የገለፁት የኪራይ ስብሳቢነት መረብ በሚል ነበር፡፡ በዕለቱ ያነበብኩት ጋዜጣ ደግሞ በኮንትሮባንድ ሊገባ የነበረ ወተት በኬላ መያዙን የሚገልፅ ክፍል ነበረው፡፡ ታዲያስ ስብሰባ ላይ ቁጭ ብዬ “የሰው ለሰው ድራማ” አስናቀ እና ኢህአዴግ ቁልጭ ብለው ይታዩኝ ጀመር፡፡ ይህን መረብ ለመበጠስ እሰከ አሁን እንዳልተቻለ እና ከፍተኛ ትግል እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒሰትሩን ጨምሮ ሚኒስትሮቹ  እየገለፁ ኢቲቪ ደግሞ አሰናቀ ለፍርድ ሳይቀርብ ለምን ሞተ ብሎ ዶክመንተሪ ይሰራል፡፡ የኪራይ ስብሳቢነት መረብ እስኪበጣጠስ ድረስ አስናቀ መኖር እና ማጋለጥ ነበረበት የሚል አቋም አለኝ፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ ጎበዝ? አሁን አንድ የቴሌቪዥን ድራማ አጨራረስ እንዴት መሆን እንዳለበት ዶክመንተሪ ያስፈልገዋል? ለማንኛውም የሰው ለሰው ድራማ ደራሲና አዘጋጆች የህዝቡን እንጂ “ባለሞያ” ተብዬዎች በኢቲቪ ያቀረቡትን አስተያየት እንደማትሰሙ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ዶክተር ደብረፅዮን በዕለቱ ሪፖርት ከሚያቀርቡት ሚኒስተሮች ቀዳሚውን ቦታ ያገኙ ነበሩ፡፡ ሪፖርት ያቀረቡት በዋነኝነት የቴሌኮሚኒኬሽን ሴክተሩን  በሚመለከትነው፡፡ ከሚመሩት መስሪያ ቤት አንፃር ሲታይም ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተሻለ መሆን ሲጠበቅባቸው ማድረግ አልቻሉም፡፡ የቀረበው ሪፖርትም በፍፁም በመሬት ላይ ካላው የቴሌ ችግር ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ በሪፖርቱ መስረት ሁሉም ችግሮች በእቅድ ከተያዘው ጊዜ ቀደም ብሎ የተተገበረ ሲሆን በአሁኑ ስዓት በተለይ በአዲስ አበባ ይህ ነው የሚባል ችግር እንደሌለ ነው ያበሰሩን፡፡ ይህ ግን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው ለመረዳት ከሪፖርታቸው በኋላ በሻይ እረፍት የተሰበሰቡት ሹመኞች ሳይቀሩ ሲያፌዙ እንደነበር ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡ ዶክትር ደብረፅዩን ከአቀረቡት ሪፖርቱ ውስጥ የቴሌን ሰራ ለመስራት የፈጠሩት አደረጃጀት አንድ ጥሩ ነገር ጠቆም አድርጎን አልፏል፡፡ ይህም ፓርላማው ማፅደቅ የማያስፈልገው የቴሌን አገልግሎት በአሰራ ሦስት ክበቦች ወይም ክልሎች መከፋፈላቸው ነው፡፡ ይህም የተደረገው ለአሰራር ቅልጥፍና ሲባል እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ተቀባይነት ያለው በጎ ጅምር ነው፡፡ በዚህ አደረጃጀት ሀረሪ ወይም ድሬዳዋ በምንም መለኪያ አንድ ክልል ሊሆን አይችሉም፡፡ አዲስ አበባ እንኳን አንድ ክልል ሊሆን አልቻለም፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ እንዲሁ፡፡ ይህ ለቴሌ አገልግሎት ምቹ የሆነ አደረጃጀት ለሌሎች የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ በሚመች መልኩ የፌዴራል ስርዓቱ ይዋቀር ለምንል ሰዎች እንደ ጥሩ መግቢያ ሊያገለግል ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህን ሀሳብ ከዶክተር ደብረፅዮን ወስዶ የህዝቦችን ቋንቋ እና ስነ ልቦና መሰረት ባደረገ ሁኔታ ቢየጠናው ጥሩ ሀሳብ ይመስለኛል፡፡ እሰኪ አንዴ ከያዝነው አስተሳሰብ ወጣ ብለን በተለየ መንገድ ለማሰብ እንሞክር፡፡ ዶክተር ደብረፅዩን ያቀረቡት ሀሳብ በሌሎች ፌዴራል መስሪያ ቤቶችም ሊሞከር ይችላል፡፡ ይህ የምክር ቤት ውሳኔ አይጠይቀም ብለዋልና፡፡
የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ባለፈው ዓመት ሰኳር እና ስንዴ እጥረት እንደነበረ በይፋ አምነዋል፡፡ ያቀረቡት ምክንያትም ሰኳር ይደርሳል ተብሎ ተገምቶ በፊንጫ እና ተንዳሆ ሰኳር ፋብሪካ በእቅዱ መሰረት ባለመድረሱ ችግር መከሰቱን ነው፡፡ እኛም ሰንል የነበረው ችግር አለ በእቅድ መስራት አልቻላችሁም እንዲሁም አትችሉም ነው፡፡ የሰንዴም የሰኳርም እጥረት የለም ሲሉን እንዳልነበር አሁን ችግር መኖሩን አምነው ከውጭ ግዥ እየተፈፀመ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ይህች ሀገር በሌላት የውጭ ምንዛሪ በሀገር ውስጥ ሊመረት የሚችልን ምርት ከውጭ እንድታሰገባ እያደረገ ያለን ፖሊሲና ፈፃሚዎቹ ተጠያቂ ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ሰኳርና ስንዴ ማቅረብ ያልቻለ የሃያ ዓመት አገዛዝ መዘዝ ሊመጣበት እንደሚችል ቢፈራ ተገቢ ነው፡፡ አንድ በግብርና ላይ የተሰማሩ ባለሀብት ፈራ ተባ አያሉ “ስንዴ ከውጭ ታዞ የሚመጣበት ገዜ እና በሀገር ውስጥ ቢመረት የሚወሰደው ጊዜ ተቀራራቢ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አስከትለውም “ኢትዮጵያ ሰንዴና ሰኳር ኤክስፖርት የምታደርግ ሀገር እንጂ ከውጭ የምታስገባ መሆን የላባትም፡፡” በማለት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ግብርና ግን መሬት ይፈልጋል መሬት ደግሞ በመንግሰት እጅ ሆኖ እንደልብ የሚገኝ አይደለም፡፡ የመሬት ፖሊሲያችን ይፈተሸ ስንል ለምን ጫጫታ ይበዛል?
የፍትሕ ሚኒሰትር ሪፖርት በጥቅምት ወር ባቀረቡት እቅድ በግርፊያ ምርመራ ያደርጋሉ ያሉዋቸውን ፖሊሶች እንዴት እንደተቆጣጠሩ ሳይነግሩን ቢጫ ታክሲ ማህበራት ጋር ስብሰባ አድርገናል እና የመሳሰሉትን ሪፖርት ማድረግ ምን ፋይዳ እንዳለው መረዳት ከባድ ነው፡፡ አስገራሚው ደግሞ ፍትህ ሚኒስትር የሚያዘጋጀው የዜጎች ቻርተር ነው፡፡ በእኔ እምነት ፍትህ ሚኒስትር ከህገ መንግሰቱ የተሻለ ሌላ የዜጎች ቻርተር የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡ በፍትህ ሰርዓቱ እምነት እንዲኖረን ህገ መንግሰቱን ማስከበር ላይ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከሌሎች የመንግሰት አካላት ጋር ተባብሮ የህገ መንግስቱን መስረታዊ ድንጋጌዎች መናድ ማቆም አለበት፡፡ ለዚህም ማሳያው በቅርቡ በመፅሔቶች እና ጋዜጦች ላይ በመንግሰት ሚዲያ የተጀመረውን ስም ማጥፋት ተከትሎ በፍትህ ሚኒስትር መሪነት ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱ ነው፡፡ ዘጠና ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ ቢበዛ 20 ሺ ኮፒ ለሚያትም  አንድ መፅሔት ሀገር ሊያጠፉ ነው የሚል መዓት ማውራት ምን አመጣው? ለነገሩ የፈሪ ዱላ የሚባለው ብዒል አንደሆነ መገመት አያሰቸግረም፡፡ ግለሰቦችን እያሳደዱ በማሰር እና አሰሮ ማሰረጃ እያፈላለኩ ነው ከሚል ፌዝ  መውጣት ይኖርብናል፡፡ መንግሰት “የፀረ ሸብር ህግ” ያሰፈልገናል ሲል የነበረው ሰዎችን ሳይዝ በቂ ማሰረጃ ለመሰብሰብ ይጠቅመኛል በሚል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ይህ ነው የሚባል ነገር ሳያቀርቡ ሰዓት ሰዓት አልቋል ቢባሉም በከተማው የተንሰራፈውን የቤት ችግር ለመቅረፍ በተለይ በማሕበር ለመገንባት ገንዘባቸውን ባንክ ላስገቡ፣ ቅድሚያ ታገኛላችሁ ተግለው ከሚፈለገው 40 ከመቶ በላይ ባንክ ያስገቡ በ40/60 የተመዘገቡ እና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊየን በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የቤት አቅርቦት ማሳካት አለመቻል አንድም ነጥብ ሊያነሱ አልቻሉም፡፡ ዜጎች ቤት እናገኛለኝ ብለው ተብደረው ባንክ ያሰቀመጡትን ገንዘብ የመንግሰት ባንክ እየነገደበት ትርፍ በትርፍ ሲሆን ዜጎች ቀጣይ ተሰፋቸው ምን እንደሆነ እንኳን ማሰረዳት አልቻሉም፡፡ አዲሱ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ የተጀመረ ሰሞን አንድ ፅሁፍ አቅርቤ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት የቤቶች ግንባታን አስመልክቶ ሂሳብ ማውራረድ ስለሚኖር ለዛሬው በዚሁ ማለፍ ይሻላል፡፡ ዜጎች ግን አሁንም ተሰፋ እያደረጉ ነው?
በመጨረሻ ሁሉም ሪፖርት አድራጊ መስሪያ ቤቶች እንደ ችግር ያነሱት “የከፍተኛ አመራር እና ፈፃሚዎች የአመለካከት ችግር መኖር” የሚለው ይገኘበታል፡፡ ይህ ችግር ሁሌም በኢህአዴግ ሰፈር እንዳለ የምንረዳው ስለሆነ መፍትሔው በየአዳራሹ እየመሸጉ ሰልጣና፣ ስልጣና እየተባለ የሀገር ሀብትና ንብረት ከማባከን ተጠያቂነት የሚያሰፍን ሰርዓት በመዘርጋት ኃላፊነቱን ብቃት ላለው ዜጋ ማስረከብ ነው፡፡ አሁን በኢህአዴግ አባልነት በመንግሰት ስልጣን ላይ የሚገኙት በአብዛኛው ከዝቅተኛ ደረጃ እስከ ማስተርስ እና ከዚያም በላይ በርቀትም ሆነ በመደበኛ ይህች ሀገር አስተምራለች፡፡ እነዚህ ኃለፊዎች ባለፉት ሃያ ዓመታት የሰለጠኑ ቢሆንም ለህዝብ መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችል አመለካከትና ክዕሎት ማደበር አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ቦታውን መልቀቅ ግድ ይላቸዋል ብንል ድፍረት ሊሆን አይችልም፡፡ ቦታውን የማስለቀቅ ኃለፊነት ደግሞ የህዝብ ነው፡፡ የህዝብ ድምፅ ይከበር ዘንድ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ ማንም የማንም ነፃ አውጪ አይደለም፡፡

