ምርጫ
አሁን ያለውን የጊዜ ሠሌዳ ጠብቆ መካሄድ አለበት የሚሉ እና አይደለም ምርጫው መዘግየት አለበት፡፡ የሚሉ የተለያዩ ግለሰቦች እና
የቡድን ወኪሎች ሙግት ላይ ይገኛሉ፡፡ በግሌ ምርጫ “በተቻለ መጠን” የጊዜ ሠሌዳውን ጠብቆ መካሄድ አበለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን
የምልበትን ምክንያት በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ምርጫው በጊዜ ሠሌዳው ካልተካሄደ አገር ትፈረሳለች ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡
ምርጫው
በሕግ በተደነገገው መሰረት በመጪው ሁለት ሺ አስራ ሁለት ግንቦት ውር ላይ መካሄድ አለበት፡፡
ሕገ መከበር አለበት በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ለሚከራከሩ መልሱ አጭር ነው፡፡ በአምስት ዓመት መካሄድ የነበረበት ምርጫ ሲራዛም
ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ምርጫ በቅንጅት ማሸነፍ ምክንያት ለሁለት ዓመት ተገፍቶ፤ ከአካባቢ ምርጫዎች ጋር እንዲደረግ
መደረጉ አንዱ ሲሆን፣ አሁንም መደረግ ካለበት ጊዜ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ በቀጣይ አራት ወር ጊዜም ሊካሄድ
አይችለም፡፡ በድጋሚ የመራዘም ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በእኔ እምነት መራዘምም አለበት፡፡ ሰለዚህ ምርጫ በጊዜ ሠሌዳ መሰረት ባለመካሄዱ
የሚፈጠር አገር የሚፈርስ ችግር የለም፡፡ ችግሩ ባልተመረጡ ሰዎች መገዛት ነው- እንችለዋለን፡፡ በተጭበረበረ ምርጫ መገዛት እና
ሳይመረጡ መግዛት ያው አንድ ዓይነት ነው፡፡
ባለፉት
ዓመታት (ምን አልባትም አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!! በሚል ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ) የተካሄዱት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች
ዋናው ጉዳይ የነበረው “ያልተመረጠ መንግሰት አይገዛንም” በሚል ነው፡፡ ግፍ፣ ጭቆና በቃን፤ ወያኔ ይወደም (ዳውን፣ ዳውን ወያኔ)፣
ወዘተ በሚል የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት የመሆን ጥያቄ ነው፡፡ በ2004 መጀመሪያ ጀምሮ የታወጀው የሊዝ ዓዋጅ
እና እርሱን ተከትሎ የመጣው የመሬት ወረራ ያንገሸገሸው ሕዝብ ድምፁን ያሰማው በመረጥኩት መንግሰት መተዳደር እፈልጋለሁ በሚል ነበር፡፡
ሰለዚህ ሕዝብ መሪውን መምረጥ እና መሾም ሲፈልግ መሻር ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ የሕዝብ መሪውን የመምረጥ ፍላጎት በጥያቄ ውስጥ
ካላስገባን ምርጫ ይራዘምን ምን አመጣው?