ቸር ይግጠመን!!!

Thursday, September 4, 2014

የኢቲቪ ጥያቄዎች እና የእኔ መልሶች


በሰሞኑ ሰለ ግል ሚዲያው ትንሽ ለማለት ሞክሬ ነበር፡፡ የዚሁ ተከታታይ የሆነውን ይህ ፅሁፍ ደግሞ በዋነኝነት የአሁኑ የኢትዮጵ ብሮድካሰት ኮርፖሬሽን ለዘጋቢ ፊልም መስሪያ ብሎ ያዘጋጀውን ጥያቄ መሰረት አድርጌ አቀርብላችኋለው፡፡ ከጥያቄው መረዳት እንደምትችሉት ጥያቄዎቹ ለውንጀላ በሚያመች መልኩ የተዘጋጁ ሰለሆነ በግልፅነት ጥያቄውን ለመመለስ የሚሞኩሩ ሰዎች እንደ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ መጠለፋቸው አይቀርም፡፡ ሚዲያ ብላችሁ አዲስ ዘመንን ስትከሱት ኢቲቪ ከሌላ ቦታ ካመጣው ጋር ቆርጦ ቀጥሎ ዘጋቢ ፊልም የግል ሚዲያውን ለመክሰስ ግብዓት ያደርጋችኋል፡፡ ይህን ለመከላከል ኢቲቪን በሩቁ ማለት ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው የቀረቡልኝን ጥያቄዎች ለኢቲቪ ብመልስ ምን ሊሆን እንደሚችል በምትረዱት ሁኔታ ከዚህ በታቸ የማቀርብላችሁ፡፡
ኢቲቪ እንደ መግቢያ በመጀመሪያ ያቀረበው ጥያቄ “ብሄራዊ ጥቅም ማለት ከኢትዮጵያ አንፃር መገለጫዎቹ ምንድናቸው?” የሚል ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ ዓላማ በመጨረሻ ላይ ከሚቀርቡት ጥያቄዎች አንፃር ስታዩት የግል ሚዲያዎቹ እነዚህን ብሔራዊ ጥቅሞች እየተጋፉ ነው የሚል መደምደሚያ ለመስጠት እንዲመቸው ያቀረበው ነው፡፡ በእኔ እምነት በቅርቡ እየሰፋ የመጣውን ሀገር ማለት? የሚለው  ተጠየቅ መሬት ሲደመር ሰው (አንድ እና አንድ ሁለት እንደሚባለው) ማለት አይደለም፡፡ ለምሣሌ የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ሀገር ማለት የእኔ ልጅን ልብ ይሏል፡፡ የመለስ ዜናውንም ሀገር ማለት ህዝብ ነውም የሚረሳ አይደለም፡፡ የዶክተር ሀይሉ ኃርሃያን የሀገር ልክፍት ግጥምም ትዝ ይለኛል፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ እንደ እልም ፈቺ፤ ለእልም ፈቺ እንተውው እና በእኔ እምነት ብሔራዊ ጥቅም ወይም የሀገር ጥቅም ማለት በአጭሩ የዜጎች ጥቅም ብዬ ነው የማስበው፡፡ የሀገረ ኢትዮጵያ ጥቅም የሚባል ነገር ሁሉ የኢትዮጵያዊያን ጥቅም ማለት ነው ብዬ ነው የምረዳው፡፡ ኢትዮጵያዊያኖች እንዴት ነው የሚጠቀሙት ብለን ወደ ዝርዝር ሰንገባ ደግሞ በሠላም ወጥቶ መግባት/መኖር፤ የሰውነት መብት መከበር፤ የህግ የበላይነት መኖር፤ ወዘተ ሲሆኑ መንግሰት እነዚህን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችለው መዋቅር እንዲኖረው ማደረግ ደግሞ የህዝቡ ዋነኛ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ አንድ አንድ ሰዎች ጥቅም የሚባለውን ነገር ከራሳቸው በላይ ዘለግ አድርገው ማየት ስለማይችሉ ለልጅ ልጆች ሀገርን እንደ ሀገር አስጠብቆ ማለፍ የእነርሱ ድርሻ አይመስላቸውም፡፡ ለዚህም ነው ድንበር ማስከበርም፣ ዛፍ መትከልም፣ ወንዝ ተራራውም እንዲጠበቅ ማድረግ የመሳሰሉት አብይ ጉዳዩች ባለቤት ያጣሉ፡፡ ንቁ ዜጎች ግን ይህን በፍፁም አይዘነጉትም፡፡ ዛፉ ጥላው አድጎ ባይጠቀሙበት እንኳን ችግኝ መትከል ሀገራዊ ሃላፊነታቸው እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ድንበር ማስከበርም እንዲሁ ለልጅ ልጆቻቸው የሚተላለፍ መሆኑን ስለሚገነዘቡ ሀገር ቆርሰው አይሰጡም፡፡ ለኢቲቪ ይህን መልስ ብሰጠው የት ሰፈር እንደሚቆርጠውና ከምን ጋር እንደሚቀጥለው መገመት አያሰቸግርም፡፡
የኢቲቪ ተከታዩ ጥያቄ “የግል ፕሬሶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች በማሰጠበቅ ረገድ ምን ያህል እየሰሩ ነው?” የሚል ሲሆን ከመጀመሪያው ጥያቄ ጋር ያለው ዝምድና ፍንትው ብሎ ይታያችኋል፡፡ በግሌ ለዚህ ጥያቄ ያለኝ መልስ “አንድም የግል ፕሬስ” የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓ፣ ለሀረብ ወይም ለሌላ አካል አሳልፎ ይሰጣል የሚል እምንት ሊኖረኝ አይችልም፡፡ በሀገራችን እንዳለመታደል ሆኖ መንግሰት የሚባለው አካል ከላይ የዘረዘርኳቸውን የህዝብ ጥቅሞች ማስጠበቅ ሲያቅተው እና ይህን ችግሩን በሌላ ማለከክ ሲፈልግ የግል ሚዲያዎቹ ቅርብ ሆኖ ያገኛቸዋል፡፡ ስለ መንግሰት በጎ በጎውን መዘመር እንጂ የመንግሰትን ኃላፊነት ያለመወጣት እና ደካማነት ሲነሳ “የሀገር/የህዝብ ጥቅም” ተነካ ብሎ ቡራ ከረዩ ማለት ይቀናዋል፡፡ እውነቱን ስንመለከተው ግን ጥቅም የተነካ ከሆነ ወይም ሊነካ ከሆነ የተነካው የሹሞች ጥቅም ነው፡፡ እርሱም እንደ ዜጋ ከሚያገኙት ሳይሆን በወንበር ተገን የሚዘርፉት ነው፡፡ የግል መልሴ ለኢቲቪ ይህ ነበር የሚሆነው፡፡

ሶሰተኛው ጥያቄ “የግል ፕሬሶቹ መሰረታዊ የሆኑ የግለሰብ መብቶቸን በሚጋፋ መልኩ እየሰሩ ይገኛሉ ይባላል፤ በዚህ ላይ እርሶ ይስማማሉ ወይ?” የሚል ነው፡፡ እነዚህ የግል ፕሬሶች ማሰረጃ የሌለው  ነገር አትመው የግል መብት ነክተው ከሆነ በማስረጃ ፍርድ ቤት ማቅርብ ይቻላል፡፡ የግለሰብ መብት የሚሉት ግን ሹመኞቹን እንደሆነ መረዳት አይከብድም፡፡ አንድ አንድ ሹመኞች የህዝብ ማስተዳደሪያ የሆኑትን የሹመት ቦታዎች ሲረከቡ አብሮ የሚመጣውን የግል መብትና ነፃነት ገደብ ይዘነጉታል፡፡ የመንግሰት ንብረት ሲያስተዳድሩ በትክክል ካልተጠቀሙ ሚዲያው ይህን ለልጆቻቸው ብሎ ዝም ብሎ ሊያልፋቸው አይችልም፡፡ ይህ በመንግሰት ሹመኞች ላይ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ህውቅናን ያገኘ ማነኛውም አይነት ታወቂነት ደረጃ ላይ የሚገኝ አርቲስት፣ ባለሀብት፣ ሯጭ፣ ወዘተ ሊሆን ይቸላል፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የግል ሚዲያዎች የግለሰቦችን መብቶች ሊጥሱ የሚችሉበት ምክንያት የለም፡፡ ማንነቱ ስለማይታወቅ ሰው ቢፅፉ ማንም ሊያነብላቸው አይችልም፡፡ ትርፉ ኪሳራ ነው የሚሆነው፡፡ በእርግጥ እነዚህን የግል መብቶች ከላይ እሰከታች የሚጣሱት ጡንቻና መዋቅር ባለው መንግሰት ነው፡፡ መንግሰት ደግሞ እነዚህን ድርጊቶች የሚፈፅመው ለህዝብ ጥቅም ስል ነው ይላል፡፡ እኛ ደግሞ በህዝብ ስም መብታችንን አትጣስ እያልን ለትግል የወጣነው በግል ሚዲያ ላይ ሳይሆን በመንግሰት ላይ ነው፡፡
አራተኛው ጥያቄ “አሁን በገበያ ላይ ያሉት የግል ፕሬሶች የጋዜጠኝነትን መሰረታዊ የስነ ምግባር መርሆዎችን ጠብቀው በመሰራት ረገድ ምን ዓይነት አዎንታዊና አሉታዊ አስተያየት አለዎት?” የሚል ነበር፡፡ ይህ በተደጋጋሚ ጋዜጠኛ ነኝ የሚሉት ሁሉ የሚያነሱት ነጥብ ሲሆን ሰምምነት ተደርሶበት ሁሉም ሊገዛለት ይገባል የተባለ የሰነ ምግባር መርሆ ግን በዓለም ላይ የለም፡፡ አብዛኞቹ የሚስማሙበት ግን ጋዜጣኛ መርዕ ማድረግ ያለበት ነገር ካለ “ተጠያቂነቱን ለህዝብ” ማድረግ ነው፡፡ ይህም ማለት የህዝቡን የመረጃ ፍላጎት ማርካት ነው፡፡ ከዚህ ተከትሎ የሚመጡ የመረጃ ትክክለኝነት፣ግብረገባዊነት፣የመሳሰሉት ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህን ጋዜጠኛው ማሟላት ካቃተው ደግሞ ተጠያቂነቱ ለህዝብ ይሁን ካልን ፍርድ ሰጪውም ህዝብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ ዓይንና ጆሮ ሲከለክላቸው ከገበያ ይወጣሉ፡፡ ብሎም ይጠፋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ “አከፋፋዮች” ናቸው እንዲህ የሚያደረጉት የሚል ክስ ውሃ አይቋጥርም፡፡ በውጭ ሀይል ግፊት ነው የሚለውም ክስ የትም የሚያደርስ አይሆንም ማለት ነው፡፡

በመጨረሻ የቀረበው ጥያቄ “የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፕሬስ አንዱ በሌላው ላይ ያላቸው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅህዕኖ እንዴት ይታያል?” የሚል ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ ዓላማ የግል ፕሬሶቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ልሣን ሆኑ የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ነው፡፡ በእውነቱ ግን ሁልጊዜ ፕሬስ  “የWatch Dog - የህዝብን ጥቅም የመጠበቅ” ስራውን መዘንጋት የለበትም - ፓርቲዎች በየተራ ስልጣን የሚይዙ ስለሆነ የፕሬስ ይሁንታን ለማግኘት መጣጣራቸው አይቀርም፡፡ ተገቢም ነው፡፡ በእኛ ሀገር ገዢው ፓርቲ “የህዝብ/የመንግስት” የሚባሉትን ሚዲያዎች ጠቅልሎ የያዘና መረጃም የማይስጥ ስለሆነ፤ የግል ሚዲያዎች ደግሞ በመንግሰት በኩል የተነፈጉትን መረጃ ለማግኘት እና የገዢው ፓርቲ ተግባርም ትክክል እንዳልሆነ ለማሳየት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ቢወግኑ ክፋት የለው፡፡ ለነገሩ መንግስት መረጃ እየሰጣቸውም ቢሆን መንግሰት መደገፍ የማይፈልግ የግል ሚዲያ ማቋቋም ነውር የለውም፡፡ ነውር የሚሆነው በመንግሰት ሚዲያ ገዢውን ፓርቲ ብቻ ማገልገል ነው፡፡ 

Tuesday, August 26, 2014

በጥፍሩም በጥርሱም ለስልጣን የሚተጋ መንግሰት …… እንዴት እንታገለው!!