ምርጫ
የዜጎች መብት ሲሆን ዜጋ የሚፈልገውን እናውቃለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደራጀ መልኩ ደግሞ አማራጭ ሃሳባቸውን ማቅረብ በፈቃደኝነት
የወሰዱት ሃላፊነታቸው ነው፡፡ ይህም ሃላፊነት በዜጎች ይሁንታ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ የያዙት ሃሣብ የፈለገ ምርጥ እና ጥልቅ ቢሆን
ሕዝብ ይሁን ብሎ የሥልጣን መንበር ካልሰጠ መተግበር አይቻልም፡፡ (ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ብቸኛውም መንገዴ የሚለው የተሳሳተ
መንገድ ነው፡፡)
የዜጎችን
መብት ተረድተናል ያሉ ተፎካካሪዎች የሚዳኙበትን ሕግና ደንብ በአግባቡ አዘጋጅቶ ጫወታውን የሚመራወው አካል ደግሞ የምርጫ አስፈፃሚው
አካል ሲሆን በምርጫ አስፈፃሚ ቅር የተሰኘ ደግሞ አቤት የሚልበት ነፃ ፍርድ
ቤት የግድ ይላል፡፡ እነዚህ አካላት የምርጫ ቦርድ እና ነፃ ፍርድ ቤት መኖር ወሳኝ የምርጫ ግብዓቶች ናቸው፡፡
ምርጫ
ይራዘም የሚሉ ሰዎች ፍርድ ቤቱ ጠንካራ/ገለልተኛ ስለአልሆነ በምርጫ ወቅት በሚፈጠሩ ችግሮች ፍትሓዊ ውሳኔ አይገኝም የሚለው አንዱ መከራከሪያቸው ነው፡፡ ፍርድ ቤቱን ገለልተኛ ለማድረግ ከዛሬ
ጀምሮ ስንት ጊዜ እንደሚፈጅ ግን በግልፅ አይናገሩም፡፡ ይባስ ብሎ
ግን ይኽው ፍርድ ቤት ሙሰኞችን እና ሌሎች ወንጀለኞችን በአፋጣኝ ለፍርድ ያቅርብ ይላሉ፡፡ በእኔ አምነት ፍርድ ቤት ገለልተኛ መሆን
አስፈላጊ መሆኑ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን ይህ ሥራ በአንድ የምርጫ ዘመን የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ ሰለዚህ መንግሰት በፍርድ ቤቶች
ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ማረጋገጥ በራሱ ፍርድ ቤቶችን አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርጋቸው ሲሆን የመዓዛ አሸናፊ የመሰሉ ሰዎች በቦታው
መሾም ከተራ ጣልቃ ገብነት ይጠብቀዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተቻለ መጠን የፍርድ ቤቱን ጫናም ለመቀነስ ተፉካካሪዎች በጨዋነት ለመጫወት
መወሰን ይገባናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ባለው ፍርድ ቤት ምርጫ ማካሄድ የምንችልበት ጊዚያው አውድ መፍጠር ይቻላል፡፡ የሚል
ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
ሌላው
የምርጫ ቦርድ ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫ ቦርደ ለሆዳቸው ያደሩ የምርጫ ቦርድ አባላትና ሠራተኞች በሰፈሩበት ሁኔታ ምን እንደሚሆን ያልረሳነው
የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ አሁን በምርጫ ቦርድ የተጀመረውን ለውጥ በአፋጣኝ ወደ መሬት አውርዶ ተግባራዊ ለማድረግ ምን ያህል
ጊዜ ይፈጃል? የሚሊዮን ብር ጥያቄ ነው፡፡ በእኔ እምነት በአርባ
ሺዎች የሚቆጠሩ ምርጫ አስፈፃሚዎችን ለማዘጋጀት የሚፈጀውን ጊዜ ማስላት እና ይህን በቴክኖሎጂ ማገዝ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የምርጫ
አስፈሚዎች ሥልጠና በሶስት ወር የሚጠናቀቅ ነው፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች አሁን ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎችን በገለልተኝነት ማሳተፍ
በተመረጡ ሰማኒያ ጣቢያዎች አምስት መቶ ምርጫ አስፈፃሚዎች ማዘጋጀት ለምን እንደ ችግር እንደሚታይ አይገባኝም? ይህ ችግር የሚሆነው
አሰመራጮቹን ግልፅ ላልሆነ ተልዕኮ ለማስልጠን ሲፈለግ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ገለልተኛ መስለው ገዢውን ፓርቲ የሚያስመርጡ
ሴረኞችን ለመመደብ፣ ይህን የሚያሟሉትን ሆድ አደሮች ለመምረጥ የሚደረግ ሽፍጥ ሥራውን ያከብደዋል፡፡