በጥፍሩም በጥርሱም ለስልጣኑ የሚተጋን መንግስት በሁሉን አቀፍ ትግል መጣል አለብን ብለው ጠብ መንጃ ቢያነሱ ክፋቱ ምን ላይ እንደሆነ አልታይህም እያለኝ ነው፡፡ ለምን በጠብ መንጃ ፍልሚያ ስልጣን መያዝ እንዳለብኝ በግሌ ባይገባኝም አሁን ግን የኢህአዴግ ዓይነት መንግሰት ከደርግ እንዴት እንደሚሻል ማሰብ እያቃተኝ ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል ሰራዊት እንዴት እንገንባ ለሚለው ጥያቄ አፋጣኝ ምለሽ ካልሰጠን በስተቀር መንግሰት በግልፅ እየደገፈ ያለው በጠብ መንጃ ሊገዳደሩ የፈለጉት ነው፡፡ በሰላም ያልነውን ሰላም እየነሳን ይገኛል፡፡ መንግሰት ሆይ ሰላም እንድትሆን ሰላም ሰላም ለምንል ዜጎች ሰላም ሰጠን የምር የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡
በፍትሕ አደባባይ የፈለገውን ማድረግ የወሰነ መንግሰት በእጅ አዙር ደግሞ በየማተሚያ ቤቱ እየሄደ መፅሄትና ጋዜጣ ታትሙና ወዮላችሁ ማለት ተያይዞታል፡፡ ይህ ከህግ ሰርዓት ውጭ በየማተሚያ ቤቱ በግንባር እና በስልክ የሚደረገው ማሰፈራሪያ ከወሮበላነት ውጭ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ መንግሰት ለህዝብ ጥቅም ሲባል ክስ መስርቻለሁ ብሎዋል፡፡ ህዝቡ የሚለው ግን ሌላ ነው፡፡ መፅሄት መቼ ነው የሚወጣው ነው፡፡ በቃ!!! ፍርድ ቤት በመፅሔትና ጋዜጦች ላይ ቢፊልግ እግድ ቢፈልግ ይዘጉ እሰኪል ድረስ ምን የሚያጣድፍ ነገር መጥቶ እንደሆነ ባናውቅም የመንግሰት አሽከሮች በየጉራንጉሩ ባሉ ማተሚያ ቤቶች ደጃፍ እየዞሩ ማሰፈራራት ተያይዘውታል፡፡ ሹሞቻችን ይህን አላደረግንም ብለው እንደሚክዱ ባውቅም ይህን ዓይነት ወሮበላነት ማስቆም ካልቻሉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ መርሳት የለባቸውም፡፡ ስህተታችውን በአደባባይ ተችተን እንዲታረሙ የሚሰጣቸው ምክር ካንገሸገቸው የመጨረሻው ቀን ሲመጣ እንደሚጠየቁ ግን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ የወሮበላ አለቃነት ከወሮበላነት በላይ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ እነዚህን ወሮበላዎች አስቁሙልን ግልፅ አቤቱታ ነው፡፡ በየሳምንት ብዙ መቶ ሺ ብር ገቢ ያገኙ የነበሩ ማተሚያ ቤቶች በህጋዊ መስመር ሳይሆን በስልክና በቃል ከወሮበሎች በሚሰጥ ማሰፈራሪያ አጅ መስጠት እና ገበያ ማባረር ደግሞ የሚያስመሰግን ፍርሃት እንዳልሆነ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ የእያንዳንዳችን ፍርሃት ተደምሮ ነው እነርሱም ያለምንም ይሉኝታ ሊያሰፈራሩን ቤታቸውን ድረስ የሚመጡት፡፡ በወረቀት ትዕዛዝ ይድረሰኝ ለማለት ወኔ የሌለው ማተሚያ ቤት የሙት ዓመትና ተዝካር ወረቀት ሲያትም ይኖራታል፡፡
መንግሰት በሚዲያዎች ላይ በዶክመንተሪ ጀምሮት የነበረውን ወደ ፍትህ አደባባይ ያመጣውን የግል ሚዲያ አሁንም ገና አልበቃውም፡፡ በጥፍርም በጥርስም ሊዘለዝል እየባተተ ይገኛል፡፡ ኢትቪ ቤታችን ድረስ መጥቶ ለሆዳቸው ባደሩ ምሁራን ተብዬዎች እና ሹመኞች ሲሳደብ ያመሻል፡፡ የኮሚኒኬሸን ጉዳዮች መስሪያ ቤት ውስጥ ዳይሬክተር ናቸው የተባሉ ታምራት ደጀኔ የሚባሉ ኃላፊ መሰሪያ ቤቱ የመንግሰት ደሞዝ የሚከፈላቸው እኔ ጭምር በምከፍለው ግብር መሆኑን ዘንግተው የግል ፕሬስ ከተቃዋሚዎች ጋር ወግኖ እየሰራ ነው ብለው ከገዢው ፓርቲ ጎን ቆመው ሲከሱን አምሽተዋል፡፡ እኚህ ግለስብ ከተቃዋሚ ጎን መሰለፍ ማን ሀጥያት ነው እንዳላቸው አላውቅም፡፡ ተቃዋሚዎች በህግ ተመዝግበው የሚሰሩ ተቋማት እንደሆኑ እና የሚደግፋቸውም የሚቃወማቸውም ሰዎቸ መኖራቸው የሚጠበቅ መሆኑን ዘንግተውታል፡፡ ለነገሩ እርሳቸው የሚደግፉት ፓርቲ ነገ ተቃዋሚ የሚባል ወንበር ላይ ሊኖር እንደሚችል በተሰፋ ደረጃ ማሰብ አልቻሉም፡፡ ለነገሩ ኢህአዴግ በጥቅም የተገዙ አባላቶቹ ስልጣን ሲያጣ አብረውት እንደማይቆዩ ይረዳዋል- እርሳቸውንም ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግ በጥርስም በጥፍርም ፍልሚያ ውስጥ የሚገባው፡፡ አቶ ታምራት ደጀኔ እንዲረዱ የምፈልገው የግሉ ፕሬስ ተቃዋሚን ቢደግፍ አንድም ነውር እንደሌለው ይልቁንም ገዢውን ፓርቲ ለመደገፍ ገዢው ፓርቲ ብቁ እንዳልሆነ ማሳያ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በገንዘብ የሚደግፋቸው ነገር ግን ተደግፈው መቆም የማይችሉ “የግል” ተብዬ ሚዲያዎች እንደነበሩ መርሳት የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ ኢፍቲን፣ ዛሚ፣ ወዘተ
ሰኞ ነሃሴ 19/2006 በቀረበው ዶክመንተሪ ተብዬ ዘባተሎ ላይ ከለየላቸው የመንግሰት ሹሞኞች እስከ ዩኒቨርሲት መምህራን አልፎ ተርፎም አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴን ያሳተፈ ነበር፡፡ እርገጠኛ ነኝ ሀይሌ በሚዲያ ላይ ስለሚታዩ ግድፈቶች አጠቃላይ ሁኔታ ነበር የሚናገረው እንጂ አሁን ክስ ስለተመሰረተባቸው የግል ሚዲያዎች አልነበረም፡፡ ቆርጦ ቀጥሉ ኢቲቪ ግን ከህዝብ ጋር ሊያጋጨው ፍላጎቱን አሳይቶዋል፡፡ ሌላው ተዋናይ ዶክትረ አሸብር ወልደጊዮርጊስ ነበሩ፡፡ ከብዙ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ነበር መልስ አሰጣጣቸው፣ የከሰሱትም ሪፖርተርን ነው፡፡ መንግሰት ደግሞ ከሪፖርተር ጋር ጉዳይ የለውም፡፡ እንዲከሱ ሲጠበቅ የነበረው ሌላ ነበር፡፡ ይቅር ብያለሁ ብለው አልፈውታል፡፡ የእርሳቸው ይቅር ባይነት ከመንግሰት ሰፈር ሊገኝ አልቻለም፡፡ ተበቃይ መንግሰት ለስልጣኑ ሲል በጥፍሩም በጥርሱም ከግል ሚዲያው ጋር ግብ ግብ ገጥሞዋል፡፡ ማን ያሸንፋል አና መቼ ወደፊት የሚታይ ነው፡፡
የቀረበውን ዘጋቢ ፊልም ማስታወሻ ይዜ ለሁሉም በስማቸው አንፃር ለመፃፍ ነበር የፈለኩት ይህን ዘባተሎ የበዛበት ድሪቷም ዘጋቢ ተብዬ ከዚህ በላይ ማለት ተገቢ ሆኖ ስለአልተመቸኝ ተውኩት …. ይህ ዘጋቢ ፊልም ተብዬ የተሰራበት ሙሉ ዶክመንት ለታሪክ እንደሚቀር ተሰፋ አለኝ፡፡ የዛን ጊዜ እንወቃቀሳለን፡፡ ምሁራን ተብዬዎች በእናንተ ተሰፋ ቆርጠናል ….. በእናንተ መምህርነት አንድም የተሻለ ጋዜጠኛ እንደማናገኝ፡፡ ለነገሩ ልጆቹ የአስተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የእኛም ናቸው እና በቤታችን ይማራሉ፡፡ ሀገር ማለት ልጄ ብለን እናስተምራለን፡፡


Sunday, August 17, 2014

የግል ሚዲያዎች ክስ ለምን?


በዚህ የፋክት ዕትም ከ“ግል ሚዲያ” ውጪ ስለ ሌላ ነገር መፃፍ ትክክል መስሎ አልታየኝም፡፡ ይህን ሳስብ ደግሞ ባለፈው ዕትም በፋክት መፅሔት በከፊል የተነሳውን የኢህአዴግ የፖሊሲ ወረቀት “የዴሞክራሲ ሰርአት ግንባታ ትግልና አብዮታዊ ዲሞክራሲ” በሚል በመጋቢት 1999 ዓ.ም የወጣውን መሰረት ማድረግ ወሰንኩ፡፡ ከዚህ የፖሊሲ ወረቀት ውስጥም “ሚዲያና ዲሞክራሲ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ላይ አተኩራለሁ፡፡ ለዚህም ምክንያቴ፣ አሁን መንግስት እንደሚለው እየወሰደ ያለው እርምጃ  ህግን የማስከበርና የህዝብ ጥያቄን የመመለስ ሳይሆን፤ በፖለቲካ ሰነዱ ላይ ያስቀመጠውን በግል ሚዲያዎች ላይ መወሰድ ያለበት ተከታታይ እርምጃ ክፍል መሆኑን በመጥቀስ ይህን የፖለቲካ ሰነድ አግኝተው ለማንበብ እድል ላልገጠማቸው አንባቢያን ማስረዳት ነው፡፡ ከዚያም በማስከተል ይህ ሰነድ፣ በፈለገው መንገድ ተተርጉሞ ህገወጦች ይለናል በሚል ነፃነታችንን አሳልፈን ለመስጠት አለመዘጋጀታችንን ይፋ ለማድረግ ነው፡፡ ነፃነት በነፃ አይገኝምና፡፡
ይህ የምርጫ 97 ዝረራ የወለደው የፖለቲካ ሰነድ ሚዲያን በሚዳስስበት ንዑስ ክፍል መግቢያ ላይ “ሚዲያ የዴሞክራሲ ስርአትን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ድርሻ ካላቸው ተቋሞች አንዱ ነው” ብሎ የሚጀምር ቢሆንም፤ ዋና ግቡ ግን ሚዲያን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል የሚተነትን ነው፡፡ የሩዋንዳን እልቂት ፈጣሪ ሚዲያዎችን ፣ የምዕራባዊያንን የሚዲያ ተቋማትን እንዲሁም በአረቡ ዓለም ያሉትን አልዓረቢያና አልጀዚራን የመሳሰሉ ሚዲያዎችን በመጠቃቀስ “ኪራይ ሰብሳቢ ሚዲያዎች” የሚል ፅንሰ ሀሳብ ለማዋለድ በሚረዳ መልኩ “የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ በልማታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በተሟላ መልኩ መተካት አለበት” ብሎ ይደመድማል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ኪራይ ስብሳቢ ሚዲያ ሲባል አቤት ማለት ይኖርብናል፡፡ ልዩነት ለዘላለም ይኑር ብለን የምንዘምር ሰዎች የኢህአዴግ “ልማታዊ ፖለቲካው ኢኮኖሚ”ን እንደ አንድ አስተሳሰብ መቀበል ብንችል እንኳን፣ ይህን አስተሳሰብ ለራሳችን ለማድረግ የምንቸገር ሰዎች አለን፡፡ ይልቁንም ከዚህ የተሻለ አማራጭ አለን ስንል፣ ይህ አስተሳሰብ በኢህአዴጎች ሰፈር “ኪራይ ስብሳቢነት” ቢሆንም በነፃነት ልናራምድ የምንችልበትን መድረክ ለመንፈግ፣ ይህ ሰነድ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡
የሚዲያ ነፃነትና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታን በሚመለከት የፖለቲካ ሰነዱ  “ሚዲያውን በነፃነትና በጤናማ አኳኋን እንዲያድግ ማድረግ ለማንም ሲባል የሚሰራ ስራ ሳይሆን በአገራችን የዴሞክራሲ ስርአትን እውን ለማድረግ ተብሎ የሚከናወን በመሆኑ ለሌሎች የዴሞክራሲ ሰርአት ግንባታ ስራዎች ከምንሰጠው ትኩረት የማይተናነስ ትኩረት ለዚህም ስራ መሰጠት አለበት” ይላል፡፡ ይህን አባባል በጥሬው ስንመለከተው ምንም ክፋት የለበትም፡፡ ነገር ግን ምን ዓይነት ‹ነፃነት› እና ምን ዓይነት ‹ጤንነት› እንደሆነ ስንመረምር ችግሩን መረዳት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ ሌሎችንም የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማለትም የብዙኃን ማኅበራትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የህዝብ ምክር ቤቶች እንዲሁም የዳኝነት ስርዓቱን ምን ያህል ነፃነት እየከለከለ ጤና እንደሚነሳቸው ስንረዳ፣ ምን ዓይነት ነፃነትና ጤና እንደታዘዘልንም መረዳት ቀላል ነው፡፡ የግል ሚዲያውም ከላይ እንደገለፅኳቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ሸፋፋ እንዲሆን የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ሚዲያውን እንደሌሎቹ የዲሞክራሲ ተቋማት ሙት እንዲሆን መፈለጉን እንረዳለን፡፡ በሙታን ውስጥ የሚገኝን ነፃነት እና ጤና የሚያውቁት ሙታኖች ብቻ ናቸው፡፡
ኢህአዴግ እንደ መንግስት የሚዲያውን አቅም መገንባት ሳይሆን እንዴት አድርጎ መዋጋት እንዳለበት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ይህንንም ለማድረግ በፖለቲካ ሰነዱ ውስጥ የተቀረፀውም በአቅም ግንባታ ሞዴል ሳይሆን በውጊያ ሞዴል ነው፤ “ኪራይ ስብሳቢነትን መዋጋት” በሚል ርዕስ ነው የተቀመጠው፡፡ በዚህ ንዑስ ርዕስ ስር በዋነኝነት የተቀመጠው የውጊያ ግንባር “የሚዲያ አውታሮች ገቢና ወጪያቸውን በትክክል እንዲያስመዘግቡና በየጊዜውም ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡” ይላል፡፡ ይህም የሚረዳው “በውጭ ሃይሎችና በፀረ ሰላም ድርጅቶች ፋይናንስ እንዳይደረግ በጥብቅ መከላከልና መቆጣጠር በጣም አስፈላጊ ይሆናል፡፡” በሚል ነው፡፡ ይህን በተመለከተ በግል ሚዲያዎች ላይ ማስረጃ ማቅረብ የተሳነው መንግስት በቴሌቪዥን በኩል ለሆዳቸው ያደሩ ሹሞችን እና ባለሞያ ነን የሚሉትን ሰብሰቦ በዘጋቢ ፊልም ‹‹መረጃ አለን፤ ከሚያትሙት አርባ አምስት ሺ፣ ሁለት ሺውን ብቻ ነው የሚሸጡት›› የሚል ፕሮፖጋንዳ ለመስራት ይዳክራል፡፡ ማስረጃ ማቅረብ ያልቻለ መንግሰት ‹መረጃ› እያመረተ ይገኛል፡፡ ወደፊት እነዚህ መረጃዎች በማስረጃ ደረጃ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብለን ብንጠረጥር አስገራሚ አይሆንም፡፡ ለነገሩ ያቃጥሉት ነበር የሚል አዳፍኔ ምስክር ይጠፋል ብላችሁ ነው፡፡
በዚህ መስመር አንድም ማስረጃ ማግኘት የተሳነው መንግስት፣ በቀጣይ በሚዲያ ተቋማት ላይ ከማስታወቂያ እና ከአንባቢ በሚገኝ ገቢ ላይ እርምጃ መውሰድን እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ቁጥጥር ስርአት አድርጎ ይዞታል፡፡ አንባቢዎችም እንደምትረዱት የመንግስትና የግል ድርጅቶች ማስታወቂያ እንዳያወጡ ከፍተኛ ጫና በመዳረጉ አሁን ጥርስ የተነከሰባቸው መፅሔቶች ማስታወቂያ ሳያወጡ በመፅሃፍ መግዣ ዋጋ መፅሔት ለመሸጥ በመገደዳቸው መንግስት ወደ ሌላ እርምጃ ተሸጋግሯል፡፡ ሌላኛው እርምጃ ከሰሞኑ የተሰማው ክስ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ነውረኛ የፖለቲካ ሰነድ ጥርስ የተነከሰባቸውን የግል ሚዲያዎች የሚገልፃቸው ነውረኛ በሆነ አገላለፅ ነው፡፡ በኢህአዴግ ሰፈር መገበርም አያስከብርም፡፡ እነዚህ የግል ሚዲያዎች አብዮታዊ ዲሞክራሲን ባይቀበሉም የመንግሰትን ስትራቴጂ የተቀበሉ ኪራይ ስብሳቢዎች በማለት ይገልፃቸዋል፡፡ ለእነርሱም “በሕጉ መሰረት የሚሰሩ ጥገኞችን በተመለከተ ግን ለስራቸው የተመቻቸ ሁኔታ የመፍጠር አሰራር ልንከተል ይገባናል” በማለት ይሰድባቸዋል፡፡ በቅርቡ ለነዚህ ጥገኞች ምን ተጨማሪ ነገር እንደሚደረግላቸው የምናየው ይሆናል፡፡ እንደምታስታውሱት ለጥገኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጎማ ሲሰጣቸው፣ የሌሎቹ ፓርቲ አባላት ደግሞ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
በኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ያልገባ ሁሉ ህገወጥ እና ጤና የሌለው ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በዲሞክራሲ፣ ሰላም እና ነፃነት ላይ የቆመ ደንቃራም አድርገው ይቦድኑታል፡፡ ህዝቡ ኢህአዴግ የሚያወራውን ይህን ሽብርና መዓት ወደ ጎን በማለት ኪራይ ሰብሳቢ ለሚላቸው የግል ሚዲያዎች መተማመኛው የፈለገውን ያህል ውድ ቢሆኑ፣ ተሻምቶ በመግዛት የአለንላችሁ መተማመኛ መስጠቱ አልተዋጠላቸውም፡፡ ሹሞቻችን ይህን የህዝብ መተማመኛ ተቀብለው ለመሄድ ፈቃዳቸው አይደለም፡፡ ይልቁንም ከህዝብ ውጭ አለቃ የለንም እያሉ በየመድረኩ የሚገዘቱ ሹማምንት፤ ህዝብን በሚንቅ መልኩ፤ ‹በህዝብ ጥያቄ መሰረት በግል ሚዲያዎች ላይ እርምጃ ወስደናል› ይሉናል፡፡ ህዝቡ እርምጃው ለምን ተወሰደ ሳይሆን የሚለው ለምን ዘገየ እያለ ነው፡፡ ህዝቡ፣ ህዝቡ፣ ህዝቡ እያሉ በመንግሰት ሚዲያ ላይ ቀርበው ይዘባበታሉ፡፡
ለማንኛውም ከላይ እንደተረዳነው የኢህአዴግ የፖለቲካ ሰነድ የሚያስቀምጠው “ዋነኛው መቆጣጠሪያ መንገዱ ኢኮኖሚያዊ ስለሆነ … ልዩ ትኩረት ሰጥተን ልንረባረብበት ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በህገወጥ ሚዲያዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚደረገው ሂደት በአስተዳደራዊ ገፅታው ብቻ ሳይሆን በፖለቲካው ገፅታው መታየት አለበት፡፡” በማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰሞኑን እየተወሰደ ያለው እርምጃ በምንም መመዘኛ የግል ሚዲያዎቹ በሀገርና በህዝብ ላይ ሽብር በመፍጠራቸው ሳይሆን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ላይ በፈጠሩት ሽብር መነሻ ብቻ ነው፡፡ እርምጃውም ፖለቲካዊ በመሆኑ፣ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር ተያይዞ በመጣ ፍርሃት የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ የግል ሚዲያዎች ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ አንገብርም በማለታቸው “ህገወጥ” በሚል ሽፋን አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩትም፣ ይህ አቅጣጫ የተቀመጠው በመጋቢት 1999ዓ.ም ከምርጫ 1997 ሽንፈት ማግስት ነው፡፡
ይህ ጉደኛ ሰነድ “አስተዳደራዊ እርምጃ ተገቢ መሆኑን ህዝቡና ከዚያም አልፎ ብዙሃኑ የሚዲያው ተዋንያን የሚቀበሉበት ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡” ይላል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ፣ መንግስት ወገቡን ታጥቆ እርምጃው ተገቢ ነው እያለ የሚሰብክን፡፡ ይህን ድራማ ለመስራት የሚጋበዙትም ሰዎች ይህን መረዳት ያለመቻላቸው አስገራሚ ነው፡፡ ሰነዱ በመጨረሻም “ለውጭው አለም በዚህ ረገድ የምንወስዳቸውን እርምጃዎች ተገቢነት ለማስረዳት ጥረት ማድረግ ያለብን ቢሆንም ጋዜጠኞች በምንም አይነት ምክንያት መታሰራቸውን የማይቀበሉ ሃይሎች በርካታ በመሆናቸው እነዚህን ለማሳመን ከመንገዳችን ወጥተን መሄድ የሚጠይቀን መኖር የለበትም፡፡” ብሎ ያጠናቅቃል፡፡ አንድም ጋዜጠኛ፣ ጋዜጠኛ በመሆኑ አይታሰርም በሚል ድርቅ ብለው የሚከራከሩን ሹሞቻችን ጋዜጠኞችን ለምን እንደሚያስሩ ግን በሰነዳቸው ላይ በፅሁፍ አስቀምጠዋል፡፡ ጋዜጠኞች የሚታሰሩት በጋዜጠኝነታቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው በያዙት አመለካከትም ጭምር ነው፡፡ ጥገኛ ለመሆን ባለመፍቀዳቸው እና ለነፃነታቸው በመቆማቸው ነው፡፡