ምርጫ
ቦርድ በቀረው ጊዜ ይህን ለማድረግ ያስቸግረኛል በሚል ተጨማሪ ጊዜ የሚጠይቅ ከሆነ ያለ በቂ አጫውች ጫወታ መጀመር ሰለሌለበት ምርጫው
ሊራዝም ቢችል በግሌ ምንም ግድ አይሰጠኝም፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህን ማድረግ የማይችልባቸውን ምክንያቶች በዝርዝ ማቅረብ ይኖርበታል
ብዬ አምናለሁ፡፡
ተፉካካሪ
ፓርቲዎች ለምርጫ እራሳቸውን ብቁ አድርገው እስኪዘጋጁ ምርጫ ይራዘም የሚል አስቂኝ ምክንያት የሚቀርብ አይመስለኝም፡፡ ሃሣብ ያለው
ለሕዝብ ለማቅረብ በቂ ጊዜ አለው፡፡ ሃሣብ ለሌው ደግሞ የፈለገ ቢራዘም በቂ አይሆንም፡፡ አሁን እንደ አዲስ ተነስቶ አገር መምራት
ሰለማይቻል ሃሳብ አለን የሚሉ ሁለትም ይሁኑ ሶሰት ሲወዳደሩ በውድድሩ ውስጥ በመሳተፍ ልምድ መቅስም የተሻለው አማራጭ ነው፡፡ የተፉካካሪዎች
አለመዘጋጀት ለምርጫ ለማራዘም ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡
ከምርጫ
በኋላ የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍራት ምርጫ ይራዘም የሚሉ ቅን ዜጎች እንዳሉም አምናለሁ፡፡ አነዚህ ቅን ዜጎች ምርጫ በማራዘም ግጭት
ማስወገድ እንደማይቻል አለመረዳታቸው ነው፡፡ የግጭት ምንጮች ተፉካካሪ ፓርቲዎች እራሳቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ተፉካካሪ ፓርቲዎች ወደ
ግጭት ላለመግባት ቁርጠኛ ውሳኔ በሕዝብ ፊት እንዲገቡ ለማስገደድ ምን ያህል ጊዜ በቂ ነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ሚዲያዎች
ሲቪል ማህበራት ይህን በማድረግ ዙሪያ ከፍተኛ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝቡ ለምርጫ ውጤት እንዲገዛ፣ ተፉካካሪዎች ከምርጫ
በኋላ ለሚያደርጉት ጥሪ ጆሮ እንዳይሰጥ ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝብ በዚህ ደረጃ ከነቃ ማንም ለጊዚያዊ ድል ሕዝብ ወደ ሞት
የሚጠራ ብጥብጥ አይከተልም፡፡ ሙከራና ፉከራ ብቻ ይሆናል፡፡
መንግስት
በጀመረው መስመር ቁርጠኛ ከሆነ እና ሁሉም የመንግሰት መዋቅሮች ማንኛውንም ሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይገድቡ መመሪያ የሚሰጥ
እና ይህ መመሪያ በሚጥሱ የመንግሰት መዋቅሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ከጀመረ በሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ
ሕዝብ የፈለገውን መርጦ ወደ መንበር ያመጣል በዚህ ጊዜ ተፉካካሪዎች ሁሉ አሸናፊ ይሆናሉ፡፡ አሁን በየቦታው የሚታዩት ግጭቶች ጊዚያዊና
የታፈኑ ዜጎችና ቡድኖች ከአፈና አገዛዝ ሲወጡ ሊከሰት የሚችል ክስተት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግሰት በመዋቅሮቹ ቁርጥና እርምጃ
ውስዶ ሠላማዊ ድባብ ማረጋገጥ የማይችል ከሆነ ምርጫ ማካሄድ አለመቻል ብቻ ሳይሆን ይህን ለማድረግ ምን ያህል እንደሚበቃው ማስላትም
ሰለማይቻል እንደ ደርግ በጊዚያዊ መንግሰት ስም ለረጅም ዓመት መቆየቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ የባስ አታምጣ የሚያሰኝ ነው፡፡
በአገራችን
ጥንቅቅ ያለ እንከን የለሽ ምርጫ ማካሄድ ላይቻል ቢችልም፡፡ በወሳኝ መልኩ ሕዝብ ለሥልጣን ባለቤት የሚያደረግ (የመረጠው ብቻ በየደረጃው
ባለ መዋቅር ሃላፊ የሚሆንበት) ሥርዓት መዘርጋት ይቻላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ለማራዘም በቂ ምክንያቶች አሉ ብዬ አላምንም፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህን ሁኔታ ገምግሞ በመረጃ
አስደግፉ ከሚሰጠው ምክንት ውጭ በሰበብ ምርጫ ማራዘም ሌሎች ብዙ ንትሮኮች ከማምጣት ባለፈ ሕዝብ የመረጠው አካል እንዳያስተዳድረው
ማድረግ ነው፡፡ ሰለዚህ ምርጫ በአፋጣኝ እላለሁ ……
ቸር
ይግጠመን
ግረማ
ሠይፉ ማሩ