እንግዲህ አስተዳደራዊውን እርምጃ ተከትሎ የሚመጣው  እስር መሆኑን ልብ ማለት አለብን፡፡ የዚያን ጊዜ ደግሞ ኢህአዴግ ከመስመር መውጣት ሳያስፈልገው “ጋዜጠኛ አላሰርንም፣ ጋዜጠኛ መሆን ወንጀል ለመስራት ሰርተፊኬት አይደለም” እያለ በመስመሩ ላይ ሆኖ ያላግጣል፡፡ ለማነኛውም በፖለቲካም ሆነ በጋዜጠኝነት ተሳትፎ የሚያደርጉ ሁሉ፣ የሚሳተፉት ይህ ጠፍቷቸው ሳይሆን ነፃነታቸው ከዚህ በላይ መሆኑን የሚረዱ በመሆናቸው ነው፡፡ ለነፃነት ሲባል ከእስርም በላይ ሞትን ለመቀበል የቆረጠን ሰው ማቆም እንደማይቻል መረዳት ግን ተገቢ እና አስፈላጊ ነው፡፡ይህን ፅሁፍ ለምታነቡ የኢህአዴግ አባላት አንድ ጥያቄ አለኝ፤ “ከጥገኝነት እና ከነፃነት” የቱ ይሻላል?

Monday, August 11, 2014

Salary Adjustment: Poor Planning Disappoints Everyone

In my commentary, headlined “Propaganda Zeroes Salary Increment” (Volume 15, Number 743, June 27, 2014), I used the phrases “government employees” and “civil servants” interchangeably to explain my position about the economic reasons for possible inflation related to the recently announced salary adjustment. Lately, however, I found it was wrong to use “government employees” and “civil servants” interchangeably.
I do not know how many of us clearly know the distinction between “government employees” and “civil servants”. In my view, the disappointing salary increment is a result of the different meanings to these names.
The politicians and bureaucrats at the civil service ministry and the Ministry of Finance & Economic Development (MoFED) were not in the same page in working out the salary adjustment. The bureaucrats have prepared a salary increment based on their definition of civil servants.
But the politician has dragged this salary adjustment to include government employees and beyond. Hence, the current salary adjustment is eroded not only by inflation, but also the scrambling due to the different definitions of names.
At the outset, unofficial sources leaked information that the salary increment has been expected to be at the range of 70pc to 100pc, the higher percentage going to low-earning civil servants. This was really sensible.
But following the wide-running expectation sparked by this information, the government officially rejected the information. Unlike the usual behavior of the EPRDF government, the denunciation came from a relatively by low-profile minister.
Why does EPRDF government muddled into such confusion?
For me, this muddling is due to lack of clarity in defining what constitute civil servants.
Are all civil servants government employees?
Not at all! Just after the announcement of the salary adjustment by the Prime Minister, a serious challenge overwhelmed the political corridor on whether to include the military or not. If this salary adjustment scheme is to include the military, it will not be for civil servants, but rather to all government employees.
That is why the expected increment reduced almost by half from the expected and leaked information. I presume the military took the slice from the civil servants.
After the surprise announcement of the salary adjustment, one of my friend, a journalist, asked me, “Does this adjustment include the military?” My answer was a prompt, no.
I said this because the prime minister, on the Civil Service Day, said that the increment is for civil servants. I said so also because I know there were salary adjustment to the military without any propaganda, based on organizational restructuring within the military and above all the salary scale and benefit scheme for the military is significantly different from the civil servants.
I do not see any good reason to mix up the civil service and the military. Later, however, I came to know that the salary increment includes the military. This is as a result of the possible expected grievance from the military that pushed the politicians to reduce a good share from the civil servant to distribute to the military.
That is why the current salary increment is not for civil servants but to all government employees and beyond. Sadly, it makes none of them happy.
This political decision was disclosed by the senior minister, Sufian Ahmed, at the Parliament session in his budget defense (not in the budget speech) in response for the question raised by one of the Members of Parliament (MPs), possibly a pre-designed question. In my unofficial discussion with some MPs regarding the current salary adjustment, however, they have failed to understand the clear distinction between government employees and civil servants.
Worse is that they have considered themselves as part of the government employee and claim to get salary adjustment.  For sure, they will get the salary increment. Unfortunately, even we, ‘elected’ representatives of the people, consider ourselves as government employees. It is shame on us!
Whatsoever the reasons for this small amount of salary adjustment, the civil servants are not happy.
Why is this salary adjustment disgusting?
Obviously, it does not compensate the eroded purchasing power of take-home money in the past three years. It also could not be taken as an opportunity for sharing the fruits of a 10-year consecutive double digit growth.
The government has claimed that we have become a nation with a per capita income of 550 dollars. But I do not know why the government wants to pay its employees well below the annual per capita income.
If it is true that we as a nation have achieved a per capita income of 550 dollars, then, the minimum salary after tax (net salary) should not be less than 1,000 Br. Anything less than this is exploitation by the government.
By the same token, then, the government should double the salary of low-earning government employees. I believe this is a justified inquiry.
Even then, it seems unfair to compare government and private employees at the professional level, not to say high-earning employees. Regarding the professional salary scale in the private sector, it is far above the government scale, even after the current salary adjustment.
The current proposed salary is less than one third of the private sector.
How could high-level professionals stay in the government sector, then, without engaging in unlawful activities that generate money?
What makes it all confusing is that the government, in principle, expects to retain high caliber professionals to pursue its duty of assuring standards and qualities, while paying them so much lower than their peers in the private sector.  
My point is that the current salary increment is not professionally done. It is not well-thought and consulted with stakeholders.
Had it been professionally done, it would have satisfied at least few groups. This unanimous contention of the increment, even before it reaches the pocket of government employees, coupled with possible inflation, relates to poor planning.
How could we get good governance out of disappointed public servants, then?
I do not expect satisfactory public service from discouraged civil servants.

- Girma Seifu Maru is a Member of Parliament (MP) from MEDREK. He can be contacted at girmaseifu32@yahoo.com. 

ድሬ ድሮ እና ዘንድሮ


ከአዲስ አበባ የሐምሌ ጭጋግ ለመሸሸ ከምጠቀምባቸው አማራጮች አንዱ ከወሩ አጋማሽ ጀምሮ ድሬዳዋ መገኘት እና የቁልቢ ገብርኤልን በዓል ትሩፋት መሻት ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚሁ ወር በጋምቤላ ለሶሰት ቀናት መገኘት በመቻሌ፤ የሐምሌን ጭጋግ ሽሽት በቆላዎቹ የሀገራችን ክፍሎች የማደርገውን ቆይታ የተሳካ አድርጎታል፡፡ የነበረንን ጉዞ አጠናቀን እግራችን ጋምቤላን ከመልቀቁ፤ በመዥንገር እና “ደገኞች” በሚባሉት ነዋሪዎች መካከል መፈጠሩ የተሰማው ግጭትና ደም መፋሰስ፣ ኢህአዴግ የዘራው የጎሰኝነት ፍሬ ማሳያ አንዱ ክፍል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ልብ በሉ! ኢትዮጵያዊነታችን ጥላ ሆኖን እንደልባችን መዘዋወር አንችልም፡፡ መጤ እና ነባር ተብዬ ፍልስፍና ነብስ ዘርቷል፡፡ በጋምቤላ ቆይታዬ የታዘብኩትን በሌላ ጊዜ ልመለስበት እችላለሁ፡፡ ለዛሬው ግን በድሬዳዋ እና አካባቢው የታዘብኩትን ላካፍላችሁ፡፡
በቁልቢ በዓል ላይ የሙስሊሙ እና የክርስቲያኑን አብሮነት ስመለከት፣ ለምን ይህን አብሮነት እና ሰላም የሚጠሉ ሰዎች ይፈጠራሉ? የሚል ጥያቄ ያጭርብኛል፡፡ ጥያቄዬውን ተከትሎ የሚመጣልኝ መልስ ደግሞ፤ በግላቸው ባላቸው ችሎታና አቅም የማይተማመኑ ነገር ግን ሰልጣን እና ጥቅም የሚሹ ወይም ደግሞ በአንድ አጋጣሚ ይህን ጥቅም ቀምሰው ጥቅም ያናወዛቸው “ልሂቃን” እና የአካባቢ ተወካይ ነን የሚሉ ግለሰቦች፤ በቡድን መብት ስም የሚፈጥሩት ውዥንብር እንደሆነ ግልፅ ሆኖ ይታየኛል፡፡ እንግዲህ በሀገራችን ሰላም የሚሰጠን፣ ለእነዚህ ጥቅም ላናወዛቸው ግለሰቦች፣ ልጓም ሲበጅ ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ ይህን አብሮነታችንን ሰኞ ዕለት በነበረው የሙስሊሞች በዓል በድሬዳዋ ከተማ ተገኝቼ ተመልክቼዋለሁ፡፡ በቡድን መብት ስም ስልጣን ላይ ያሉት ወገኖች ግን ይህ ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የሚሹ አይመስሉም፡፡ እናስተዳድረዋለን በሚሉት ከተማ እዚህም እዚያም የሚፈጥሩት ችግር፣ ሙስሊሙን እና ክርስቲያኑን የከተማ ነዋሪ እያማረረው ነው፡፡
ድሬዳዋ በቅርቡ የከተሞች ቀንን እንደምታስተናግድ እየተሰማ ነው፡፡ ከተማዋን ለማስዋብ በሚል ሰበብ በመንገድ ላይ የሚገኙ አጥሮች ቀለም እንዲቀቡ ቀጭን መመሪያ ተላልፏል፡፡ የመመሪያው መቅጠን ደግሞ መመሪያ አውጪውን አካል ትዝብት ላይ ጥሎታል፡፡ መመሪያው፣ “የሚቀባው የቀለም መለያ ቁጥር፣ የቀለም ቀቢውን ስልክ ቁጥር እና ስሙን ጨምሮ” እንደሚያስተላልፍ ያዛል፡፡ የሚገርም ጊዜ ላይ ደርሰናል ማለት ነው፡፡ ይህ ቀጭን ትዕዛዝ የደረሳቸው አንድ ባለሆቴል ሰውዬ “ቀለሙን አስቀባለሁ እነርሱ ላዘዙኝ ቀለም ቀቢ ግን አስቀብቼ መመሪያ አውጪዎቹ ኮሚሽን አይበሏትም” ነበር ያሉኝ፡፡ ህዝብ እንዲያስተዳድሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቦታ የያዙ ሰዎች፣ ይህን ያህል የማሰቢያ አቅላቸውን የሚያስት የጥቅም ግንኙነት እንዴት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ማሰብ ይከብዳል፡፡ እንግዳ ሊመጣ ነው ቤት እናፅዳ ማለት የአባት ቢሆንም፣ በዚህ ደረጃ መመሪያ ማቅጠን ግን ምክንያቱ ግልፅ ነው፡፡
የድሬዳዋ ከተማ በፅዳት እጅግ ምስጉን እንደነበር ማንም ይመስክራል፡፡ ነበር ያልኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ አንደኛው ድሬዳዋ ውስጥ በአሁኑ ጉብኝቴ ከወትሮ በተለየ የፅዳት መፈክሮች በብዛት መመልከቴን ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በአጋጣሚ ወደ ጤና ቢሮ እና አካባቢው ጎራ ባልኩበት ጊዜ ከጤና ቢሮ 50 ሜትር ርቀት በማይሞላ ቦታ ላይ መንገድ ዘግቶ የተከማቸውን ቆሻሻ እና በየውሃ መውረጃ የሚታየው ፍሳሽ ድሬዳዋን የሚመጥን አለመሆኑን በመታዘቤ ነው፡፡ ወግ ደርሶን እኛም ድሮ ለማለት በቃን፡፡ ቆሻሻ የሚመጥነው ከተማ ባይኖርም፤ በፅዳት መፈክር ያበደችው ድሬ አሁን ለከተሞች ቀን ለታሰበው ጽዳት ቀድመን እናቆሽሻት በሚል የተጠመደች ትመስላለች፡፡ በተለምዶ “ፋይናንስ” ተብሎ ከሚታወቀው የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ከሚገኝበት መቶ ሜትር ርቀት ላይ አዲስ በሚገነባው ፍርድ ቤት ህንፃ አጥር ስር የተከማቸው ቆሻሻ የአዲስ አበባን “ቆሼ” ያስታውሳል፡፡ ይህ እንግዲህ ከተማውን ለሚያስተዳድሩ አካላት ከእይታ ውጭ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ እነርሱ ከቀለም ቀቢ የሚገኝ ኮሚሽን ላይ አፍጥጠው፤ የከተማውን ቆሻሻ የሚያነሳ ጠፍቶ የተለያዩ ሰበቦችን ይደረድራሉ፡፡
ድሬ ሲታሰብ የከዚራ ጥላውንም ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የድሬ ጥላ የነበሩት ዛፎች እየተመናመኑ፣ ቀድሞ የነበሩ ቤቶች እየፈረሱ፣ አዲስ ህንፃ በከዚራ ሊሰራ የፈረሱ ቦታዎች ታጥረው ይገኛሉ፡፡ በአስደናቂ ፍጥነት የተጠናቀቀው የዳሽን ባንክ ህንፃም እንደተጠበቀው ለከዚራ ድምቀት አልሰጠም፡፡ ለአንድ የባጃጅ ሾፌር “ህንፃዎቹ ሲያልቁ ከዚራ ይደምቃል” የሚል አስተያየት ስሰጠው፣ የመለሰልኝ መልስ ይበልጡኑ አስገርሞኛል፡፡ ሾፌሩ፣ “በሲሚንቶ ክምር ከተማ አይደምቅም” ነበር ያለኝ፡፡ ‹‹እንዴት?›› ብዬ ጥያቄዬን ሳስከትል “ድሬዳዋ ፎቅ ሳይሆን ሰው ነው የሚያስፈልጋት፤ ድሬዳዋ ማነው ፎቅ ላይ ወጥቶ የሚገበያየው?” ብሎ መልስ ሰጠኝ፡፡ ስለዚህ የድሬዳዋ ከተማ የነዋሪዎቿን ስነ-ልቦና ያገናዘበ ግንባታ መሻቱን ተረድቻለሁ፡፡ ይህ ታዲያ የማን ኃላፊነት ነው? ብዬ ብቻዬን ስቆዝም፤ የባጃጅ ሾፌሩ በሀዘን ስሜት እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ ሰዎች የድሮ ነገር አይወዱም፡፡ የነበረውን ባቡር ጣቢያ አፍርሰው ሌላ ይሰራሉ፤ ከዚራን አጥፍተው ሳቢያን እንዲለማ ይፈልጋሉ፡፡ የድሮ ከዚራ እንዲኖር የሚፈልጉ አይመሰለኝም፡፡” በእውነትም ከዚራን ማፍረስ ለምን ቅድሚያ ተሰጠው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡
ከዚራን ከማፍረሱ ጎን ለጎን ደግሞ በዚያ አካባቢ በብዛት በሚገኙት የኪራይ ቤቶች ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች አስተዳደሩ ሌላ ስጋት ጋርጦባቸዋል፡፡ ቀደም ሲል ሲከፍሉት የነበረውን በመቶዎች የሚቆጠር ኪራይ በመከለስ፤ ስምንትና አስር ሺ ብር እንዲከፍሉ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ እንደሆነ በከተማው ይወራል፡፡ አንዳንዶች ከምርጫ በፊት ተግባራዊ ላያደርጉት ይችላሉ የሚል ተስፋ ቢኖራቸውም፤ የማይቀር ዕዳ ነው የሚሉት ያመዝናሉ፡፡ ለምን መንግስት እንዲህ ያደርጋል ያልኳቸው አንድ ነጋዴ፤ “ለአባይ ግድብ ገንዘብ እስኪሞላ እኛ ማለቃችን ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ነጋዴዎች በደረጃ ተመድበው የቦንድ ግዢ እንዲፈፅሙ፣ “የነጋዴዎች ተወካይ” የሚገኙበት ኮሚቴ ወስኗል የሚል መረጃ ደርሶኛል፡፡
ድሬዳዋ በመኖሪያ ቤት ችግር ከሚጠቀሱ ከተሞች አንዷ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ በድሬ ቀደም ሲል መንግስት ህጋዊ የመሬት እደላ በማቆሙ ምክንያት በችግር ተገፍተው በህገ-ወጥ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሰርተው ሲኖሩ የነበሩ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደህጋዊነት ከተቀየሩ በኋላ፤ መፍትሔ ይገኛል ተብሎ ቢጠበቅም፣ የከተማው የመሬት አስተዳደር አሁንም  የዘመቻ ስራው አብቅቶ መደበኛ የቤት መስሪያ ቦታ የማይቀርብ በመሆኑ፣ በከተማው ዙሪያ አሁንም ህገ-ወጥ ግንባታዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለጥ ያለ ሜዳ የነበረው በምስራቅ በኩል የሚገኘው ወደ ሽንሌ መውጫ መንገድ፣ ያለ እቅድ በተሰሩ ጎጆዎች ታጉሮ የስደተኛ መንደር ይመስላል፡፡ በፕላን የተጀመረች ጥንታዊቷ ከተማ ድሬ፤ ዛሬ በሃያ አንደኛው ክፍለ-ዘመን ያለፕላን በዘፈቀደ እየተለጠጠች ትገኛለች፡፡ ድሬ ይህን ጉዷን በከተሞች ቀን ለሚታደሙት እንግዶች እንደማታስጎበኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቀለም እየተቀቡ ያሉት የከተማው ዋና ዋና መንገዶችም ለታይታ መሰራታቸው ያስታውቃል፡፡
መቼም ድሬዳዋ ሲነሳ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ጉዳይ መነሳቱ አይቀርም፡፡ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር እንዲሞት የተፈረደበት መሆኑ ግልፅ ቢሆንም፤ ለምን እንደሆነ በውል ባልታወቀ ምክንያት ከድሬዳዋ ጅቡቲ አንድ ባቡር ማንቀሳቀስ ተጀምሮ እንደነበር በሚዲያ ሲራገብ ነበር፡፡ የድሬዳዋ ነዋሪም አዲሱ ባቡር ስራ እስኪጀምር ድረስ በዚሁ ማዝገም ጥሩ ነው ብሎ ሲጠብቅ፣ በግለሰቦች ግጭት ምክንያት አሁንም እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከመተሃራ በሰቃ ሀይቅ ጀምሮ ከመቶ ኪሎሜትር በላይ የሚሆን ሀዲድ ለማደስ፤ ከጣሊያን ኩባንያ ጋር በቢሊዮን የሚገመት ብር የወጣበት ፕሮጀክት አንድም ጥቅም ሳይሰጥ ተጠናቋል፡፡ ይህ ሁሉ የሀገር ሀብት እንዲባከን የተደረገበት ምክንያት ተድፈንፍኖ መቅረቱ ግን በዚህች ሀገር ተጠያቂነት እንደሌለ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ድሬዳዋ መስመር አግልግሎት መስጠት ካቆመ ብዙ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፤ የባቡር ሀዲዶቹም አልፎ አልፎ መሬት ውስጥ እየተቀበሩ ቀሪዎቹም እየተዘረፉ እንደሚገኙ የድርጅቱ ሰራተኞች በምሬት ይናገራሉ፡፡
የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት በህግ እስከአሁን ባይፈርስም፣ ሰራተኞቹን በሙሉ ተረክቦ ያለስራ ደሞዝ የሚከፍለው የብረታ ብረትና ኢንጂነርኒግ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ይህ ኮርፖሬሽን ለምን እዚህ ግቢ ውስጥ ገባ ለሚለው ጥያቄ ብዙ መላ ምቶች ቢኖሩም፣ ብዙዎች የሚሰጡት ምላሽ በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው ለመቶ ዓመት የተከማቹ ብረታ-ብረቶች እና ሌሎች ማሽኖች ያለምንም ስርዓት የሚገኙበት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከሚከፍለው ደሞዝ ጋር ሲነፃፀር የሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ ስለሆነ መግባቱ አያስገርምም የሚሉት ይበዛሉ፡፡ በዋነኛነት የሚያነሱት ጥቅሙም እንደተቋም ለድርጅቱ ተገበያይቶ ሳይሆን ለህገ-ወጥ አሰራር የተመቸ መሆኑን ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በሀገር ውስጥ የወዳደቁ ብረታ-ብረቶቸን ከመንግስት ተቋማት ያለምንም ውድድር ይሰበሰብ እንደነበረና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለከፍተኛ ሙስና የተጋለጠ ነው በሚል ከፀረ ሙስና ኮሚሽን በቀረበ ሪፖርት መነሻ፤ ከመንግስት ተቋማት ግዢ እንዲያቆም መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑንም እንደማግኔት ብረት ይስባል ይሉታል፡፡
ድሬዳዋ ለደረቅ ወደብ ዋነኛ ተመራጭ ብትሆንም፣ እስከ አሁን ድረስ በጊዜያዊነት ካልሆነ በቀር የደረቅ ወደብ አገልግሎት እንድትሰጥ አልተደረገም፡፡ በከተማ ምስረታ ታሪክ ረዥም ዕድሜ ያካበተችው፣ በአንፃራዊነት የተሻለ አገልግሎት መስጠት የምትችለው ድሬዳዋ ተዘላ፤ “ሞጆ” የደረቅ ወደብ እንድትሆን መመረጧ ድሬዎችን ያስገርማቸዋል፡፡ በተለይ የጅቡቲ ድሬዳዋ ምልልስን በማፋጠን፣ ከፋተኛ ጭነት የሚጭኑ መኪኖችን ውጤታማነት ለማሳደግ እና በሀገር ውስጥ የስርጭት ስራ ላይ የሚሳተፉ መካከለኛ የጭነት መኪኖችን ተሳትፎ ለማጎልበት የሚረዳው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ አገልግሎት ለምን ችላ እንደተባለ ምላሽ የሚሰጥ የለም፡፡ መልሱ፣ ‹‹አቦ ድሬ ባለቤት የላትም!›› የሚል ነው፡፡ በድሬ የደረቅ ወደብ ግንባታ እንደሚከናወን በአንድ ወቅት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት አቶ አባይ ፀሐዬ ሲናገሩ በአጋጣሚ በቦታው የነበርኩ ቢሆንም፤ ተመሳሳይ ቃል በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርም ተገብቶ እንደነበረ የከተማው ነዋሪዎች በቁጭት ያሰታውሱታል፡፡
ድሬዳዋ ለጅቡቲ ካላት ቅርበት አኳያ  ወደውጭ የሚላክም ሆነ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ምርት ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች መንደር ዝግጅት ደፋ ቀና ብትልም፤ በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት አየር ከአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ዙሪያ ለመውጣት ገና ብዙ እንደሚቀረው ዋና ማሳያው ድሬዳዋ ነች፡፡ ድሬን ድሮ እና ዘንድሮ ስናያት እዚህም እዚያም ከበቀሉት ጥቂት ህንፃዎች እና የኮብል ስቶን መንገዶች ውጭ፣ ለነዋሪው በሚመጥን ልክ የኢኮኖሚ እንቅሰቃሴ ማየት አይቻልም፡፡ ድሬ አሁንም በጊዜያዊነት የከተሞችን ቀን ወይም ሌላ በዓልን ለማስተናገድ ከሚደረግ ሽር ጉድ ወጥታ ለዘላቂ የነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚሰራ አስተዳደር ያስፈልጋታል፡፡

ገዢው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በኮሚቴ የሚያስተዳድራት ድሬዳዋ፣ ከሃያ ዓመት በላይ በቁልቁለት ጉዞ ውስጥ ለመገኘቷ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ይህ የቁልቁለት መንገድ ደግሞ የተቀየሰው በገዢው ፓርቲ እና ሃላፊነት አለብኝ በሚለው የፌዴራል መንግስት አማካኝነት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ድሬዳዋ በህገ-መንግስት የተቋቋመው የመንግስት መዋቅር አካል አይደለችም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ለምን በፌዴራል ከተማነት ተመደበች? ብሎ ቅሬታ ያለው ባይኖርም ለእድገቷ የሚያስብላት የድሬዳዋ ልጅ የሌለ ይመስል፤ አባል ድርጅቶች ከክልሎቻቸው በሚመድቧቸው ካድሬዎች ውክልና መተዳደሯ፣ ከተማዋን የሚመጥን ዕድገት ላለመምጣቱ አንዱ መንስዔ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በድሬዳዋ እና በሀረር የሚደረጉ ምርጫዎች በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በድርጅታዊ አሰራር የሚወሰኑ መሆናቸውም ጉልህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከተማይቱ፣ ኦሮሞና ሱማሌ ተራ በተራ በከንቲባነት የሚያስተዳድሯት ምስኪን ከተማ ነች፡፡ ለማንኛውም፣ የህዝብ ምርጫ እንዲከበር በዘር ሳይሆን በድሬዳዋ ልጅነት ወንበሩ ክፍት ይሁን፡፡ የድሬ ልጆችም ለከተማቸው ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ዋናው ጭብጥ ግን፣ የድሬ ልጆች የግል ነፃነትን ለሚቀማው ኢሕአዴግ አባል ለመሆን አለመመቸታቸው ነው፡፡